Ethiopia Zare's weekly news digest, week 30th, 2012 Ethiopian calendar

ከመጋቢት 21 - 27 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

የዓመቱ ሠላሳኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች

ኢዛ (ከመጋቢት 21 - 27 ቀን 2012 ዓ.ም.)፦ ያሳለፍነው ሳምንትም ቀዳሚ መነጋገሪያ ሆኖ የቀለው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝና ከዚሁ ጋር ተያያዥነት ያላቸው ጉዳዮች ናቸው። በኢትዮጵያ አንፃር ሰሞናዊውን የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ የሚመለከቱ መረጃዎች በተለየ የሚታየው ከቀዳሚዎቹ ሦስት ሳምንት የበለጠ ቁጥር ያላቸው ተጠቂዎች መገኘታቸው ሪፖርት መደረጉ ነው። ከዚህም ሌላ የመጀመሪያዎቹ ሁለት በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ሕይወት ማለፉም የተነገረው ባሳለፍነው ሳምንት የመጨረሻ ቀን ነው።

እስከ እሁድ መጋቢት 27 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ በኮሮና ቫይረስ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር 43 ደርሷል። ከዚህ ውስጥ ከአንድ ሦስተኛ በላይ የሚኾነው የተገኘው ባሳለፍነው ሳምንት ነው። ከሰኞ መጋቢት 21 ቀን 2012 እስከ መጋቢት 27 ቀን 2012 ዓ.ም. ብቻ በኮሮና ቫይረስ የተጠቁት ሰዎች ቁጥር 16 ኾኗል። ይህ ማለት በኮሮና ቫይረስ የተያዘ ሰው ኢትዮጵያ ውስጥ መገኘቱ ከተገለጸበት መጋቢት 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ጀምሮ በአራት ሳምንታት ውስጥ ከፍተኛ ቁጥር የተመዘገበበት ሳምንትና ሁለት ሕይወታቸው ያለፉ ተጠቂዎች የተገለጸበት ነው። ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ባሳለፍነው ሳምንት የተከናወኑ በርካታ ተግባራት የነበሩ ሲሆን፤ በተለይ የክልል መንግሥታት የትራንስፖርት እንቅስቃሴዎችን ማገታቸው አንዱ ነው። ከአዲስ አበባ ውጭ የኮሮና ቫይረስን ለመመርመር የሚያስችሉ እንቅስቃሴዎች እንደሚጀመሩ መገለጹም ከሳምንቱ ዐበይት ጉዳዮች አንዱ ነው።

እንደ ኢትዮጵያ ሁሉ የጐረቤት አገሮች ሪፖርቶች የሚያመለክቱት ቫይረሱ ከመቼውም ጊዜ በላይ እየተሠራጨ መኾኑንና አሳሳቢነቱም ጐልቶ መምጣቱን ነው። እስከ እሁድ መጋቢት 27 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ ጅቡቲ ከ35 በላይ የቫይረሱ ተጠቂዎች መገኘታቸው ስትገልጽ፣ ኬንያ 122፣ ሶማሊያ 7፣ ኤርትራ 29 ተጠቂዎችን አስመዝግበዋል። ሌሎቹም አገሮች ከሚያደርጉት ሪፖርት መገንዘብ ተችሏል። እስከ መጋቢት 26 ቀን 2012 ዓ.ም. ያለ መረጃ በአፍሪካ ከስምንት ሺሕ በላይ የቫይረሱ ተጠቂዎች ተመዝግበዋል። 330 በላይ ሞተዋል።

ይህ ጉዳይ የአፍሪካ አገራትን እያሳሰበ በመምጣቱ መንግሥታት በቴሌ ኮንፈረንስ በተደጋጋሚ እየመከሩበት ነው። ምን መፍትሔ ይመጣል የሚለውን ወሳኝ ጥያቄ በምን መልኩ ለመመለስ እንደሚችሉ ባይታወቅም መረጃዎቹ በጋራና በተናጠል የሚያደርጓቸውን ምክክር ቀጥለዋል።

ከሰሞኑ ከዚሁ ጉዳይ ጋር በተያያዘ ጐልቶ የታየው ቫይረሱን ወረርሽኝ ለመከላከል የኢትዮጵያ መንግሥት የተለያዩ የንብረትና የገንዘብ ድጋፎችን እያሰባሰበ ሲሆን፤ የተለያዩ ግለሰቦችና ባለሀብቶች ለለይቶ ማቆያና ማከሚያ እንዲያገለግል ሕንፃዎቻቸውንና ቤቶቻቸውን መንግሥት እንዲጠቀምበት መፍቀዳቸው ነው። እንዲህ ያለው ልገሳ በአዲስ አበባ የሚታወቁ ትላልቅ ሕንፃዎች እና ሆቴሎች ለዚሁ አገልግሎት እንዲውሉ ተሠጥተዋል። በክልልም እንዲሁ የተደረገ ሲሆን፣ በብሔራዊ ደረጃ እየተሰበሰበ ካለው የገንዘብና የንብረት ድጋፍ ባሻገር፤ ክልሎችም በየአካባቢያቸው ቫይረሱን ለመከላከል ለሚያስፈልገው ዝግጅት ገንዘብና ንብረት እያሰባሰበ ነው። የክልሎቹን ሳይጨምር በብሔራዊ ደረጃ ለተደራጀው የእርዳታ አሰባሳቢ ኮሚቴ እስካሁን ከ200 ሚሊዮን ብር በላይ ጥሬ ገንዘብ ከተለያዩ ግለሰቦችና ተቋማት ተለግሷል። በተለይ እስካሁን ድጋፍ ያደረጉ ከ10 የሚበልጡ ባንኮችና ኢንሹንስ ኩባንያዎች ከ100 ብር በላይ መለገሳቸው ተገልጿል።

