Ethiopia Zare's weekly news digest, week 51st, 2012 Ethiopian calendar

ከነኀሴ 18 - 24 ቀን 2012 ዓ.ም. የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

የዓመቱ ሃምሳ አንደኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች

ኢዛ (ከነኀሴ 18 - 24 ቀን 2012 ዓ.ም.) ባሳለፍነው ሳምንት ውስጥ አነጋጋሪ ከነበሩ ዜናዎች መካከል ኢዜማ ከመሬት ወረራና ከኮንዶሚኒየም አሰጣጥ ጋር ተያይዞ ሊሰጥ የነበረው መግለጫ መከልከሉ ነው። አዲሷ ምክትል ከንቲባ ሳምንቱን በተለያዩ ክንውኖች የዜና ሽፋን የተሰጣቸው ሲሆን፤ ጐልቶ የሚጠቀስላቸው ደግሞ የከተማዋን የሰላም ምክር ቤት በይፋ ማቋቋማቸው ነው። ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ግድያ ለመፈጸም ቦምብ በመወርወር ተጠርጥረው ጉዳያቸው በፍርድ ቤት ሲታይ የነበሩት አምስት ተከሳሾች፤ ጥፋተኛ መባላቸው የተሰማው በዚህ ሳምንት ነበር። ፍርዳቸው ጥቅምት 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ይጠበቃል።

ከፍርድ ቤት ውሎ ጋር ተያይዞ በነአቶ ጃዋር መሐመድ ላይ መሰማት የተጀመረው የዓቃቤ ሕግ ምስክሮች በሳምንቱ የፍርድ ቤት ውሎ የሚጠቀስ ዜና ነው። የፌዴራል ፖሊስ የደንብ ልብስ በይፋ መቀየሩ የተገለጸበትና በአዲሱ ዓመት በአዲስ የደንብ ልብስ ለሥራ እንደሚሰማራ በሳምንቱ መጨረሻ ላይ ተገልጿል። የታላቁ ህዳሴ ግድብ የሦስትዮሽ ስብሰባ በዚህ ሳምንት የተካሔደ ሲሆን፤ ቀጣይ ስብሰባው በአዲሱ ዓመት አራተኛው ቀን ላይ ይካሔዳል። አሜሪካ ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ በከፊል ለማቋረጥ ወሰነች የተባለው ዜናም በሳምንቱ ትኩረት ከተሰጣቸው ዜናዎች ውስጥ የሚጠቀስ ነበር።

የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን በቅርቡ በተለያዩ የኦሮሚያ ከተሞች የተፈጠረው ኹከት በቀጥታ ኦርቶዶክስ ላይ ያነጣጠረ ጥቃት ነበር ብላ ጠንከር ያለ መግለጫ የሰጠችበትም ሳምንት ነው።

በሕገወጥ የቴሌኮም የማጭበርበር ተግባር አሥራ አንድ ግለሰቦች ለሕገወጥ ተግባራቸው ከሚጠቀሙት መሣሪያ ጋር እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል። ግለሰቦቹ ቴሌን በዓመት ከ137 ሚሊዮን ብር በላይ ያሳጡት ነበር።

ሕወሓት እየሠራው ያለውን ሕገወጥ ተግባር የፌዴራል መንግሥቱ ችላ ብሎታል በማለት የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ምሁር ወቀሱ። ከዚሁ ጋር ተያይዞ ዶክተር አረጋዊ በርሔ በትግራይ ክልል ከምርጫው ጋር በተያያዘ የዜጐች ስቃይ ብሷል ሲሉ መግለጫ ሰጥተዋል።

ሕወሓት የ30 አርሶ አደሮች የሰሊጥ እርሻን እንዲወድም አድርጓል የሚለው ዜናም በአነጋጋሪነቱ የሚጠቀስ ነው። የወልቃይት ጠቀዴ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴም ይህንኑ ጉዳይ ኮንኖ መግለጫ አውጥቷል።

ከፖለቲካ ነክ ወሬዎች ባሻገር ከክረምቱ ጋር ተያይዞ በተፈጠረ ጐርፍ ብዙዎችን ያፈናቀለና ማስጠንቀቂያ የተሰጠበት ሳምንት ኾኖ አልፏል። አዲስ አበባም ብዙም ባልተለመደ ሁኔታ ጠንከር ያለ በረዶ ያስተናገደችበት ክስተት ታይቷል። ብዙ ተስፋ ተሰጥቶት የነበረውና በ2012 በጀት ዓመት 5.1 ቢሊዮን ብር ለማግኘት የታቀደ ቢኾንም፤ የተገኘው ሁለት ቢሊዮን ብቻ ኾኗል። ዋነኛውም ምክንያት ኮቪድ 19 ነው። በኢትዮጵያ ዛሬ ዝግጅት ክፍል የተጠናከሩትን የሳምንቱን አንኳር ወሬዎች እነኾ!

