Ethiopia Zare's weekly news digest, week 4th, 2013 Ethiopian calendar

ከመስከረም 25 - ጥቅምት 1 ቀን 2013 ዓ.ም. ሳምንቱን አንኳር ወሬዎች በጨረፍታ

 

የዓመቱ አራተኛ ሳምንት አንኳር ማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ክንውኖች

ኢዛ (ከመስከረም 25 - ጥቅምት 1 ቀን 2013 ዓ.ም.) ከመስከረም 25 እና 30 ቀን 2013 ዓ.ም. በኋላ መንግሥት የለም በሚል ላለፉት ሦስትና አራት ወራት ሲነገር የነበረ ሲሆን፤ እነዚህ ቀናት ያለፉት ደግሞ በዚህ ባሳለፍነው ሳምንት ነው። ሁለቱ ቀናት አልፈው ተከታዮቹ ቀናት ቀጥለዋል።

መንግሥት አይኖርም በተባለበት በዚህ ባሳለፍነው ሳምንት፤ መንግሥት ቀጣይነቱን ያሳየበት፤ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤትና የፌዴሬሽን ምክር ቤት በጋራ ስብሰባ ሥራ መጀመራቸውን የገለጹበት ኾኗል።

ባሳለፍነው ሳምንት ከዚህ ዐበይት ጉዳይ ባሻገር የተለያዩ ክንውኖች የተካሔዱበት ነው።

ከሳምንቱ ዐበይት ዜናዎች ውስጥ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በትግራይ ክልል ላይ ያሳለፈው ውሳኔ ተጠቃሽ ነው። በዚሁ ጉዳይ የትግራይ ክልል ምክር ቤት የሰጠውም ምላሽ የሳምንቱ አነጋጋሪ ዜና ሲሆን፤ የአገሪቱን የፖለቲካ ትኩሳትም ከፍ ያደረገ ነው። ባሳለፍነው ሳምንት ሌላው አነጋጋሪ ዜና የነበረው የፌዴሬሽን ምክር ቤት በደቡብ ክልል የሚገኙ አምስት ዞኖችና አንድ ልዩ ወረዳ በጥምረት ያቀረቡትን የክልልነት ጥያቄ ሕዝበ ውሳኔ እንዲሰጥበት መወሰኑ ነው። የኦነግ አመራሮች ውዝግብ ሌላው ከሳምንቱ ዜና ውስጥ የሚጠቀስ ሲሆን፤ በዚህ ጉዳይ ምርጫ ቦርድ የመጨረሻ ውሳኔ እሰጣለሁም ብሏል።

ከኦነግ ሊቀመንበርነታቸው ተነስተዋል የተባሉት አቶ ዳውድ ኢብሳ በኦሮሚያ የሽግግር መንግሥት ይመሥረት በማለት ያሠራጩት መግለጫ በአስደማሚነቱ የሚጠቀስ ኾኗል። የአዲስ አበባን ሕገወጥ የመሬት ወረራና ያልተገባ የኮንዶሚኒየም ዕደላን የሙጥኝ የያዘው ኢዜማ፤ ጉዳዩ አሁንም አሳሳቢ ነው ብሏል። እንዲያውም በዚህ ጉዳይ እንዳልነጋገርበት ሕገ መንግሥታዊ መብቴ ተነክቷል በሚል ክስ መመሥረቱን ያስታወቀው በዚህ ሳምንት ነው። በፌዴራል ደረጃ ያሉ እና በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ያሉ አባሎቹን ሥራችሁን ለቃችሁ ሪፖርት አድርጉ ያለው በዚህ ሳምንት ሲሆን፤ ሁለት የፓርቲው እንስት አመራሮች አስተያየት ሰጥተውበታል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት አፈ ጉባዔ በትግራይ ክልል ምክር ቤት ላይ ያሳለፈው ውሳኔ እንደተጠበቀ ቢኾንም፤ ለመነጋገር አሁንም በሩ ዝግ ያለመኾኑን አመልክተዋል።

ብልጽግና በተለያዩ የአገሪቱ ክፍሎች ያሉ የትግራይ ተወላጆችን አነጋግሯል። በሳምንቱ ለየት ብሎ ሊጠቀስ የሚችለው ክንውን በተያዘለት የጊዜ ገደብ ሥራው ተጠናቅቆ የተመረቀው የእንጦጦ ፓርክ ነው። የአገሪቱ ዋነኛ ከሚባሉ የቱሪስት መዳረሻ አንዱ ይኾናል የተባለው እንጦጦ ፓርክ በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ አሕመድ ተመርቆ ሥራ ጀምሯል። እንደ አገር ተፈታታኝ ኾኖ የመጣው ሰሞናዊ ጉዳይ የአንበጣ መንጋ ከመቼውም ጊዜ በላይ በከፋ ሁኔታ በተለያዩ ክልሎች የደረሱ ሰብሎችን ዶግ አመድ እያደረገ መኾኑ ነው። ከአሳሳቢነቱ አንጻር መንግሥት ትኩረት ይሰጠው ዘንድ ጥሪ እየተላለፈ ነው።

