Ethiopia Zare's weekly news digest, week 36rd, 2012 Ethiopian calendar

ከግንቦት 3 - 9 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

የዓመቱ ሠላሳ ስድስተኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች

ኢዛ (ከግንቦት 3 - 9 ቀን 2012 ዓ.ም.) ያሳለፍነው ሳምንት በአገሪቱ ለመጀመሪያ ጊዜ የሕገ መንግሥት ትርጓሜን በተመለከተ የሕግ ምሁራን በግልጽ የመከሩበት መድረክ ተዘጋጅቶ ውይይት የተደረገበት ነው። የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንትና የሕገ መንግሥት አጣሪ ኮሚቴ ሰብሳቢም በሕገ መንግሥቱን ትርጓሜ ላይ የተደረገ የመጀመሪያው መድረክ ስለመኾኑ ሳያመለክቱ አላለፉም። በዚህ መድረክ ላይ የሕግ ምሁራን የተለያዩ አስተያየቶችነ የሰጡበት ሲሆን፤ ሕገ መንግሥታዊ ትርጉም እንዲሰጥ መወሰኑ አግባብ እና የተሻለ አማራጭ ስለመኾኑ ብዙዎች የጠቆሙበት ነው።

የሳምንቱ ሌላው ዐቢይ ዜና የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ የ27 የፖለቲካ ፓርቲዎችን መሰረዙን መግለጹ ነው። ያልተጠበቀና አነጋጋሪ የነበረው በሕወሓት የተፈጠረ መኾኑ የሚነገርለት እና ዋና ጽሕፈት ቤቱን መቀሌ በማድረግ ከመንግሥት በተፃራሪ የቆመ ነው ተብሎ ይታመን የነበረው የፌዴራል ኃይሎች ጥምረት፤ ያሳለፈው ውሳኔ ነው። ከሕወሓት ውጭ በአዲስ አበባ ባካሔደው ስብሰባ ከዚህ ቀደም ሲያራምድ የነበረውን አቋሙን መቀየሩንና በምርጫው መራዘም ላይ ድጋፉን መስጠቱን አስታውቋል።

ሌላው ዐቢይ ዜና የነበረው የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የተዘጉ የቤተእምነቶች በሮች ተከፍተው በጥንቃቄ አገልግሎት እንዲጀምሩ መወሰኗ ነው። በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ድንጋጌዎችን ተላለፉ የተባሉ በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር የዋሉበት ሳምንት ኾኖ አልፏል።

ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር በተያያዘ መንግሥት የተለያዩ ኢኮኖሚያዊ ማሻሻያዎችን ያደረገ ሲሆን፤ እስካሁን የተደረጉ ማሻሻያዎችን በዚህ ሳምንት አጠናክሮ ይፋ ማድረጉ ከተጠቃሽ ሳምንታዊ ጉዳዮች ውስጥ ይካተታል። የሕወሓት በክልል ደረጃ ምርጫ አደርጋለሁ ብሎ የሰጠው መግለጫም ከሳምንቱ አነጋጋሪ ዜናዎች አንዱ ነበር። በእነዚህና በሌሎች ሳምንታዊ ክንውኖች ዙሪያ በኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ዝግጅት ክፍል የተጠናከረው ዘገባ እንደሚከተለው ይቀርባል። መልካም ንባብ!

የሕግ ባለሙያዎችና የሕገ መንግሥት ትርጉም

ባሳለፍነው ሳምንት ዐበይት ተብሎ ሊጠቀስ የሚችለው ዜና የሕገ መንግሥት ጉዳዮች አጣሪ ጉባዔ ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ለቀረበለት የሕገ መንግሥት ትርጉም ጥያቄ ምላሸ ለመስጠት ከባለሙያዎች አስተያየት ለማሰበሰብ ያዘጋጀው መድረክና በመድረኩ የተሰነዘሩ አስተያየቶች የሚመለከተው ነው። ጉባዔው ምርጫ በሚደረግበት ወቅት በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 93 ቁጥር 1 መሠረት ከአቅም በላይ የኾነ አደጋ፣ የውጭ ወረራ፣ ሕገ መንግሥቱን አደጋ ላይ የሚጥል ችግር፤ በሽታ ወይም ወረርሽኝ ሲከሰት ምን መደረግ አለበት? ሌሎች አገራት በሕገ መንግሥታቸው መሠረት የሚወስዱት አማራጭስ ምንድን ነው? የሚል ጥያቄ ለምሁራን ቀርቦ ምልከታቸውን ያንጸባረቁበት ነበር።

የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ከዓለም አቀፍ ተሞክሮዎች ጋር በማስተሳሰር ሐሳባቸውን የገለጹበት ሲሆን፤ የሕገ መንግሥት ትርጉሜን በተለከተ እንዲህ ያለ መድረክ ተዘጋጅቶ የማያውቅ በመኾኑ የብዙዎችን ትኩረት የሳበ ነበር።

በአገር አቀፍ ደረጃ የተከሰተውን ወረርሽኝ ለመከላከል ሲባል አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ መታወጁ አግባብ ስለመኾኑ ያመለከቱት የሕግ ባለሙያዎች፤ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ የታወጀበት ምክንያት በጣም አስፈላጊ የኾኑ ጉዳዮችን ቅድሚያ ለመስጠት እንደኾነ ያረጋገጡበት ነው ማለት ይቻላል። የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ የሚታወጀበት ጊዜ ምርጫ እንዲካሔድ ሕገ መንግሥቱ በደነገገበት ጊዜ ላይ ሲወድቅ፤ ሕገ መንግሥቱ ጥያቄውን ሊፈታ የሚያስችል ግልጽ ድንጋጌ ማስቀመጡን ማየት እንደሚገባም የምሁራኑ ማብሪሪያዎች አመልክተዋል።

የሕግ አጣሪ ኮሚቴ እና ፌዴሬሽን ምክር ቤት የተለያዩ ሐሳቦችን በመሰብሰብ ሕገ መንግሥቱን ማሻሻል ያስፈልጋል ወይም አያስፈልግም የሚለውን ለማየት መሥራት እንደሚያስፈልግ የጠቀሱም አሉ።

በምርጫ ጉዳይ ላይ የተለያዩ አገራት የተለያየ የሕገ መንግሥት የማሻሻያ አሠራር እንዳላቸው በማስታወስም፤ የኢትዮጵያም ጉዳይ ከዚህ አንፃር መታየት እንዳለበት ጠቁመዋል።

ምርጫ ለማካሔድ በርካታ ሥራዎች የሚያስፈልጉ በመኾኑ ሥራውን ሊያደናቅፍ የሚችል እንደ ወረርሽኝ እና ሌሎች ችግሮች ሲከሰቱ፤ አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ማወጅ እንደሚቻል ከእነዚህ የሕግ ምሁራን ማብራሪያ መገንዘብ ተችሏል።

በሕገ መንግሥት ምርጫ በሚደረግበት ወቅት የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ሲታወጅ ምን መደረግ እንዳለበት በግልጽ ስላላስቀመጠ መፍትሔው የሕገ መንግሥት ትርጉም መኾኑንም ይኸው በመጀመሪያው ቀን በተደረገ ውይይት መመልከት ተችሏል።

በዚህ መድረክ ላይ ጐልተው ከተሰጡት አስተያየቶች ውስጥ በኢትዮጵያ በተከሰተው የኮሮና ወረርሽኝ ምክንያት የታወጀው የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅና ምርጫን በተመለከተ የተለያዩ የሕግ ባለሙያዎች የተለያዩ ሐሳብ እንደሚሰጡ የተናገሩት የሕግ ምሁር ይሁኑ እንጂ፤ ሁሉም የሕግ ባለሙያዎች ባላቸው የቴክኒክ እውቀት ልክ አስተያየት ቢሰነዝሩም የመጨረሻውን ውሳኔ የሚያሳልፈው ሕገ መንግሥት የመተርጎም ሥልጣን የተሰጠው አካል መኾኑን ነው። ስለዚህ በኢትዮጵያ የተከሰተው ወቅታዊ ችግር መፍትሔ የሚያገኘው ሥልጣን በተሰጠው አካል የሕገ መንግሥት ትርጉም ሲሰጥበት መኾኑን አብራርተዋል።

በዓለም ላይ በአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ምክንያት 47 ምርጫዎች መራዘማቸውን የገለጹት ሌላው የአዲስ አበባ ዩኒቨርስቲ የሕግ ምሁር ደግሞ፤ እንደ ቦሊቪያ፣ ኬንያ፣ ብራዚል፣ ካናዳ፣ ጀርመን እንዲሁም ቺሊና ሩሲያ ያሉ አገሮች ክልላዊና ብሔራዊ ምርጫዎቻቸውን እንዲራዘሙ ማድረጋቸውን በመጥቀስ፤ በኢትዮጵያ ምርጫው እንዲራዘም መደረጉም ሕገ መንግሥታዊ መርህ ነው ብለዋል።