በሕወሓት ተግባር የፌዴራል መንግሥቱን ዝምታ ምሁሩ ወቀሱ

ሕወሓት እየፈጸመ ያለውን ሕገወጥና ያልተገባ ተግባር የፌዴራል መንግሥት ችላ ብሎታል በማለት አንድ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ምሁር ወቀሱ።

የፌዴራል መምህሩ ዶክተር ሲሳይ ጣሴ እንደገለጹት፤ በአሁኑ ወቅት በሕወሓት አመራሮች እየተፈጸመ ያለውን ግፍና በዜጐች ላይ እየደረሰ ያለውን በደል የፌዴራል መንግሥቱ ችላ ማለቱ ተገቢ ያለመኾኑንና አሁን ላይ ዝም የማለቱን አሳሳቢነት ሳይገልጹ አላለፉም። የፌዴራል መንግሥቱ ለቀድሞ የሶማሌ ርዕሰ መስተዳድር አብዲ ኢሌ ላይ የወሰደውን እርምጃ በማስታወስ፤ አሁን በትግራይ ክልል በሕወሓት የሚፈጸመውን በደልም ችላ ማለት አልነበረበትም የሚል አንደምታ ያለውን ሐሳባቸውን በዚህ ሳምንት ባደረጉት ቃለ ምልልስ ገልጸዋል። (ኢዛ)

ምርጫው በትግራይ የዜጐችን ስቃይ አብሷል ተባለ

ባሳለፍነው ሳምንትም በትግራይ ክልል ስለሚካሔደው ምርጫ በተለያዩ ወገኖች የሚሰጡ አስተያየች እየተደመጡ ነው። ከሰሞኑ የትግራይ ዴሞክራሲ ፓርቲ (ትዴፓ) ሊቀመንበር፤ ሕወሓት በትግራይ ክልል አካሒደዋለሁ የሚለውን ምርጫ የሚቃወሙ ዜጎች ለሞትና ስቃይ እየተዳረጉ መኾኑን አስታውቀዋል።

በክልሉ የነበረው አፈና ሕወሓት ለምርጫ የሚያደርገውን እንቅስቃሴ ተከትሎ ስለመባባሱም ሊቀመንበሩ ዶ/ር አረጋዊ በርሄ አመልክተዋል።

እንደ እርሳቸው ገለጻ ምርጫው የአገሪቱን ሕገ መንግሥት፣ የክልሉን ሕገ መንግሥትና የምርጫ ቦርድን አሠራር የጣሰ ከመኾኑ ሌላ ኢኮኖሚያዊ፣ ፖለቲካዊና ማኅበራዊ ጫና እያስከተለ እንደሚገኝም አብራርተዋል።

በክልሉ በተለያዩ አካባቢዎች ተቃውሞዎች መነሳታቸውንም በመጥቀስ፤ ብዙ ዜጎች ለድብደባ፣ ለከባድ እንግልት፣ ለእስራትና ለሞት እየተዳረጉ በማመልከት፤ ሕወሓት እየሠራ ነው ያሉትን ተግባር አምርረው ተቃውመዋል።

ለሕዝቡ ጥቅም መዋል የሚገባው ገንዘብም እየባከነ እንደሚገኝም በዚሁ ሰሞናዊ ገለጻቸው አመልክተዋል። (ኢዛ)

