Ethiopia Zare's weekly news digest, week 47th, 2012 Ethiopian calendar

ከሐምሌ 20 - 26 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

የዓመቱ አርባ ሰባተኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች

ኢዛ (ከሐምሌ 20 - 26 ቀን 2012 ዓ.ም.) ያሳለፍነው ሳምንት የተለያዩ ክዋኔዎች የታዩበት ነው። ከፖለቲካው አንፃር ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ከተፎካካሪ ፓርቲ መሪዎች ጋር ያደረጉት ውይይት አንዱ ነው። በዚህ መድረክ መንግሥት ሕግ የማስከበር ሥራውን አጠናክሮ ይቀጥላል ማለታቸው ጐልቶ የሚጠቀስ ነው።

በቅርቡ በአገሪቱ በተፈጠረው ኹከት እና ብጥብጥ ጋር ተያይዞ በሕግ ቁጥጥር ሥር ከዋሉት ውስጥ የብልጽግና አባላት የበለጠውን ቁጥር ስለመያዙ መናገራቸውን ተጠቃሽ ጉዳይ ነው።

ባሳለፍነው ሳምንት አነጋጋሪ ከነበሩ ዜናዎች መካከል የኦነግ ሊቀመንበር ዳውድ ኢብሳ በቤት እንዲቆዩ መደረግና ይህንኑ ተከትሎ ከሊቀመንበርነታቸው ተነስተዋል፣ በሌላ ተተክተዋል የሚለው ጉዳይ አሁንም እንቆቅልሽ ኾኖ መሰንበቱ ነው። አሁንም በዚህ ዙሪያ ያሉ መረጃዎች ያልጠሩ ሲሆን፣ የፓርቲው አመራሮችም የተለያዩ አስተያየቶች እየሰነዘሩ መኾኑ ደግሞ ብዥታን የፈጠረ ጉዳይ ኾኖ ዘልቋል።

የትግራይ ክልላዊ ምክር ቤት በትግራይ ክልል ምርጫ ለማድረግ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ተከትሎ የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሰጠው ማስጠንቀቂያ ከሳምንቱ አንኳር ዜናዎች መካከል አንዱ ነው። ክልሉ ምርጫ አደርጋለሁ ማለቱ ሕገመንግሥታዊ ያለመኾኑንና ይህንን ካላቆመ እርምጃ እንደሚወስድ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በጥብቅ አስታውቋል። ነገር ግን እስካሁን የትግራይ ክልልም ኾነ ሕወሓት በዚህ ማስጠንቀቂያ ዙሪያ ምላሽ ያልሰጠ መኾኑም በቀጣይ ምን ይኾናል የሚለውን ጥያቄ አጭሯል።

በቅርቡ በኢትዮጵያ በተከሰተው ኹከትና ብጥብጥ ጋር ተያይዞ በሕግ ቁጥጥር ሥር የሚገኙት አቶ ጃዋር መሐመድና አቶ እስክንድር ነጋ በሳምንቱ አጋማሽ ፍ/ቤት ቀርበዋል። ተለዋጭ ቀጠሮም ተሰጥቷቸዋል።

ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ ከሰሞኑ የሰጡት አንድ ቃለ ምልልስ የብዙዎችን ትኩረት ስቦ ነበር። በተለይ የትግራይ ክልል ምርጫ አደርጋለሁ ከሚለው እንቅስቃሴ አንፃር የሰጡት አስተያየት፤ የአገር ሰላም የሚያፈርስ እንዳይኾን የሚል ሥጋታቸውን ያመለከቱበት ነበር።

በዚህ ሳምንት ከሌሎች ሳምንታት በተለየ ከፍተኛ የኮሮና ቫይረስ ተጠቂዎች የተገኙበት ነው።

በኢትዮጵያ በአንድ ቀን 915 የሚኾኑ ሰዎች በቫይረሱ መጠቃታቸው ሪፖርት የተደረገበት ሲሆን፤ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በቫይረሱ የተጠቁ ሰዎች ቁጥር ከ17 ሺሕ በላይ መድረሱ የተመለከተበት ነው።

ከቢዝነስ ዜናዎች ኢትዮ ቴሌኮም ዓመታዊ ገቢውን ከዕቅድ በላይ በማሳደግ ከ47.7 ቢሊዮን ብር በላይ ማግኘቱን ያስታወቀበት ነው። በኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ የተዘጋጀውና እንዲህ ያሉ ሳምንታዊ ክንውኖችን የምንቃኝበት ሪፖርት እንደሚከተለው ቀርቧል። መልካም ንባብ!