ከመጀመሪያው ቀን የውይይት መድረክ ከተጠናቀቀ በኋላም የተለያዩ የሕግ ባለሙያዎች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ከአገር መጥፋቱ ከተረጋገጠ ጊዜ በኋላ መንግሥት ለ11 ወራት በሥልጣን መቆየት የሚያስችለውን የሕገ መንግሥት የሥልጣን ትርጉም እንዲሰጠው የሚል ሐሳብ አቅርበዋል።

የጠቅላይ ፍርድ ቤት ፕሬዝዳንትና የሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ ሰብሳቢ ወይዘሮ መዓዛ አሸናፊም በበኩላቸው፤ ጉባዔው ምክረ ሐሳቦችን ሊቀበልም ላይቀበሉም የሚችል መኾኑን በማመላከት፤ በ10 ቀናት ውስጥ የውሳኔ ሐሳቡን ለፌዴሬሽን ምክር ቤት እንደሚያቀርቡ ገልጸዋል።

የኢትዮጵያ የሕግ ባለሙያዎች ማኅበርም “ምርጫ የሉዓላዊነት ጉዳይ ከመኾኑ በፊት የነበሩት የአገር ግዛት እና ሕዝብ ከመንግሥት ይልቅ ደኅንነታቸው ሊጠበቅ ይገባል” የሚለውን ሐሳቡን ያስታወቀ መኾኑንም ለማወቅ ተችሏል። በጥቅል ሲታይ አብዛኛዎቹ የሕግ ምሁራን ሕገ መንግሥት ትርጓሜውን አግባብነት እና የተሻለ አማራጭነት ያንጸባረቁ ናቸው ማለት ይቻላል።

ኢትዮጵያውያን የሕግ ባለሙያዎች በአራት ቀናት ውስጥ 15 የሕገ መንግሥት ትርጓሜ ጽሑፎች ከተለያዩ የዓለማችን ክፍሎች ለሕገ መንግሥት አጣሪ ጉባዔ እንደደረሰውም ታውቋል። (ኢዛ)

የፌዴራሊስት ኃይሎች ጥምረት ያልተጠበቀ ውሳኔና ሕወሓት

ሕወሓትን ጨምሮ 25 የሚኾኑ የፖለቲካ ፓርቲዎችን የያዘ ነው የተባለው እና በዋናነት በሕወሓት አስተባባሪነት የተቋቋመው የኢትዮጵያ ፌዴራሊስት ኃይሎች ጥምረት፤ የምርጫ 2012 በተመለከተ ቀድሞ ያራምደው የነበረውን አቋም በመለወጥ፤ አሁን ላይ የምርጫውን መራዘም እንደሚደግፍ ያስታወቀው በዚህ ሳምንት ነው። እስካሁን የተለያዩ ጉባዔዎቹንም በመቀሌ በማካሔድ የሚታወቀው ይህ ጥምረት፤ አስቸኳይ መደበኛ ስብሰባውን በአዲስ አበባ አካሒዷል። ቀደም ሲል በመቀለ ጉባዔና በሌሎች ስብሰባዎች ምርጫውን በተያዘለት የጊዜ ሰሌዳ መካሔድ አለበት ብሎ አቋሙን ሲገልጽ የነበረውን፤ አሁን ግን በአዲስ አበባ ስብሰባ በመቀመጥ ቀደም ብሎ ምርጫው መራዘም የለበትም የሚለውን አቋሙ ስሕተት በመኾኑ፤ መንግሥት ያቀረበውን የመፍትሔ ሐሳብ እንደግፋለን ብሏል።

ወቅቱ የኮሮና ቫይረስ የዓለምን ሁኔታ በብዙ መልክ እየቀየረ ያለበት መኾኑን በመግለጽም፤ የኢትዮጵያም ነባራዊ ሁኔታ ከዚህ የተለየ ስላልኾነ የወቅቱ ቀዳሚ አጀንዳ ኮሮናን መከላከልና የተደቀኑ የሉዓላዊነት ሥጋቶችን ማክሸፍ በመኾኑ፤ የምርጫ መራዘም ውሳኔውን እንቀበላለን በማለት ከሕወሓት የተለየ አቋሙን አሳውቋል።