ከቢዝነስና ኢኮኖሚ ክንውኖች አንጻር የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ግለሰቦች ከባንክ በቀን ማውጣት የሚገባቸውን ጥሬ ገንዘብ መጠን በከፍተኛ ሁኔታ እንዲቀንስ መመሪያ ማውጣቱ ነው። በባሕር ዳር ሦስተኛው የኢንዱስትሪ ፓርክም የተመረቀው ባሳለፍነው ሳምንት መጀመሪያ ላይ ነው።

በይበልጥ በፌዴራል መንግሥትና በትግራይ ክልል ምክር ቤት መካከል የተፈጠረውን አለመግባባት ላይ ያተኮረው የኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ የሳምንቱ ጥንክራችን እንደሚከተለው ቀርቧል። መልካም ንባብ!

መስከረም 25 እና 30 አለፉ፤ አገርም መንግሥትም አሉ

ከወራት በፊት ሲቀነቀን የነበረው ከመስከረም 25 ወይም 30 2013 በኋላ መንግሥት የለም በማለት የተፈጠረው ውዥንብር ብዙ ሲነገርለት ነበር።

እነዚህ በቁጥር የተጠቀሱት ቀናት ደግሞ ያለፉት በዚህ ባሳለፍነው ሳምንት ነው። እነዚህ ቀናት ከመድረሳቸው በፊት በኢትዮጵያ ከመስከረም 25 በኋላ ሕጋዊ መንግሥት የለም። በዶክተር ዐቢይ የሚመራው መንግሥት ያበቃለታል የሚልና ኢትዮጵያም የምትፈርስበት ወቅት ነው በሚል ሟርት ሁሉ ሲነገር ነበር።

ይህንን በማቀንቀን ረገድ ሕወሓትን የተስተካከለው ባይኖርም፤ ጽንፈኛ የኦሮሞ ቡድኖች ይህንኑ ሲያስተጋቡ ቆይተዋል። አሁን ላይ እስር ላይ የሚገኙት ጃዋር መሐመድና አቶ ልደቱ አያሌውም ከመስከረም 25 በኋላ ሁላችንም እኩል ነን፤ አሁን ያለው መንግሥት ያበቃለታል፣ ፖሊስና መከላከያም ለመንግሥት አይታዘዝም በማለት መስከረም 25 ቀንና መስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም.ን ሰዎች በሥጋት እንዲያስቡት ቢያደርጉም፤ በመንግሥት ደረጃ ከመስከረም 25 በኋላ ምንም የሚለወጥ ነገር የለም፤ መንግሥት ይቀጥላል በማለት ሕዝብ እንዳይረበሽ የሚለወጥ ነገር የለም ብለው ሲገልጹ ቆይተዋል። ከፍተኛ የጸጥታ ኃይሎችም ከመስከረም 25 በኋላ መንግሥት የለም የሚሉ ወገኖች ወዮላችሁ ብለው በማስጠንቀቅ ቆምጠጭ ያለ አቋማቸውን አሳውቀዋል።

መስከረም 25 እና 30 ሲደርስ ግን የኾነው ነገር በእርግጥም እንደ ብዙዎቹ ኢትየጵያውያንና መንግሥት እምነት ሁለቱ ቀናት እንደ ማንኛውም ቀናት አልፈዋል። እንዲያውም መስከረም 25 ቀን የሁለቱ ምክር ቤቶች የጋራ ስብሰባ አካሒደው ሥራቸውን በይፋ የሚጀምሩበት ኾነ። መስከረም 30 ቀን 2013 ደግሞ በኢትዮጵያ ቀዳሚ የቱሪስት መዳረሻ ይኾናል የተባለውና በጠቅላይ ሚኒስትትር ዐቢይ አሕመድ ሐሳብና አመራር ተገንብቶ የተጠናቀቀው እንጦጦ ፓርክ ተመረቀ። በማግስቱም ጥቅምት 1 ቀን 2013 ቀጠለ። አገርም መንሥትም ቀጠሉ። (ኢዛ)

በሕወሓትና በፌዴራል መንግሥቱ መኻል ያለው እሰጥ አገባ

የሰሞኑ ዋነኛ አጀንዳና የብዙዎች መነጋገሪያ የኾነው ጉዳይ፤ በፌዴራል መንግሥትና በትግራይ ክልል መካከል ያለው እሰጥ አገባ ወቅታዊ የፖለቲካ ትኩሳት ኾኗል።