ሕግ የማስከበር እርምጃና ጠቅላይ ሚኒስትሩ

ባሳለፍነው በሳምንት መጀመሪያ ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ያደረጉት ውይይትና በመድረኩ ላይ ያስተላለፉዋቸው መልእክቶች በሳምንቱ ትኩረት ካገኙ ጉዳዮች መካከል አንዱ ነው።

በተለይ ሕግን ከማስከበር አንፃር መንግሥታቸውን አቋም በድጋሜ ያንፀባረቁበትም ነው። በኹከትና ግርግር እጃቸው ያለበት የገዥውም ኾነ የተፎካካሪ ፓርቲ አባላት ላይ የሚወሰደው ሕጋዊ እርምጃም ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተናገሩ።

መንግሥት የንጹኀን ደም በማፍሰስ በአቋራጭ ሥልጣን ለመያዘ የሚደረግን ሙከራ እንደማይታገስ በድጋሜ በዚሁ መድረክ ላይ ያንፀባረቁ ሲሆን፤ በቅርቡ በአገሪቱ በተፈጠረው ኹከትና ግርግር እጃቸው ያሉባቸው የገዥውም ኾነ የተፎካካሪ ፓርቲዎች አባላት በቁጥጥር ሥር ይውላሉ።

ከሰሞኑ ቀውስ ጋር ተያይዞ የተፎካካሪ ፓርቲዎች አባሎቻችን እየታሰሩብን ነው ብለው ላነሱት ጥያቄ፤ ጠቅላይ ሚኒስትሩ የትኛውም ፓርቲ አባል ይሁን በድርጊቱ እጁ ያለበት ከተገኘ ሕጋዊ እርምጃ ይወሰድበታል ብለዋል። እንዲያውም እስካሁን እርምጃ ከተወሰደባቸው ውስጥ የብልጽግና አባላት ቁጥር እንደሚበልጥም ጠቁመዋል።

ሰላምና የአገር ሕልውናን አደጋ ላይ ለመጣል የሚደረግ ማናቸውም ዐይነት ሙከራ መንግሥት የማይታገሰው ቀይ መስመር መኾኑን ያስገነዘቡት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ የድሀ ኢትዮጵያውያንን ልጆች እያጋጩ በአቋራጭ ወደ ሥልጣን ለመምጣት የሚደረግ ሙከራ እንዳለ ጠቅሰው፤ በድርጊቱ እጃቸው ያለበት ግለሰቦችን ለምን ተጠየቁ የሚለው ሐሳብ ተቀባይነት የለውም በማለት ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ለቀረበላቸው ጥያቄ በሰጡት ምላሽ አስገንዝበዋል።

በኹከትና ግርግር እጃቸው ያለበት የገዥውም ኾነ የተፎካካሪ ፖለቲካ ፓርቲ አባላቶችን በሕግ ተጠያቂ የማድረጉ ሥራ ተጠናክሮ እንደሚቀጥል ያስገነዘቡት ዶክተር ዐቢይ፤ በቅርቡ በኦሮሚያ አንዳንድ አካባቢዎች ከተፈጠረው ኹከት ጋር በተያያዘ በርካታ የብልጽግና አመራሮች መታሰራቸውን ለአብነት በማንሳት፤ ሽማግሌዎችን አደራጅቶ በመላክ በሕግ ጥላ ሥር ያሉ ሰዎችን ለማስፈታት የሚደረግ ጥረት መኖሩንም በማስታወስ፤ ይህ ጉዳይ አሁን ላይ የማያዋጣ መኾኑን የሚያመላክት ምላሽ የሰጡበት ነበር።

