Ethiopia Zare's weekly news digest, week 26th, 2012 Ethiopian calendar

ከየካቲት 23 - 29 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

የዓመቱ ሃያ ስድስተኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች

ኢዛ (ከየካቲት 23 - 29 ቀን 2012 ዓ.ም.)፦ ባሳለፍነው ሳምንት ዐበይት ጉዳዮች መካከል በታላቁ ህዳሴ ግድብ ዙሪያ ኢትዮጵያና ግብጽ የገቡበት የቃላት ጦርነትን የሚስተካከል የለም። ሳምንቱን ሙሉ በዚህ ጉዳይ እየወጡ ያሉ መረጃዎች ቀዳሚውን ሥፍራ የያዙ ናቸው። የአገር ውስጥ ሚዲያዎች የመክፈቻ ዜናዎቻቸው በዚሁ ወቅታዊ ጉዳይ ላይ ያነጣጠረ ነው። የህዳሴ ግድብ የመሠረት ድንጋይ ከተጣለና ግንባታው ተጀምሮ አሁን ያለበት ደረጃ እስኪደርስ ድረስ ውስጥ ውስጡን ካልኾነ በቀር በግብጽና በኢትዮጵያ መካከል ጠንከር ያለ የቃላት ምልልስ የተደረገበት ጊዜ አልነበረም።

ኢትዮጵያ ከዋሽንግተኑ የሦስትዮሽ ድርድር ላይ እንደማትገኝና ድርድሩ እንዲራዘም ካሳወቀችበት ጊዜ ወዲህ ግን፤ ግብጽ በተለየ መንገድ ኢትዮጵያን ለመጫን ብላ ያሰበቻቸውን የተለያዩ ትንኮሳ አዘል እንቅስቃሴዎችን አድርጋለች። በዋሽንግተን የተቀመረውን ውል ኢትዮጵያ እንድትፈርም ከአሜሪካ ጋር በመኾኑ ጫና ፈጥራለች። ከኢትዮጵያ አንፃርም በዓባይ ጉዳይ ጠንከር ያሉ መግለጫዎችን ያወጣችበት ጊዜ ቢኖር ይኸው ያሳለፍነው ሳምንት ነው ማለት ይቻላል።

በዓባይ ውኃና በህዳሴው ግድብ ጉዳይ ኢትዮጵያ የሌሎችን ይሁንታ የማትሻ መኾንዋንም አፅዕኖት ሠጥታ ያስታወቀችበት፤ ኢትዮጵያውያንም በዚህ አጀንዳ ላይ ያላቸው አቋም የጠነከረ ኾኖ ወጥቷል። ግድቡን ለማስጨረስ በሚደረገው የገንዘብ ድጋፍ ላይ እንደ አዲስ የተነሣሱበት ሳምንት ነው ማለት ይቻላል። በጉዳዩ ዙሪያ የሚመለከታቸው ምሁራን ወደ ሚዲያ ወጥተው ከወቅታዊው ውዝግብ አንፃር ምን መኾን እንደሚገባውና ኢትዮጵያ መከተል ይገባታል ያሉትን ምክረ ሐሳብ ከሌላው ጊዜ በተለየ የተሰማው በዚሁ ባሳለፍነው አንድ ሳምንት ነው። ኢትዮጵያ በያዘችው ፕሮግራም መሠረት የግድቡን የውኃ ሙሌት የምትጀምር መኾኑን ቁርጥ ያለ አቋሟን በማሳወቅ፤ በሦስተኛ ወገን ጣልቃ ገብነትም ኾነ ግብጽ ጫና ለመፍጠር በምታደርጋቸው የተለያዩ ሙከራዎች የግድቡን ሥራ ኢትዮጵያ ለአፍታ የማታቆም መኾኑንም በይፋ ይታወቅልኝ ብላለች።

ከዚህ አውራ ከምንለው የሳምንቱ ወሳኝ አገራዊ ጉዳይ ባሻገር ሌሎች ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳዮች የተሰሙበት ነው። ባልተጠበቀ ሁኔታ ሚኒስትርና ሚኒስትር ዴኤታዎችን ጨምሮ 15 የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች በአምባሳደርነት እንዲሾሙ ተደርጐ፤ የያዙትን ሥልጣን እንዲለቁ መደረጉ አንዱ ነው። ይህ ምደባ በብዙዎች ያልተጠበቀ የተባለ ሲሆን፣ እርምጃው በአገሪቱ የሥልጣን እርከን ውስጥ ቁልፍ ሚና ያለውን የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ቁንጮ ሰው የሸኘም ነው። በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ ከፍተኛ ሚና ያለው የአገሪቱ ትልቁ ባንክ ፕሬዝዳንት ኾነው ሲያገለግሉ የቆዩት አቶ ባጫ ጊና በተሾሙ በ16 ወራቸው ኃላፊነታቸውን ለቀው በአዲስ የተተኩትም በዚህ ሳምንት ነው። ጊዜው ከምርጫ ጋር የተያያዙ ክስተቶች በርክተው የሚሰሙበት ነውና፤ የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ ከሰሞኑ ከአንድ ፓርቲ የአባላት ፊርማ ጋር ተያይዞ ግድፈት በማግኘቱ፤ ጉዳዩ በፌዴራል ፖሊስ እንዲጠራ መላኩንና ከተለያዩ ፓርቲዎች ለቀረቡ አቤቱታዎች ምላሽ የሠጠበትን መረጃ ያሳወቀበት ነው።

የብልጽግና ፓርቲ በአሥር ሺህ ሰዎች የሚቆጠሩ አባላቱን ለሥልጠና አስገብቶ ማጠቃለያው ያረፈው በዚህ ሳምንት ሲሆን፣ በሥልጠና ማጠቃለያው ላይ ዶ/ር ዐቢይ የሠጡት ማሳሰቢያም ነበር። ከሰሞኑ ከተቃዋሚው ጐራ ተከታታይ መግለጫዎችን በማውጣት ሊጠቀስ የሚችል ካለ ኦነግ ነው። የኦነግ መግለጫ በአባላቴ ላይ እየደረሰ ነው ያላቸውን በደል የዘረዘረበት ሲሆን፤ በሌላኛው መግለጫው ደግሞ የአዲስ አበባና የድሬዳዋ ጉዳይ ላይ ፓርላማው ውሳኔ ያሳልፍ የሚል መልእክት የያዘ ነበር።

