Ethiopia Zare's weekly news digest, week 2nd, 2013 Ethiopian calendar

ከመስከረም 11 - 17 ቀን 2013 ዓ.ም. ሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

የዓመቱ ሁለተኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች

ኢዛ (ከመስከረም 11 - 17 ቀን 2013 ዓ.ም.) ባሳለፍነው ሳምንት የተለያዩ ፖለቲካዊ፣ ማኅበራዊና ኢኮኖሚያዊ ክንውኖች ውስጥ የመከላከያ ሚኒስትሩ ምክትል ኤታማዦር ሹምና የፌደራል ፖሊስ ኮምሽነር ከወቅታዊ የአገሪቷ ሁኔታ አንጻር የሰጡት ተመሳሳይ ማስጠንቀቂያ ይጠቀሳል። ሁለቱም የአገሪቱ ከፍተኛ አመራሮችም የሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ውጭ የሚደረግ እንቅስቃሴን አንታገስም ብለዋል።

ከሳምንቱ አነጋጋሪ ዜናዎች ውስጥ ከጸጥታ ችግር ጋር ተያይዞ ወደ አዲስ አበባ የሚገቡ መንገዶች መግቢያ ላይ ጥብቅ ቁጥጥር እየደረገ መኾኑን የሚመለከተው ነው። ቁጥጥሩ ተሽከርካሪዎች በመጡበት እንዲመለሱ ያደረገ ነበር።

የብር ኖት ለውጡን ተከትሎ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሕገወጥ መንገድ የሚዘዋወር ገንዘብ ስለመያዙ እየተሰማ ሲሆን፤ ሐሰተኛ ገንዘቦችን ለመቀየር ሙከራዎች ስለመደረጋቸው የተሰማበት ሳምንት ነው። 180 ሺሕ ብር ሐሰተኛ ገንዘብ ወደ ባንክ ለማስገባት የተደረገ ሙከራም ከሽፏል። የጦር መሣሪያን ጨምሮ ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች የተያዙትም በሳምንቱ አጋማሽ ነው።

በፌዴራል መንግሥት ሕገወጥ በተባለው ምርጫ ወንበር የያዙት ሕወሓቶች፤ የትግራይ ክልል ምክር ቤት ስብሰባን አካሒደው ዶ/ር ደብረጽዮንን የክልሉ ፕሬዝዳንት አድርጌያለሁ ብለዋል።

የሚኒስትሮች ምክር ቤት የ1954ቱ የወንጀለኛ መቅጫ ሕግና ሌሎች ሕግጋትን ለማሻሻል ውሳኔ አሳልፏል። የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ እንዳይካሔድ ውሳኔ ሲያሳልፍ፤ ይህ ምርጫ በትግራይም ይካሔዳል ብሏል። ምርጫ ቦርድ የምርጫ ዝግጅቴን ጀምሬያለሁ ማለቱም ተገልጿል።

ቢዝነስ ነክ ከኾኑ ዜናዎች፤ አቢሲኒያ ባንክ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የኾነውን የቨርቹዋል ባንክ አገልግሎት መጀመሩ ይጠቀሳል። የአዲስ አበባ አስተዳደር ካቢኔ ለጤና ባለሙያዎች የገቢ ግብር ወጪን ለመሸፈን ውሳኔ አሳልፏል።

እንዲህ ካሉት ከሳምንቱ ክንውኖች ውስጥ የተመረጡትንና ሌሎች ሳምንታዊ ክንውኖችን የያዘው የሳምንቱ ጥንቅር በኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ተጠናክሮ እንደሚከተለው ይቀርባል። መልካም ንባብ!

ቀጣዩ ምርጫ በትግራይም ይካሔዳል

የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባሳለፍነው ሳምንት ባካሔደው ስብሰባው ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ እንዲካሔድ ውሳኔ ሲያሳልፍ፤ ይህንን ውሳኔ ተከትሎ አፈ ጉባዔ ታገሰ ጣፎ በሰጡት መግለጫ፤ ምርጫው በሁሉም ክልሎች የሚካሔድ ሲሆን፤ ይህም የትግራይ ክልልን የሚጨምር (የሚያካትት) እንደኾነ አመልክተዋል።

የትግራይ ክልል የራሴን ምርጫ አድርጌያለሁ ቢልም፤ ይህ ምርጫ ሕገወጥ ስለመኾኑ በፌዴሬሽን ምክር ቤት ጭምር የተወሰነ በመኾኑ ስድስተኛው አገራዊ ምርጫ በትግራይም ይካሔዳል። (ኢዛ)