ሕግን እንደፈለጉ የሚጥሱ ሰዎችን በሽምግልና ስም የማስፈታት ሥልጣን የለኝም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ሒደቱ በራሱ የዴሞክራሲና የሕግ የበላይነት ልምምድን እንደሚያቀጭጨው አብራርተው፤ እጃቸውን እንደማያስገቡ ተናግረዋል። የተፎካካሪ ፓርቲዎች አባላት ኹከትና ብጥብጥ የሚፈጥሩ አባላት በመንግሥት ውስጥ ጭምር መኖራቸውን የጠቀሱበት መድረክ ሲሆን፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩም ሌቦች በመንግሥታቸው ውስጥ ጭምር መኖራቸውን ገልጸው፤ ይህንን የማፅዳት ሥራ እንደሚሠራና ተፎካካሪዎችም ውስጣቸውን እንዲመለከቱ ሳያሳስቡ አላለፉም። ግጭትና ብጥብጥ ከሰማይ የማይወርድ በመኾኑም፤ ሁሉም የቤት ሥራውን ይሥራ ብለዋል። (ኢዛ)

እንቆቅልሽ የኾነው የኦነግ ሊቀመንበር ጉዳይ

የኦሮሞ ነፃነት ግንባር (ኦነግ) ሊቀመንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ መኖሪያ ቤት በፌዴራል ፖሊስ መከበቡን የፓርቲው የሥራ ኃላፊዎች የገለጹት ከአስር ቀን በፊት ነበር።

በተለይ የፓርቲው ቢሮ ኃላፊ አቶ ገዳ ኦልጅራ በአቶ ዳውድ ኢብሳ ቤት አካባቢ የሚገኘው የጸጥታ ኃይል የሊቀመንበሩን ደኅንነት ለመጠበቅ መሰማራቱን ከፖሊስ መስማታቸውን ሲገልጹ ሌሎች መረጃዎችም በተመሳሳይ መልኩ ሲናፈሱ ነበር።

አቶ ዳውድ ኢብሳ ከመኖሪያ ቤታቸው መውጣትና መግባት እንዳልቻሉና ወደ ውጪ የሚወጡ ከኾነም በጸጥታ ኃይሎች በቁጥጥር ሥር ሊውሉ እንደሚችሉ ተነግሮአቸው ከሁለት ሳምንታት በላይ ከቤታቸው ሳይወጡና የስልክ ግንኙነታቸውም ተቋርጦ እንደነበር ተነግሮ ነበር።

ይህ ጉዳይ አቶ ዳውድ መውጣት መግባት አልቻሉም ተብሎ ከመነጋገር ባለፈ በወቅቱ አነጋጋሪ የነበረው ተያያዥ ጉዳይ አቶ ዳውድ በሌሉበት የፓርቲው ከፍተኛ አመራር አባላት ስብሰባ መቀመጣቸውንና የእርሳቸውን ከሥልጣን መነሳት የሚገልጽ ዜና ተነገረ። አቶ ዳውድ ከኃላፊነታቸው ተነስተው ምክትላቸው ተክቷቸዋል ተባለ፣ ቆይቶም አቶ ዳውድ ከሊቀመንበርነታቸው አልተነሱም የሚል መረጃ ከፓርቲው ወጣ። ይህ ግራ የሚያጋባ ጉዳይ አሁንም ያልጠራ ስለመኾኑ መገንዘብ ይቻላል።

አቶ ዳውድ በቤት እንዲቆዩ በተደረገበት ወቅት ለቢቢሲ እንደገለጹት፤ ”ሐምሌ 10 ላይ የፌደራል ፖሊስ የደንብ ልብስ የለበሱ፤ እኔ የፌደራል ፖሊስ አባላት ናቸው ብዬ ነው የማምነው፤ መልእክት ተቀብለው የመጡ ናቸው ‘ለደኅንነትህ ሲባል ከቤት አትውጣ፤ በአካባቢውም ጥበቃ እናደርጋለን’ ሲሉ በጥሞና ነገሩኝ" ይላሉ።

ሐምሌ 17 ላይ "ቤት ውስጥ ያሉትም ወደ ውጪ እንዳይወጡ" የሚል ትእዛዝ እንደደረሳቸው የገለጹት አቶ ዳውድ፤ ይህንንም ለደኅንነት ጥበቃ ነው ብለው በማሰብ እንዳመኑም መናገራቸውን ያመለክታል።

"ለጥበቃ የመጣው የፖሊስ ኃይልና ስልኬን የዘጋው አካል ግንኙነት ይኑራቸው አይኑራቸው የማያውቀው ነገር የለም" የሚሉት አቶ ዳውድ፤ ስልካቸው ግን ከሐምሌ 17 ቀን 2012 ዓ.ም. ተዘግቷል ብለዋል። ከአሁን በኋላ ለደኅንነትህ ጥንቃቄ እያደረክ መንቀሳቀስ ትችላለህ መባላቸውን የጠቆሙ ሲሆን፤ በዚህም መሠረት ዓርብ ዕለት ከቤታቸው ወጥተው ወደ ፓርቲያቸው ጽሕፈት ቤት በመሔድ ጉዳያቸውን ከውነው እንደተመለሱም ተናግረዋል።