ሕገወጥ ምርጫ ባካሔደው የትግራይ ክልላዊ መንግሥት ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት በተለይ የድጐማ በጀት እንዲቆም፤ ከክልሉ ካቢኔ ጋር የፌዴራል መንግሥት አካላት ምንም ዐይነት ግንኙነት እንዳያደርግ የወሰነው በዚህ ባሳለፍነው ሳምንት ነው።

ይህ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ውሳኔ የክልሉ ሕዝብ እንዳይጐዳ የፌዴራል መንግሥት ከወረዳ ቀበሌና ከተማ አስተዳደሮች ጋር ግንኙነት በማድረግ የሚሠራ ስለመኾኑ የሚጠቁም ነው።

የሕወሓት አመራሮች ኢ-ሕገ መንግሥታዊ በኾነ መንገድ ያካሔዱትን ምርጫ ማቆም ባለመቻላቸው፤ በፌዴራል መንግሥት የተወሰደው እርምጃ አግባብነት ያለው ነው ቢባልም፤ አንዳንድ ወገኖች ግን የፌዴራል መንግሥት ከትግራይ ክልል የወረዳ ቀበሌና ከተማ አስተዳደሮች ጋር እንዴት ሊገናኝ ይችላል የሚለው ጉዳይ የሚያሳስባቸው ስለመኾኑ እየገለጹ ነው። ለዚህም ቀበሌ ድረስ ያለው በሕወሓት አባላት የተያዘ ኾኖ ሳለ፤ ያሰበውን ለማስፈጸም አይችልም ብለው እየሞገቱ ናቸው።

የፌዴራል መንግሥት የያዘውን አቋም ተከትሎ ከሕወሓት አመራሮች እየተሰጠ ያለው ምላሽም ነገሮችን እያከረረ ስለመምጣቱ እያሳየ ነው። ከሰሞኑ ከዚሁ ጉዳይ ጋር የተናገሩት አቶ ጌታቸው ረዳ፤ ጦርነት እንደታወጀብን የሚታይ ነው ብለው የፌዴራል መንግሥቱን ውሳኔ ገልጸውታል።

የትግራይ ክልል ርዕሰ መስተዳድር አቶ አብረሃም ተከስተም፤ መንግሥት የበጀት ድጐማውን ካቆመ እኛም የምንሰበስበውን ግብር ገቢ አናደርግም በማለት እስከመናገር የደረሱት በዚሁ ሳምንት ነው።

እንዲህ ባለው መንገድ እየሔደ ያለው መካረር መጨረሻው ምን ሊኾን እንደሚችል ማወቅ ባይቻልም፤ ሁለቱም ወገኖች አንዱ ሌላውን እውቅና አልሰጥም በሚል የቃላት ጦርነቱ እንደቀጠሉ ነው።

አንዳንድ የፖለቲካ ተንታኞች ደግሞ፤ ሕወሓት ሕገወጥ ተግባራቱንና ኢ-ሕገ መንግሥታዊ ሥራዎችን እየተመለከቱ ለእርምጃ ጊዜ መውሰዱ ያመጣው ችግር ስለመኾኑ ይጠቅሳሉ። እንዲያውም የትግራይ ክልል ሕገ መንግሥት ጥሶ ምርጫ ሲያካሒድ በፍርድ ቤት ማሳደግ የሚቻልበት እድል እንደነበር ያላቸውን አተያይ ያመለክታሉ።

አሁን ላይ እንደ ዋና ጉዳይ እየታየ ያለው ግን የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ ውሳኔ እንዴት ይፈጸማል የሚለው ሲሆን፤ ውሳኔውን ለማስፈጸም የሚፈጠሩ ችግሮች ሊያሳስብ እንደሚገባ የሚጠቅሱ አስተያየቶች በሳምንቱ ውስጥ ሲንሸራሸሩ ነበር። (ኢዛ)

ኢዜማ የመናገርና የመሰብሰብ መብቴ ተነክቷል በሚል ክስ መሥርቷል
- የመሬት ወረራው እርምጃ እየተወሰደበት አይደለም ብሏል

ከሳምንቱ አነጋጋሪ ዜናዎች መካከል ኢዜማ በቅርቡ በአዲስ አበባ ከተማ የመሬት ወረራና አግባብ ካልኾነ የኮንዶሚኒየም እደላ ጋር ተያይዞ ሕገወጥ ተግባሩን በፈጸሙት ላይ ሕጋዊ እርምጃ አለመወሰዱን ማስታውቁ ነው።