እንዲህ ያሉበት ተግባራት በተለያዩ መልኩ እየታየ ቢኾንም፤ በግብይት ውስጥ ግን አሁንም ያልተገቡ ተግባራት መስተዋላቸው አልቀረም። በዚህ ምክንያት ሕገወጥ የንግድ ሥራ ሲፈጽሙ ነበሩ የተባሉ ከ15 ሺሕ በላይ ነጋዴዎች የተለያየ እርምጃ የተወሰደባቸው መኾኑ የተገለጸውም በዚህ ሳምንት ነው። ባእድ ነገሮችን ቀላቅሎ የእጅ ማጽጃ በሚል ሲሸጥ መያዙም ከሰሞኑ አሳዛኝ ወሬዎች አንዱ ነው። በዚህ ሳምንት ክፍሎች የአገሪቱ ክልሎች በተለየ በከተማ ውስጥ የሚደረጉትን እንቅስቃሴዎች እንደማይቋረጡ የገለጸው የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ነው።

በዚህ ሳምንት ዐበይት ከነበሩት ዜናዎች መካከል ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ የአዲስ አበባ ከንቲባ የሠጡት መግለጫ ነው። በዚህ መግለጫቸው ይበልጥ ትኩረት ያገኘው አንደበታቸው አዲስ አበባ እንቅስቃሴን እንደማይገታና ቁጥጥር እያደረገ እንቅስቃሴው እንዲቀጥል መወሰኑንም ምክትል ከንቲባ ታከለ ኡማ ገልጸዋል።

ሌላው የሳምንቱ ዐበይት ዜና ምርጫ ቦርድ ቀጣዩን ምርጫ በያዘው የምርጫ ሰሌዳ መሠረት ለመከወን ያለመቻሉን መግለጸ ነው። ይህንን በይፋ ካስታወቀ በኋላ እስካሁን ሁለት የፖለቲካ ድርጅቶች ብቻ አካሔዱን በመቃወም መግለጫ አውጥተዋል። በሶማሌ ክልል ተፈጠረ የተባለው ችግር ሌላው አነጋጋሪ ዜና ነበር። በክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት ላይ መፈንቅለ መንግሥት ተሞከረ የተባለ ቢሆንም፤ ቆይቶ የወጣው መረጃ ግን የክልሉን የጸጥታ ኃይል ኃላፊ በአዲስ እንዲተኩ መደረጉን የሚገልጽ ኾኗል።

የሃይማኖት ተቋማት የየእምነቱ ተከታዮች በቤት ኾነው ጸሎት እንዲያደርሱ የወሰኑትም በዚህ ሳምንት ነበር። ሌላው የሳምንቱ ዐበይት ክንውን ተደርጐ የሚወሰደው የህዳሴ ግድብ ግንባታ የተጀመረበት ዘጠነኛ ዓመትን በማስመልከት የተሠጡ መረጃዎች ናቸው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ኮሮናንም እንከላከላለን፤ ግድቡንም እንጨርሳለን ሲሉ፤ የግድቡን ፕሮጀክት የሚመሩ ኃላፊዎችም የግድቡ ሥራ 72.4 በመቶ መድረሱና በሐምሌ 2012 ዓ.ም. ግድቡን ውኃ መሙላት እንደሚጀመር በድጋሚ ያረጋገጡበትና በግድቡ ዙሪያ ሰፋ ያሉ ማብራሪያዎች የሠጡበት ሳምንት ነው። ከሳምንቱ ዐበይት ክንውኖች የተወሰኑት እንደሚከተለው በኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል ቀርቧል።

አፍሪካና የኮሮና ወረርሽኝ

ከሌሎች አህጉሮች አንፃር ሲታይ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭት በአፍሪካ አነስተኛ ቢመስልም፤ ቀስ በቀስ እየተስፋፋ መጥቷል። ሁኔታውም አሳሳቢ መኾን ጀምሯል። እስከ መጋቢት 26 ቀን 2012 ዓ.ም. ያሉ መረጃዎች በአፍሪካ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎች ቁጥር ከስምንት ሺሕ መብለጡ መረጃዎች እያመለከቱ ነው።

የጆን ሆፕኪንስ ዩኒቨርሲቲ መረጃና ሌሎች አኀአዛዊ መረጃዎች እንደሚጠቁሙት እስከ መጋቢት 26 ቀን 2012 ዓ.ም. ድረስ በአፍሪካ ከስምንት ሺሕ ሦስት መቶ (8,300) በላይ በቫይረሱ ተይዘዋል።

በዓለም አቀፍ ደረጀ በቫይረሱ ሕይወታቸውን ያጡ ሰዎች ቁጥር ከ65 ሺሕ መድረሱ የተነገረ ሲሆን፤ በዚሁ ቫይረስ የሞቱት ሰዎች ቁጥር ከ330 በላይ ነው።