እንደ ታሪካዊ ክስተት ከሚታየው ከሳምንቱ ዐበይት ዜና መሐል ሊካተት የሚችለውና ብዙዎችን ያነጋገረው ጉዳይ፤ ለሦስት አሥርት ዓመታት ለተጠጋ ጊዜ ታሪካዊ እውነቱ ተዘንግቶ የነበረውን የካራማራ ድል በዚህ ሳምንት በተለየ ማስታወስና መዘከር የተቻለበት መኾኑ ነው።

የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር አዲስ ሚኒስትር ዴኤታ የተሾመለት በዚህ ሳምንት ነው። የቀድሞው የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር ኃላፊነታቸውን ከለቀቁ ወዲህ በቦታው ሰው ያልተሾመ ሲሆን፤ እስካሁንም ቦታው ክፍት ኾኖም አዲስ ሚኒስትር ዴኤታ ተሹሟል።

ከሳምንቱ አሳዛኝ ዜናዎች ውስጥ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሁለት ኢትዮጵያውያን መገኘታቸው መገለጹ ነው። እነዚህ ኢትዮጵያውያን የተገኙት በመካከለኛው ምሥራቅ ሲሆን፤ የኢትዮጵያ የጤና ሚኒስቴርም ይህንን አረጋግጧል። ቫይረሱን ለመከላከል በመንግሥት ደረጃ እየተሠራ ያለው ሥራም ጐልቶ የታየበት ሳምንት ነው። ካለፉት ስድስት ዓመታት ወዲህ ኢትዮጵያውያን ሴቶችን ሁሌም በታሪክ እንዲታወሱ የሚያደርገው፤ በሴቶች አብራሪዎች ብቻ የሚደረገው ጉዞ ዘንድሮም በማርች 8 ዋዜማ ዕለት ወደ ዋሽንግተን በረራ ተደርጓል።

በኢትዮጵያ የማስታወቂያ ኢንደስትሪ ውስጥ እንደ ፈር ቀዳጅ የሚታወቁት አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ ሥርዓተ ቀብር የተፈፀመበት ሳምንት ነው። ከቢዝነስ ነክ ዜናዎች በሳምንቱ መጨረሻ ላይ የተሰሙት ሁለት ዜናዎች በተለየ ሊታዩ የሚችሉ ናቸው። አንደኛው በአፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ ላይ ይቀመጣል የተባለ የጫጩት መፈልፈያና ከዶሮ ጋር የተያዙ ምርቶች የሚመረቱበት ማምረቻ ተመርቆ ሥራ የጀመረ መኾኑ መገለጹ ነው። ሌላው በአዲስ አበባ በቀን 80 ሺሕ ዳቦ ማምረት ይችላል የተባለው “ሸገር ዳቦ ማምረቻ” የኮንስትራክሽን ሥራው ተጠናቅቆ፤ የማሽን ተከላ መጀመሩን የሚያመለክተው ነው።

ከሰሞናዊ ዜናዎች ውስጥ በዓባይና የህዳሴ ግድብን የተመለከተው ጉዳይ ላይ ትኩረት በማድረግ ከሳምንቱ የተመረጡ ዜናዎች የተወሰኑትን የኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል ተጠናክረው እንደሚከተለው ይቀርባሉ።

የዓባይ ጉዳይ በዘመነ ዐቢይ

የዓባይ ወንዝና የህዳሴ ግድብ ጉዳይ ወቅታዊ አገራዊ አጀንዳ ኾኗል። ግብጽ በቀጥታም ኾነ በተዘዋዋሪ በዓባይ ውኃ ላይ የበላይ ለመኾን ያላትን ገደብ የለሽ ፍላጎት ለማርካት፤ በዘመናት መካከል እያደረገች ከነበረው ጥረት ሁሉ በአደባባይ ጐልቶ ከተስተጋባባቸው ጊዜያት ውስጥ የሰሞኑ በተለየ የሚታይ ነው። የአገሪቱ ባለሥልጣናትና ሚዲያዎች ይህንኑ እያንጸባረቁ ይገኛሉ። ዲፕሎማቶችዋ የዐረብ አገሮች ከግብጽ ጐን እንዲቆሙ ለማድረግ በሸረበችው ሴራ፤ ዐረብ ሊግ ለኢትዮጵያ ምቹ ያልኾነ ውሳኔ እንዲያሳልፉ ያደረገችው በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ነበር።

የግብጽ ለየት ያለ እንቅስቃሴ ግን በኢትዮጵያ በኩል የበለጠ ጠንከር ያለ አቋም እንድትይዝ እድል የሠጠ፤ ሕዝቡንም ወደ አንድ አመለካከት ያሰባሰበ ኾኗል። ይህም ካሳለፍነው ሳምንት መጀመሪያ ቀን ጀምሮ ሳምንቱን ሙሉ በዚህ ጉዳይ ላይ በርካታ መልእክቶች እንዲተላለፉ አድርጓል። ከወቅታዊው የዓባይና የህዳሴ ግድብ አንፃር ባሳለፍነው ሳምንት የመጀመሪያውን መግለጫ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ከሠጠ በኋላ በማግስቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩና የመስኖ፣ ውኃና ኢነርጂ ሚኒስትሩ የሠጡት መግለጫ፤ አሜሪካ በትሬዠሪ ዲፓርትመንት በኩል የወጣው መግለጫ ያልተገባ መኾኑን አፅንኦት ሠጥታ አስታውቃለች። በዓባይ ወንዝ የመጠቀም መብቷን በሌላ አካል የሚወሰን ያለመኾኑን ከማንጸባረቁም በላይ፤ ግብጽ የሚበጃት አሁንም ድርድሩ መኾኑን ያሳወቀበት መግለጫ ነበር። በዚህ መግለጫ ላይ የኢትዮጵያ አቋም ጠንካራ መኾኑን የሚያሳየው፤ ኢትዮጵያ የግድቡን ውኃ መሙላት ሥራ በያዘችው እቅድ መሠረት የምትጀምር መኾኑን እንዲታወቅላት ማወጇ ነው። ይህ የኢትዮጵያ አቋም በግልጽ ከተነገረ በኋላ፤ ግብጽ የዐረብ ሊግ በዓባይ ጉዳይ ግብጽ የምታራምደውን አቋም የሚደግፍ የውሳኔ ሐሳብ እንዲያሳልፍ ማድረጓ ነው። በግብጽ ይሽከረከራል የተባለው ዐረብ ሊግ ይህንን ውሳኔ ማሳለፉ ግን፤ በኢትዮጵያ ወገን ቁጣ መቀስቀሱ አልቀረም። በዚህ ላይም መንግሥት አንድ ነገር ማለት ነበረበትና በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር በኩል መግለጫ አውጥቷል። የዐረብ ሊግን መግለጫ ከማውገዝ አልፎ ተቀባይነት የሌለውና በጭፍን የተወሰነ በሚል የሊጉን ለግብጽ ያደላ ወገንተኝነት ተችቷል። እዚህ ላይም ዓባይን የመጠቀም መብቷን በማሳወቅ፤ የምሠራው ሥራ አግባብ ነው በማለት ለዐረብ ሊግ የውሳኔ ሐሳብ ያጣጣለችበትን መግለጫ አውጥታለች።