ደኅንነትን በተመለከተ ሥጋት እንዳለ አቶ ዳውድ ኢብሳ የተናገሩ ሲሆን፤ በተለይ "ከአማራ ክልል ከፍተኛ አመራሮች እና ከድምፃዊ ሐጫሉ ግድያ በኋላ፤ የኾነ ነገር ሊፈጠር እንደሚችል ማንም የሚረዳው ነገር ነው" በማለት ይህንን ከግንዛቤ በማስገባት እንደሚንቀሳቀሱ በዚሁ ቃለ ምልልሳቸው ላይ ሳይጠቅሱ አላለፉም።

ይሁን እንጂ ከተለያዩ የኦነግ የፓርቲ አባላት ስለተፈጠረው ሁኔታ በተለያየ መልኩ መረጃ ሲሰጥ የነበረ ሲሆን፤ አንዳንድ መረጃዎች የፓርቲ አመራር ለውጥ ስለመደረጉ ሲገልጹ፤ በሌላ ወገን ደግሞ አቶ ዳውድ ኢብሳ ለጊዜው መሥራት በሚችሉበት ሁኔታ ላይ ናቸው በማለታቸው ጉዳዩ አሁንም ብዥታ ውስጥ እንደገባ ነው።

በዕድሜ የገፉት የፓርቲውን ሊቀመንበር በአዲስ የመተካት ሐሳቡ ስለመኖሩ ግን በተለያየ መንገድ ቢገለጽም፤ እርሳቸው በሌሉበት በተደረገው ስብሰባም ምክትላቸው እርሳቸውን ተክተው እንዲሠሩ መነገሩም ሁኔታውን እንቆቅልሽ አድርጐት ቆይቷል። በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ደግሞ አቶ ዳውድ እንደገና ለደኅንነታቸው ተብሎ ቤት እንዲቆዩ ተደርጓል። (ኢዛ)

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ማስጠንቀቂያና የትግራይ ክልል ዝምታ

የሳምንቱ ዐበይት ዜና ኾኖ ብዙ ያነጋገረው ጉዳይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለትግራይ ክልል የሰጠውን ማስጠንቀቂያ የተመለከተ ነው።
ፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ይህንን ደብዳቤ ጻፈ የተባለው ከአንድ ሳምንት በፊት ሲሆን፤ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ደግሞ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ከተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር በነበራቸው ውይይት በትግራይ ክልል ይካሔዳል ስለተባለው ምርጫ የሰጡት ማብራሪያ ነበር። በዚህ ማብራሪያቸው እንደጠቆሙትም ከትግራይ ክልል ጋር ተያይዞ ለተነሳላቸው ጥያቄም "በትግራይ ክልለ ተቀምጠው የክልሉን ሕዝብ ከሌሎች ወንድሞቹ ጋር ለማጋጨት የሚሠሩ አካላት ቢኖሩም፤ መንግሥት ከክልሉ ሕዝብ ጋር ግጭት የመፍጠር ፍላጎት የለውም" ብለዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት ክልሉን እንዲመራ የተቋቋመው መንግሥት እስከቀጣዩ ምርጫ ድረስ በሥልጣን እንዲቆይ መወሰኑንም ያስታወሱት፤ ከዚህ አንፃር ክልሉ አደርገዋለሁ ያለው ምርጫ ትርጉም እንደሌለው ጠቅሰው፤ "በምርጫው ከሕወሓት ውጭ ሌላ ፓርቲ ወደ ሥልጣን ቢመጣ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔን የሚጥስ በመኾኑ ተቀባይነት አይኖረውም፤ ወደ አልተፈለገ ግጭትም ያመራል" በማለት መግለጻቸው ይታወሳል።

ከዚህ በኋላ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ለትግራይ ክልል በጻፈው ደብዳቤ መነሻን ያደረገው የኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ በኮቪድ 19 ወረርሽኝ ምክንያት ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ ማካሔድ እንደማይችል ያቀረበውን ሪፖርት መነሻ በማድረግ፤ የሕገ መንግሥት ትርጉም እንደተሰጠበት በማስታወስ ነበር።