በሰሞኑ የጥምረቱ መግለጫው ላይ ያከለው፤ “ጥምረቱ ለዜጎች ሁለንተናዊ ጥቅምና ለአገር ደኅንነት ለመታገል የተመሠረተ እንጂ የማንም ቡድን መልእክት ተቀባዮች አይደለንም” በማለት ከሕወሓት መመሪያ የሚሰጠው ነው የሚለውን ትችት አስተባብሏል።

የህዳሴ ግድብም በተባለበት የጊዜ ገደብ እንዲከናወንና ሕዝቡም ድጋፉን እንዳያቋርጥ ጥምረቱ ጠይቋል። የኢትዮጵያ ፌዴራሊስት ኃይሎች ጥምረት የመጀመሪያ ጉባዔውን በአዲስ አበባ ያደረገ ሲሆን፣ ይፋዊ ቢሮውን በከተማዋ መክፈቱንም አስታውቋል።

ይህ የጥምረቱ ኃይሎች ውሳኔ በብዙዎች ዘንድ ያልተጠበቀ መኾኑ የተገለጸ ሲሆን፤ ጥምረቱ ከሕወሓት እጅ ጠምዛዥነት አላቆታል ያስባለ ነው። ክስተቱ ለሕወሓት ሽንፈት መኾኑን የሚገለጹ ያሉ ሲሆን፤ በአዲስ አበባው ስብሰባ ላይ ያልነበሩ ጥቂት የጥምረቱ አባላት ግን አብዛኛዎቹ የጥምረቱ አባላት የወሰዱት ውሳኔ ሕገወጥና አግባብ አይደለም የሚል አስተያየት ሰጥተዋል። የጥምረቱ ሊቀመንበር ግን ከዚህ በተቃራኒ የተወሰደው እርምጃ አግባብ ነው ብለዋል። በሌላ በኩል ደግሞ ግንባት 7 ቀን ወደ መቀሌ ለማምራትና ስብሰባ ለመቀመጥ በቦሌ አውሮፕላን ማረፊያ የነበሩ አምስት የጥምረቱ አባላት መታሰራቸውን የትግራይ ኮሙዩኒኬሽን ቢሮ አስታውቋል። እነዚህ ታሰሩ የተባሉት ሰዎች በአዲስ አበባ ከብልጫዎቹ የጥምረቱ አባላት ያሳለፉትን ውሳኔ ያልተቀበሉ ናቸው ተብሏል። (ኢዛ)

የቤተክርስቲያን በሮች እንዲከፈቱ ተወሰነ

ኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ኢትዮጵያ ውስጥ መከሰቱ ከተገለጸ ጊዜ ወዲህ የተለያዩ እንቅስቃሴዎችን ገድቧል። በተለይ የሃይማኖት ተቋማት በየእምነት ቦታዎቻቸው ይሰጡዋቸው የነበሩትን ሃይማኖታዊ አገልግሎትም እንዳያከናውኑ እስከ ማድረግ ደርሷል። ለቫይረሱ ሥርጭት ምክንያት ሊኾን እንደሚችል ታምኖ ቤተ እምነት ተገኝቶ ሃይማኖታዊ ሥርዓትን መፈጸም ለጊዜው እንዲገታ የሁሉም የእምነት ተከታዮች ለተከታዮቻቸው ባስተላለፉት መልእክት፤ ቤተእምነቶች የዘወትር ተግባራቸውን ከመከወን ተቆጥበው ቆይተዋል። ባሳለፍነው ሳምንት ግን የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን ለሳምንታት ተቋርጦ የቆየውን የቤተክርስቲያን አገልግሎት መልሶ ለማስጀመር ስለመወሰኗ አስታውቃለች። ይህም የቤተክርስቲያኗ ውሳኔ የተቋረጠው የቤተክርስቲያን አገልግሎት ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ እንዲቀጥል በማሰብና ይህንንም ለማስፈጸም ያስችላል ያለችውን አሠራር በመተግባር እንደኾነም አስታውቃለች።

ቤተክርስቲያኗ እዚህ ውሳኔ ላይ መድረሷን በማስመልከት ብፅዕ ወ ቅዱስ አቡነ ማትያስ የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋሕዶ ቤተክርስቲያን ፓትርያርክ እንደገለጹት በቤተክርስቲያኗ አጥቢያዎች የሚሰጠው አገልግሎት መቋረጡ በምእመኑ መንፈሳዊ ሕይወት ላይ ችግር ማስከተሉን እና ፍጹም ጥንቃቄ በተሞላበት መንገድ አገልግሎቱ እንዲቀጥል ሲኖዶሱ ስለመወሰኑም አስታውቀዋል። (ኢዛ)