በዚህ ጉዳይ ከዐረብ ሊግ አገሮች ሱዳን የዐረብ ሊግ የውሳኔ ሐሳብን በመቃወም የወሰደችው አቋም በመልካም የሚታይ ሲሆን፣ በጅቡቲና በሶማሊያ ነገር ደግሞ ያስተዛዘበ መኾኑ አልቀረም። በተለይ ጅቡቲ ከኢትዮጵያ ጋር ካላት ግንኙነት አንፃር በዚህ ውሳኔ ውስጥ ስሟ መነሳቱ እንደ ኢትዮጵያ መጐርበጡ አልቀረም። የዓባይና የህዳሴ ጉዳይ እንዲህ ያሉ ተመሳሳይ ክስተቶችን ያሳለፈ ቢኾንም፤ የግብጽና የአሜሪካ አካሔድ ምን ሊያስከትል እንደሚችል ባይታወቅም፤ ኢትዮጵያ ጥቅሟን የሚያስነካና ሉዓላዊነትን የሚጋፉ ተግባራት እንደማትፈጽም፤ ሕዝብም ኾነ ዓለም እንዲያውቅላት በማድረግ፤ ግድቡን ለመጨረስ የሚያስችሉ ተግባራት ላይ እንድታተኩር እድል ሠጥቷታል። አዳዲስ የገቢ ማሰባሰቢያ ፕሮግራሞች የተሰናዱ ሲሆን፤ ይህም በፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በይፋ እንዲጀመር ተደርጓል።

በሳምንቱ ውስጥ በህዳሴ ግድብና ከወቅታዊ ሁኔታው አንፃር በይፋ ሐሳባቸውን የሠጡ ምሁራን፣ ታዋቂ ሰዎች በተከታታይ የተደመጡ ሲሆን፤ በተለይ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ገዱ አንዳርጋቸው “የዓባይ ግድብ እየተሠራ ያለው በኢትዮጵያ ሉአላዊ ግዛት ነው። እየተገነባ ያለው በኢትዮጵያ ሕዝብና መንግሥት ጥሪት ነው። ወንዙ የሚመነጨውና የሚፈሰው በኢትዮጵያ ሉአላዊ ግዛት ውስጥ ነው። ወደ ኢትዮጵያ ከታችኛው ተፋሰስ አንድ ኩባያ ውኃ አይፈስም። ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን የመጠቀም ሙሉ መብት አላት” የሚለው ይጠቀሳል። አያይዘውም ሌሎች አገሮችን ጥቅም እንዳይጐዳ ነው ጥንቃቄ የምናደርገው። ይህ ማለት ዓባይ የእኛ መብት አይደለም ማለት እንዳልኾነ ሊታወቅ ይገባል። በፉከራና በዛቻ የትኛውም አገር አያተርፍም ብለዋል።

በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በሚደረጉ ድርድሮች ላይ ዋነኛ ተሳታፊ የሆኑት ኢንጂነር ዶክተር ስለሺ በቀለም፤ ከሰሞኑ ሕዝቡ በድርድሩ ዙሪያ ያለውን ግንዛቤ ለማሳደግ ተከታታይ ማብራሪያ ሠጥተዋል። የኢትዮጵያ ፍላጐት ምን እንደኾነ አስቀምጠዋል። በድርድሩ ወቅት የግብጽ አደነቃቃፊ ተግባራትም ምን ምን እንደኾኑ በመግለጽ አስረድተዋል። ግድቡ ያለበትን ደረጃና በቀጣይ ኢትዮጵያ የምትሠራቸውን ሥራዎች ያመላከቱት ሚኒስትሩ፤ በተለይ ከውኃ አሞላሉ ጋር የጠቀሱት አንድ ነገር ቢኖር፤ የግድቡን የውኃ ሙሌት በተያዘው ፕሮግራም መሠረት ኢትዮጵያ የምትጀምር መኾኑን ነው። ለሰሞኑ ውዝግብ እንደ ዋና መነሻ ተደርጐ የሚወሰደው የአሜሪካን የትሪዠሪ ዲፓርትመንት (ግምጃ ቤት) መግለጫ ነበርና፤ ይህ መግለጫ ኢትዮጵያ ያልተወደደና ጣልቃ ገብነትን ያመለከተ ስለነበር ተገቢው ምላሽ ተሠጥቶበታል።

ይሁንና ይህ የዲፓርትመንቱ መግለጫ ተገቢ ያለመኾኑን የገለጹት ኢትዮጵያውያንና የኢትዮጵያ መንግሥት ብቻ አለመኾኑን የተመለከትንበት ሳምንት ኾኗል። ከኢትዮጵያ አልፎ በአሜሪካ ኮንግረስ አባላት ጭምር የዲፓርትመንቱ መግለጫ ተቃውሞ ቀርቦበታል። የኮንግረስ አባላቱም በጉዳዩ ማብራሪያ እስከመጠየቅ ደርሰዋል። የቀድሞው አምባሳደር ዴቪድ ሺንም ጉዳዩን በተመለከተ “የአሜሪካ መንግሥት ለግብጽ ያደላ ሥራ እየሠራ መኾኑን በግልጽ ተናግረው፤ በኢትዮጵያ፣ በግብጽና በሱዳን መካከል ያለውን ድርድር አሜሪካ በታዛቢነት የምትከታተል ቢኾንም፤ በውኃ አሞላሉ ዙሪያ የአሜሪካ ግምጃ ቤት ያወጣው መግለጫ ግራ የሚያጋባ ነው” ብለውታል። ተደራደሪ አገራቱ ስምምነት ላይ ስለመድረሳቸው በይፋ ሳይታወቅ አሜሪካ ያወጣችው መግለጫና ድርድሩ ሳይቋጭ ግድቡን የውኃ መሙላት እንዳይደረግ ማለቷንም “አስገራሚ” በማለት ገልጸውታል። አሜሪካ መግለጫ መሥጠት ካለበት በውጭ ጉዳይ ሚኒስትር በኩል ነበር ብለው ነገሩን “አድሏዊ” ብለውታል። የአፍሪካ ሕብረት ደግሞ፤ መፍትሔው ሦስቱ አገራት ድርድራቸውን ይቀጥሉ የሚል ነው።

