20210302 adwa

Ethiopia Zare's weekly news digest, week 48th, 2012 Ethiopian calendar

ከሐምሌ 27 - ነኀሴ 3 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

የዓመቱ አርባ ስምንተኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች

ኢዛ (ከሐምሌ 27 - ነኀሴ 3 ቀን 2012 ዓ.ም.) ያሳለፍነው ሳምንት የተለያዩ ክዋኔዎች የተስተናገዱበት ነው። የታላቁ ህዳሴ ግድብ ድርድር በዚህ ሳምንት ተጀምሮ መልሶ ተቋርጧል። ዛሬ ሌላ ዙር ይጠበቃል። ከፖለቲካ አንፃር የብልጽግና ፓርቲ ቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮምሽን የመዋቅር አደረጃጀት ሊያደርግ መኾኑ ሲገለጽ፤ የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ደግሞ በዝግ ግምገማ የገባበት ሳምንት ነበር። በዚህ መሐል አፈትልኮ የወጣው የኦሮሚያ ክልላዊ መንግሥት ምክትል ፕሬዝዳንት ንግግር በሳምንቱ መጨረሻ ላይ አጀብ ያሰኘ ኾኖ ብቅ ብሏል።

በብልጽግናና በሕወሓት መካከል ያለውን ቁርሾ በሽምግልና ለመፍታት የተደረገው ጥረት በዚህ ሳምንት ሳይሳካ ቀርቷል። የሶማሌ ክልል ፕሬዝዳንት አቶ ሙስጠፌ መሐመድ ስለ ሕወሓት የሰጡት አስተያየት አስገራሚ ከሚባሉ የሳምንቱ ዜናዎች መካከል የሚካተት ነው። የቀድሞ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ስዩም መስፍን ወደ አንድ የትግራይ ክልል ተጉዘው የገጠማቸው ተቃውሞም ሌላው የሳምንቱ ተጠቃሽ ዜና ነው። የአዲስ አበባ ከተማ ከንቲባ ከምክር ቤታቸው ስለአበረከቱት አስተዋጽኦ እውቅናና ሽልማት ያገኙት በዚህ ሳምንት ነበር።

እስካሁን እንቆቅልሽ ኾኖ የቆየውና በደምቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጠለፋ ጋር በተያያዘ በጉዳዩ እጃቸው ያሉባቸው 17 ሰዎች ፍርድ ቤት ቀርበዋል። ጠቅላይ ፍ/ቤት በ2012 በጀት ዓመት ከ15 ሺህ በላይ መዛግብትን እልባት ሰጥቼ 82 በመቶ እቅዴን አሳክቻለሁ ማለቱም ከሰሞኑ ዜናዎች አንዱ ነበር።

ከመደመር መጽሐፍ የተገኘን 110 ሚሊዮን ብር ጠቅላይ ሚኒስትሩ ለቀዳማይ እመቤት ጽሕፈት ቤት ማስረከባቸው ሰፊ ሽፋን ያገኘ ዜና ነበር። ቤይሩትን ያራደው ከባድ ፍንዳታ አንድ ኢትዮጵያዊ ሲቀጥፍ አስሩ ላይ ጉዳት አድርሷል። ከታላቁ ህዳሴ ግድብ አጠገብ ሲጠፋ በነበረ ሕይወት ተጠያቂ ናቸው የተባሉ ታጣቂዎች ተይዘዋል።

የፓስፖርትና መሰል አገልግሎቶች ከወራት በኋላ ደግሞ ሊጀመሩ መኾኑ፣ በኢትዮጵያ በኮሮና ቫይረስ ከሚያዙ ሰዎች ውስጥ 80 በመቶው ምልክት የማይታይባቸው ስለመኾኑ የተነገረው በዚህ ሳምንት ነው። የእነአቶ ጃዋር የፍ/ቤት ውሎም በዚህም ሳምንት ሲደረግ ቀጠሮ ተሰጥቶበታል። አቶ እስክንድር ነጋ ያቀረበው የዋስትና ጥያቄ ውድቅ ኾኗል። አዲስ አበባ ለ2013 በጀት ዓመት 61 ቢሊዮን ብር በጀት ጸድቆላታል።

ቢዝነስ ነክ ከሆኑ ዜናዎች ውስጥ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በ2012 በጀት ዓመት ከ40 ቢሊዮን ብር በላይ ዋጋ ያላቸውን ምርቶች ማገበያየቱን አስታውቋል።

የሕወሓት ኩባንያ የኾነው ትራንስ ኢትዮጵያ መጋዘኖቹ እየታሸጉ መኾኑ መገለጹ ከሳምንቱ ቢዝነስ ነክ ዜናዎች ውስጥ የሚካተቱ ናቸው። በኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ የተጠናከረውን የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች እነኾ!