ወረርሽኙ ያስከተላቸው ኢኮኖሚያዊ እርምጃዎች

የኮሮና ወረርሽኝ የአገሪቱን ኢኮኖሚ እየፈተነ ከመኾኑ ጋር ተያይዞ፤ መንግሥት ይህንን ተፅእኖ ለመቋቋም የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰደ ነው። በሳምንቱ አጋማሽ ላይ የጠቅላይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት ይፋ ባደረገው መረጃ፤ በኮሮና ቫይረስ የተነሳ በተከሰተው የኢኮኖሚ መቀዛቀዝ ምክንያት አነስተኛ ገቢ ያላቸው የማኅበረሰብ ክፍሎች ተጨማሪ ቀውስ እንዳያገኛቸው የተለያዩ እርምጃዎች እየተወሰዱ መኾኑን አስታውቋል።

እስካሁንም የመኖሪያ ሁኔታን ማመቻቸት እና የቤት ኪራይን ጨምሮ ልዩ ልዩ ድጋፍ ማድረግ፣ ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል የሚደረጉ ልገሳዎች ተጠናክረው እንዲቀጥሉ ማበረታታት ሥራዎች ተሠርተዋል። የኢኮኖሚ መረጋጋት እና ከቀውስ ፈጥኖ ማገገምን ማረጋገጥ፣ በወረርሽኙ ክፉኛ ለተጎዱ የንግድ ተቋማት ድጋፍ ማድረግ፣ አገልግሎት ሰጪዎች እና አምራቾች ሥራቸውን እንዲቀጥሉ ማድረጉን መግለጫው አመልክቷል። በቅርቡም ከተወሰዱ እርምጃዎች መካከል ሚያዝያ 22 ቀን 2012 ዓ.ም. ውሳኔ የተሰጠባቸው ከ3099 ለሚበልጡ ግብር ከፋዮች እስከ 2015 የግብር ዓመት ማብቂያ ድረስ የሚቆይ ውዝፍ የግብር ክፍያ (ዋናውን ግብር፣ ወለዱን እና ተያያዥ ቅጣቶችን ጨምሮ) እንዲቀር ተደርጓል። ከዚህም ሌላ ከ2008 እስከ 2011 ዓ.ም. ያለው ጊዜ የግብር መጠን ትንተና የደረሰባቸው ግብር ከፋዮችን ወለድ እና ቅጣት እንዲሰረዝ መደረጉንና ግብር ከፋዮቹ ያለባቸውን ዋና የግብር መጠን 25 በመቶ በ30 ቀናት ውስጥ መክፈል የሚጠበቅባቸው ሲሆን፤ ቀሪውን 75 በመቶ ደግሞ የክፍያ ስምምነቱ ከተፈረመበት ቀን አንስቶ በአንድ ዓመት ጊዜ ውስጥ መክፈል እንዲችሉ የተወሰደውን እርምጃ አሳውቋል።

የጡረታ መዋጮ እስከ ሐምሌ 2012 ዓ.ም. ድረስ መተላለፉንና ለጥቃቅን እና አነስተኛ የንግድ ተቋማት የሚደረግ የብድር ድጋፍ፤ የኢትዮጵያ የልማት ባንክ ጥቃቅን እና አነስተኛ የንግድ ተቋማትን የገንዘብ እጥረት ለመፍታት ሲባል የብድር አገልግሎትን ያመቻቸ መኾኑንም በኢኮኖሚ ጉዳዮች ላይ ስለተወሰዱ እርምጃዎች የሚያትተው መረጃ ያሳያል። አገልግሎቱን ለማፋጠን ሲባል ደግሞ ይህንን ሥራ ብቻ የሚያከናውን መስኮት መዘጋጀቱን፤ እንዲሁም አነስተኛ የገቢ መጠን ያላቸውን የንግድ ተቋማት፣ ገበሬዎችን እንዲሁም የሸማቾች ማኅበራትን ለመደገፍ ሲባል ለአነስተኛ የብድር እና ቁጠባ ተቋማት እና ማኅበራትም ጭምር የብድር አገልግሎት ይቀርባል ተብሏል።