በተለይ ኮአሜሪካ ኮንግረስ አባላት መካከል ኮንገረስ ማንስቴቨን ሃናስፎርድ የአሜሪካኑን የግምጃ ቤት ዲፓርትመንት ኃላፊን የሞገቱበትና ዲፓርትመንቱ ያወጣው መግለጫ መድሎ ያለበት፣ ኢትዮጵያ ላይ ተፅዕኖ ያደረገ ነው በማለት አውግዘዋል። እንዲህ ያለውን ውሳኔ የማይቀበሉ መኾኑንና አሁንም ኢትዮጵያን ልትሰሟት ከፈለጋችሁ ትመጣለች በማለት ያላቸውን አቋም ገልጸዋል። በተመሳሳይ ሌሎች የኮንግረስ አባላትም ተመሳሳይ ሐሳባቸውን የገለጹበት ሳምንት ነበር።

ከውጭ ያለው ምልከታ እንዲህ ያለው እየኾነ ባለበት ሰዓት፤ በአገር ውስጥም ይኸው የዓባይ የሰሞኑ ትኩሳት ኢትዮጵያውያንን ወደ አንድ መስመር እያመጣ ነው። በሰሞኑ ጉዳይ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል በሚባል ደረጃ፤ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ያለው አመለካከት በቶሎ ግንባታውን የመጨረስ ስለመኾኑ በተከታታይ በየሚዲያዎቹ እየተሠጡ ያሉ አስተያየቶች ያመለክታሉ።

ለግድቡ ድጋፍ በማድረጉ በኩል በተወሰነ ደረጃ ተቀዛቅዞ የነበረ ሲሆን፤ ከሰሞኑ ግን የገንዘብ ድጋፍ የማድረግ እንቅስቃሴ እንደገና መታየት ጀምሯል።

በፍላጐት ጭምር ከሰሞኑ መታየት የጀመረው ሌላው እውነት፤ የተለያዩ የሙያ ማኅበራትና ተቋማት ጉዳዩ ይመለከተናል በማለት አቋማቸውን እያንጸባረቁ መኾኑን ነው። ከእነዚህ ውስጥ የአማራ ምሁራን መማክርትና የኢትዮጵያ ዩኒቨርሲቲት የምክክር መድረክ ይገኙበታል። በተለይ የዩኒቨርሲቲዎቹ የምክክር መድረክ ባወጣው መግለጫ፤ በታላቁ የህዳሴ ግድብ ግንባታ ዙሪያ ኢፍትሐዊ የኾነ ውሳኔ ለመወሰንና ለማስወሰን አንዳንድ ኹነት የተዛባ ውሳኔ እንዲሠጥ ጫና ለመፍጠር እየጣሩ ይገኛሉ ብሏል። በአንድ ወቅት ተመሳሳይ የተዛባ ውሳኔ በLeague of Nations ሲተላለፍ የወቅቱ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር የነበሩት የሚከተለውን ብለው ነበር።

“አገሬ ኢትዮጵያ በዓለም ሸንጎ ላይ ፍርድ ተነፍጓት ስታዝን የመጀመሪያ ጊዜ አይደለም። ለነፃነቷና ለመብቷ ከኮሎኒያልስት ጣሊያን ጋር በየጊዜው ስትዋጋ ያሸነፈችውም ብቻዋን ነው። የተጠቃችውም ብቻዋን ስለሆነ፤ አገሬ መቼውንም በሚደርስባት አደጋ ከማንም እርዳታ አገኛለሁ ብላ አትጠብቅም።”

“ዛሬም ኾነ ነገ ነፃነቷን ለመጠበቅ፣ ታሪኳን ለማስከበር አስፈላጊውን ዝግጅት ማድረግ አለባት። እሷ እራሷ ብቻ ናት፤ እንዳሉት ሁሉ አሁንም ያለን ትውልዶች የተዛባውን ሚዛን ማስተካከል ያለብን እኛው ነንና የዓድዋውን ድል በተባበረው በአያቶቻችን ክንድ እንዳሸነፍነው ሁሉ፤ የህዳሴውንም ግድብ በተባበረው አንድነታችን፣ ክንዳችንና ሀብታችን ሠርተን የምንጨርሰው መኾናችንን እያረጋገጥን፤ አቋማችንን በጋራ ስንገልጽ መነሻ ያደረግነው የግድቡ መገንባት በአገሪቱ ፍትሐዊ ተጠቃሚነት ላይ ልዩነት እንደሌለው፣ ኮሎኒያሊስቶች አፍሪካንና ሀብቷን ለመቀራመት አውጥተውት የነበረና አሁን የሚያፈሩበት የ1029 እና የ1929 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ባልተወከለችበት የሕግ ተገዥ የምትኾንበት ሕጋዊም ኾነ አመክኖያዊ ነገር የሌለ መኾኑን፣ የአገራችን ምሁራን በሠሯቸው ጥናቶች ግድቡ የሚገነባው ለመሬት መንቀጥቀጥ ተጋላጭ ባልኾነ ቦታ ከመኾኑ በተጨማሪ፤ ውኃው ግብጽ ወይም ሱዳን ላይ ቢከማች ኖሮ በትነት የሚባክነውን ውኃ ስለሚያስቀር ተመራጭ የሚያደርገው መኾኑን ነው።