ይህ ብቻ ሳይኾን በእነዚህ ሕገወጥ ተግባራት ላይ ከአዲስ አበባ አስተዳደር ጋር ለመነጋገር ቃል ከተገባ በኋላ፤ የተያዙ ፕሮግራሞች ስለመሰረዛቸው ያመለከተው ኢዜማ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ በጽሕፈት ቤቱ ለማካሔድ ያቀደው ውይይት እንዳይካሔድ በከተማ አስተዳደሩ መታገዱን ፓርቲው አስታውቋል። ኢዜማ በሕገ መንግሥቱ የተሰጠኝ መብት እንዲገደብ ተደርጓል ብሎ በከፍተኛ ፍርድ ቤት ክስ መሥርቻለሁ ብሏል።

የፓርቲው የክስ ጭብጥ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር፤ በሕገ መንግሥቱ የተሰጠኝን የመሰብሰብ እና ሐሳብን በነፃነት የመግለጽ መብቴ በመገደቡ በሚል ክስ የተመሠረተ መኾኑን በሳምንቱ አጋማሽ ላይ በሰጠው መግለጫ አስታውቋል።

እስከአሁንም እንዳይወያይ መከልከሉ አግባብ ያለመኾኑንና በዚህ ጉዳይ ላይ ፍርድ ቤት ትእዛዝ እንዲሰጠው ጠይቋል።

እንደ ኢዜማ መግለጫ፤ በአሁኑ ወቅትም የመሬት ወረራ መኖሩን፤ ከዚህ ጋር የተያያዙ ሕገወጥ ተግባራት ሊታረሙ አለመቻላቸውንም ጭምር አመልክቷል። (ኢዛ)

የትግራይ ሕዝብ ጫና እንዲያደርግ ተጠየቀ

የፌዴሬሽን ምክር ቤት በሳምንቱ አጋማሽ ላይ የትግራይ ክልል ምክር ቤትን በተመለከተ ውሳኔ ካሳለፈ በኋላ የተለያዩ አስተያየቶች እየተንሸራሸሩ ነው። ሰሞኑንም የፌዴሬሽን ምክር ቤቱ አፈ ጉባዔ አቶ አሕመድ ፋራህ የትግራይ ሕዝብ በክልሉ እየተካሔደ ያለውን ኢ-ሕገ መንግሥታዊ አካሔድ ለማስቆም ጫና ማድረግ እንዳለበት አሳስቧል።

ምክር ቤቱ የትግራይ ክልልን የሚመራው የፖለቲካ ድርጅት የሚያደርገውን ሕገወጥ እንቅስቃሴ ተከትሎ ያሳለፈው ውሳኔ፤ የክልሉን ሕዝብ መብትና ተጠቃሚነት ለማረጋገጥ ያለመ ስለመኾኑ ገልጸዋል።

የፌዴሬሽን ምክር ቤት የፌዴራል መንግሥቱም ይሁን የክልል መንግሥታት ሕገ መንግሥቱን አክብረው እንዲንቀሳቀሱ የማድረግ ኃላፊነት እንዳለበት የጠቆሙት አፈ ጉባዔው፤ በዚህም መሠረት የትግራይ ክልልን የሚመራው የፖለቲካ ድርጅት የፌዴሬሽን ምክር ቤት የሚወስናቸውን ሕጎች የማስከበር ውሳኔዎች ወደ ጎን ችላ በማለት በሕገወጥ መልክ እየተንቀሳቀሰ በመኾኑ ውሳኔ ስለመተላለፉ አስታውሰዋል።

የክልሉ ሕዝብ እንደማንኛውም የአገሪቱ ሕዝቦች ሰብአዊና ዴሞክራሲያዊ መብቱ እንዲከበር የፌዴሬሽን ምክር ቤት ዋነኛ ፍላጎት መኾኑን በማመልከት፤ አሁንም ቢኾን ግን ነገሮች በሰላማዊ መንገድ ለመፍታት የተዘጋ በር ያለመኖሩን የሚያመለክት አስተያየት ሰጥተዋል። (ኢዛ)

ሐሰተኛ 80 ሺህ ብር ተያዘ

የብር ኖት ለውጡን ተከትሎ በሕገወጥ መንገድ የሚንቀሳቀስ ገንዘብ ላይ የሚደረገው ቁጥጥር የቀጠለ ሲሆን፤ ባሳለፍነው ሳምንትም በአማራ ክልል በአዊ ብሔረሰብ አስተዳደር በአንድ ቀበሌ ውስጥ ሐሰተኛ 80 ሺህ ባለ አንድ መቶ የብር ኖት ተይዟል።

የአካባቢው ፖሊስ ጽሕፈት ቤት እንዳስታወቀው የእንጅባራ ነዋሪ የኾኑ ሁለት ግለሰቦች መስከረም 28 ቀን 2013 ዓ.ም. ሐሰተኛ ብር ይዘው ሲንቀሳቀሱ እጅ ከፍንጅ ተይዘዋል።

ባለ 100 ብር ኖት የኾኑትን 80 ሺህ ብር ሐሰተኛ ገንዘብ የተያዘባቸው ሁለት ግለሰቦች ላይ ምርመራ እየተደረገባቸው ነው። (ኢዛ)