የህዳሴው ግድብ

የታላቁ ህዳሴ ግድብ ጉዳይ አሁንም መጓተቱን ቀጥሏል። በዚህ ሳምንት የሦስቱ አገራት ተደራዳሪዎች ድጋሚ በጠረጴዛ ዙሪያ የተቀመጡ ቢሆንም፤ ያለውጤት ተበትኗል። ነገር ግን እንደገና ሰኞ ነሐሴ 4 ቀን 2012 ዓ.ም. በድጋሚ ይቀመጣሉ ተብሎ የነበረ ቢኾንም፤ በድጋሚ ለነኀሴ 11 ተሻግሯል።

ድርድሩን በተመለከተ በዚህ ሳምንት የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንደገለጸው ኢትዮጵያ በህዳሴ ግድብ ዙሪያ ከተፋሰሱ የታችኞቹ አገራት ጋር የሚካሔደው ድርድር ውጤታማ እንዲኾን አበክራ ትሠራለች ብሏል። የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ድርድሩ ዛሬ እንደሚቀጥል በሚመለከትም በቀጣይነት በግድቡ ቴክኒካዊ ጉዳዮች ላይ የሚካሔዱ ድርድሮች ላይ ኢትዮጵያ ፍትሐዊ የተፈጥሮ ሀብት አጠቃቀምን መሠረት ያደረገ ውይይት ለማካሔድ ዝግጅት እንዲደረግም የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ቃል አቀባይ ዲና ሙፍቲ ተናግረዋል።

ኢትዮጵያ ሌሎቹ አገራት በተደጋጋሚ ጊዜ የግድቡን ድርድር ሲያቋርጡ፤ እኔም በቃኝ ከዚህ በኋላ ብላ የቆመችበት ወቅት እንደሌለ የተናገሩት አምባሳደር ዲና፤ በድርድሩ ተስፋ ሳትቆርጥ በሚኖሩ ድርድሮች ላይ በቀጣይነትም እንዳምትነሳተፍ አስታውቀዋል።

ሰሞኑን ተጀምሮ የተቋረጠውን ውይይት አስመልክተው እንደተናገሩት፤ ኢትዮጵያ የግድቡ ውኃ እየተሞላ በዘላቂ ተጠቃሚነት ዙሪያ በቀጣይ ጊዜያት እንወያይ የሚል ፕሮፖዛል አቅርባለች። የግብጽ እና የሱዳን ተደራዳሪዎች ግን ፕሮፖዛሉን ለማየት ጊዜ ይሰጠን በሚል ድርድሩን አቋርጠው እንደነበርም ቃል አቀባዩ አስታውሰዋል። (ኢዛ)

የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ዝግ ግምገማ

ከሳምንቱ ቀዳሚ ከሚባሉ ዜናዎች ውስጥ በሳምንቱ መጨረሻ አካባቢ የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ በክልል ባጋጠመው ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ በማተኮር ግምገማ መቀመጡ ነው።

ይህንኑ ግምገማ በተመለከተ ዝርዝር መረጃ ባይኖርም ግምገማው በክልሉ ወቅታዊ ጉዳዮች ላይ ትኩረቱን አድርጎ እየተካሔደ ስለመኾኑ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ በትዊተር ገጻቸው ላይ አመልክተዋል።

በግምገማው ላይ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድን ጨምሮ ሌሎች ከፍተኛ የክልሉ የብልጽግናና የፌዴራል የሥራ ኃላፊዎች የተካፈሉበት ነው። (ኢዛ)

ብልጽግናና ኮምሽኑ

ብልጽግና ፓርቲ ራሱን በራሱ እያረመ የሚሔድበት ጠንካራ አደረጃጀት እንደሚበጅለት መነገሩ ባሳለፍነው ሳምንት ከተደመጡት ዜናዎች ውስጥ የሚካተት ነበር። ይህ የተገለጸው የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ቁጥጥርና ኢንስፔክሽን ኮሚሽን፤ ከለውጡ በፊትና በኋላ ያለውን የሥራ እንቅስቃሴና የኮሚሽኑ መዋቅር አደረጃጀት ጥናትን በተመለከተ እየተደረገ ካለው ግምገማ በኋላ ነው።