የመከላከያና የፖሊስ ማስጠንቀቂያ

ባሳለፍነው ሳምንት የመከላከያ ሚኒስቴር ምክትል ኤታማዦር ሹምና የፌዴራል ፖሊስ ኮምሽነር ከሕገ መንግሥታዊ ሥርዓቱ ውጭ የሚንቀሳቀሱ ማናቸውም አካላት ላይ እርምጃ እንደሚወስዱ አስጠንቅቀዋል።

በተለይ ከመስከረም 25 በኋላ መንግሥት የለም በሚል ችግር ለመፍጠር የሚንቀሳቀሱ አካላት ስለመኖራቸው በመጠቆም፤ እነዚህ አካላትን መታገስ እንደማይችሉና እርምጃ ለመውሰድ የሚገደዱ ስለመኾኑ አስጠንቅቀዋል።

ከመስቀልና ከኢሬቻ በዓል ጋር ተያይዞ በዓሉን ለማወክ የሚንቀሳቀሱ ኃይሎች እንዳሉ ደርሼበታለሁ ያለው የፌዴራል ፖሊስ፤ የአዲስ አበባ መግቢያዎች ላይ ጥብቅ ፍተሻ እያደረገ መኾኑን፤ እንዲሁም ለዚሁ ሽብር ጥቃት ተሳታፊ ለመኾን ተዘጋጅተው ነበር ያላቸውንም ስለመያዙ ጠቁመዋል።

በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ ከአማራ ክልል ወደ አዲስ አበባ ይገቡ የነበሩ የሕዝብ ተሽከርካሪዎች እንዲመለሱ የተደረገበት ምክንያት ይኸው ከሽብር ጋር በተያያዘ በደረሰ መረጃ ሲሆን፣ ቁጥጥሩ ግን በአንድ መስመር ብቻ ያለመኾኑንና በሁሉም ወደ ከተማዋ በሚገቡ ተሽከርካሪዎች ላይ የተወሰደ ነው የሚል አንደምታ ያለው መረጃም ሰጥተዋል።

ምክትል ኤታማዦር ሹሙ ትኩረት የሰጡት፤ ከመስከረም 25 በኋላ መንግሥት የለም ብለው በሚያራግቡ አካላት ላይ እርምጃ የሚወስድ ስለመኾኑና ጥያቄ ያላቸው የፖለቲካ ፓርቲዎች የሽግግር እና ባለአደራ መንግሥት እያሉ የሚናገሩትን ያቁሙ በማለት አስጠንቅቀዋል።

ለፖለቲካ ጉዳዮች መፍትሔው ምርጫ መኾኑን በመግለጽም፤ ከዚህ ውጭ መንቀሳቀስ እንደማይቻልም በመጥቀስ መከላከያ ሠራዊቱን አትፈታተኑ በሚል አሳስበዋል። (ኢዛ)

የትግራይ ክልል ምክር ቤትና ዶክተር ደብረጽዮን ሹመት

በፌዴሬሽን ምክር ቤት እና በፌዴራል ደረጃ ሕገወጥ የተባለውን ምርጫ ያካሔደው የትግራይ ክልል ምክር ቤት፤ ባካሔደው ስብሰባ ላለፉት ሁለት ዓመት ተኩል የክልሉ ምክትል ፕሬዝዳንት በመባል ክልሉን በበላይነት ሲመሩ የቆዩትን ዶ/ር ደብረጽዮን ገብረሚካኤልን የክልሉ ፕሬዝዳንት አድርጐ መሰየሙን አስታውቋል።

አዲስ አፈ ጉባዔም የሰየመ ሲሆን፣ የክልሉ መንግሥት ያካሔድኩት ሹመት ለአምስት ዓመት የሚቆይ ነው ቢልም፤ የፌዴራል መንግሥቱ በተቃራኒው ተቀባይነት በሌለው ምርጫ የተደረገ ስለኾነ እንደተደረገ እንደማይቆጠር ማስታወቁ አይዘነጋም። (ኢዛ)

ሐሰተኛ ገንዘቦች እየተያዙ ነው

ከመስከረም 4 ቀን 2013 ዓ.ም. ኢትዮጵያ የብር ኖቷን እንዳምትቀይር ከተገለጸበት ጊዜ ጀምሮ የአገሪቱ ባንኮች ከስድስት ሺሕ በላይ በሚኾኑ ቅርንጫፎቻቸው የብር ለውጥ በማካሔድ ላይ ናቸው። አንዳንድ መረጃዎች እንደሚያመለክቱት አዲሱ የብር ኖት ከጥቂት አካባቢዎች በሙሉ በሁሉም የአገሪቱ ክፍል ተሰራጭቷል።