የዳውድ ኢብሳ ጥሪ እና የብልጽግና አቋም

አቶ ዳውድ እመራዋለሁ የሚሉት የኦሮሞ ነፃነት ግንባር በኦሮሚያ ክልል አስቸኳይ የሽግግር መንግሥት እንዲመሠረት ጥሪ ስለማስተላለፉ የተነገረው በዚህ ሳምንት ነው።

በአቶ ዳውድ ኢብሳ የሚመራው ቡድን በሰጠው መግለጫ፤ በአሁኑ ወቅት በኦሮሚያ የመንግሥት መዋቅሮች እየተሸራረፉ፣ ሕግም እየተጣሰ ይገኛል የሚለውን እምነቱን ያንጸባረቀ ሲሆን፤ አሁን ያለውን መንግሥት ሕጋዊ አለመኾኑን በመጥቀስ በክልሉ የሽግግር መንግሥት መመሥረት ይኖርበታል ብሏል።

አሁን ያለው መንግሥት ምርጫውን ያራዘመበት ሒደት የፖለቲካ ተቋማት ተሳትፎን ያላረገገጠ በመኾኑ፤ ቅቡልነት የለውም የሚለው የአቶ ዳውድ ቡድን፤ አገር አደጋ ውስጥ እንዳትገባ የሽግግር መንግሥት አስፈላጊ ነው ይላል።

ይህ ኦነግ ያስተላለፈው የሽግግር መንግሥት ይመሥረት ጥሪ ግን ፋይዳ የሌለው መኾኑን የኦሮሚያ ብልጽግና ፓርቲ አመራሮች በተለያየ መንገድ አስተያየት ሰጥተውበታል። መንግሥት ምርጫውን ለማካሔድ ዝግጁ መኾኑንም አፅንኦት ሰጥተው ገልጸዋል። ጥሪውን ያስተላለፉ የተባሉት አቶ ዳውድ ኢብሳ ከኦነግ ሊቀመንበርነታቸው የተነሱና አሁን የሚያሰሙት ድምፅም ቢሆን ለማኅበራዊ ገጾች ፍጆታ የሚውል ስለመኾኑ በመግለጽ ጭምር ድርጊታቸውን አጣጥለውታል። (ኢዛ)

የእንጦጦ ፓርክ ተመረቀ

ከአገሪቱ በዋናነት ከሚጠቀሱ የቱሪስት መዳረሻ ይኾናል ተብሎ የታመነበት የእንጦጦ ፓርክ ግንባታ በአንድ ዓመት ውስጥ ተጠናቅቆ ለምረቃ የበቃው ባሳለፍነው ሳምንት ነው።

ለአንድ ራት 5 ሚሊዮን ብር በመስጠት በተሰበሰበው ገንዘብ የተገነባው ይህ ፓርክ፤ በውስጡ የተለያዩ መዝናኛዎችና የተለያዩ አገልግሎቶችን የያዘ ዓይነግቡ በኾነ መንገድ የተገነባ ነው።

አዳዲስ አገልግሎቶችን በማካተት ለቱሪስት ምቹ የኾኑ ግንባታዎችን አካትቶ የተገነባው የእንጦጦ ፓርክ፤ መስከረም 2012 ዓ.ም. ግንባታው ተጀምሮ፤ መስከረም 30 ቀን 2013 ዓ.ም. ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር ዐቢይ በተገኙበት ተመርቋል። መንግሥት ጀምሮ መጨረስን በአግባቡ ያሳየበት ፕሮጀክት ስለመኾኑ የተጠቀሰ ሲሆን፤ ፓርኩ ከሚያስገኘው ኢኮኖሚያዊ ጠቀሜታ ባሻገር፤ በእንጦጦ ተራራ አካባቢ እንጨት በመልቀም ይተዳደሩ የነበሩ ከ400 በላይ እናቶች የሥራ እድል የፈጠረም ነው።

በምረቃ ሥነ ሥርዓቱ ላይ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ፤ “ይህ ውብ ስፍራ እንዲገነባ ያደረጋችሁ ሁሉ እንኳን ደስ ያላችሁ!” ብለው፤ ኢትዮጵያ ድሀ ብቻ ሳትሆን፤ ብርቱ፣ የሚያስቡ፣ ያሰቡትን የሚያሳኩና የሚተገብሩ ልጆች ያሏት ናት በማለት፤ በዚህ ፕሮጀክት ላይ አሻራቸውን ያኖሩትንም አወድሰዋል። ኢትዮጵያን የመቀየር ትብብር አስፈላጊነትን ያወሱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ፤ ብዙ ሞት ነጋሪዎች ቢኖሩም፤ ኢትዮጵያ እንደምትበለጽግ እርግጠኛ ሆኜ እናገራለሁም ብለዋል።