በሳምንቱ አጋማሽ ላይ በአዳማ በተደረገው ምክክር፤ የክልሉ የቁጥጥር ኢንስፔክሽን ኮሚሽን አመራሮች የተሳተፉበት ነበር።

የቁጥጥር ኮሚሽኑ ኮምሽነር አቶ አወቀ ኃይለማርያም በመድረኩ መክፈቻ እንዳሉት፤ ከዚህ በፊት የተከሰተውን የፓርቲ ውስጥ ድክመት ያስከተለውን ውድቀት በመጥቀስ፣ አሁን ከዚህ በፊት በኢሕአዴግ ዘመን እንደተለመደው የይስሙላ ተቆጣጣሪ ኮሚሽን መኾን እንደማይችል ገልጸዋል።

ጠንካራና ፓርቲው ራሱን በራሱ እያረመ እንዲሔድ ማድረግ የሚያስችል አደረጃጀት እንዲሆንም ይሠራል ያሉት ኮሚሽነሩ፤ ተልዕኮው ምን መምሰል እንዳለበትና የሚሠሩት ሥራዎችም በዚህ መድረክ በግልጽ የሚቀመጡበት ይኾናል ተብሏል። (ኢዛ)

ያልተሳካው ሽምግልና

በሕወሓትና በብልጽግና ፓርቲ መካከል ያለውን ልዩነት በሽምግልና ለመፍታት የተለያዩ ጥረቶች ሲደረጉ ቆይተዋል። ባሳለፍነው ሳምንትም በሕወሓት ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል በአቶ አዲስዓለም ባሌማ የሚመራ የሕወሓት አሸማጋይ ቡድን ወደ አዲስ አበባ በመምጣት ለመሸማገል የተደረገው ጥረት አልተሳካም።

ሽምግልናው ያልሰመረው ብልጽግና ፓርቲ ሕወሓት ወደ ሕጋዊ መስመር እስካልመጣ ድረስ ምንም ዐይነት ሽምግልና ሊኖር አይችልም በማለቱ ነው። ብልጽግና ፓርቲ ሕወሓት ሕገ መንግሥቱን አክብሮ እስካልተቀንሳቀሰ ድረስ ምንም ዐይነት ምክክርና ድርድር አያስፈልግም፤ ሽምግልናም አይኖርም በማለቱ ነውም ተብሏል። (ኢዛ)

ሙስጠፌ ይናገራሉ

ከለውጡ ወዲህ በተለያዩ አገራዊ ጉዳዮችና በተለይም በወቅታዊው ለውጥ አቀንቃኝነታቸው በተደጋጋሚ ስማቸው የሚነሳው የሶማሌ ክልል ምክትል ፕሬዝዳንት አቶ ሙስጠፌ መሐመድ በዚህ ሳምንት በተለይ ሕወሓትን በተመለከተ የሰጡት ቃለምልልስ የብዙዎችን ትኩረት የሳበ ነበር። በዚህ ቃለምልልሳቸው የሕወሓትን የቀደመ አስተዳደር በዓለም እስካሁን ብቸኛው በጣም የሚጠላትን አገር የመራ ፓርቲ ሕወሓት ብቻ ነው በማለት ነበር።

“ሕወሓት የሚጠላውን ነገር ሁሉ “አማራ ነህ” ይለዋል” ያሉት ሙስጠፌ፤ “ዶ/ር ዐቢይ ኦሮሞ እንደኾነ ስለማያውቁ ሳይኾን የጠሉትን ሁሉ አማራ ብለው መጥራት ስለሚፈልጉ ነው። ይኼውም ለእነሱ አማራ ማለት ጠላት ማለት ነው” በማለት የሕወሓትን ተግባራት ተችተዋል።

ሕወሓት ማለት’ኮ አገር እየመራ አገራዊ ተቃርኖዎችን የሚተነትን አስማተኛ ድርጅት፤ የትም ዓለም አገር እየመራ አገሪቱን የሚመራበት አካሔድ ትክክል ባለመኾኑ ሊፈርስ ይችል ይኾናል እንጂ፤ ከሕወሓት ውጭ መሪው አገር እንድትፈርስ የሠራ የለም የሚል ጠንከር ያለ አቋማቸውን አንጸባርቀዋል።