ከዚህ የብር ለውጥ ጋር ተያይዞ የመጣ ነው የተባለ ችግር ባይኖርም፤ በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች በሕገወጥ መንገድ የተሳሳቱና ሲዘዋወሩ የነበሩ ብሮች ተይዘዋል።

ከዚህ ሌላ ባንኮች አልፎ አልፎ ሐሰተኛ የብር ኖቶች ቢያጋጥሟቸውም፤ ባለፈው ሳምንት ግን ከ180 ሺሕ ብር በላይ ሐሰተኛ ወደ ባንክ ቀርቦ ሊመነዘር ሲል መያዙ ከብር ምንዛሪ ለውጡ ጋር ወደ ባንክ የቀረበ ከፍተኛ የሐሰተኛ ገንዘብ ኾኖ ታይቷል።

180 ሺሕ ሐሰተኛ ገንዘብ ወደ ባንክ ሲያስገቡ የተያዙት ሁለቱ ግለሰቦች በቡና ኢንተርናሽናል ባንክ መቐለ ሞሚና ቅርንጫፍ በታተመ እና እናት ባንክ አዲሃቂ ቅርንጫፍ በታተመ ማሸጊያ የተጠቀለለ ከ180 ሺሕ ብር በላይ ሐሰተኛ ገንዘብ እንደነበር ፖሊስ አስውቋል። ይህ ገንዘብ ወደ ንብ ኢንተርናሽናል ባንክ ወስደው ሊቀይሩ ሲሉ ነው በቁጥጥር ሥር የዋሉት ግለሰቦቹ፤ የያዙትን ሐሰተኛ ብር ንብ ባንክ ካዛንቺስ ቅርንጫፍ ካሉ ሠራተኞች ጋር 40 በመቶ ለባንክ 60 ከመቶ ለራሳቸው ለማዋል ስምምነት አድርገው የፈጸሙት መኾኑም ተጠቅሶ፤ ግለሰቦቹ ከመኪናቸው አውጥተው ብሩን ሊመነዝሩ ሲሉ በባንኩ ጥቆማ በተደረገ በክትትል በቁጥጥር ሥር መዋላቸውም ታውቋል።

ከዚሁ ድርጊት ጋር የተሰጠው ተጨማሪ መረጃ፤ ሁለቱ ግለሰቦች በቱሉ ዲምቱ በሚገኘው መኖሪያ ቤታቸው በተደረገ ፍተሻ ተመሳሳይ መጠን ያለው ሐሰተኛ ብር መያዙን ማስታወቁ ነው። (ኢዛ)

አኀዳዊ ነው የተባለው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ እንዲሻሻል ተወሰነ

በአሁኑ ወቅት በሥራ ላይ ያለው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት በ1954 ዓ.ም. የታወጀና አኀዳዊ የመንግሥት አወቃቀርና አስተዳደር ሥርዓትን የተከተለ በመኾኑ እንዲሻሻል የሚኒስትሮች ምክር ቤት ባሳለፍነው ሳምንት መጨረሻ ላይ ውሳኔ አሳልፏል።

ምክር ቤቱ ማሻሻያው ያስፈለገበት ብሎ ከገለጻቸው ማብራሪያዎች ውስጥ አገሪቱ ከምትተገብረው የፌደራል ሥርዓትና በክልልና በፌዴራል መንግሥታት መካከል ያለውን ሕገ መንግሥታዊ የሥልጣን ክፍፍል ያላገናዘበ በመኾኑ የሚለው ተጠቅሷል።

ከዚህም ሌላ በአገሪቱ በርካታ የሰብአዊ መብት ስምምነቶችን በተይም የሲቪልና የፖለቲካል መብቶች፣ የሕፃናት መብቶች፣ የሴቶች መብቶች እና ሌሎች መብቶችን የተመለከቱ ዓለም አቀፍና የሕጉራዊ ስምምነቶችን ተቀብላ፤ የአገሪቱ ሕግ አካል ያላደረገቻቸው በመኾኑ፤ እነዚህን ለውጦች ያገናዘበ እና በሥራ ላይ ካሉ ሕጎች ጋር የሚጣጣም ለውጥ ማድረግ ተገቢ በመኾኑም ነው ተብሏል። ከዚህም ሌላ በሌላ በኩል በሥራ ላይ ያለው የወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕግ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ግልጽነት የጎደለው ከመኾኑ ጋር ተያይዞ ማሻሻል የሚኖርበት እርምጃው ስለመወሰዱ ያመላክታል።