ምርቶቻቸውን ወደ ውጭ አገራት ለሚልኩ አምራቾች የሚደረግ ድጋፍ፤ በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን አማካኝነት በሚደረግ ግምገማ መሠረት፣ ምርቶቻቸውን ለዓለም አቀፍ ገበያ መላክ ያልቻሉ አምራቾች ለሚቀጥሉት ሁለት ወራት ምርታቸውን ለአገር ውስጥ ተጠቃሚዎች እንዲያቀርቡ ይፈቀዳል።

በቅርቡ የተወሰዱ እርምጃዎች ከመጋቢት እስከ ሚያዝያ 2012 ለአደጋ ጊዜ ወጪ የሚኾን መጠባበቂያ አምስት ቢሊዮን ብር (150 ሚሊዮን ዶላር) ስለመመደቡና ኮሮና ቫይረስን ለመከላከል ከሚያገለግሉ ግብአቶች ላይ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች ላይ የሚጣል ግብር እንዲቀር መደረጉ በመንግሥት ከተወሰዱ እርምጃዎች መካከል ተጠቃሽ ኾነው በመግለጫው ላይ ታትቷል።

ለንግድ ሥራዎች የተጨማሪ እሴት ታክስ ተመላሽ በቀልጣፋ ሁኔታ እንዲካሔድ መደረጉን፣ በባንኮች ተቀማጭ የሚኾን ጥሬ ገንዘብ እና የብድር አሰባሰብ ሁኔታ የሚቀንስ መኾኑን ከግምት ውስጥ በማስገባት ለባንኮች የ21 ቢሊዮን ብር (630 ሚሊዮን ዶላር) ድጋፍ መደረጉንም አስታውሷል። ይህም በኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ጫና ለደረሰባቸው ዘርፎች የሥራ ማስኬጃ ካፒታል ኾኖ የሚያገለግል ነው።

ለውጭ ምንዛሬ አስገቢዎች እና ከኮሮና ቫይረስ ጋር ተያያዥነት ያላቸውን ግብአቶች ለሚያመርቱ የአገልግሎት ቅድሚያ መሰጠቱን፣ በተንቀሳቃሽ ስልኮች አማካኝነት ማስተላለፍ የሚቻለው የገንዘብ መጠን እንዲጨምር ማድረግ፣ ባንኮች በእጅጉ ለተጎዱ እንደ ሆርቲካልቸር፣ ሆቴሎች እና ቱሪዝም ላሉ ዘርፎች የብደር ክፍያ ጊዜን ለማራዘም እንዲችሉ የብሔራዊ ባንክ የብድር መመሪያ ደንብን ማላላት፣ ለውጭ ገበያ የሚውሉ አበባዎች ላይ የነበረውን አነስተኛ የዋጋ ተመን እንዲያነሱ ተደርጓል።

መንግሥት በኢኮኖሚው ዘርፍ የታየውን መቀዛቀዝ በተጨማሪ እርምጃዎች የሚደግፍ ስለመኾኑም መግለጫው የሚያመለክት ሲሆን፤ በሰሞኑ መግለጫ ላይም “ቀጣይ እርምጃዎች የኮሮና ቫይረስ ኢኮኖሚያዊ ተፅዕኖ ከላይ በተዘረዘሩት እርምጃዎች አማካኝነት ብቻ ሊቀለበስ ስለማይችል፣ መንግሥት ሁኔታዎችን መዝኖ እንደየአስፈላጊነቱ ተጨማሪ እርምጃዎችን የሚወስድ ይሆናል” በማለት አስታውቋል። (ኢዛ)

ሕገወጥ መሣሪያዎች ጉዳይ

ሕገወጥ የጦር መሣሪያ ዝውውርን ለመከታተልና አዘዋዋሪዎችን በቁጥጥር ስር ለማዋል የሁሉን ስምሪት እንደሚጠይቅ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ባስገነዘቡት ያሳለፍነው ሳምንት፤ በተለያዩ አካባቢዎች በሕገወጥ መንገድ ሲዘዋዋሩና ተሸሽገው የነበሩ የጦር መሣሪያዎች ተይዘዋል። በተለይ ግንቦት 7 ቀን 2012 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ከኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ወረዳ 7 ልዩ ቦታው ቤተል አካባቢ በአንድ መኖሪያ ቤት 10 ሽጉጥ፣ 110 የሽጉጥ ጥይት፣ 26 ክላሽን-ኮቭ ጠብመንጃ፣ 25 መሰል ባዶ ካርታ፣ ጥይት ለመሙላት የተዘጋጀ ባሩድ የተገኘ መኾኑን የአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማው ፖሊስ መምሪያ አስታውቋል።

በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ክልል ሲንቀሳቀሱ በተገኙ ከወንጀሉ ጋር ግንኙነት ያላቸውን ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር በማዋል በግለሰቦቹ ምሪት በኮልፌ ቀራኒዮ ክፍለ ከተማ ክልል በመኖሪያ ቤት ውስጥ የተደበቀው የጦር መሣሪያ መያዙን የመምሪያው ኃላፊ ገልጸዋል። በዚሁ መረጃ ከዚህ ቀደም በአዲስ ከተማ ክፍለ ከተማ ወረዳ ስምንት ልዩ ቦታው ሳጥን ተራ ተብሎ ከሚጠራው አካባቢ፤ መጋቢት 22 ቀን 2012 ዓ.ም. አንድ መትረየስ እና ሰባት ክላሽን-ኮቭ ጠብመንጃ ከተገኘ ጀምሮ፤ ፖሊስ በወንጀሉ ላይ ተከታታይነት ያለው ጥናትና ክትትል ሲያደርግ መቆየቱንና የጦር መሣሪያዎች መያዛቸውን አመልክቷል። ግለሰቦቹ የጦር መሣሪያዎቹን ለምን ተግባር እንደሚያውሏቸው ለማረጋገጥ በምርመራ ላይ መኾኑንም ይኸው የመምሪያው መረጃ ያመለክታል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ ከቱርክ በሁለት ኮንቴይነር የጦር መሣሪያ በሕገወጥ መንገድ ወደ አገር ያስገቡት ተከሳሾች ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ኾነው እንዲከታተሉ ውሳኔ መሰጠቱን ጠቅላይ ዓቃቤ ሕግ ያስታወቀው በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ነው።

እንደ ዓቃቤ ሕግ መረጃ ተከሳሽ መሐመድ ጀማል አራጋው፣ ዘይኑ አሕመድ ሙሐመድ፣ ሰይድ አሕመድ ይማም፡ ሐጎስ አመሃ አረጋዊ፡ ሐይደር ኑርየ አገሽን፣ መሐመድ ሀሚድ ሙሐመድ፣ ፋጡማ አሕመድ ሲራጅ፣ ሰይድ ሐሰን አሐመድ የተባሉት ግለሰቦች በ1996 ዓ.ም. የወጣውን የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32(1) (ሀ) እና በ2012 ዓ.ም. የወጣውን የጦር መሣሪያ አስተዳደርና ቁጥጥር አዋጅ ቁጥር 1177/2012 አንቀጽ 4(1) እና 22(3) ስር የተመለከቱትን ድንጋጌዎች የተላለፉ በመኾኑ ፖሊስ በቁጥጥር ስር እንዳዋላቸው አስታውሷል።

ተከሳሾች ፈቃድ ሳይኖራቸው ከቱርክ አገር በሁለት ኮንቴይነር ተጭኖ በጅቡቲ ወደብ በኩል ሊበርቲ ሺፒንግ ኤንድ ሎጂስቲክስ ኤል.ኤል.ሲ. በተባለ ድርጅት አማካኝነት በኤሌክትሮኒክስ ዕቃዎች ሽፋን ወደ ኢትዮጵያ የገባውን የጦር መሣሪያ በማዘዋወር ቀጠና የተያዙ ናቸው። ይህ በሁለት ኮንቴይነር የተጫነው መሣሪያ 501 ካርቶን ቱርክ ሠራሽ ሽጉጥ፣ ሞዴሉ 9 ሚሊ ሜትር EKOL P29 የኾነ የጦር መሣሪያ ለማዘዋዋር፣ ለመግዛት፣ ለመሸጥ ወይም ለማጓጓዝ በማሰብ በፈጸሙት ወንጀል ዓቃቤ ሕግ ክስ መስርቶባቸዋል። በዚሁ መሠረት ግንቦት 7 ቀን 2012 ዓ.ም. ፍርድ ቤት ቀርበው ክርክር የተደረገ ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱ ለ7ኛ ተከሳሽ ፋጡማ አሕመድ ሲራጅ ዋስትና በመፍቀድ፤ ሌሎች ተከሳሾች ጉዳያቸውን በማረሚያ ቤት ኾነው ክሳቸውን እንዲከታተሉ በማዘዝ በክስ መቃወሚያ ላይ ብይን ለመስጠት ለሰኔ 3 ቀን 2012 ቀጠሮ መስጠቱን ይገልጻል። (ኢዛ)