ከለውጡ ወዲህ የአዲስ አበባን ገጽታ እየለወጡ ያሉት የሸገርና የአንድነት ፓርክም ተጠቃሽ ናቸው። በተመሳሳይ የቱሪስት መዳረሻ ይኾናሉ የተባሉት እና ከአዲስ አበባ ውጭ በሦስት ክልሎች የሚገነቡ ፓርኮችም ግንባታቸው ይጀመራል ተብሎ እየተጠበቀ ነው። (ኢዛ)

የሕወሓት ጥሪና የሁለቱ እንስቶች ምላሽ

በፌዴራል መንግሥትና በትግራይ ክልል ምክር ቤት መካከል የተፈጠረው አለመግባባት በሁለቱም ወገን የተለያዩ እርምጃዎችን እየወሰድን በማለት እየወሰዱዋቸው ያሉት አቋሞች ወቅታዊውን የፖለቲካ ትኩሳት አግሎታል።

ባሳለፍነው ሳምንት በሕወሓት በኩል ከተወሰዱት እርምጃዎች መካከል አንዱ፤ በፌዴራል ደረጃ ያሉ የሕወሓት አባላትና የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የሕወሓት አባላት ኃላፊነታቸውን ለቀው ሪፖርት እንዲያደርጉ የሚል ይገኝበታል።

እነዚህ የፌዴራል ባለሥልጣናትና የምክር ቤቱ አባላት ለሕወሓት ጥሪ የሰጡት ምላሽ ግልጽ ባይኾንም፤ በሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባላቱ መካከል በሳምንቱ መጀመሪያ ላይ በሁለቱ ምክር ቤት የጋራ የመክፈቻ ሥርዓት ላይ የተገኙት አንድ የሕወሓት አባል ብቻ ኾነዋል። ጥሪ ከተደረገላቸው መካከል አንዱ የኾኑትና የታላቁ ህዳሴ ግድብ ማስተባበሪያ ጽሕፈት ቤት ዋና ዳይሬክተር ወ/ሮ ሮማን ገብረሥላሴ አንዷ ናቸው። ለሕወሓት ጥሪ በሰጡት መልስ፤ “እኔ የምሠራው ህዳሴው ግድብ ላይ ነው፣ ግድቡ ደግሞ የሁሉም ብሔር፣ የሁሉም ሕዝብ ሀብት ነው” ብለዋል።

እንደ ወይዘሮ ሮማን ሁሉ ኃላፊነታችሁን ልቀቁ የተባሉትና በሁለቱ ምክር ቤቶች መክፈቻ ላይ የተገኙት ብቸኛዋ የትግራይ ሕዝብ ተወካይ ወይዘሮ ያየሽ ተስፋሁነኝ ናቸው። ሕወሓት ከአባልነታቸው ተነስተው ሪፖርት እንዲያደርጉ ቢጽፍላቸውም ጥያቄውን አልተቀበሉትም። ከፓርቲው አባላት መካከል ቢኾኑም፤ የሕዝብ ድምፅ በማክበር ወደ ስብሰባው መምጣታቸውን ለኢትዮጵያ ቴሌቪዥን ተናግረዋል።

“የተለያየ ፓርቲ ወክለን ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ብንገባም ምክር ቤት ስንገባ ግን የኢትዮጵያ ሕዝብ ወኪል ነን” ያሉት ወ/ሮ ያየሽ፤ አንድ የምክር ቤት አባል ከአባልነቱ የሚነሳው የወከለው ሕዝብ አይወክለኝም ሲል፤ አልያም የሥራ ዘመኑ ሲያበቃ መኾኑን በማመልከት፤ የሕወሓትን ጥሪ እንደማይቀበሉ አሳውቀው ሥራቸውን እንደሚቀጥሉ አመልክተዋል።

ወይዘሮ ያየሽ በሰሞኑ የሕወሓት ጥሪና ተያያዥ ጉዳዮች ለተለያዩ ሚዲያዎች በሰጡት መግለጫ፤ አንድ ፓርቲ በዘፈቀደ ተነሱና ውጡ ስላለ ብቻ ፓርላማን ለቅቆ መውጣት ሕጋዊ ተቀባይነት የሌለው መኾኑን ነው።

የአንድ ፓርቲ ጫናና ተፅዕኖም ኾነ ጽንፍ የረገጠ አመለካከት፤ የመረጠኝን ሕዝብ በጽናት ከማገልገል እንደማያግዳቸው በመግለጽ የሕወሓትን ጥሪ ወደ ጎን በመተው በፓርላማ ስብሰባው ላይ ተገኝተዋል።