“ከዚህ በላይ በቀረበው መነሻነትም ከዚህ በታች የተዘረዘሩትን ባለ ስድስት ነጥብ የአቋም መግለጫ አውጥተናል።

  1. የጀመርነው እውን ለማድረግ ሁለንተናዊ ድጋፍ እንደምናደርግ እናረጋግጣለን፣
  2. የህዳሴው ግድብ የአንድነታችን ተምሳሌት በመኾኑ በዘር፣ በኃይማኖትና በፖለቲካ አመለካከት ልዩነት ሳይኖር የመንግሥትን አቋም የኢትዮጵያ ሕዝብ እንዲደግፍ እንጠይቃለን።
  3. እኛ ጠግበን በብርሃን እየኖርን፤ እናንተ በረሃብና በጨለማ ኑሮ ከሚልና እራስ ወዳድ አስተሳሰብን በፅኑ እናወግዛለን።
  4. እኛ የኢትዮጵያ የመንግሥት ዩኒቨርሲቲ አመራሮች በመላው ዓለም የሚገኙ ኢትዮጵያውያንና ትውልደ ኢትዮጵያውያን የየድርሻቸውን እንዲወጡና ዲፕሎማሲያዊ ጫና እንዲያሳድሩ ጥሪያችንን እናስተላልፋለን።
  5. የዐረብ ሊግ በኢትዮጵያ ህዳሴ ላይ ሰሞኑን የወሰደውን ኢ-ፍትሐዊ ውሳኔ እየተቃወምን፤ የአፍሪካ ሕብረት እንዲህ ዐይነት ጣልቃ ገብነትን እንዲቃወምና መርኅንና ሕግን መሠረት በማድረግ ከኢትዮጵያ ጐን እንዲቆም እንጠይቃለን።
  6. የአሜሪካ መንግሥት በታዛቢነት ገብቶ ሀብትና የዲፕሎማሰያዊ ኃይሉን በመጠቀም ወደ አደራዳሪነት እራሱን ከማሸጋገር በላይ፤ የወሳኝነት ሚና ያለው የሚመስል መግለጫ ማውጣቱን አጥብቀን እንቃወማለን።” በማለት የኢትዮጵያ መንግሥት ዩኒቨርሲቲዎች የምክክር መድረክ ገልጿል።

ይህንን የግድብ ሥራ አጠናቅቆ ለአገልግሎት ማብቃት ቀዳሚ አጀንዳ ከመኾን አልፎ ከወትሮው በተለየ ስለግድቡ እስካሁን ሲደረጉ ስለነበሩ ድርድሮችና አጠቃላይ የግድቡ ወቅታዊ ሁኔታ ዝርዝር መረጃዎች እየተሠጡም ነው።

በዚህ ግድብ ዙሪያ እየታየ ያለው መነቃቃት ከውጭ እየተቃጣ ያለውን ጣልቃ ገብነት ለመከላከልና የሕዝቡንም አመለካከት ሁሉም እንዲያውቀው የሚያግዝ ሲሆን፤ አሁን በተናጠል እየተሠራ ያለውን ሥራ የበለጠ ያሳያል ተብሎ የታመነበት ታላቅ ሰልፍ መጋቢት 6 ቀን 2012 እንደሚካሔድ ታውቋል።

ይህ በአዲስ አበባ የሚካሄደው ሰልፍ፤ ኢትዮጵያውያን በህዳሴው ግድብ ላይ ያላቸውን አቋም ለማሳወቅ ሲሆን፣ ሁሉም የሕብረተሰብ ክፍል የበኩሉን እንዲወጣ ለማድረግ ነው።

ይህ ሰሞናዊው ትኩሳት በምን መንገድ መጓዝ እንዳለበት የተለያየ አስተያየት ቢሠጥም፤ ጉዳዩ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ መንግሥት ጊዜ ሊሠጡት የሚገባ ሥራ መኾኑ አልቀረም። መንግሥታቸው እየወሰደ ያለው አቋም እየተደገፈ ሲሆን፤ እርሳቸውም በተደጋጋሚ እንደገለጹት ግድቡ ማለቅ ባለበት ጊዜ አለማለቁ አሁን እንደመጣው ዐይነት ጥያቄዎች ያስከተለ ቢኾንም፤ በምንም ሁኔታ ቢኾን የግድብ ሥራው እንደማይቆም አስረግጠው ተናግረዋል። በዚህ ሳምንት በግድቡ ዙሪያ ከተናገሩት መካከል፤ "በአሁኑ ሰዓት የሚያስፈልገው ጀግንነት በአንድነት ኾኖ ታላቁን የህዳሴ ግድብ ማጠናቀቅና ኢትዮጵያ ከራስዋ አልፎ ለጐረቤቶቿ የኃይል ምንጭ ማድረግ ነው” ማለታቸው ይጠቀሳል። (ኢዛ)

በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ኢትዮጵያውያን ጉዳይ

የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን መግታት አልተቻለም። ቫይረሱ በሁሉም አቅጣጫ እየተዛመተ ነው። ቫይረሱ ከተዳረሰባቸውና በብዛት በቫይረሱ የተጠቁና ሕይወታቸውን ያጡ ዜጐች ተበራክተው ካሉበት የሩቅ ምሥራቅ አገሮች ሌላ፤ በመካከለኛው ምሥራቅ አገሮችም አዳዲስ የቫይረሱ ተጠቂዎች መገኘታቸው እየተገለጸ ነው።

ካሳለፍነው ዓርብ ጀምሮ ከተባበሩት ዐረብ ኤምሬትስ እየተሠራጩ ያሉ ዘገባዎች የኢትዮጵያን ስም የጠቀሰ መኾኑ ድንጋጤ መፍጠሩ አልቀረም። የተባበሩት ዐረብ ኤምሬትስን የጤና ሚኒስቴር ዋቢ በማድረግ የተለያዩ ዓለም አቀፍ ሚዲያዎች እንደገለጹት፤ በተባበሩት ዐረብ ኤምሬትስ ከተገኙት 45 የቫይረሱ ተጠቂዎች ውስጥ ሁለቱ ኢትዮጵያውያን መኾናቸውን የሚጠቁም ነው።

ይህ መረጃ ከዓርብ የካቲት 27 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ የተለያዩ መገናኛ ብዙኀን የተቀባበሉት ነው። ይህንን ዘገባ ተከትሎ የጤና ሚኒስቴር እንዳስታወቀውም ሁለት ኢትዮጵያውያን በቫይረሱ መያዛቸውን ለማረጋገጥ ችሏል። በመካከለኛው ምሥራቅ በኮሮና ቫይረስ መጠቃታቸው የተነገረው ሁለት ኢትዮጵያውያን፤ ነዋሪነታቸው እዚያው የተባበሩት ዐረብ ኤምሬትስ ውስጥ ሲሆን፣ እስካሁን ማንነታቸው አልተገለጸም።