በዚህ ዙሪያም ለምክር ቤቱ የቀረበው ማብሪሪያ እንዳከለው፤ አሁን ላይ ከሚፈጸሙ ውስብስብና የረቀቁ ወንጀሎች አንጻር፤ እንዲሁም ዘመኑ ከደረሰበት የወንጀል ሳይንስ ጋር አብረው የማይሔዱ በርካታ ድንጋጌዎች የተካተቱበትና መሠረታዊ ክፍተት ያለበት በመኾኑ ማሻሻሉ አስፈላጊ ስለመኾኑ ያመላክታል።

የዚህ ማሻሻያ ሌላም ሊጠቀስ የሚችል ምክንያት እንዳለው የሚጠቁመው መረጃ፤ እንደዚሁም “ሕብረተሰባችን የወንጀል ጉዳዮችን የሚፈታበት የዳበሩ ባሕላዊ ሥርዓቶች ያዙለት ቢኾንም፤ በወንጀለኛ መቅጫ ሥነ ሥርዓት ሕጉ ውስጥ በአግባቡ አልተካተቱም” የሚል ነው። በመኾኑም በ1954 ዓ.ም. የወጣው እና በሥራ ላይ ያለው የወንጀለኛ መቅጫ ሕግ ሥነ ሥርዓት በዘመናዊም ኾነ በባሕላዊ አግባብ የሚታዩ እድገቶችን እና ተግባሮችን አሟልቶ ያልያዘ ኾኖ ስለተገኘ፤ የወንጀል ሕግ ሥነ ሥርዓት እና የማስረጃ ሕግ ማውጣት በማስፈለጉ ለዚህ ማሻሻያ ረቂቅ የቀረበው ረቂቅ አዋጅ ማሻሻያዎች በማድረግ የሚኒስትሮች ምክር ቤት ረቂቁ ይጸድቅ ዘንድ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አስተላልፎታል። (ኢዛ)

አቢሲኒያ ባንክ የመጀመሪያ የቨርችዋል የባንክ ማዕከል ሥራ አስጀመረ
በአንድ ማሸን ከ15 በላይ አገልግሎት ይሰጣል

ከሳምንቱ ዐበይት የቢዝነስ ዜናዎች ውስጥ አቢሲኒያ ባንክ በኢትዮጵያ የመጀመሪያ የኾነውን የቨርችዋል ባንከ ማዕከል በማስመረቅ አገልግሎት መጀመሩ ነው። ይህ አገልግሎት በአንድ ኤቲኤም መሰል ማሽን ከ15 በላይ አገልግሎት የሚሰጥ ነው።

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ ዶ/ር ይናገር ደሴ በተገኙበት የተመረቀው ይህ ማሽን፤ አንድ ደንበኛ በአንድ ቅርንጫፍ በመሔድ ያገኝ የነበረውን አገልግሎት ወደዚህ ማሽን በመቅረብ 24 ሰዓት አገልግሎት እንዲያገኝ ያስችለዋል።

ማሽኑ ከሚያከናውናቸው ከ15 በላይ አገልግሎቶች ውስጥ ቼክ መመንዘር፣ ገንዘብ በሐዋላ ማስገባት፣ ገንዘብ ማስገባት የውጭ ገንዘቦችን መመንዘር፣ ገንዘብ ወጪ ማድረግ ጥቂቶቹ ናቸው።

ቨርችዋል የባንክ ማዕከል ደንበኞች በቪዲዮ ኮንፈረንስ አማካኝነት በርቀት ባሉ የደንበኞች አማካሪዎች በመታገዝ የባንክ አገልግሎት የሚያገኙበትም መኾኑ ተገልጿል። ይህንን መሰሉን አገልግሎት ባንኩ በአዲስ አበባ ባሳለፍነው ሳምንት አራት ማሽኖችን ሲያስመርቅ፤ በቀጣዩ ወሮች ተጨማሪ 15 ማሽኖችን ያክላል። (ኢዛ)

የመዲናዋ አስተዳደር ካቢኔ በጤና ተቋማት ለሚሠሩ ሠራተኞች የገቢ ግብር ወጪን ለመሸፈን ውሳኔ አሳለፈ

የአዲስ አበባ ከተማ አተዳደር ካቢኔ በጤና ተቋማት ለሚሠሩ ሠራተኞች የገቢ ግብር ወጪን ለመሸፈንና በ669 ሚሊዮን ብር በፊንፊኔ ልዩ ዞን ለሚገኙ ተማሪዎች የተለያዩ አገልግሎቶችን ለማቅረብ ውሳኔ አሳለፈ።