አንድ ግለሰብ በፓርቲ ተወዳድሮ የፓርላማ አባል ከኾነ በኋላ ተገዢ የሚኾነው ለሕዝቡ፣ ለሕሊናውና ለሕገ መንግሥቱ ነው ያሉት ወይዘሮ ያየሽ፤ የኮሮና ወረርሽኝ የኢትዮጵያ ብቻ ሳይሆን የዓለም ሥጋት በመኾኑ በሕጋዊ አግባብ አገራዊ ምርጫው በመተላለፉ፤ ሕወሓት የፓርላማው የሥራ ጊዜው አብቅቷል ማለቱ ፈጽሞ አሳማኝ እንዳልኾነና የማይቀበሉት መኾኑን አስታውቀዋል። ሌሎች የፓርላማ አባላትም ተመሳሳይ እርምጃ ይወስዱ ዘንድ ጥሪም አቅርበዋል። (ኢዛ)

ምርጫ ቦርድ ሁለተኛውን ሕዝበ ውሳኔ ሊያካሒድ ነው

ከሰሞናዊው ዐበይት ዜናዎች መካከል በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ አምስት ዞኖችና አንድ ልዩ ወረዳ ክልል ለመመሥረት ያቀረቡት ጥያቄ በፌዴሬሽን ምክር ቤት በሙሉ ድምፅ አጽድቆታል።

በደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ የሚገኙ አምስት ዞኖችና አንድ ልዩ ወረዳ በጋራ አንድ ክልል ለመመሥረት ቀደም ሲል ለፌዴሬሽን ምክር ቤት ጥያቄ አቅርበው እንደነበር የሚታወስ ሲሆን፤ በሳምንቱ አጋማሽ ላይ የፌዴሬሽን ምክር ቤት ባካሔደው መደበኛ ስብሰባ፤ በጉዳዩ ላይ ተወያይቶ የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ አጽድቋል።

በዚህም አጀንዳ ላይ ምክር ቤቱ ሰፊ ውይይት ያካሔደበት ሲሆን፤ በተለይ በጥምረት ክልል እንሁን ብለው ከቀረቡት አምስት ተጣማሪዎች በፊት እንደ ወላይታ ያሉ ዞኖች ያቀረቡት የክልልነት ጥያቄ ሳይመለስ፤ ይህንን መመለስ ተገቢ ነው ወይ? የሚል ሙግት የቀረበበትም ነበር። ኾኖም ምክር ቤቱ የአምስቱ ዞኖችና አንድ ወረዳ ያቀረቡትን ጥያቄ ተቀብሎ በማጽደቅ በብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስፈጻሚነት ሕዝበ ውሳኔ እንዲደራጅ የቀረበውን የውሳኔ ሐሳብ በሙሉ ድምፅ ሊያጸድቀው ችሏል።

ጥያቄውን ያቀረቡት የከፋ፣ ቤንች፣ ሸኮ፣ ምዕራብ ኦሞ፣ ዳውሮ፣ ሸካ ዞኖችና የኮንታ ልዩ ወረዳ ሲሆኑ፤ እነዚህ ዞኖቹ ተቀራራቢ ቋንቋ፣ ባህል፣ ታሪክና መልክዓ ምድራዊ አቀማመጥ ስላለን አንድ ላይ ብንኾን የተሻለ ነው በሚል ጥምረቱ የተፈጠረ ሲሆን፤ ሕዝበ ውሳኔው ተደርጐ የሚገኘው ውጤት “የደቡብ ምዕራብ ኢትዮጵያ” 12ኛው ክልል ይኾናል የሚል እምነት አሳድሯል። በአሁኑ ወቅት በደቡብ ኢትዮጵያ ወደ 13 የሚኾኑ የክልል ጥያቄዎች እየቀረቡ መኾኑ ይታወቃል። (ኢዛ)

ብልጽግናና የትግራይ ተወላጆች ውይይት እያካሔዱ ነው

በዚህ ሳምንት ለየት ባለ መንገድ ከሚጠቀሱ ክንውኖች ውስጥ በተለያዩ የአገሪቱ ከተሞች ውስጥ የሚገኙ የትግራይ ክልል ተወላጆች ጋር የብልጽግና ፓርቲ ውይይት ሲያደርግ መሰንበቱ ነው።

ይህ ውይይት የፌዴሬሽን ምክር ቤት ካሳለፈው ውሳኔ በኋላ የተካሔደ ሲሆን፤ እስከአሁን በደሴ፣ በባሕር ዳር፣ በድሬዳዋ፣ በአዳማ፣ በአዲስ አበባና በሌሎች ከተሞች የተካሔደ ተካሒዷል። የሕወሓት አመራር እየፈጠረ ነው የተባለው ችግር ይውይይት ተደርጎበታል።