አስቸኳይ ጊዜ አዋጁና እስር

ባሳለፍነው ሳምንት ለየት ባለ ሁኔታ ሊታይ የሚችል ጉዳይ ካለ በአንድ ቀን በሺዎች የሚቆጠሩ ሰዎች በፖሊስ ቁጥጥር ስር መዋላቸው ነው። ይህም በአስቸኳይ ጊዜ አዋጁ ክልከላ ከተደረገባቸው ድርጊቶች ውስጥ በገበያ ቦታዎች፣ በትራንስፖርት መሳፈሪያ አካባቢዎች፣ ሕዝብ በብዛት በሚገኝባቸው እና ሕዝባዊ አገልግሎት በሚሰጥባቸው ተቋማት ጭምር እርቀትን በማይጠብቁ እና የአፍና የአፍንጫ መሸፈኛ ማክስ ሳያደርጉ በሚንቀሳቀሱ ግለሰቦች ላይ ቁጥጥር በማድረግ እርምጃ እንደሚወስድ ፖሊስ ካስጠነቀቀ በኋል የተወሰደ እርምጃ ነው ተብሏል።

በዚሁ መሠረት በአዲስ አበባ በተመረጡ 20 ቦታዎች ላይ ቁጥጥር ተደርጎ ክልከላውን በጣሱ ግለሰቦች ላይ እርምጃ መወሰዱን የአዲስ አበባ ፖሊስ ኮሚሽን አስታውቋል። ይህ እርምጃ አግባብ አይደለም የሚል አስተያየቶች ቢሰነዘሩም፤ አስቸኳይ ጊዜ አዋጁን ለማስፈጸም የተወሰደ ስለመኾኑ ተገልጿል። ይህም ቢኾን ግን በአንድ ዕለት ብቻ የአፍና የአፍንጫ ማስክ ባለማድረግ 1 ሺሕ 941 እና አካላዊ ርቀትን ባለመጠበቅ 860፣ እንዲሁም እጅ ለእጅ ሲጨባበጡ የተገኙ 12 ግለሰቦች በአጠቃላይ ከ2 ሺ 8 መቶ በላይ የአስቸኳይ ጊዜ አዋጅ ክልከላውን የጣሱ ግለሰቦችን በቁጥጥር ስር ማዋላቸውን ፖሊስ አስታውቋል።

ይህ በእንዲህ እንዳለ በአዲስ አበባ የተወሰደውን እንዲህ ያለ የእስር እርምጃ የኢትዮጵያ ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ዋና ኮሚሽነር ዶ/ር ዳንኤል በቀለ፤ “የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ የኮሮና ቫይረስ ሥርጭትን ለመከላከል አስፈላጊ የጤና መመሪያ ሲሆን፤ ሕብረሰቡም ሊከተለው የሚገባ ነው” ብለዋል። በእርግጥም የአስቸኳይ ጊዜ ደንቡ ማንኛውም ሰው እንደ ገበያ ቦታዎች፣ ሱቆች፣ የትራንስፖርት አገልግሎቶች ባሉ የሕዝብ አገልግሎት መስጫ ቦታዎች እና በሌሎች ሕዝብ በሚበዛባቸውና የአካል መራራቅን መጠበቅ በማይቻልባቸው አካባቢዎች፤ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ማድረግ እንዳለበት እንደሚደነግግም አስታውሰዋል። ከዚህ ውጪ ግን በየትኛውም ቦታ የአፍና አፍንጫ መሸፈኛ ሳያደርጉ የተገኙ ሰዎች ላይ ሁሉ የሚደረግ የዘፈቀደ እስር ከሕግ ውጭ ከመኾኑም በላይ፤ ለነገሩ ሁኔታ ተመጣጣኝ ያልኾነ እርምጃ እና የታለመለትን ዓላማ የሚቃረን በመኾኑ፤ በአስቸኳይ ሊቆይ እንደሚገባ አስገንዝበዋል። አያይዘውም በዚህ ሁኔታ የታሰሩ ሰዎችም በአስቸኳይ ሊፈቱ ይገባል በማለት አስታውቀዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