አሁንም ሕወሓት ከግብጽ ጋር ይሠራል የሚል እምነት ያላቸው አቶ ሙስጠፌ፤ ሕወሓት አይደለም ከግብጽ ከየትኛውም ኃይል ይሁን ኢትዮጵያን የሚያጠፋለት ከኾነ አይተባበርም ማለት እንደማይቻልም በዚሁ ቃለምልልሳቸው አመልክተዋል። (ኢዛ)

አቶ ስዩምና የገጠማቸው ተቃውሞ

ከሰሞኑ አነጋጋሪ ዜናዎች የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር አቶ ስዩም መስፍንን ገጠማቸው የተባለ አንድ ክስተት ነው። አቶ ስዩም በተደጋጋሚ የተቃውሞ ድምፅ በሚሰማበት የትግራይ ክልል ወጅራት በመሔድ “የፌደራል መንግሥት፣ ኤርትራ እና አማራ ሊወረን ነው ታገሉ” በማለት የወጅራት ነዋሪዎችን ለመቀስቀስ ተጉዘው ያሰቡት ሳይኾን መመለሳቸው ነው።

አቶ ስዩም መስፍን የወጅራት ሕዝብን ሰብስበው፤ “ከድሮ ጀምሮ የወጅራት ሕዝብ ጀግና ነው፤ አልገዛም ባይ ነው፤ ስለዚህ አሁንም የፌደራል መንግሥት፤ ኤርትራ እና አማራ ሊወረን ነው ታገሉ” በማለት ቢቀሰቅሱም ተቃውሞ ገጥሟቸዋል።

አቶ ስዩም የወረዳዋ ነዋሪዎች ያቀረበውን ጥያቄ ለማለባበስና ሌላ ውዥንብር ሊፈጥሩባቸው ቢሞክሩም፤ ሕዝቡ ግን “እኛ የተሰበሰብነው ጥያቄያችንን ልትመልሱልን መስሎን እንጂ፤ ከማንም ጋር አንዋጋም። በውጊያ ያተረፍነው ነገር የለም” በማለት ነዋሪዎቹ ለአቶ ስዩም ምላሽ ሰጥተዋል።

ከወጅራት ነዋሪዎች በተደጋጋሚ ወረዳችን ይመለስልን የሚል ሰላማዊ ሰልፎች ቢደረጉም፤ መንግሥት ይኼን ከመመለስ ይልቅ ሌላ ስም በመለጠፍ እያሸማቀቃቸው የነበረ ሲሆን፤ አቶ ስዩም ሲመጡ ጥያቄያችን የወረዳ ነው እንጂ ቅስቀሳ አይደለም ማለታቸው ታውቋል። (ኢዛ)

ሽልማት ለታከለ ኡማ

የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ከአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ምክር ቤት እውቅና የተሰጣቸው በዚህ ሳምንት ነበር። ምክር ቤቱ ለኢንጅነር ታከለ ኡማ እውቅናና ሽልማቱን ያበረከተላቸው፤ በተለይ የሚሠሩ ሥራዎች የከተማዋ ነዋሪዎችን ያማከለ እንዲኾን በማድረግ በኩል ውጤታማ ሥራዎችን በመከናወናቸው ስለመኾኑ ተገልጿል።

አስታዋሽ አጥተው ለዘመናት የተዘነጉ የማኅበረሰብ ክፍሎችን ማዕከል ያደረጉ ሥራዎችን በመሥራት ላበረከቱት አስተዋጽኦ የእውቅና ሽልማቱ የተበረከተላቸው ስለመኾኑ የተገለጸ ሲሆን፣ በተጨማሪም የከተማዋን ታሪካዊና የቱሪዝም መስህብነት የሚያጎሉ፤ እንዲሁም የነዋሪዎችን ችግር የሚፈቱና ኢኮኖሚያዊ ሚና ያላቸው ታላላቅ ፕሮጀክቶችን ማስጀመራቸውና በታሰበላቸው ጊዜ እንዲጠናቀቅ ማስቻላቸው ለእውቅናው ካበቁዋቸው ምክንያቶች ውስጥ ተካትተዋል።

በከተማዋ ለሚገኙ ተማሪዎች ምግብ፣ የትምህርት ቁሳቁስ እና ዩኒፎርም እንዲቀርብ አመራር መስጠታቸው፤ ሥራውንም ተቋማዊ እንዲኾን ማድረጋቸውና ሌሎች በጐ ተግባሮቻቸው ተዘርዝረው እውቅናውን እንዲያገኙ ተደርጓል። (ኢዛ)

የደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ጠለፋና ተከሳሾች

የደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ጠለፋ የአንድ ሰሞን አነጋጋሪ ጉዳይ ነበር። የዚህ ጠለፋ ድራማ ዛሬም ድረስ እንቆቅልሽ እንደኾነ ነው። ይሁንና በዚህ ጠለፋ እጃቸው አሉባቸው የተባሉ ግለሰቦች ፍ/ቤት ቀርበዋል።

የደንቢዶሎ ዩኒቨርሲቲ ተማሪዎችን በመጥለፍ እነዚህ ግለሰቦች የተመሠረተባቸው ክስ በሽብር ወንጀል ነው። በነከሊፋ አብዱራህማን የክስ መዝገብ ከተከሰሱት 17 ግለሰቦች መካከል፤ ዘጠኙ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት የቀረቡ ሲሆን፤ በሦስት የሽብር ወንጀል የተከሰሱት ተከሳሾቹ በፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት ቀርበው የተከሰሱበት ወንጀል ተነብቦላቸዋል። ከዚህ ጋር ተያይዞ ተከሳሾቹ ለፌዴራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት መቃወሚያ በጽሑፍ ማቅረባቸውም ታውቋል።

በዚህ ሳምንት የእነዚህ ተከሶሾች ጉዳይ የያዘው ፍ/ቤት ዓቃቤ ሕግ በመቃወሚያው ላይ ምላሽ እንዲሰጥና ትእዛዝ ለመስጠት ፍርድ ቤቱ ለነሐሴ 25 ቀን 2012 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቷል። (ኢዛ)

ጠቅላይ ፍርድ ቤት ከ15 ሺህ በላይ መዝገቦች እልባት ሰጠ

የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በተጠናቀቀው በ2012 በጀት ዓመት ለ15 ሺህ 563 የሚኾኑ መዛግብትን እልባት ስለመስጠቱ የገለጸው በዚህ ሳምንት ነበር።

የፍርድ ቤቱ ከፍተኛ አመራሮችና ዳኞች በዳኝነት ዘርፉ የ2012 ዕቅድ አፈጻጸም ላይ ያካሔዱትን ውይይት ተከትሎ እንደተገለጸው፤ የፌደራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት በ2012 በጀት ዓመት ለ19 ሺህ 981 መዛግብት እልባት ለመስጠት ታቅዶ የነበረ ሲሆን፤ ለ15 ሺህ 563 መዛግብት እልባት በመስጠት የዕቅዱን 82 በመቶ ማከናወን ተችሏል ተብሏል።

የፌደራል ፍርድ ቤቶች የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ ለመከላከል በከፊል ዝግ ኾነው እንዲቆዩ እስከተወሰነበት መጋቢት ወር ድረስ፤ እልባት ማግኘት ከሚገባቸው 13 ሺህ 987 መዛግብት ውስጥ፤ 12 ሺህ 085 መዛግብት እልባት ማግኘታቸውንም የፍ/ቤቱ የኮምዩኒኬሽን ዳይሬክቶሬት አስታውቋል።

እልባት ከተሰጣቸው 15 ሺህ 563 መዛግብት መካከል 14 ሺህ 780 ጉዳዮች ወይም 95 በመቶ ያህሉ ከአንድ ወር እስከ አንድ ዓመት ባለው ጊዜ ውስጥ ውሳኔ ያገኙ ናቸው ብሏል። (ኢዛ)

ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከአንድ መቶ አስር ሚሊዮን ብር በላይ ለቀዳማዊት እመቤታቸው አበረከቱ

በዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተሰናድቶ ለሽያጭ ከቀረበው ከመደመር መጽሐፍ ሽያጭ የተገኘ 110 ሚሊዮን 671 ሺህ ብር የሚኾነውን ለቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት ተበረከ። ይህንን ገንዘብም ጠቅላይ ማኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ለቀዳማዊት እመቤት ዝናሽ ታያቸው አበርክተዋል።

ገንዘቡ በቀዳማዊት እመቤት ጽሕፈት ቤት በኩል በሁሉም የአገሪቷ ክልሎች እየተገነቡ ላሉ ትምህርት ቤቶች እንደሚውል ተገልጿል። እየተገነቡ ካሉት 20 ትምህርት ቤቶች ውስጥ ሰባቱ ተገንብተው ያለቁ ሲሆን፤ 13ቱ ት/ቤቶች ደግሞ ከ90 በመቶ በላይ ግንባታቸው መጠናቀቁ ታውቋል። (ኢዛ)