ኾኖም በዚህ ጉዳይ ላይ የኢትዮጵያ ጤና ሚኒስቴር እንደገለጸው በእነዚህ ሁለት ኢትዮጵያውያን ጉዳይ ሁለቱ ኢትዮጵያውያን በቅርብ ጊዜ ወደ ኢትዮጵያ የጉዞ ታሪክ እንዳላቸው ለማወቅ መረጃ ሲያሰባስብ እንደነበር ነው። ነገር ግን የተገኘው መረጃ እነዚህ ሁለት ኢትዮጵያውያን ወደ ኢትዮጵያ በቅርብ የጉዞ ታሪክ የሌላቸው መኾኑን ለማረጋገጥ መቻሉን ነው። ባለፉት ሁለት ዓመታት እዚያው የሚኖሩ መኾናቸውን ማረጋገጥ መቻሉን መረጃው ጠቁሟል። በሌላ በኩል ግን ቫይረሱ ወደ ኢትዮጵያ ይገባል የሚለው ሥጋት ባየለበት በዚህ ወቅት፤ እንዲህ ያለው ዜና ከአገር ውጭ መሰማቱ ደግሞ ቫይረሱን ከመከላከል አንፃር ኢትዮጵያ እየሠራች ያለውን ክትትልና ተያያዥ ሥራዎች አጠናክራ እንድትቀጥል ያመላከተ ነው።

የካቲት 27 ቀን 2012 ዓ.ም. የኢትዮጵያ ማኅበረሰብ ጤና ኢንስቲትዩት እንደገለጸው፤ የቫይረሱ ምክትል የታየባቸው ሁለት ሰዎች በለይቶ ማቆያ ክትትል እያደገባቸው ሲሆን፤ የምርመራ ውጤታቸው እየተጠበቀ ነው። እስካሁን በተመሳሳይ በለይቶ ማቆያ እንደገቡ የተደረጉና ምርመራ የተደረገላቸው 27 ሰዎች፤ ከቫይረሱ ነፃ መኾናቸው ተገልጿል። እንዲህ ያሉ መረጃዎች መደጋገም የሚፈጥረው ሥጋት እንደተጠበቀ ኾኖ፤ ጤና ሚኒስቴርና የኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት በኮሮና ቫይረስ ላይ በተከታታይ መረጃዎችን እየሠጡ ሲሆን፤ በተንቀሳቃሽ ስልክም ቫይረሱ ያሳያል የተባሉ ምልክቶችን ከተመለከቱ ጥቆማ ማድረሻ ስልክ ቁጥር እንዲደርስ አድርጓል።

ከዚህም ሌላ የካቲት 21 ቀን 2012 ዓ.ም. የኮሮና ቫይረስ መከላከልና ተያያዥ ጉዳዮችን ለመምራት የተቋቋመው ብሔራዊ ኮሚቴ ባለፈው ቅዳሜ ስብሰባ ተቀምጦ እንደነበር ተገልጿል። ቅዳሜ የካቲት 28 ቀን 2012 ዓ.ም. ምክትል ጠቅላይ ሚኒስትር ደመቀ መኮንን የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል እየተሠሩ ያሉ ሥራዎችን፤ ከሌሎች ጉዳዩ ከሚመለከታቸው ባለሥልጣናት ጋር ኾነው ጐብኝተዋል። በኢትዮጵያ ሕብረተሰብ ጤና ኢንስቲትዩት ውስጥ የሚገኘውንና በአገር ውስጥ የቫይረሱ ሥርጭት የመረጃና የመቆጣጠሪያ ማዕከል እያደረገ ያለውን ዝግጅትም ተዘዋውረው ጐብኝተዋል ተብሏል። እንዲህ ያሉ ዝግጅቶች ቫይረሱ በኢትዮጵያ ቢከሰት እንኳን ከቁጥጥር ውጭ እንዳይወጣ ያግዛል ተብሏል። (ኢዛ)

ከፍተኛ የመንግሥት ኃላፊዎች የተሰናበቱበት “ሹመት”

ከሰሞኑ ሚኒስትርና ሚኒስትር ዴኤታዎችን ጨምሮ በተለያዩ የመንግሥት ኃላፊነት ላይ የነበሩ 15 የመንግሥት ተሿሚዎች፤ በአንድ ጊዜ አምባሳደር ኾነው መሾማቸው ለብዙዎቹ እንግዳ ነበር።

ማክሰኞ ከመደበኛው የመንግሥት ሠራተኞች መውጫ ሰዓት አካባቢ ከአገሪቱ ፕሬዝዳንት ቢሮ የወጣው መግለጫ፤ እነዚህ 15 አምባሳደር ኾነው መሾቸው በተገለጸበት ወቅት ብዙዎቹ እስከ ዕለቱ በሚታወቁበት ኃላፊነት ላይ ኾነው ከቢሮዋቸው እንደነበሩ ውስጥ አዋቂዎች ይገልጻሉ። ብዙዎች እንደሚገምቱት ይህንን ያህል ቁጥር ያለው ከኃላፊነታቸው ስለመነሳታቸው ሳይገለጽ የአምባሳደርነት ሹመት ስለማግኘታቸው ሲገለጽ የመጀመሪያ ሊሆን ይችላል ብለዋል።

ኾኖም መሾማቸው እንጂ ከኃላፊነት መነሣታቸውን የማይገልጸው ከፕሬዝዳንት ቢሮ የወጣው መረጃ፤ በተዘዋዋሪ እነዚህ 15 ሰዎች ይዘውት ከነበረው ኃላፊነት ስለመልቀቃቸው የሚያረጋግጥ መኾኑ አልቀረም።

ገና የምደባ ቦታቸው ካልለየው ከእነዚህ ተሿሚዎች ውስጥ፤ በየትኛውም አገር ቁልፍ የሥልጣን ቦታ ተደርገው ከሚወሰዱ አንዱ የኾነውን የጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ የሚመሩት አቶ ብርሃኑ ፀጋዬን፣ የሴቶች ወጣቶችና ሕፃናት ሚኒስትሯና ሁለት የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሮች ይገኙበታል። በኢትዮጵያ ኢኮኖሚ ውስጥ የጐላ ሚና ያለው የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳን አቶ ባጫ ጊናም አምባሳደር ኾነው ተሹመዋል ከተባሉት ውስጥ ስማቸው ተዘርዝሯል። ይህም እነዚህ 15 ባለሥልጣናት ይዘውት በነበረው ቦታ አዳዲስ ተሿሚዎች ይተካሉ ማለት ነው። እስካሁን ባለው መረጃ ከ15ቱ በአንዱ ቦታ ብቻ አዲስ ተሿሚ ተመድቧል። ይህ ሹመት በፍጥነት የተከናወነው ቦታው ክፍተት ሊፈጠርበት የሚችል በመኾኑ ነው።