በአፍሪካ ከ705 በላይ ሰዎች ደግሞ ከወረርሽኙ ማገገማቸውን ተነግሯል፤ ከአፍሪካ 1 ሺሕ 505 በቫይረሱ የተያዙ ሰዎችን በመያዝ ደቡብ አፍሪካ ቀዳሚ ነች።

በአልጄሪያም 1 ሺ 171 ሰዎች በቫይረሱ ሲያዙ፣ 105 ሰዎች ሕይወታቸው አልፎ፤ 65 ሰዎች ደግሞ እንዳገገሙ ይኸው የዩኒቨርሲቲው መረጃ ያሳያል።

በግብጽም እስካሁን ባለው መረጃ መሠረት 985 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፣ ከእነዚህም 216 ሲያገግሙ፤ 66 ሰዎች ሕይወታቸው አልፏል ተብሏል።

858 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ የተያዙበት ሞሮኮ ከእነዚህ ውስጥ 62 ሰዎች ሲያገግሙ 50 ሰዎች ሞተዋል።

የምሥራቅ አፍሪካ ወቅታዊ መረጃ እንደሚያሳየው ደግሞ እስከ መጋቢት 26 ቀን 2012 ባለው መረጃ ከፍተኛ ቁጥር ያለውን የኮሮና ቫይረስ ተጠቂ ያስመዘገበችው ኬንያ ናት። በኬንያ 122 ሰዎች በቫይረሱ እንደተያዙ ገልጻለች። ከእነዚህም 4 ሰዎች ሲያገግሙ፤ 4 ሰዎች ደግሞ ሕይወታቸው ማለፉን የሚያመለክት ነው።

በአፍሪካ አነስተኛ ሕዝብ ካላቸው ጥቂት አገሮች መካከል አንዷ የኾነችው ጅቡቲ 50 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ ተይዘውበታል። በኤርትራ 29 ሰዎች፣ በሶማሊያ 7 ሰዎች በቫይረሱ የተያዙ ሲሆን፤ እስካሁን የተመዘገበ ሞት ግን ሪፖርት አላደረጉም።

Total Coronavirus Cases in Ethiopia
በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ የተያዙ ሰዎችን ጠቅላላ ቁጥር፣ ከቀን ጋር በማዛመድ የተሠራ ግራፍ፤ የቀን አቆጣጠሩ እ.ኤ.አ. ነው።

በኢትዮጵያም እስከ እሁድ ድረስ 43 ሰዎች በኮሮና ቫይረስ መያዛቸው የተገለጸ ሲሆን፣ አራቱ ሲያገግሙ ሁለት ሞት ተመዝግቧል። ደቡብ ሱዳንም የመጀመሪያውን ተጠቂ ሪፖርት አድርጋለች። በእነዚህ አገሮችም የተጠቂዎቹ ቁጥር እየጨመረ መኾኑን ያመለክታል። (ኢዛ)

ጠቅላይ ሚኒስትሩና ተፎካካሪ ፓርቲዎች በኮሮና ዙሪያ

ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በአንፃራዊነት ከወራት ቆይታ በኋላ ከተለያዩ የአገሪቱ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በግንባር ተገናኝተው በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ መክረዋል።

በመድረኩ የኮሮና ቫይረስ በኢትዮጵያ ላይ የሚያሳድረውን ተፅዕኖ እና መንግሥት የሚወስዳቸውን ተጨማሪ እርምጃዎች በተመለከበ የተወያዩ ሲሆን፣ ውይይቱም ነገ ሰኞ መጋቢት 28 ቀን 2012 ዓ.ም. ይቀጥላል ተብሏል።

“አካላዊ ርቀትን ተግባራዊ ስለምናደርግ ሁሉንም የፖለቲካ ፓርቲዎች በአንድ ላይ ለማግኘት አይቻልም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ፣ በአነስተኛ ቡድን በመኾን ለሁለት ተከታታይ ቀናት ስብሰባው እንደሚደረግም ገልጸዋል።

ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት እሁድ መጋቢት 27 ቀን 2012 ዓ.ም. የተካሔደው ውይይት ገንቢ ነበር ብለዋል። ምስጋና በማቅረብም ከዚህ በኋላ በመቀጠል የሚካሔዱ ውይይቶችም ተመሳሳይ ውጤት እንደሚያስገኙ ያላቸውን እምነት የገለጹበት ነበር። (ኢዛ)

የጠቅላይ ሚኒስትሩ ምግብ የማካፈል ጥሪ

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባሳለፍነው ሳምንት ተከታታይ መግለጫዎችን ሠጥተዋል። በተለይ መጋቢት 25 ቀን 2012 በሠጡት መግለጫ ወረርሽኙን ለመከላከል ይቻል ዘንድና በቤት ቆይታውን ለማጠናከር በቀን አንድ ሰው ለመመገብ እንዲቻል ዜጐች እንዲዘጋጁ ጥሪ አቅርበዋል።