የኢፌዴሪ ሕገ መንግሥት ምርጫን በወቅቱ ለማካሔድ ከአቅም በላይ የኾነ እክል ሲያጋጥም ምን መደረግ እንዳለበት በግልጽ ባለመደንገጉ እና ሕገ መንግሥቱ በሚፈቅደው መሠረት ክፍተቱን በሕገ መንግሥት ትርጉም መሙላት ተገቢ መኾኑን በማመን ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ እንዲራዘም መወሰኑንም ከፌዴሬሽኑ የወጣው ደብዳቤ ያስታውሳል።

ኾኖም ግን የትግራይ ክልል መንግሥት ይህን ውሳኔ ወደ ጎን በመተው በክልሉ ምርጫ ለማካሔድ ወስኖ እንቅስቃሴ እያደረገ መኾኑን ማረጋገጡንና የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 102 መሠረት በፌዴራልና በክልል ነፃና ትክክለኛ ምርጫ በገለልተኛነት ማካሔድ የሚችለው የብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አለመኖሩንም ያስታወቀበት ነበር።

የፌዴሬሽኑ ደብዳቤ የትግራይ ክልል ምርጫን በሚመለከት የወሰነው ውሳኔና የራሱን የምርጫ ኮሚሽን በማቋቋም ጭምር እያካሔደ ያለው እንቅስቃሴ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስድስተኛውን አገራዊ ምርጫ በሚመለከት ሰኔ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. ያሳፈውን ውሳኔ ያላከበረ ከመኾኑም ባሻገር ግልጽ የኾነ የሕገ መንግሥት ጥሰት እንደኾነ አስታውቋል።

በተለይ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 62(9) መሠረት ማንኛውም ክልል ሕገ መንግሥቱን በመጣስ ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንደኾነ የፌደራሉ መንግሥት ጣልቃ የሚገባበትን ሥርዓተ ለመደንገግ በወጣው አዋጅ ቁጥር 359/1995 አንቀጽ 12ን በማስታወስ የትግራይ ክልል እያካሔደ ያለውን እንቅስቃሴ ካላቆመ የፌዴራል መንግሥቱ ጣልቃ የሚገባበት አግባብ አለመኖሩ የጠቆመም ነበር። በፌዴሬሽን ምክር ቤት የተጠቀሱ ሕገ መንግሥታዊ አንቀፆችና ሌሎች ድንጋጌዎች መሠረት በአንድ የክልል መንግሥት ተሳትፎ ወይም እውቅና ሕገ መንግሥቱን ወይም ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን ባለማክበር የሚደረግ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የጣለ እንቅስቃሴ ወይም ድርጊት እንደኾነ በግልጽ በመደንገጉ የትግራይ ክልል ምርጫን ለማካሔድ የጀመረው እንቅስቃሴ ሕገ መንግሥቱን የሚቃረን ሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱን አደጋ ላይ የሚጥል መኾኑን አስገንዝቧል። የኢትዮጵያ የፌዴራል ሥርዓት የሚጎዳ አካሔድ ስለመኾኑም አመልክቷል።

ስለዚህ ማንኛውም ሕግ ወይም የመንግሥት አካል ውሳኔ ከሕገ መንግሥቱ ጋር የሚቃረን ከኾነ ተፈጻሚነት እንደማይኖረው ታውቆ የክልሉ መንግሥት ሕገ መንግሥቱንና የፌዴሬሽን ምክር ቤቱን ውሳኔ እንዲያከብርና የጀመረውን ኢ-ሕገ መንግሥታዊ እንቅስቃሴ በአፋጣኝ እንዲያቆም የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ አስጠንቅቋል። ክልሉ እንዲህ ያሉ ሕገ መንግሥታዊና ሌሎች ድንጋጌዎችን በመጣስ ምርጫ የሚያደርግ ከኾነ ፌዴሬሽኑ መንግሥታዊ ሥልጣኑን ተጠቅሞ እርምጃ የሚወስድ ስለመኾኑ አሳስቧል።