በዚህም የወቅቱ ዓለም አቀፍ ሥጋት የኾነው የኮሮና ቫይረስ ወረርሽኝ በአገራቱ እና በከተማዋ ከተከሰተበት ከመጋቢት ወር 2012 ዓ.ም. ጀምሮ የሕክምና አገልግሎት በመስጠት፤ እንዲሁም በማስተባበር የተሰማሩ በከተማው አስተዳደር ሥር በሚገኙ የጤና ተቋማት ሁሉ የሚገኙ የጤና ባለሙያዎች እና ድጋፍ ሰጪ ሠራተኞችን ለመደገፍ ነው። እንደ ካቢኔው ውሳኔ ይህ ወረርሽኝ በኢትዮጵያ ሥጋት መኾኑ እስከሚያበቃበት ጊዜ ድረስ የከተማ አስተዳደሩ የገቢ ግብር ወጪያቸውን ለእነዚህ የጤና ባለሙያ ሠራተኞች የሚሸፍን እንደኾነ አስታውቋል። ይህ ውሳኔው አስተዳደሩን ምን ያህል ወጪ እንደሚያስወጣው ባይገለጽም፤ ትልቅ እርምጃ ተደርጐ ተወስዷል። ከአንድ ሳምንት በፊት በወጣ መረጃ በኢትዮጵያ ከ1300 በላይ የሕክምና ባለሙያዎች በኮሮና ቫይረስ ስለመያዛቸው መገለጹ አይዘነጋም።

ከዚሁ ዜና ጋር በተያያዘ የከተማው ካቢኔ አዲስ አበባ በዙሪያዋ ባሉ በፊንፊኔ ልዩ ዞን በሚገኙ 346 ትምህርት ቤቶች ውስጥ ለሚማሩ 152 ሺሕ ተማሪዎች ድጋፍ እንዲደረግ መወሰኑን አስታውቋል።

በዚህም 669.2 ሚሊዮን ብር የትምህርት ቁሳቁስ፣ የተማሪ ደንብ ልብስ፣ ጫማ እና የትምህርት ቤት ምገባ አገልግሎት እንዲቀርብ ለማድረግ በልዩ ሁኔታ ውሳኔው ስለመተላለፉ የከተማዋ ፕሬስ ሴክሬታሪያት አስታውቋል። (ኢዛ)

ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ ኮንትሮባንድ ተያዘ

በሳለፍነው ሳምንት በተለያዩ የአገሪቱ ክፍል የጦር መሣሪያን ጨምሮ ከ18 ሚሊዮን ብር በላይ ግምት ያላቸው የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ተይዘዋል። እንደ ገቢዎች ሚኒስቴር መረጃ እነዚህ የኮንትሮባንድ ዕቃዎች ደረቅ ጫት፣ እህል፣ ትምባሆ እና ሌሎች ዕቃዎች ናቸው።

ዕቃዎቹ የተያዙትም በተለያዩ የጉምሩክ መቆጣጠሪያ እና መቅረጫ ጣቢያዎች ነው። ከዚህ ውስጥ 13.7 ሚሊዮን ብር ግምታዊ ዋጋ ያለው ደረቅ ጫት ከአገር ሊወጣ ሲል ያቤሎ የመቆጣጠሪያ ጣቢያ ተይዟል። 8,980 ኪሎ ግራም መጠን እንዳለው የተገለጸው ደረቅ ጫት፤ በሕገወጥ መንገድ ወደ ኬንያ ሲጓጓዝ እንደተያዘ ነው።

ሌላው የተያዘው የኮንትሮባንድ ዕቃ ግምታቸው 3.5 ሚሊዮን ብር የኾነ የውጭ ማሽላና ዘይት ነው። ሌላው የተያዘው የኮንትሮባንድ ዕቃ በደቡብ ክልል ሲሆን፤ ይህም በኢትዮጵያ ለሚገኙ ለደቡብ ሱዳን ስደተኞች በእርዳታ የገባ ጠቅላላ ግምታዊ ዋጋው 1.14 ሚሊዮን ብር የኾነ ማሽላ፣ ስንዴ እና አተር ክክ ነው። ይህ የእርዳታ እህል ከጋምቤላ ክልል ወደ አዲስ አበባ በሕገወጥ መንገድ በመጓጓዝ ላይ እያለ፤ በጅማ ጉምሩክ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ተይዟል። ቆቦ ላይ ደግሞ ሦስት ሽጉጦች በሴራሚክ ውስጥ ደብቆ ለማሳለፍ ሲሞከር ተይዟል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!