ኢሚግሬሽን ተመልሻለሁ ብሏል

ከኮሮና ወረርሽኝ ጋር ተያይዞ አገልግሎቶቻቸውን ባቀደው ልክ መሥራት ካልቻሉት ውስጥ አንዱ የኢምግሬሽን ዜግነትና ወሳኝ ኩነት ኤጀንሲ ነው። ሰሞኑን ይፋ ባደረገው መረጃ ግን፤ ወደ ሥራዬ ልመለስ ነው ብሏል።

በዚህም ሥራ የፓስፖርት፣ የቪዛ ማራዘም፣ የትውልድ መታወቂያና የመኖሪያ ፍቃድ እድሳት የሚፈልጉ ደንበኞች ቀድመው ኦንላይን ቀጠሮ አስይዘው ወደ ኤጀንሲው በቀጠሯቸው በመሔድ አገልግሎት የሚያገኙበት ሥርዓት መዘርጋቱን አሳውቋል። ይህ አገልግሎትም ከአንድ ወር በኋላ ተግባራዊ እንደሚኾን የተገለጸ ሲሆን፤ ኦንላይን አገልግሎት ማግኘት ለማይችሉ ተገልጋዮች ደግሞ፤ በተቋሙ በሚኖረው መጨናነቅ ሳቢያ ለኮቪድ 19 እንዳይጋለጡ አማራጭ ቅርንጫፍ ቢሮዎችን ለመክፈት ግንባታ መጀመሩን ተነግሯል። (ኢዛ)

በኢትዮጵያ በኮሮና ከተጠቁት 80 በመቶ የሚኾኑት ምልክት የሌለባቸው ናቸው

በኢትዮጵያ የኮሮና ቫይረስ ከተገኘባቸው 80 በመቶ የሚኾኑት የበሽታው ምልክት የማይታይባቸው እና የሕመም ስሜት የሌላቸው መኾኑን የጤና ሚኒስቴር ከሰሞኑ ባወጣው መግለጫ አስታውቋል።

የበዓል ሰሞን የነበሩ መዘናጋቶች የፈጠሯቸው ንክኪዎች፣ ሕብረተሰቡ ያለጥንቃቄ ሲሳተፍባቸው የነበሩ ሰልፎች አሁን ላለው የኮሮና ቫይረስ መስፋፋት ምክንያቶች መኾናቸውንም የሚያመለክተው ይኸው መረጃ፤ በሽታው ሌሎች አገራት ላይ እንዳደረሰው ጉዳት ባለማድረሱ ሕብረተሰቡ “እኛን አያጠቃንም” በማለት የጥንቃቄ መንገዶችን ችላ በማለቱ የቫይረሱ ሥርጭት እየተስፋፋ መምጣቱንም ይጠቁማል። (ኢዛ)

የሊባኖስ ፍንዳታና ኢትዮጵያውያን

ባሳለፍነው ሳምንት መጀመሪያ ላይ የሊባኖስ ዋና ከተማ ቤይሩትን ያራደው ፍንዳታ በሳምንቱ መጨረሻ የሞቱት ሰዎች ቁጥር 154 ላይ መድረሱ ተገልጿል። በርካታ ኢትዮጵያውያን ይኖሩበታል በተባለችው ቤይሩት ውስጥ እስካሁን ይፋ በኾነ መረጃ ወደ አራት መቶ ሺህ ገደማ ኢትዮጵያውያን በሊባኖስ እንደሚኖሩ የሚገመት ሲሆን፤ በዚያ የሚገኘው የኢትዮጵያ ቆንጽላ ጽሕፈት ቤትም አደጋው ከደረሰ ጀምሮ የኢትዮጵያውያን ጉዳይ እየተከታተለ ነው ተብሏል።

በሊባኖስ የሚገኙ ኢትዮጵያውያንን በተመለከተ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር እንዳስታወቀው ደግሞ እስካሁን ድረስ ባለው መረጃ 10 ኢትዮጵያዊያን ላይ ጉዳት የደረሰ ሲሆን፣ ከእነዚህም መካከል የአንድ ኢትዮጵያዊ ሕይወት ማለፉን አረጋግጧል። (ኢዛ)