ከዚህ ዜና መሰማት በኋላ ከተለያዩ ወገኖች ከተሰጡ አስተያየቶች መገንዘብ እንደሚቻለው የፌዴሬሽን ምክር ቤት የትግራይ ክልል በአቋሙ ከጸና የፌዴራል መንግሥት በጉዳዩ ጣልቃ እንዲገባ ውሳኔ የሚያሳልፍ መኾኑን ነው። እርምጃው በጀት ከመያዝ ጀምሮ ሌሎችንም ሊያጠቃልል ይችላል ተብሏል። የትግራይ ክልል ግን እስካሁን ምላሽ አልሰጠም። (ኢዛ)

የአነጋጋሪው የሌ/ጄኔራል ባጫ ደበሌ ቃለ ምልልስ

ከሰሞኑ ትኩረት ከሳቡ ቃለምልልሶች ውስጥ የቀድሞው ከፍተኛ የመከላከያ ሚኒስቴር መኮንን ሌተናል ጄኔራል ባጫ ደበሌ ያደረጉት ቃለ ምልልስ ተጠቃሽ ነው። ጄኔራሉ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮች ላይ ሰፋ ያለ ማብራሪያ የሰጡ ሲሆን፤ ከሕወሓት ጋር በተገናኘ የሰነዘሩት ሐሳብ ጐልቶ የታየ ነበር ማለት ይቻላል።

በተለይ የትግራይ ክልል ምርጫ ለማድረግ እያደረገ ካለው እንቅስቃሴ ጋር ተያይዞ በትግራይ ክልል ምርጫ እናደርጋለን የሚለው ነገር ከጸጥታም፣ ከሕግም አኳያ በአግባቡ መታየት እንዳለበት የጠቆሙበት ነው።

በጦርነት ካልኾነ በስተቀር ሐሳቤን ወደ መድረክ ማቅረብ አልችልም የሚለው የፖለቲከኛ ባሕርይ ስላለመኾኑ በማስገንዘብ፤ ይልቁንም የዚህ ዐይነቱ ባሕርይ በሶማሊያ የነበሩ የጦር አበጋዞች ባሕርይ ነው። ይህ ባሕርይ አገሪቱንና ሕዝቦቿን ብዙ ዋጋ ከማስከፈል ባለፈ ያመጣው መፍትሔ እንዳልነበረ በማስታወስ፤ በትግራይ ክልል ይካሔዳል የተባለው ምርጫ ሊያስከትል የሚችለውን ተፅእኖ አመላክተዋል።

"200ሺ ይሁን 400ሺ ወጣቶችን ሰብስቦ ጠብመንዣ ማሸከም ዋጋ የለውም" ያሉት ሌተናል ጄኔራል ባጫ ጦርነትን ማሸነፍ የሚቻለው መሣሪያ በመከመር፣ የሰው ኃይል በማብዛት እና ዘራፍ በማለት አለመኾኑንም ጠቅሰዋል። ከጦርነት ውጭ ይህን ነገር ላገኝ አልችልም ብለህ ሕዝቡን የምታሳምንበት በቂ ምክንያት ሊኖርህ ይገባል። አሁን ባለው የአገሪቱ ተጨባጭ ሁኔታ ወደ ጦርነት የሚወስድ ምንም ነገር እንደሌለም በዚሁ ቃለምልልስ ተናግረዋል።

መንግሥት ከማንኛውም ክልል ጋር ጦርነት ሊገጥም እንደማይችል ያስገነዘቡት ሌተናል ጄኔራል ባጫ፣ የትኛውም ክልል የፌዴራል መንግሥት ጦርነት ሊገጥም እንደማይችልና ይህን የሚያደርግ ከኾነ ዓላማውን እንደሚስት አስረድተዋል። "እንደዛ ዐይነት ነገር ይመጣል ብዬም አላስብም" ያሉት ጄኔራሉ፣ "በኢትዮጵያ ጦርነት ሊኖር አይችልም" የሚል እምነታቸውንም ሰንዝረዋል።

"በትግራይ ክልል ምርጫ እናደርጋለን የሚለው ነገር ከጸጥታም፣ ከሕግም አኳያ በአግባቡ መታየት አለበት" በማለት ተናግረዋል። ምርጫን የሚመራው በፌዴራል መንግሥት የተቋቋመው የምርጫ ቦርድ እንጂ ተወዳዳሪ የፖለቲካ ፓርቲ አለመኾኑን ጠቅሰው፤ ማንኛውም ተወዳዳሪ ፓርቲ ምርጫ ማዘጋጀት እንደማይችልም አመልክተዋል።