የ30 አርሶ አደሮች የሰሊጥ እርሻ በሕወሓት ወደመ መባሉ እያነጋገረ ነው

ከሰሞኑ ለየት ብሎ ከተሰሙ ዜናዎች ውስጥ በወልቃይት ጠገዴ አፅሚ ሃርማዝ በተባለ ቀበሌ ከ300 ሔክታር መሬት በላይ የነበረ የሰሊጥ እርሻ ኾን ተብሎ እንዲወድም መደረጉ ነው። ይህ በሕወሓት አመራሮች በተሰጠ ትእዛዝ የተፈጸመ ነው የተባለው ውድመት የተከሰተው ነሐሴ 19 ቀን 2012 ዓ.ም. ሲሆን፤ የሰሊጥ እርሻውም የ30 ገበሬዎች ነበረ ተብሏል።

ይህንን ተፈጸመ የተባለውን ድርጊት አስመልክቶ ከ300 ሔክታር በላይ በሰሊጥ የተሸፈነ የአርሶ አደሮች ማሳ በሕወሓት ትእዛዝ በመርዝ መውደሙን የወልቃይት ጠገዴ የአማራ ማንነት አስመላሽ ኮሚቴ አስታውቋል።

ሕወሓት በወልቃይት፣ ጠገዴ እና አካባቢው እያራመደው ባለው ኢ-ሰብአዊ ድርጊትና ማን አለብኝነት የአማራ ማንነት ጥያቄ አቅርባችኋል በሚል ሰበብ ከዚህ ቀደም እንደሚደረገው ሁሉ አርሶ አደሮችን በኢኮኖሚ የማሽመድመድ እና ለስደት የመዳረግ ስትራቴጂውን ገፍቶበታል ብሏል፤ የወሰንና ማንነት አስመላሽ ኮሚቴው።

በወልቃይት ጠገዴ መሬት አፅሚ ሃርማዝ ቀበሌ ልዩ ስሙ ስየ በተባለ ቦታ ላይ የ30 አርሶ አደሮች የሰሊጥ ማሳ በማላታይን መርዝ እንዲወድም መደረጉን የጠቆመው ይህ መግለጫ፤ አርሶ አደሮቹ በተማጽኖ ቢጠይቁም “ከመንግሥት ተልከናል” ባሉ ግለሰቦች አማካኝነት በትግራይ የልዩ ኃይል አባላት ጥበቃ እየተደረገላቸው ማሳዎቹን ማላታይን መርዝ በመርጨት አውድመዋል ይላል። ምን አጠፋን? ለሚለው የገበሬዎቹ ጥያቄ “አማራዎች እዚህ ምን አላችሁ? ይህ የትግራይ መሬት ነው” የሚል ምላሽ ብቻ እንደተሰጣቸው ኮሚቴው ገልጿል።

ሕወሓት በአካባቢው እያደረሰ ያለውን ግድያ፣ ማሳደድና ዘር ማጥፋት የፌዴራል መንግሥት ጣልቃ ገብቶ እንዲያስቆምም ኮሚቴው በዚሁ መግለጫ ላይ ጥሪ አቅርቧል። (ኢዛ)

ግድቦች በመሙላታቸው ማስጠንቀቂያ ተሰጠ

ክረምቱ አየል ብሎ ከታየበት የነሐሴ ወር መጀመሪያ ጀምሮ ግድቦች የሞሉ ስለኾኑ የማስተንፈስ ሥራ እየተሠራ በመኾኑ አሥራ አንድ ግድቦች አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች እንዲነሱና ጥንቃቄ እንዲያደርጉም የተፋሰስ ባለሥልጣን ያስታወቀው በዚህ ሳምንት ነው። እንደ ባለሥልጣኑ መረጃ የማስተንፈስ ሥራው ይከናወንባቸዋል ብሎ የጠቀሳቸው በቆቃ፣ ግልገል ጊቤ፣ ተከዜ፣ ጣና ለበስ በተለይም ፎገራና ደንቢያ፣ ግልገል ጊቤ ሦስት፣ መልካ ዋከና፣ ፊንጫ፣ አመርቲነሽ፣ ከሰም፣ መካከለኛው አዋሽ፣ ተንዳሆ፣ ታችኛው አዋሽ እና የገናሌ ዳዋ ግድቦች ናቸው።

በተለይ ከሰም ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያሻው ያስገነዘበው ባለሥልጣኑ፤ በተጠቀሱት ግድቦች አካባቢ ያሉ ነዋሪዎች ጥንቃቄ እንዲያደርጉም አሳስቧል። ከሰሞኑ ከክረምቱ መጠንከር ጋር ተያይዞ በአፋር፣ በደቡብ እና በኦሮሚያ ክልሎች አንዳንድ ወንዞች ሞልተው ወደ 100 ሺሕ የሚኾኑ ዜጐችን ማፈናቀላቸው ተነግሯል። (ኢዛ)