በተለይ መንግሥት የትግራይን ሕዝብ የሚጎዳ አንዳችም ነገር እንደማያደርግ በተገለጸባቸው እነዚህ መድረኮች፤ የትግራይ ተወላጆችም የሕወሓትን አመራር ያወገዙበትና ከብልጽግና ፓርቲ ጋር ለመቆም ቃል የገቡበት ጭምር ነበር ተብሏል። በየመድረኮቹ የተለያዩ ሐሳቦችም ስለመሰንዘራቸው የተጠቀሰ ሲሆን፤ “ወደ ትግራይ ኑ!” የሚለውንም ጥሪ የማይቀበሉ ስለመኾናቸው ገልጸዋል ተብሏል። (ኢዛ)

የአንበጣ መንጋ አርሶ አደሮችን ባዶ እጃቸውን እያስቀረ ነው

ከሰሞኑ ጎልተው ከታዩ አገራዊ ጉዳዮች አንዱ፤ በአብዛኛው የአገሪቱ ክልሎች እንደ አዲስ የተቀሰቀሰው የአንበጣ መንጋ ለመሰብሰብ የደረሰ ሰብልን ዶግ አመድ እያደረገ መኾኑ ነው።

የአንበጣ መንጋውን እያደረሰ ያለውን ውድመት ለመከላከል ጥረት ቢደረግም የተሳካ ባለመኾኑ፤ በአማራ፣ በትግራይና በሌሎች የአገሪቱ ክልሎች ባሉ አንዳንድ ወረዳዎች የአርሶ አደሮች የደረሰ ሰብል በአንበጣ መንጋ ተበልቶ በማለቁ፤ ከዚህ በኋላ አርሶ አደሮቹ እርዳታ ጠባቂ ኾነዋል በማለት በአዘኔታ እየገለጹ ነው።

አሁንም የአንበጣ መንጋው በተለያዩ አቅጣጫዎች እየተዛመተ በመኾኑ፤ ችግሩ የከፋ እንደሚኾን ተገምቷል። (ኢዛ)

በቀን በጥሬ ገንዘብ ከባንክ ማውጣት የሚቻለው የገንዘብ መጠን ቀነሰ
- ለግለሰቦች ይፈቀድ የነበረ ወጪ ከ200 ሺህ ወደ 50 ሺህ ብር ወርዷል
- የኩባንያዎችም ወጪ ወደ 75 ሺህ ብር ዝቅ ብሏል

የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ከጥቂት ወራት በፊት በጥሬ ገንዘብ ከባንክ የሚወጣ የገንዘብ መጠን ላይ ገደብ እንዲጣል ያወጣውን መመሪያ ዳግም በማሻሻል፤ ግለሰቦች በቀን ከባንክ በጥሬ ገንዘብ ማውጣት የሚችሉት 50 ሺህ ብር ብቻ እንደኾነ ያሳወቀው ባሳለፍነው ሳምንት ነው።

ከሦስት ወራት በኋላ ደግሞ በተከለሰው መመሪያ ኩባንያዎችም በቀን በጥሬ ገንዘብ የሚያወጡት የገንዘብ መጠን ከ300 ሺህ ብር ወደ 75 ሺህ ብር ወርዷል። በቀድሞ መመሪያ ግለሰቦች በቀን ማውጣት ይችላሉ ተብሎ ተጠቅሶ የነበረው 200 ሺህ ብር ሲሆን፣ በአዲሱ መመሪያ ግን ወደ 50 ሺህ ብር እንዲወርድ ተወስኗል።

ይህ ውሳኔ በጥሬ ገንዘብ የሚደረግን እንቅስቃሴ ለመገደብ ያለመ ቢኾንም፤ በጥሬ ገንዘብ ላይ የተመሠረተ ግብይት ጐልቶ በሚታይበት አገር በቀን ከባንክ የሚወጣው የገንዘብ መጠን በዚህን ያህል ደረጃ መቀነሱ በኢኮኖሚው ላይ ጫና እንዳይፈጥር የሚል መከራከሪያ እየተነሳበት ነው።

ኾኖም የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ይህንን መመሪያ ባንኮች እንዲያስፈጽሙ አዟል። አዲሱ መመሪያ በቀን ወጪ የሚደረገውን ይቀንስ እንጂ በወር ውስጥ ሊወጣ የሚችለውን መጠን አልቀነሰም። በቀድሞ መመሪያ ግለሰቦች በወር አንድ ሚሊዮን ብር ማውጣት እንደሚችሉ ይፈቅዳል። ኩባንያዎችም በቀን ከባንክ የሚያወጡት ጥሬ ገንዘብ መጠን ወደ 75 ሺህ ብር ቢወርድም በወር ማውጣት የሚችሉት ከ3 ሚሊዮን ብር በላይ መብለጥ የለበትም የሚለው የቀድሞ መመሪያ እንዲጸና መወሰኑን መረጃዎች ያመለክታሉ። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!