አንድ ቤተሰብ ለሌላ አንድ ቤተሰብ በቀን አንድ ምግብ ለማካፈል የሚያስችል ዝግጅት እንዲያደርግም አሳስበዋል።

ዶ/ር ዐቢይ “ማዕድ ማጋራት” በማለት በገለጹት በዚህ እሳቤ መንግሥት የኮሮና ወረርሽኝ የከፋ ጉዳት ቢያደርስ በየቤቱ ምግብ ለማድረስ አቅሙም ኾነ መንገዱ ስለማይኖረው፤ ሰዎች በምግብ እጦት እንዳይጎዱ አንድ ቤተሰብ በቀን አንድ ምግብ ሌላ ቤተሰብ ለማቅረብ ዝግጅት እንዲደረግ የሚያመለክት ነው።

ከዚህም ሌላ የዩኒቨርሲቲ መምህራን እና ወጣቶችም እረፍታቸውን ተጠቅመው ከዚህ ችግር እንዴት መሻገር እንደሚቻል ጥናት፣ ምርምር እና አዳዲስ የፈጠራ ሥራዎች እንዲሠሩ ጥሪ ያሳበቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የኪነጥበብ ባለሙያዎችም በኮሮና ቫይረስ ዙሪያ ወረርሽኙን ለማሸነፍ ተስፋ የሚሠጡ ሥራዎችን እንዲሠሩም ጠይቀዋል። (ኢዛ)

ኮሮና ያሰናከለው ምርጫና የሁለቱ ፓርቲዎች ተቃውሞ

በሌላ ወቅት ቢሆን በኢትዮጵያ ውስጥ ብዙ ውዝግብ ይፈጥር የነበረ በነሐሴ 2012 ዓ.ም. የሚካሔውን ምርጫ 2012 በጊዜ ሰሌዳዬ መሠረት ማድረግ አልችል ብሎ ብሔራዊ የምርጫ ቦርድ በዚህ ሳምንት አጋማሽ ላይ ይፋ ሲያደርግ፤ ግን ምክንያቱ ከኮሮና ቫይረስ ጋር የተያያዘ ነበርና ውሳኔው ይህ ነው የሚባል ተቃውሞ አላስተናገደም ማለት ይቻላል።

ቦርዱ በጊዜ ሰሌዳው መሠረት ምርጫውን ለማካሔድ እንደማይችል ውሳኔ ላይ ከመድረሱ በፊት የኮሮና ወረርሽኝን በተመለከተ ከፖለቲካ ፓርቲዎች ጋር በተደረገው ውይይት አብዛኞቹ ፓርቲዎች የችግሩን ግዝፈት እና በምርጫ ላይ የሚኖረውን ተጽእኖ ተገንዝበው ቦርዱ ከሚመለከታቸው የመንግሥት አካላት ጋር ተመካክሮ አማራጭ የአፈጻጸም እቅድ ሊኖረው እንደሚገባ መምከራቸውን ቦርዱ በዚሁ ጉዳይ ላይ ያወጣው መግለጫ አመልክቷል። ይሁን እና በዚህ አግባብ የሚወሰደው እርምጃ ችግሩ ከሚጠይቀው በላይ የኾነ መዘናጋት እንዳያመጣ ቦርዱ በወረርሽኙ አፈጻጸማቸው የማይስተጓጎል ሥራዎችን እንዲያጠናቅቅ አሳስበዋል።

ቦርዱ በውሳኔው መሠረት የሚኾነው የዳሰሳ ጥናት በአማካሪ ባለሙያዎቹ ተሠርቶ እንዲቀርብለትም አድርጓል። የተፈጠረው አጠቃላይ ሁኔታ ከታቀደው የምርጫ ምዝገባና ቀጣይ እርምጃዎች ላይ ሊያሳድር የሚችለውን ተፅዕኖ ባግባቡ ለመዳሰስ ያስችለው ዘንድ፤ በዳሰሳ ጥናቱ ላይ ተመሥርቶ ቦርዱ ሁለት የቢኾን ሁኔታ ግምቶች ማስቀመጡንም ከመግለጫው መገንዘብ ተችሏል።

በመኾኑም ቦርዱ እነዚህን የቢኾን ሁኔታ ግምቶች መርምሮ እንዲሁም ከባለድርሻ አካላት ጋር ካደረጋቸው ምክክሮች ያገኘውን ግብአት ታሳቢ በማድረግ ውሳኔ ላይ ሊደርስ መቻሉ ተገልጿል። በተፈጠረው ሁኔታ የተነሳ ቦርዱ ባወጣው የጊዜ ሰሌዳ መሠረት ምርጫውን ማካሔድ የማይቻለው መኾኑን በመረዳት ያወጣውን የጊዜ ሰሌዳ በመሰረዝ በሰሌዳው መሠረተ መከናወን ያለባቸው ተግባራት ለጊዜው እንዲቆሙ መወሰኑ አንዱ ነው።

ቦርዱ የወረርሽኙ ሥጋት ተወግዶ ሁኔታዎች ሲመቻቹ እንደገና ግምገማ በማድረግ አዲስ የምርጫ ኦፕሬሽን እቅድና ሰሌዳ በማውጣት እንቅስቃሴውን የሚያስጀምር ስለመኾኑም ገልጿል።