በጠቅላይ ሚኒስትሩ ላይ ቦምብ የወረወሩ ተከሳሾች ጥፋተኛ ተባሉ

ከሰሞኑ አንድ የተሰማ ዜና ወደኋላ ሁለት ዓመት የኾነውን የሚያስታውስ ነው። ይህም ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በመስቀል አደባባይ የተፈጸመን አንድ ያልተጠበቀ ክስተት ይመለከታል።

ሰኔ 16 ቀን 2010 ዓ.ም. በአዲስ አበባ መስቀል አደባባይ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ በተካሔደ የድጋፍ ሰልፍ ላይ ቦምብ በመወርወር ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይን ለመግደል የተደረገ ሙከራ ነበር። በዚህ የሽብር ወንጀል ተጠርጥረው የታሰሩ ሰዎች ጉዳያቸው የተዘነጋ ቢመስልም፤ በዚህ ሳምንት ግን በዚህ የሽብር ወንጀል የተከሰሱ አምስት ተከሳሾች ጥፋተኛ ተብለዋል።

ጌቱ ቶሎሳ፣ ብርሃኑ ጃፋር፣ ጥላሁን ጌታቸው፣ ደሳለኝ ተስፋዬ እና ባሕሩ ቶላ በተባሉት ተከሳሾች ላይ የጥፋተኝነት ፍርዱን ያስተላለፈው የፌደራሉ ከፍተኛ ፍርድ ቤት 1ኛ የወንጀል ችሎት ነው።

ተከሳሾቹ በ1996 ዓ.ም. የወጣውን የኢፌዴሪ የወንጀል ሕግ አንቀጽ 32/1ሀ እንዲሁም አንቀጽ 38 እና የፀረ ሽብርተኝነት አዋጅ ቁጥር 652/2001 አንቀጽ 3 ሥር የተመለከተውን በመተላለፍ ክስ የቀረበባቸው ናቸው። በአገሪቱ ያውን ለውጥ ተከትሎ በጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ የሚመራ መንግሥት መኖር የለበትም በሚል የራሳቸውን ዓላማ ለማራመድ በማሰብ መንቀሳቀሳቸውን ዓቃቤ ሕግ የክስ መዝገብ ያመለክታል።

በሰኔ 16ቱ ጥቃት የሁለት ሰዎች ሕይወት ሲያልፍ ከ163 በላይ ሰዎች ላይ ደግሞ ከከባድ እስከ ቀላል የአካል ጉዳት እንደደረሰባቸው ይታወሳል። በፍርድ ቤቱ ውሳኔ መሠረት በተከሳሾቹ ላይ የቅጣት ውሳኔ ለመስጠት ለጥቅምት 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ሰጥቷል። ተከሳሾቹም እስከ ጥቅምት 17 ድረስ ግን የቅጣት ማቅለያዎችን ማቅረብ እንደሚችሉ ፍርድ ቤቱ ትእዛዝ ሰጥቷል። (ኢዛ)

በህዳሴ ግድብ ዙሪያ

የኢትዮጵያ፣ ሱዳን እና ግብጽ የውኃ ጉዳይ ሚኒስትሮች ቅዳሜ ዕለት ስብሰባ በሣምንቱ መጨረሻ ስለመካሔዱ የውኃ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር አስታውቋል። በስብሰባው ዙሪያም ባወጣው መግለጫ በስብሰባው የሒደቱ ታዛቢ የኾኑት የደቡብ አፍሪካ፣ የአውሮፓ ሕብረት እና የአሜሪካ ተወካዮች እንዲሁም የአፍሪካ ሕብረት የወከላቸው ባለሙያዎች ስለመገኘታቸው ጠቅሷል።

አያይዞም በስብሰባው ላለፈው አንድ ሳምንት በአገራቱ ባለሙያዎች በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ አሞላል እና ውኃ አለቃቀቅ ደንብ ላይ ሲከናወን የነበረው የባለሙያዎች ድርድር ሪፖርት እንደቀረበና የአገራቱ ባለሙያዎች ከነሐሴ 15 ቀን 2012 ጀምሮ የበይነ መረብ ስብሰባቸውም አስታውሷል።