ይህም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ፕሬዝዳንት በመኾን ሲያገለግሉ በነበሩት በአቶ ባጫ ምትክ አቶ አቤ ሳኖ ተሹመዋል። አቶ አቤ ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ መጥተው የባንኩ ፕሬዝዳንት መኾናቸው የተገለጸው አቶ ባጫ በተሾሙ ማግስት በመኾኑ፤ ለዚህ ቦታ ቀድሞ ዝግጅት መደረጉን አመላክቷል። ምክንያቱም አቶ አቤ የአቶ ባጫን ቦታ መተካታቸው እስከተነገረበት ጊዜ ድረስ፤ የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ፕሬዝዳንት በመኾን እያገለገሉ ነበርና ነው።

በተሰናባቹና በአዲሱ ፕሬዝዳንት መካከል ርክክብ የተደረገውም አዲሱ ሹመት በተገለጸ ማግስት ነው። ርክክቡ ኬክ በመቁረስ ጭምር የተደረገ ሲሆን፤ በዚያው ዕለት አቶ አቤ ከኢትዮጵያ ንግድ ባንክ ማኔጅመንት አባላት ጋር ተዋውቀው አዲሱ ቢሯቸውን ተረክበዋል። አቶ አቤ ከዚህ ቀደም የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን ከሁለት ዓመት በላይ በፕሬዝዳንትነት ያገለገሉ ናቸው። የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ የመጀመሪያው ፕሬዝዳንት ሲሆኑ፤ በዚሁ ኃላፊነታቸው ከ10 ዓመታት በላይ አገልግለዋል።

አቶ ባጫ የኢትዮጵያ ንግድ ባንክን በፕሬዝዳንትነት ያገለገሉት ወደ አንድ ዓመት ተኩል አካባቢ ነው። ሐምሌ 2010 ዓ.ም. ወደ ኢትዮጵያ ንግድ ባንክ እስኪመጡ ድረስ፤ የኦሮሚያ ኢንተርናሽናል ባንክ ምክትል ፕሬዝዳንት ኾነው ሲያገለግሉ እንደነበር ይታወሳል።

አቶ ባጫን ጨምሮ አብዛኛዎቹ የሥራ ኃላፊዎች እስከዚህ ሳምንት አጋማሽ ድረስ የነበራቸው ኃላፊነት ሁለት ዓመት የቆየ ዕድሜ ያልሞላቸው ናቸው። ከነበሩበት የኃላፊነት ቦታ ወደ አምባሳደርነት የተዛወሩበት ምክንያት አልተገለጸም። ኾኖም በእነዚህ ሰዎች ላይ የተገኘ ነገር ቢኖር ነው የሚለው መላምት ግን መሰማቱ አልቀረም። የሥራ አፈፃፀማቸው ሊሆን ይችላል የሚሉም አልታጡም። ነገር ግን የፖለቲካ ውሳኔ ያለበት መኾኑ ይታያል። አሁን የአምባሳደር ሹመታቸው የት የት አገር ያርፋል? የሚለውና በእነርሱ እግር የሚተኩት እነማን ናቸው የሚለው ጥያቄ ከሰሞኑ መልስ ያገኛል ተብሎ ይጠበቃል። (ኢዛ)

የጫጩትና የዳቦ ማምረቻዎች

ከሳምንቱ ቢዝነስ ነክ ዜናዎች ውስጥ በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙም ባልተለመደ ሁኔታ ከፍተኛ መጠን ያለው የጫጩት ማምረቻ ወደ ሥራ መግባቱና በልዩ ክትትል እየተገነባ ያለው ግዙፍ የዳቦ ማምረቻ የኮንስትራክሽን ግንባታው ተጠናቅቆ የማሽነሪ ተከላ መጀመሩ ነው።

በኢትዮጵያ ግዙፍ የሚባለውና በአፍሪካ በሁለተኛ ደረጃ ላይ እንደሚቀመጥ የተነገረለት “ኢትዮ ቺክን” የተባለው የጫጩት ማስፈልፈያ ፋብሪካ የተገነባው በናዝሬት ሲሆን፣ ቅዳሜ የካቲት 28 ቀን 2012 ዓ.ም. ተመርቋል። ይህ ፋብሪካ በሳምንት 700 ሺሕ ጫጩቶችን የማስፈልፈል አቅም አለው። ከ150 ሚሊዮን ብር በላይ ኢንቨስት የተደረገበት ነው። ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴና የኦሮሚያ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሽመልስ አብዲሳ በተገኙበት ፋብሪካው ተመርቋል። ይህ ፋብሪካ በይፋ ቅዳሜ ይመረቅ እንጂ፤ ካለፈው ዓመት ጀምሮ ሥራ ላይ የነበረ ሲሆን፤ በዚህ አንድ ዓመት ውስጥ ከ20 ሚሊዮን በላይ ጫጩቶችን በማስፈልፈል ማከፋፈሉ ተገልጿል።

ሌላው በአዲስ አበባ ከተማ ውስጥ እየተገነባ ያለው ግዙፍ የዳቦ ማምረቻ የሥራ ሒደትን የሚመለከተው መረጃ ነው። “ሸገር ዳቦና ዱቄት ፋብሪካ” የሚል መጠሪያ የተሠጠው ግዙፍ ፋብሪካ፤ በመንግሥት ልዩ ክትትል እየተገነባ ነው። በሜድሮክ ኢትዮጵያ እየተገነባ ያለው ይህ ፋብሪካ፤ የግንባታው ሥራ ሲጀመር በስድስት ወር እንዲጠናቀቅ ታስቦ ነው። ነገር ግን አጠቃላይ ሥራው በጥቂት ወራት መዘግየትም ቢሆን እንደሚጠናቀቅ ለማወቅ ተችሏል።

በቀን ከ80 ሺህ በላይ ዳቦ የሚያመርተው ይህ ፋብሪካ፤ በአሁኑ ወቅት ሙሉ የኮንስትራክሽን ግንባታው አልቆ የማሽነሪ ተከላ መጀመሩና ትናንት የካቲት 29 ቀን 2012 ዓ.ም. የአዲስ አበባ ከንቲባ በተገኙበት በተደረገ ጉብኝት ለማረጋገጥ ተችሏል። ይህም ይህ ግዙፍ ፋብሪካ በሁለት ወር ውስጥ ሥራ የሚጀመር መኾኑን አመላክቷል። የዚህ ፋብሪካ ሥራ መጀመር በአነስተኛ ዋጋ ዳቦ ለማቅረብ ያስችላል ተብሎ ይጠበቃል።