ቦርዱ ባደረጋቸው ምክክሮችና የዳሰሳ ጥናት ላይ በግልጽ የተለዩ፤ በኮቪድ 19 የማይስተጓጎሉ፣ የቦርዱን የምርጫ አፈጻጸም ዝግጁነት የሚጨምሩ፣ ሁኔታው ተቀይሮ፤ ተቋሙ ወደ መደበኛ ተግባሩ ሲመለስ በተገቢው ሁኔታ ምርጫን ለማስፈጸም የሚያስችል ሁኔታን የሚፈጥሩ ተግባራትን እያከናወነ መቆየት እንዳለበትም ምርጫ ቦርድ ወስኗል።

በሕገ መንግሥቱ በተቀመጠው መሠረት በሥራ ላይ የሚገኘው የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሥልጣን ጊዜው ከሚያበቃበት አንድ ወር አስቀድሞ ቦርዱ አጠቃላይ ምርጫውን ማድረግ የማይችል መኾኑን ምክር ቤቱ ተገንዝቦ፣ ከዚህ አንፃር የሚሠጠው ውሳኔ በኖር ለመነሻነት ያገለግለው ዘንድ ይህ ውሳኔ እንዲሁም ቦርዱ ያደረገው የዳሰሳ ጥናት ሰነድ ለሕዝብ ተወካዮች እንዲተላለፍ ስለመወሰኑም አስታውቋል። ይህ የምርጫ ቦርድ ውሳኔ የሚጠበቅ እንደነበር ብዙዎች ሲናገሩ ተሰምቷል። ከተፎካካሪ ፓርቲዎችም ዘንድ ይሄ ነው የሚባል አስተያየት ባይሠጥበትም በዚህ ጉዳይ ላይ ይፋዊ ትችት የሰነዘሩት ኦነግና ኦፌኮ ናቸው። ሁለቱም የፖለቲካ ፓርቲዎች ይፋዊ በኾነ መግለጫቸው፤

የኮቪድ-19 በአጠቃላይ በዓለም አቀፍ ማኅበረሰብ በተለይም በኢትዮጵያ እንዲሁም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የምርጫ 2012 እቅድና የጊዜ ሰሌዳ አፈጻጸም ላይ ተግዳሮቶችን ደቅኖ ቦርዱን እየተፈታተነ መኾኑን እንደሚረዱ ያመለከቱት ሁለቱ ፓርቲዎች፤ ይሁንና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ እዚህ ውሳኔ ላይ ለመድረስ የሔደበት መንገድ ትክክል አይደለም ብለው እንደሚያምኑ ገልጸዋል። ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ለሌላ ዙር የታቀደው ስብሰባ ሳይደረግ ቀርቶ ቦርዱ ሌላው ቢቀር በውስጥ መስመር እንኳ የፖለቲካ ፓርቲዎችን ሳያሳውቅ መጋቢት 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ያወጣው መግለጫና ውሳኔ አግባብ እንዳልኾነ ይጠቅሳሉ።

“ምርጫውን ለማራዘምም ኾነ ቀጣዩ እርምጃ ምን መኾን አለበት በሚለው ላይ ሁሉን ባለድርሻ አካላት ሳያማክር መንግሥትም ኾነ የትኛውም አካል አንዳች ውሳኔ እንዳያስተላልፍ አጥብቀን እናሳስባለን።” ያሉት ሁለቱ ፓርቲዎች የአገሪቱ ጉዳይ ይመለከተናል፣ ያገባናል ከሚሉት ባለድርሻ አካላት ጋር ውይይት፣ ክርክር፣ ምክክር እና ስምምነት ላይ ሳይደረስ በመንግሥት አካል ውሳኔ ብቻ ምርጫውን ማራዘምና ቀጣዩ የአገሪቱን ዕጣ ፈንታ ለመወሰን መሞከር የባሰ አገራዊ ቀውስ ሊያስከትል ይችላል የሚለውን እምነታቸውንም በዚሁ መግለጫቸው ላይ አካትተዋል።

ዴሞክራሲን ማስፈን፣ ግጭቶችን ማስወገድ እና የተፈጥሮ አደጋዎች መቆጣጠር ባልተቻለበት ሥርዓት፣ የአገሪቱ ኢኮኖሚ የተሽመደመደበት እና ማኅበራዊ ቀውሶች በተንሰራፉበት ሁኔታ ውስጥ ምርጫውን የማራዘም ውሳኔ ኾነ ከመስከረም 2013 በኋላ ሊኖር የሚችል መንግሥትን ለመወሰን አሁን ላለው መንግሥት ብቻ የሚተው ጉዳይ አይደለም ብለው እንደሚያምኑም ሁለቱ ፓርቲዎች በጋራ ያወጡት መግለጫ አመልክቷል።

“ምንም እንኳ ቦርዱ ለውጥ ለማምጣት ያደረጋቸው እንቅስቃሴዋች የሚያስመሰግኑት ቢሆንም፤ ግልጽነት የጎደላቸው አንዳንድ አሠራሮች በቦርዱ ላይ ያለንን እምነት እየሸረሸረ መኾኑን ቅሬታችንን መግለጽ እንወዳለን።” ያሉት ኦነግና ኦፌኮ የ2012 የኢትዮጵያ ምርጫን ለማራዘምም ኾነ በአጠቃላይ ቀጣዩ እርምጃ ምን መኾን አለበት ወይም ምን መደረግ አለበት በሚለው ላይ መንግሥት፣ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የሲቪክ ማኅበረሰብ ድርጅቶችና ሌሎች ባለድርሻ አካላት በተለይም መንግሥትና የፖለቲካ ፓርቲዎች ተገናኝተን ተከታታይ ውይይት እና ምክክር እንድናደርግና ሁላችንም ያሉንን አማራጭ ሐሳቦች ማቅረብ እንድንችል መንግሥት ሁኔታዎች እንዲያመቻችላቸውም ጠይቀዋል። (ኢዛ)