ምርጫን የሚያዘጋጀው ከፖለቲካ ፓርቲ ነፃ የኾነ በፌዴራል የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሚቋቋም፣ በአገሪቱ ምርጫ ኮሚሽን መኾኑን በመግለጽ፤ "ምርጫ እናዘጋጃለን የሚሉት ወንድሞቻችን እነሱ የፖለቲካ ፓርቲ እንጂ ምርጫ ኮሚሽን አይደሉም፤ የረሱትና ያላወቁት ነገር የፖለቲካ ፓርቲ መኾናቸውን ነው" ብለዋል። በክልል አሸናፊ ፓርቲ ቢኾኑም ምርጫን የማዘጋጀት ሥልጣን እንደሌላቸውና ይህ አንድ የጸጥታ መደፍረስ ምንጭ ሊሆን ስለሚችል ቢታሰብበት መልካም እንደኾነ ሳያሳስቡ አላለፉም።

መንግሥት በአንዳንድ ጉዳዮች ትዕግሥት ማድረጉ ትክክል መኾኑን የሚስማሙበት ቢሆንም፤ ወንጀል ላይ በተይም ሊታለፍ በማይገባ ወንጀል ትዕግሥት ማድረግ እንደማይገባው ተናግረዋል። (ኢዛ)

የጃዋርና የእስክንድር ቀጠሮ

በቅርቡ በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞችና በአዲስ አበባ ከተፈጠረው ኹከት ጋር ተያይዞ በሕግ ቁጥጥር ሥር ከሚገኙት ተጠርጣሪዎች መካከል አቶ ጃዋር መሐመድና አቶ እስክንድር ነጋ ፍ/ቤት ቀርበው በድጋሚ ተጨማሪ የጊዜ ቀጠሮ የተሰጣቸው ባሳለፍነው ሳምንት አጋማሽ ላይ ነበር።

ጉዳያቸው በፌዴራል የመጀመሪያ ፍርድ ቤት አራዳ ምድብ ችሎት እየታየ ያለው የአቶ ጃዋር መሐመድ ላይ ፖሊስ ተጨማሪ የ14 ቀን የምርመራ ጊዜ የጠየቀ ሲሆን፤ ፍርድ ቤቱም የፖሊስን የ14 ቀን ተጨማሪ ጥያቄ በማየት የ12 ቀን ፈቅዷል። በመኾኑም አቶ ጃዋር ለነሐሴ 5 ቀን 2012 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷቸዋል።

አቶ ጃዋር ፍርድ ቤት በቀረቡበት ወቅት ኹከት እና ብጥብጥ በተከሰተባቸው የኦሮሚያ ክልል አካባቢዎች የተሰማራው የምርመራ ቡድን በርካታ የሰው ሞት እና የንብረት ውድመት የተመለከተ መረጃ መላኩን ፖሊስ ለፍርድ ቤቱ የገለጸበት ነበር።

አቶ ጃዋር በበኩሉ የተከሰተው ወንጀል እሱን እንደማይመለከት እና ሚዲያዎች በተገቢው መንገድ ችሎቱን እንዲታደሙ ፍርድ ቤቱን ጠይቋል። የአቶ ጃዋር ጠበቆችም የምርመራ ሥራው አዲስ አለመኾኑንና ፖሊስ የጠየቀው የጊዜ ቀጠሮ ውድቅ እንዲኾን ወይም ጥቂት ቀን እንዲኾንም ጠይቀው ነበር።