መንግሥት ለዚህ ፋብሪካ በተለየ ትኩረት መሥጠቱን የሚያመላክተው የግንባታውን ሒደት ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በግንባር በመገኘት መመለከታቸው አንዱ ሲሆን፤ ከንቲባ ኢንጂንየር ታከለ ኡማ በተደጋጋሚ ወደ ግንባታው ቦታ በመሔድ ሥራውን መከታተላቸው ነው። ፋብሪካው ከተጀመረ ጊዜ ወዲህ ከአምስት ያላነሰ ጊዜ የሥራ ሒደቱን በቦታው ተገኝተው አይተዋል። (ኢዛ)

በሴት ቀን የኢትዮጵያውያን ሴት አብራሪዎች ታሪካዊ በረራ ቀጥሏል

ያሳለፍነው ሳምንት በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚከበረው የዓለም የሴቶች ቀን ያረፈበት ነው። በሳምንቱ የመጨረሻ ቀን ላይ የዋለው ማርች 8 በኢትዮጵያ በተለያየ መልኩ የሚከበር ነው። ይህንኑ በዓል በተመለከተ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ፤ እናቶችና እኅቶቻችን ደጀን ኾነው ሳይደግፉት የተገኘ አንድም ኢትዮጵያዊ ድል ያለመኖሩን በመግለጽ፤ የሴችን ሥራዎች ያወደሱበትን መልእክት አስተላልፈዋል።

ከቅርብ ዓመታት ወዲህ ግን ኢትዮጵያ ማርች 8ን ዓለም በተለየ የሚያየውን አንድ ክንውን የምትፈጽምበትና “ሴቶች ይችላሉ!” የሚለውን በተግባር የምታሳይበትን ታሪካዊ ክንውን ትፈጽማለች። ይህም በሴት የበረራ ባለሙያዎች የምታደርገው በረራ ነው።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ ከማርች 8 ጋር በተያያዘ በሴቶች ብቻ የሚመራ ታሪካዊ የበረራ ፕሮግራሙን ዘንድሮም ወደ ዋሽንግተን አድርጓል።

በኢትዮጵያውያን የበረራ ባለሙያዎች እየተመራ የሚደረገውን የዘንድሮውን በረራ ፕሬዝዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ በተገኙበት ሽኝት የተደረገለት ሲሆን፤ ከአዲስ አበባ ተነስቶ በደብሊን በኩል ወደ አሜሪካ የሚያቀና ነው። ትናንት የካቲት 29 ቀን 2012 ዓ.ም. እኩለ ቀን አካባቢ ደብሊን ደርሷል። በሴቶች ብቻ የሚመራው በረራ፤ ዛሬ አሜሪካ ዋሽንግተን ዲሲ ይደርሳል።

ባለፉት አምስት ተከታታይ በረራዎች በስኬት የተጠናቀቀ ሲሆን፤ ዘንድሮም ይኸው እየተተገበረ ነው። ከፓይለቶች ጀምሮ ሙሉ የበረራው አባላት ሴቶች የኾኑበትን የኢትዮጵያ አየር መንገድ ባለሙያዎችን ወደ ዋሽንግተን ለመሸኘት የተዘጋጀው ፕሮግራም ላይ እንደተገለጸው፤ ከአየር መንገዱ በአመራር ሠጪነትና በተለያዩ የኃላፊነት ቦታዎች ላይ ከሚገኙት ውስጥ 32 በመቶው ሴቶች መኾናቸው ተገልጿል።

የኢትዮጵያ አየር መንገድ በሴቶች የሚመራው የበረራ ቡድን ውስጥ ፓይለቶች፣ ግራውንድ ቴክኒሻኖች፣ የበረራ ቴክኒሻኖች፣ ሆስተሶችና ሌሎች የበረራ አባላቱ በሙሉ ሴቶች ናቸው።

ኢትዮጵያ በታሪክ ውስጥ ለመጀመሪያ ጊዜ በሴቶች ብቻ የሚመራ በረራ አንድ ብላ የጀመረችው ኅዳር 2008 ዓ.ም. ነው። ከዚህ ከመጀመሪያው በረራ በኋላ በረራውን ከማርች 8 ጋር በማስተሳሰር ዘንድሮ ለስድስተኛ ጊዜ ወደ አሜሪካ መብረር ችለዋል። (ኢዛ)

የባለ ካባው ማስታወቂያ ነጋሪ ሽኝት

በኢትዮጵያ ውስጥ ዘመናዊ የማስታወቂያ ባለሙያ አቶ ውብሸት ወርቃለማሁ ሥርዓተ ቀብር የተፈጸመው በዚህ ሳምንት ነበር። በኢትዮጵያ የማስታወቂያ ሥራ በእርሳቸው ትክክል የሥራ ባለሙያ እንደሌለ ስለእርሳቸው ምስክርነት የሚሠጡ የዘርፉ ባለሙያዎች ሲገልጹ ተደምጧል። ለዘመናዊ የማስታወቂያ ሥራ መጀመርና በዘርፉ በርካቶች እንዲጓዙ በማድረግም የነበራቸው አስተዋጽኦ ከፍተኛ እንደነበር ተገልጿል። አቶ ውብሸት በሙያቸው አንቱ ከመባል ባለፈ የተለያዩ ተቋማትንም በመምራት የሚታወቁ ሲሆን፤ እንደማሳያ የሚጠቀሰው የአዲስ አበባ ንግድ ምክር ቤትና የኢትዮጵያ ንግድ ምክር ቤትን ፕሬዝዳንት ኾነው ማገልገላቸው ነው።

ከትከሻቸው ካባ ጣል በማድረግ የሚታወቁት ውብሸት ወርቃለማሁ፤ ኢትዮጵያዊነትንና አንድነትን በማቀንቀን የሚታወቁ ነበሩ። አቶ ውብሸት ባደረባቸው ሕመም በሕክምና ሲረዱ ቆይተው በ82 ዓመታቸው ማረፋቸው ታውቋል።

ለጥቂት ባለውለታዎች እንደሚደረገው ሁሉ በመስቀል አደባባይ አስከሬናቸው ሽኝት ተደርጐላቸው፤ የካቲት 25 ቀን 2012 ዓ.ም. የቀብር ሥርዓታቸው በቅድስሥላሴ ካቴድራል ተፈጽሟል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