ለደቡብ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤት ኃላፊ ተሾመ

ከሰሞኑ የብልጽግና ፓርቲን ከሚመለከቱ ዜናዎች መካከል አንዱ የደቡብ ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መሰየሙን የሚመለከት ነው።

በዚህም መሠረት የደቡብ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽ/ቤትን በኃላፊነት እንዲመሩ አቶ ጥላሁን ከበደ ተሹመዋል። አቶ ጥላሁን በትምህርት ዝግጅት ሁለተኛ ዲግሪ ያላቸው ሲሆን፣ በቀድሞ የጋሞ ጎፋ ዞን ከወረዳ አመራርነት አንስቶ ዞን ዋና አስተዳዳሪነት ማገልገላቸው ተጠቅሷል።

የደቡብ ክልል ብልጽግና ፓርቲ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ ኾነው እስኪሾሙ ድረስም በደቡብ ብሔሮች፣ ብሔረሰቦችና ሕዝቦች ክልላዊ መንግሥት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የእርሻና ተፈጥሮ ሀብት ልማት ቢሮ ኃላፊ በመኾን ሲያገለግሉ ነበር ተብሏል። ከዚህም ሌላ የብልጽግና ፓርቲ ሥራ አስፈጻሚ ኮሚቴ አባል ናቸው። (ኢዛ)

የሶማሌ ክልል ግርግር እና መቋጫው

በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ከምሥራቁ የአገሪቱ ክፍል ከሶማሌ ክልላዊ መንግሥት ርዕሰ ከተማ ጅጅጋ የተሰማው ዜና በመልካም የሚታይ አልነበረም። ጉዳዩ ኦፊሻላዊ መግለጫ ሳይሠጥበት ቀኑን ሙሉ ሲንገዋለል የነበረው አጭር መረጃ በክልሉ ምክትል ርዕስ መስተዳድር አቶ ሙስጠፌ ኡመር ላይ መፈንቅለ መንግሥት ተደረገ የሚል ነበር። ይህ ዜና የጠራ ማረጋገጫ ሳይኖረው ውሎ መጨረሻ ላይ የተሰማው ዜና፤ መፈንቅለ መንግሥት ሳይሆን በአሠራር ደረጃ የነበረ አለመግባት መከሰቱን ነው። ይህም ያለመግባባት የክልሉ የጸጥታ ኃላፊ በመኾን ሲያገለግሉ የነበሩትን በአዲስ ለመተካት በተፈጸመው ሒደት ላይ ግን ግርግር ተፈጥሮ እንደነበር ነው።

ቆየት ብሎ የክልሉ መግለጫ እንዳስታወቀው ተፈጠረ ስለተባለው ግርግር የጠቀሰው ነገር ባይኖርም፤ ዶክተር ሁሴን ሀሺ ቃሲም የሶማሌ ክልል የፍትሕና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ ኾነው እንዲያገለግሉ በክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሙስጠፌ መሐመድ መሾማቸውን አስታውቋል። ዶ/ር ሁሴን ከአዲሱ ሹመታቸው ቀደም ብሎ የክልሉ ፕሬዝዳንት ከፍተኛ አማካሪ በመኾን ሲያገለግሉ የቆዩ ናቸው።

የዶክተር ሁሴን ከ19 ዓመታት በላይ በዓለም አቀፍ ልማት በሰላም ግንባታ እና ፖሊሲ ትንተና ዘርፎች የሠሩ ስለመኾኑም ተጠቅሷል። በፐፕሊክ ፖሊሲ የዶክትሬት ዲግሪያቸውን ማግኘታቸውንም መረጃው ያመለክታል።

እርሳቸው እንደተኳቸው የተደረጉት የቀድሞው የፍትሕና ጸጥታ ቢሮ ኃላፊ በምን ምክንያት እንደተነሱ አልተገለጸም። ምንጮች እንደጠቆሙት የሰሞኑ ግርግር የተፈጠረው የቀድሞው የቢሮ ኃላፊ መነሳት የለብኝም በማለታቸው እንደኾነ ነው። (ኢዛ)

አደገኛው ወንጀልና የባለሥልጣኑ ማሳሰቢያ

ከኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ ከሰሞኑ ከተሰሙ አሳዛኝ ዜናዎች ውስጥ አልኮልና እስፕሬ ፎርማሊ እና ሽቶ ጋር ቀይጠው የሸጡ ግለሰቦች በፖሊስ ቁጥጥር ሥር መዋላቸውን የሚመለከተው ይጠቀሳል።

በአዲስ አበባ ክፍለ ከተማ ወረዳ አንድ ልዩ ቦታ መርካቶ ምዕራብ ሆቴል አካባቢ አልኮልና እስፕሬ ፎርማሊና ሽቶ ቀላቅለው ሲሸጡ ነበር የተባሉትን አራት ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል። የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ለእጅ ጽዳት የሚያገለግለው አልኮል ያለውን ተፈላጊነት እንደ መልካም አጋጣሚ በመጠቀም እነዚህን የተለያዩ ምርቶች በመደበላለቅ ሲሸጡ የነበሩት ተጠርጣሪዎች የተያዙት በሕዝብ ጥቆማ ነው።