ከህዳሴው ግድብ አቅራቢያ ሸፍጥ እየተመታ ነው

ከጥቂት ሳምንታት ወዲህ በተደጋጋሚ ሲነገሩ ከነበሩ ዜናዎች ውስጥ በቤኒሻንጉል ክልል ጉባ አካባቢ የታየው የጸጥታ ችግር ነው። በዚህ አካባቢ የታጠቁ ኃይሎች የሰው ሕይወት አጥፍተዋል።

ይህ የታጠቁ ኃይሎች ቡድን በቀደሙት ሳምንታት 15 ንጹኀን ሰዎችን የገደለ ስለመኾኑ የተገለጸ ሲሆን፤ በዚህ ሳምንት አጋማሽ ላይ ግን ይፋ እንደተደረገው በአካባቢው የዘር ግጭትና አለመረጋጋት ለመፍጠር አልሞ ሲንቀሳቀስ የነበረው ቡድን አካል ናቸው የተባሉ 121 ተጠርጣሪዎች መያዛቸው ተገልጿል። የክልሉ ፖሊስ እንደገለጸው ከእነዚህ 121 ተጠርጣሪዎች የተለያዩ የጦር መሣሪያዎች በቁጥጥር ሥር ውለዋል።

ቡድኑ የብሔር ግጭት ለመፍጠር፣ አካባቢው የህዳሴ ግድብ መገኛ መኾኑን ተከትሎ አለመረጋጋት እንዲፈጠር፤ በዚህም እንደ ክልል ብሎም እንደ አገር ትልቅ ጥፋት የመፍጠር ዓላማ ያለው ስለመኾኑም የክልሉ ፖሊስ ኮምሽን አስታውቋል።

በጉዳዩ ላይ ተጨማሪ መረጃ የሰጡት የክልሉ ፖሊስ ኮምሽን ኮሚሽነር መሐመድ ሐምደኒል፤ “ቡድኑ አሁን አገርን እየመራ ያለው ፓርቲም ኾነ ለውጡ እኛን አይወክለንም፤ በማለት ወጣቱንና ሕዝቡን ለአመጽ የሚቀሰቅሰው ቡድን በክልሉ ከሚገኙ ተፎካካሪ ፓርቲዎች ጋር ትልቅ የጥፋት ቅንጅትና ተገቢ ድጋፍ ያገኛል” ብለዋል።

በተለይም በለውጥ ላይ በምትገኘው የአገሪቱ አሁናዊ ሁኔታ ላይ ያኮረፈው ሕወሓት በአካባቢው በኢንቨስትመንት ስም የሚገኙ ባለሀብቶችን በመጠቀም ቡድኑ ለያዘው የጥፋት ተልዕኮ መሳካት የተለያዩ ድጋፎችን ሲያደርግ እንደነበር በዚሁ መረጃ ተጠቅሷል።

ከተያዙት ከግለሰቦች ጋር ቡድኑ ሲጠቀምባቸው የነበሩ አንድ አርፒጂ የተባለ የቡድን የጦር መሣሪያ ከ3 አቀጣጣይ እና 1 ቅምቡላ ጋር፣ 6 ክላሽ፣ 17 ኋላቀር የጦር መሣሪያዎች እንዲሁም 293 የብሬን እና 30 የክላሽ በአጠቃላይ 223 የጥይት ፍሬ መያዙ ታውቋል። (ኢዛ)

ለአዲስ አበባ 61 ቢሊዮን ብር በጀት ጸደቀ

የአዲስ አበባ ከተማ ምክር ቤት የአዲስ አበባ ከተማ ለ2013 በጀት ዓመት ያስፈልጋታል ያለውን የ61 ቢሊዮን ብር በጀት አጸደቀ።

በዚህም ምክር ቤቱ ለበጀት ዓመቱ ለካፒታል እና ለመደበኛ ሥራ ማስኬጃ የቀረበለትን 61 ቢሊዮን ብር በጀት ያጸደቀው በሳምንቱ አጋማሽ ላይ ለሁለት ቀናት ባካሔደው መደበኛ ስብሰባው ላይ ነው። (ኢዛ)