በተመሳሳይ በአቶ እስክንድር ነጋ የክስ መዝገብን የተመለከተው ፍርድ ቤትም ፖሊስ የ14 ቀን ተጨማሪ የምርመራ ጊዜ የጠየቀበት ነበር። የምርመራ ቡድኑ አቶ እስክንድር አዲስ አበባ ውስጥ ተጀምሮ አዲስ አበባ ውስጥ ይጠናቀቃል በሚል መርኅ ሰኔ 24 ቀን 2012 ዓ.ም. በአዲስ አበባ ውስጥ በተፈጠረ ግጭት ዙሪያ ምርመራ እያካሔደበት ሲሆን፤ የብሔር እና የሃይማኖት ግጭት እንዲቀሰቀሰ ወጣቶችን በማስታጠቅ እና ገንዘብ በማደል ባደረገው ቅስቀሳ የ14 ሰዎች ሕይወት ስለ መጥፋቱ ፖሊስ ማመልከቱ ይታወሳል። ከዚህም ሌላ ንብረት መውደሙን በተመለከተ የሰው እና የሰነድ ማስረጃ ሲያደራጅ መቆየቱን ለችሎቱ የጠቀሰ ሲሆን፤ የምርመራ ቡድኑ በተሰጠው ጊዜ የሰው እና የሰነድ ማስረጃዎችን ማሰባሰብ እና መሰል ሥራዎችን ማከናወኑን አስታውቋል። ይሁን እንጂ ተጠርጣሪው የሚጠቀሙባቸውን የኤሌክትሮኒክስ ውጤቶችን በመሰወሩ የማፈላለግ እና በግጭቱ የሞቱ ሰዎችን የሕክምና ምርመራ ውጤት ብሎም ተያያዥ የምርመራ ሥራዎችን ለማከናወን ተጨማሪ 14 ቀናት ያስፈልገኛል በማለቱ፤ የፖሊስን ጥያቄ የተመለከተው ፍርድ ቤቱ የፖሊስን የ14 ቀን ጥያቄ ወደ ዘጠኝ ዝቅ አድርጐ ዘጠኝ የምርመራ ቀናት ፈቅዷል።

የአቶ እስክንድር ጠበቆች ግን የምርመራ ቡድኑ ከሆስፒታል የሚፈልጋቸውን መረጃዎች ለመውሰድ የፈጀበት ረዜ ተገቢነት የለውም ብለዋል። እንዲሁም ምርመራው ካለፈው አዲስነት የለውም በሚል ተያያዥ ጥያቄዎችን አንስተዋል። የምርመራ ቡድኑም በጠበቆች አስተያየት ላይ ምላሽ ሰጥተዋል።

ግራ ቀኙን የመረመረው ችሎቱ ከወንጀሉ ውስብስብነት አንፃር ፖሊስ ከጠየቀው 14 ቀናት ውስጥ ዘጠኝ ቀናት በመፍቀድ ለነሐሴ 1 ቀን 2012 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ መስጠቱ ታውቋል። (ኢዛ)

የኢትዮ ቴሌኮም ገቢ በ31 በመቶ አድጐ 47.7 ቢሊዮን ብር ኾነ

ከሳምንቱ ቢዝነስ ነክ ዜናዎች ውስጥ ኢትዮ ቴሌኮም በ2012 በጀት ዓመት ከ47.7 ቢሊዮን ብር በላይ ገቢ ማስገባቱን ማሳወቁ ነው።

የኢትዮ ቴሌኮም ዋና ሥራ አስፈፃሚ ወ/ት ፍሬሕይወት ታምሩ እንደገለጹት፤ ኢትዮ ቴሌኮም በ2012 በጀት ዓመት ያገኘው ገቢ ካለፈው ዓመት ጋር ሲነፃፀር፤ ሰላሳ አንድ ነጥብ አራት (31.4) በመቶ ጭማሪ ያሳየ መኾኑን ነው። እንደ እሳቸው አባባል ገቢውን በ25 በመቶ ለማሳደግ አቅዶ የነበረ ቢሆንም፤ ከዕቅዱ 105 በመቶ ማሳካት መቻሉን ነው። ኢትዮ ቴሌኮም በበጀት ዓመቱ ለመንግሥት 11.3 (አሥራ አንድ ነጥብ ሦስት) ቢሊዮን ብር ግብር መክፈሉንም ጠቁመዋል። በበጀት ዓመቱ ከውጭ አገር አገልግሎት እና ጥሪ በውጭ ምንዛሪ 147.7 (መቶ አርባ ሰባት ነጥብ ሰባት) ሚሊዮን ዶላር ማግኘቱንና ይህም ከ2011 በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር በ50 በመቶ ማደጉንም አስታውቋል።

መረጃዎች እንደሚያሳዩት በኢትዮጵያ 46.2 (አርባ ስድስት ነጥብ ሁለት) ሚሊዮን ሰዎች የኢትዮ ቴሌኮም አገልግሎቶች ተጠቃሚ መኾናቸውን ነው። ከዚህም ውስጥ 44.5 (አርባ አራት ነጥብ አምስት) በመቶ የድምፅ እንዲሁም 23.8 (ሃያ ሦስት ነጥብ ስምንት) በመቶ የኢንተርኔት ተጠቃሚ ናቸው። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!