በቀጣይ የሚኖረውን ሒደት በሚመለከት አገራቱ የድርድሩን ሒደት የሚገልጥ ደብዳቤ ለደቡብ አፍሪካዋ ዓለም አቀፍ ግንኙነት እና ትብብር ሚኒስትር እና የአፍሪካ ሕብረት የአስፈጻሚ ምክር ቤት የወቅቱ ሊቀመንበር የተከበሩ ዶ/ር ናዴሊ ፓንዶር ለመላክ መስማማታቸውን ይኸው መግለጫ አመልክቷል።

በመግለጫው ማጠቃለያ ላይም ሱዳን የምትሰጠው ማረጋገጫ የሚጠበቅ ኾኖ፤ የሦስትዮሽ ስብሰባው መስከረም 4 ቀን 2013 ዓ.ም. እንደሚቀጥል ይጠበቃል ብሏል። (ኢዛ)

የኦሮሚያ ብልጽግና የተለያዩ እርምጃዎች እየወሰድኩ ነው አለ

የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ በየደረጃው ተልዕኮን ማዕከል ያደረገ ግምገማና የማጥራት እርምጃ በመውሰድ፤ መልሶ የማደራጀት ሥራ ያከናወነ መኾኑን የፓርቲው ጽ/ቤት ኃላፊ የገለጹት ባሳለፍነው ሳምንት ነበር። የጽሕፈት ቤት ኃላፊው እንደገለጹት፤ ይህ እርምጃውም በሕዝቡ ውስጥ ካለው የአብሮነትና የሰላም እሴት የመነጨ የጽንፈኛ አጀንዳትን የማክሸፍ እርምጃ ጋር ተዳምሮ ከዚህ በኋላ ያለው ጊዜ ተስፋዎች ደግሞ ይበልጥ የሚጎለብቱበት ይኾናል።

የጽሕፈት ቤቱ ኃላፊ አቶ ፍቃዱ “ፓርቲው የሚወያየው፣ የሚገመግመውና የሚያጠራው ተስፋን ለማለምለም ነው እንጂ፤ የነበረውን ችግር ለማስቀጠል አይደለም” ብለዋል። “ይኼን ሁሉ የሚያደርገውም በሁሉም ረገድ ከችግር ለመውጣት ነው። ኾኖም በአንድ ግምገማና በአንድ ኮንፈረንስ ሁሉም ችግሮች በአንድ ጊዜ ጠርተው ይጠፋሉ ማለት አይቻልም” በማለት አክለዋል።

በቅርቡ የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ ከፍተኛ አመራሮች ኮንፈረንስም በወቅታዊ የአገራዊ ሁኔታ እንዲሁም የክልሉ ሁኔታ፣ ብልጽግና ያለበትን ደረጃ፤ እንዲሁም እንደ አጠቃላይ አንድ ፓርቲ ያሉበትን ጠንካራና ደካማ ጎኖች ማዕከል ያደረገ፤ ምን ድሎች ተገኝተዋል የሚለውን ማዕከል አድርጎ የገመገመ መኾኑንም ኃላፊው ከሰጡት ሰሞናዊ ማብራሪያ ላይ ገልጸዋል።

በቅርቡ በኦሮሚያ ክልል ከተፈጠረው ኹከት ጋር ተያይዞ በተፈጠረው ውድመት በአመለካከትም ይሁን በተግባር በዛ ችግር ውስጥ ባይኖሩም ያ ሁሉ ጥፋት በሚደርስበት ጊዜ መከላከልና ጉዳቱን ማስቀረት ባለመቻላቸው ጭምር ተጠያቂ ስለመኾናቸው ጠቅሰው፤ በዚህ አግባብ ከመዋቅር የተወገዱ አሉ፤ ሒደቱ እየተጣራም በቀጣይ በሕግም የሚጠየቁ እንደሚኖሩ አመልክተዋል። (ኢዛ)

የአዲስ አበባ የሰላም ምክር ቤት ተመሠረተ
የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ፕሬዝዳንት የምክር ቤቱን ይመራሉ

