ሌቱ እስኪነጋ (አንዱዓለም በቀለ)
ሌቱ እስኪነጋ
አንዱዓለም በቀለ - ከስዊዘርላንድ
ጆሮ አልሰማ አይል - ብዙ ጉድ ይሰማል፥
ቴዲ ታስሯል ብለው - ሲገርመኝ ሰንብቷል፥
ደግሞ አሁን ተፈታ - ብለው ይነግሩኛል፥
በቃ አሁን ይብቃ - ተዉ ዝም በሉ፥
“የሌባ ዓይነ ደረቅ” - ሆኖ እንጂ ነገሩ፥
ለኔ እንደሚገባኝ - ወዲ ነው ሚስጥሩ፥
እንዴት የታሰረ - ሰው አሰርኩኝ ይላል?!
እራሱን ያልፈታ - እንዴት ፈታሁ ይላል?!
ቴዲም ይገርመዋል - ይሄን አይነግረንም፥
ሀገር በእስር ሆና - ነፃ ወጣሁ አይልም።
ፍትህ በግረሙቅ - የፊጥኝ ተጠፍሮ፥
ሐቅ ገደል ገብቶ - ነፃነት ተቀብሮ፥
ነፃ ሰው ነኝ ብሎ - መች በነፃ ኖሮ፥
ከወገኑ ጋራ - ሁሌ አንጀቱ አሮ።
በልጅነት ዕድሜው - ሽማግሌ ሆኖ፥
ሲመክር ኖረ እንጂ - ፍቅር ሠላም ብሎ፥
ቢላችሁን ጣሉ - ሞፈር ያዙ ብሎ።
አንድነት እንዲሆን - መለያየት ቀርቶ፥
በዜማው አስውቦ - በቅኔ አዋዝቶ፥
እስላም ክርስቲያኑ - እንዲኖር ተስማምቶ፥
ቤቱ እንደማይጠበን - መከረ እንጂ ተግቶ፥
ላፍታ መች አረፈ - ቴዲ ተመቻችቶ?
ብርሃን እንዲሆን - ጨለማው ተገሎ፥
ከወገኑ ጋራ - ወትሮም ወህኒ ሆኖ፥
ወደ አምላክ ጮኸ እንጂ - አይነጋም ወይ ብሎ፥
ነፃ ሰው ነኝ ብሎ - ቴዲ መች ኮብልሎ!
እናም ወገግ እስኪል - ሌቱ እስኪነጋ፥
እስኪነጋ በጣም - ብርሃን እስኪወጣ፥
መለከት ተነፍቶ - ትንቢት እስኪፈታ፥
ወደ ምስራቅ ዞረን - እስኪሆን እፎይታ፥
አበባዬሆሽም - እስኪዜም በደስታ፥
“አሳሪ” ነኝ ባዩም - እራሱ እስኪፈታ፥
መቼ ሊዘናጋ - ቴዲ ለአንድ አፍታ፥
ድሮም አልታሰረ - ዛሬም አልተፈታ።
አንዱዓለም በቀለ ከስዊዘርላንድ