በተመሳሳይ ዜናም የኢትዮጵያ ምግብና መድኃኒት ባለሥልጣን ሳይመዘገቡና የብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ ሳያገኙ የተለያዩ ግለሰቦችና ተቋማት በሕገወጥ መልኩ የእጅ ንጽሕና መጠበቂያ (Hand sanitizers) ነው በማለት አምርተው ገበያ ላይ እያቀረቡ በመኾናቸው ሕብረተሰቡ ጥንቃቄ እንዲያደርግ ጠይቋል።

ባለሥልጣኑ በአሁኑ ወቅት የኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚያስፈልጉ የእጅ ንጽሕና መጠበቂያ ምርቶች በሕጋዊ መንገድ በስፋት ተመርተው ገበያ ላይ እንዲቀርቡ ጊዜያዊ ፍቃድ በመሥጠት ላይ ይገኛልም ብሏል። ኾኖም የገበያ ጥናትና ከሕብረተሰቡ በደረሰ ጥቆማ መሠረት፤ በባለሥልጣን መሥሪያ ቤቱ ሳይመዘገቡና የብቃት ማረጋገጫ ፍቃድ ሳያገኙ የተለያዩ ግለሰቦችና ተቋማት በሕገወጥ መልኩ የእጅ ንጽሕና መጠበቂያ አምርተው ገበያ ላይ እያቀረቡ መኾናቸውን በማስታወቅ፤ ሕብረተሰቡ ጥንቃቄ ያድርግ ብሏል። ትክክለኛ አይደለም ያላቸውን ምርቶችም በስም በመዘርዘር ሕብረተሰቡ እንዲያውቃቸው አድርጓል። (ኢዛ)

እስረኞችን መፍታት ቀጥሏል ምክንያቱ ኮሮና ነው

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በሺዎች የሚቆጠሩ የሕግ ታራሚዎችን ከእስር እንዲፈቱ እያደረገ ነው። በዚህ ሳምንትም ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ በተለያዩ የወንጀል ዐይነቶች የፍርድ ውሳኔ ያገኙና ይቅርታ ከተደረገላቸው 4011 የሕግ ታራሚዎች በተጨማሪ፤ በሁለተኛ ዙር ለ1559 የሕግ ታራሚዎች ይቅርታ መደረጉን አስታውቋል።

ይቅርታ የተደረገላቸው ታራሚዎች ዝርዝርም ከፌዴራል ማረሚያ ቤቶች አስተዳደር እስከ ሦስት ዓመት የተፈረደባቸው እና በአመክሮ ሊፈቱ ከአንድ ዓመት በታች የሚቀራቸው 1425 ታራሚዎች፣ የፌዴራል ማረሚያ ቤት አስተዳደር በቫይረሱ ሥጋት አዳዲስ ፍርደኞችን ባለመቀበሉ ምክንያት በአዲስ አበባ በ10ሩም ክፍለ ከተሞች በፖሊስ ጣቢያዎች ከሚገኙ ፍርደኞች ሦስት ዓመትና ታራሚ ኾነው በትግራይ ክልል የሚገኙ ከሦስት ዓመት በታች የተፈረደባቸው 19 ፍርደኞች እንዲሁም በሐረሪ ክልል ለሚገኙ 26 የፌዴራል ታራሚዎች በአጠቃላይ ለ1559 ታራሚዎች ይቅርታ እንደተደረገላቸው ታውቋል። በዚህ ሳምንት በተመሳሳይ ሁኔታ የደቡብ ክልልም ከ12 ሺህ በላይ የሚኾኑ ታራሚዎችን በይቅርታ እንዲፈቱ ወስኗል። (ኢዛ)

የታላቁ ህዳሴ ግድብ በኮሮና ዘመን

ያሳለፍነው ሳምንት የታላቁ ህዳሴ ግድብ ግንባታ የተጀመረበት ዘጠነኛ ዓመት የተወሳበት በተለያዩ ፕሮግራሞች የተዘከረበትም ነው።

የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጉዳይ ቀዳሚ አጀንዳነቱን ደብዘዝ አደረገው እንጂ የህዳሴ ግድብ ዘጠነኛ ዓመት አከባበር ከቀደሙት ጊዜያት በበለጠ ጐልቶ በታየ ነበር። ምክንያቱ ደግሞ ኢትዮጵያ በዓባይ ወንዝ የመጠቀም መብቷን የምደራደርበት ጉዳይ አይኾንም ብላ ዓለም ይስማልኝ ያለችበት ወቅት፤ የግድቡን ውኃ ለመሙላት የሦስተኛ ወገን ውሳኔ እንደማትጠበቅ በግልጽ የተናገረችበት፤ ውኃ ለመሙላት የተዘጋጀበት ወቅት በመኾኑ ነው።

ከሰሞኑ የግድቡ ግንባታ የተጀመረበት ዘጠነኛ ዓመት ለመዘከር በተዘጋጁ የፓናል ውይይቶችና የተለያዩ መግለጫዎች መገንዘብ እንደተቻለውም የኮሮና ቫይረስ ሥጋት ቢሆንም፤ የታላቁ ህዳሴ ግድብን የግንባታ ግስጋሴ የሚገታው ነገር አለመኖሩን ነው።