ለአዲስ አበባ ሰላምና መረጋጋት ይሠራል የተባለው የአዲስ አበባ የሰላም ምክር ቤት መቋቋሙ ይፋ የኾነው ባሳለፍነው ሳምንት አጋማሽ ላይ ነው። ከአዲሷ ምክትል ከንቲባ ሰሞናዊ ክንውኖች መካከል አንዱ የኾነው የሰላም ምክር ቤት ቀበሌ ድረስ የሚወርድ መዋቅር ይኖረዋል። ይህንን ምክር ቤት እንዲመሩም የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲው ፕሬዝዳንት ፕሮፌሰር ጣሰው ወልደሃና ፕሬዝዳንት፣ አርቲስት መቅደስ ፀጋዬ ደግሞ ምክትል ፕሬዝደንት ኾነው ተመርጠዋል።

የሰላም ምክር ቤቱን ምስረታ በማስመልከት ወ/ሮ አዳነች አቤቤ በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ላይ “ተመራጮች ለአዲስ አበባችን የሰላም ጉዳይ ይመለከተናል በማለት ከነዋሪው ጋር በመሰለፋችሁ ያለኝን ታላቅ ክብር እና አድናቆት እየገለጽኩ፤ ከፊታችሁ ትልቅ ሥራ የሚጠበቅባችሁ መኾኑን ሳልገልጽ አላልፍም።” ብለዋል።

ለከተማዋ ሁለንተናዊ ብልጽግና የዕለት ተዕለት ሰላም ወሳኝ በመኾኑ ይህ የሰላም ምክር ቤት የተጣለበትን ሕዝባዊ አደራ እና ይዞት የተነሳውን በጎ ዓላማ ከግብ በማድረስ ታሪካዊ ኃላፊነታቸውን በሚገባ እንዲወጡም የአደራ መልእክት አስተላልፈዋል። (ኢዛ)

ቴሌን ሲያከስሩ የነበሩ በቁጥጥር ሥር ዋሉ

ከሰሞኑ ከወንጀል ድርጊቶች ጋር በተያያዘ ሊጠቀስ የሚችለው ዜና በሕገወጥ የቴሌኮም ማጭበርበር ድርጊት የተጠረጠሩ 11 ግለሰቦች ከነመሣሪያቸው በቁጥጥር ሥር መዋላቸውን ያስታወቀው ደግሞ የብሔራዊ መረጃ ደኅንነት አገልግሎት ነው።

እነዚህ ተጠርጣሪዎች ከውጭ አገር ወደ ኢትዮጵያ የሚደረጉ የስልክ ጥሪዎችን በኢትዮ ቴሌኮም ሳተላይት ኔትወርክ በኩል ማለፍ ሲገባቸው፤ ሕገወጥ የቴሌኮም መሣሪያዎች ሕጋዊ ፈቃድ ሳይኖራቸው ወደ አገር ውስጥ በማስገባትና ዓለም አቀፍ ጥሪዎችን በመጥለፍ በራሳቸው መስመሮች ለደንበኞች እያቀረቡ ሕገወጥ ድርጊት ሲፈጽሙ በቁጥጥር ሥር የዋሉ የብሔራዊ መረጃ አገልግሎት አስታውቋል።

ይኸው የድርጅቱ መረጃ እንደሚያመለክተው ግለሰቦቹ ለዚህ ሕገወጥ ተግባር ሲጠቀሙባቸው የነበሩ 11 ኔትዌይ (ሲምቦክስ)፣ 26 ቲፕሊንክ፣ 1 ሺሕ 339 ሲም ካርዶች፣ 20 ፍላሽ ዲስክ፣ 11 ላፕቶፕ እና ሌሎች ሕገወጥ የቴሌኮሙኒኬሽን መሣሪያዎች በቁጥጥር ሥር አውሏል። በዚህ ሕገወጥ ድርጊት ኢትዮ ቴሌኮምን በዓመት እስከ 137 ሚሊዮን ብር እንደሚያሳጣው በመግለጫው ላይ አመልክቷል። (ኢዛ)