በ2012 በጀት ዓመት 40 ቢሊዮን ብር ግብይት ተፈጽሟል

ባሳለፍነው ሳምንት ይፋ ከኾኑ ቢዝነስ ነክ መረጃዎች ውስጥ አንዱ የኢትዮጵያ ምርት ገበያ በ2012 በጀት ዓመት 761,914 ሜትሪክ ቶን ምርት በ40 ቢሊዮን ብር ማገበያየቱን የሚመለከተው አንዱ ነው። የኢትዮጵያ ምርት ገበያ እንዳስታወቀው የ2012 አፈጻጸሙ ከዕቅዱ በምርት መጠን 99 በመቶ በዋጋ ደግሞ 113 በመቶ ሲያሳካ ነው ተብሏል። የ2012 አፈጻጸሙ ካለፈው በጀት ዓመት ጋር ሲነፃፀር ደግሞ በግብይት መጠን 12 በመቶ በዋጋ በ18 በመቶ መጨመሩን አመልክቷል።

የዚህ ዓመት የግብይት መጠንና ዋጋ እስከዛሬ ምርት ገበያው ካከናወነው ግብይት ከፍተኛ ነው። በበጀት ዓመቱ ከተገበያየው ምርት መጠን ውስጥ ቡና 40.5 በመቶ፣ ሰሊጥ 34.4 በመቶ ድርሻ እንዳላቸው የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንድም አገኘው ነገራ ተናግረዋል። ለአገራችን ከፍተኛ የውጭ ምንዛሬ የሚያስገኘው ቡና ግብይት ከዕቅድ በላይ በመጠን 10 በመቶ፣ በዋጋ 19 በመቶ በመከናወኑ ለአገራዊ የወጪ ንግድ መሻሻል አስተዋጽኦ ነበረውም ብለዋል።

እንደ ምርት ገበያው መረጃ በበጀት ዓመቱ 308,303 ቶን ቡና በ24.8 ቢሊዮን ብር፣ 262,099 ቶን ሰሊጥ በ11.4 ቢሊዮን ብር፣ 78,208 ቶን አኩሪ አተር በ1.1 ቢሊዮን ብር፣ 59,210 ቶን አረንጓዴ ማሾ በ1.6 ቢሊዮን ብር፣ 47,825 ቶን ነጭ ቦሎቄ በ1.04 ቢሊዮን ብር፣ 6,259 ቶን ቀይ ቦሎቄ በ103 ሚሊየን ብር ግብይታቸው ተከናውኗል።

የኢትዮጵያ ምርት ገበያ ባለፉት 12 ዓመታት 6.6 ሚሊዮን ሜትሪክ ቶን ምርት በ275 ቢሊዮን ብር ማገበያየቱም ታውቋል። (ኢዛ)

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ባንኮች ኢንቨስትመንት ሊያደርጉ ነው

የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር እና በኢትዮጵያ ውስጥ በመንቀሳቀስ ላይ የሚገኙ ባንኮች በጋራ ኩባንያ በማቋቋም ለመሥራት ተስማምተዋል። የአዲስ አበባ ከተማ ምክትል ከንቲባ ኢንጂነር ታከለ ኡማና የባንኮች ፕሬዝዳንቶች ደረሱበት በተባለው ስምምነት መሠረት አንድ አትራፊ ኩባንያ በማቋቋም በጋራ ለመሥራት ነው የተስማሙት።

በአክሲዮን ኩባንያ ደረጃ የሚዋቀረው ይህ ኩባንያ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደርና ሁሉንም ባንኮች በአክሲዮን ባለቤትነት የሚያቅፍ ሲሆን፤ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መሬት በማቅረብ በዐይነት የአክሲዮን ባለድርሻ እንደሚኾን ታውቋል።

ባንኮችም በጥሬ ገንዘብ በማዋጣት አሁን ስምምነት የተደረሰበትን ኩባንያ በማኅበር በአዲስ አበባ ከተማ ለተለያዩ ቢዝነሶችና አገልግሎቶች የሚውል ዘመናዊ ሞል (የገበያ አዳራሽ) እንደሚገነባ ይጠበቃል።

አስተዳደሩ ለዚህ ዘመናዊ ሕንፃ ግንባታ የሚሆን ቦታ ቦሌ መንገድ ፍሬንድሽፕ ሕንፃ ጐን ያለውን ክፍት ቦታ መስጠቱ ታውቋል። አስተዳደሩ ከዚህ ኢንቨስትመንት የሚገኘውን ትርፍ ለተለያዩ ማኅበራዊ አገልግሎት ወጪ መሸፈኛ እንዲያውለው ታስቦ የተሰናዳ ኢንቨስትመንት መኾኑም ተነግሯል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!