የውኃ፣ የመኖና ኢነርጂ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ፣ ኢትዮጵያ የምታከናውነው ግድብ ግንባታ ለሌሎች የውጭ አገራት ተፅዕኖና ለየትኛውም የአገር ውስጥ ችግሮች ሳይበገር ይቀጥላል ማለታቸውም ለዚህ አንድ ማሳያ ነው።

ሚኒስትሩ ግድቡ የተጀመረበትን ዘጠነኛ ዓመት አስመልክቶ በሠጡት መግለጫ እንደገለጹት፤ በመጪው ክረምት ሐምሌ 2012 ግድቡ 4 ነጥብ 9 ቢሊየን ሜትሪክ ኪዩብ ውኃ ለመያዝ የሚያስችለው ሥራ እየተሠራ ነው።

ስለዚህ ሕብረተሰቡ ይህንን አገራዊ ዕቅድ ከማሳካት ሊያግደው ከሚችለው ኮሮና ቫይረስ ተጋላጭነት እራሱን በመጠበቅ፣ ተሳትፎውን ማጠናከር እንደሚገባም አሳስበዋል።

ከሰሞኑ የግድቡ ግንባታ በቀጥታ ከሚመለከታቸው የተለያዩ መሥሪያ ቤቶች ኃላፊዎች ገለፃ ለመረዳት እንደተቻለው፤ የግንባታ ሥራው በሐምሌ ወር የውኃ ሙሌቱን ለማስጀመር በሚያስችል ደረጃ ላይ መኾኑን ነው። ከዚህ አንፃር የኢትዮጵያ የመብራት ኃይል ሥራ አስኪያጅ እንደጠቀሱት ደግሞ፤ “በተለያዩ ምክንያቶች ግድቡን በታቀደለት ጊዜ ውኃ መሙላት ባይቻል ግን አገሪቱ ግድቡ በአንድ ዓመት ያመነጨው ከነበረው ኃይል አንድ ቢሊዮን ዩሮ ገቢ ታጣለች” ብለዋል።

የፕሮጀክቱ የሲቪል ኢንጂነሪንግ ክንውን 86 በመቶና የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራው 44 ከመቶ የደረሰ ሲሆን፤ በአጠቃላይ የግድቡ ግንባታ 72.4 በመቶ እንደደረሰም ተናግረዋል። ግድቡን ለማስፈጸም እስካሁንም በጥቅሉ 13.4 ቢሊዮን ብር ገቢ በአገር ውስጥና በውጭ ከሚገኙ ዜጎች መገኘቱንም ለማወቅ ተችሏል።

ከሰሞኑ ግድቡን የሥራ እንቅስቃሴ በተመለከተ ሰፊ ማብራሪያ ከሠጡት መከከል የታላቁ ህዳሴ ግድብ ሥራ አስኪያጅ ኢንጅነር ክፍሌ ሆኖ ይገኙበታል። እርሳቸው ከተናገሩት ውስጥ፤ የግድቡ ሥራ ከብረታ ብረትና ኢንጂነሪንግ ኮርፖሬሽን (ሜቴክ) ተነጥቆ ሌሎች ኮንትራክተሮች ከተሠጠ በኋላ አመርቂ ውጤት መገኘቱን ነው።

ይህንን አባባላቸውን በማጠናከርም ግድቡ እንዳይጠናቀቅ መሰናክል ኾኖ ከቆየው ከሜቴክ ተነጥቆ የብረታ ብረት ሥራዎች ወደ ሁለትና ሦስት የተለያዩ ኮንትራክተሮች እንዲተላለፉ በማድረግ የተወሰነው ውሳኔና የተሠራው ሥራ አመርቂ ውጤት ማስገኘቱን አብራርተዋል።

ቀደም ሲል ሜቴክ ከሥራው ሲወጣ 25 በመቶ ብቻ የነበረው የኤሌክትሮ መካኒካል ሥራዎች አሁን 44 በመቶ መድረሱን በምሳሌነት ጠቅሰዋል። በሜቴክ ሲሠራ የነበረው የሃይድሮሊክ ስቲል ስትራክቸር የታችኛው ክፍል ውኃ ማስተንፈሻ የብረት ሥራዎች ጥራታቸውን ያልጠበቁ እና ብየዳቸውም በሙያዊ መንገድ የተገጠሙ ባለመኾናቸው እንዲነሱ ተደርጎ እንደገና በጥራት እየተገነቡ እንደሚገኝ በመግለጽም ልዩነቱን አመላክተዋል።

በሜቴክ ተሠርተው የነበሩ አንዳንድ የብረት ሥራዎች ተነስተው ድጋሚ መሠራታቸውን ያስታወሱት ሥራ አስኪያጁ፤ በብረት ሥራው ላይ ማስተካከያዎች ባይደረጉና እንደነበር ቢቀመጥ ኖሮ፤ ምናልባት አስር ዓመት አገልግሎ እንደገና ከባድ ጥገና ውስጥ የሚያስገባና አገሪቱም ላይ ከባድ ኪሳራ የሚያደርስ እንደነበር በዚሁ ገለጻቸው ላይ ተናግረዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