የኢትዮጵያ የቱሪዝም ገቢ በእጅጉ ቀንሷል
5.1 ቢሊዮን ብር ታቅዶ የተገኘው 2 ቢሊዮን ብር ነው

በ2012 በጀት ዓመት ኢትዮጵያ ከውጭ ጎብኝዎች ለማግኘት ያቀዳቸውን ያህል ያለማግኘቷ ታወቀ። የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴር ባሳለፍነው ሳምንት በሰጠው መግለጫ በ2012 በጀት ዓመት ከውጭ ጎብኝዎች 5.1 ቢሊዮን ዶላር ገቢ ለማግኘት ቢታቀድም አፈጻጸሙ ከግማሽ በታች ኾኖ የተገኘው ሁለት ቢሊዮን ብር ብቻ ነው ብሏል።

እንደ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ መረጃ በተጠናቀቀው በጀት ዓመት 1.5 ሚሊዮን የውጭ ቱሪስቶችን ለመሳብ ታቅዶ አፈጻጸሙ ግን 541 ሺሕ ብቻ ነው። ገቢው ከእቅድ በታች እንዲህ የወረደበት ዋነኛ ምክንያት የኮሮና ወረርሽኝ ነው። (ኢዛ)

ኢትዮጵያ በአንድ ዓመት በብድር እና በእርዳታ 106.8 ቢሊዮን ብር አግኝታለች

ኢትዮጵያ ከፍተኛ የሚባል ብድርና እርዳታ ስለማግኘቷ ከገንዘብ ሚኒስቴር የወጣው መረጃ ከሰሞኑ ገንዘብ ነክ ከኾኑ ዜናዎች በቀዳሚነት ሊቀመጥ የሚችል ነው። እንደ ገንዘብ ሚኒስቴር መረጃ ኢትዮጵያ በ2012 በጀት ዓመት በብድር እና በእርዳታ 106.87 ቢሊዮን ብር ማግኘቷን አመልክቷል።

ከዚህ ውስጥ 37.38 ቢሊዮን ብሩ ከተለያዩ የፋይናንስ ተቋማት እና ለጋሽ አገራት በብድር የተገኘ መኾኑን የጠቀሰው መረጃ፤ 69.495 ቢሊዮን ብሩ ደግሞ አዲስ ብድር እና እርዳታ ነው ተብሏል።

ይህም በበጀት ዓመቱ ለማግኘት ከታቀደው 81.3 በመቶ አፈጻጸም ማሳየቱን የሚያመለክት ነው። ከዚሁ ጋር ተያይዞ በበጀት ዓመቱ ለፕሮጀክቶችና ፕሮግራሞች ማስፈጸሚያ ከውጭ የገንዘብ ምንጮች 142.3 ቢሊዮን ብር መገኘቱንም የሚኒስቴሩ መረጃ አመልክቷል። (ኢዛ)

አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን ድጋፍ በከፊል እንደምትቀንስ ተገለጸ

ከታላቁ ህዳሴ ግድብ ጋር ተያይዞ ኢትዮጵያ እየወሰደች ያለውን አቋም ተከትሎ፤ አሜሪካ ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን የገንዘብ ድጋፍ በተወሰነ ደረጃ ለማቋረጥ ስለመወሰኗ የተሰማበት ሳምንት ነው።

የአሜሪካ የውጭ ጉዳይ መሥሪያ ቤትን መረጃ ጠቅሶ ፎሪን ፖሊሲ የተባለው የመረጃ ምንጭ እንዳስታወቀው፤ የአሜሪካ መንግሥት ለኢትዮጵያ የምትሰጠውን እርዳታ በከፊል ለመቀነስ አስተላለፈች በተባለው ውሳኔ፤ ኢትዮጵያ ልታጣ የምትችለው 130 ሚሊዮን ዶላር አካባቢ ነው።

ይህ የአሜሪካ መንግሥት ውሳኔ እንደሚተላለፍ መነገር የጀመረው ከአንድ ወር በፊት ሲሆን፤ በተለይ ኢትዮጵያ የግድብን የውኃ ሙሌት ማካሔድ ለዚህ ውሳኔ መፋጠን ምክንያት ነው እየተባለ ነው።

አሜሪካ እንዲህ ያለውን እርምጃ በመውሰድ ኢትዮጵያ ላይ ጫና ለመፍጠር እየሞከረች ነው ተብሏል። እስካሁን በዚህ መረጃ ላይ የኢትዮጵያ መንግሥት አቋሙን ያላሳወቀ ቢኾንም፤ ጉዳዩ የብዙዎች መነጋገሪያ ኾኖ ሰንብቷል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!