ዳግማዊ ዳዊት “ፍቺውና ላግባሽ” በሚል ርዕስ ለገጠመው ግጥም፤ ደሳለኝ በርሄ “ዳግማዊ ዓይኑ ይጥፋ!” በሚል ርዕስ በግጥም ምላሽ ሰጥቶታል። በግጥም መመላለስ ብዙ የተለመደ ባይሆንም፤ ገጣሚዎቻችን የሃሳብ ጦርነታቸውንም ሆነ መደጋገፋቸውን ቢያዘወትሩ መልካም ነው ብለን እናምናለን። ሁለቱንም ግጥሞች አቅርበናቸዋል። መልካም ንባብ!!!

 

ፍችውና ላግባሽ

ዳግማዊ ዳዊት ሐምሌ 2001 ዓ.ም.

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.  

 

አንች የልቤ ንግሥት - የእኔ ዴዝዲሞና

የጣና ዳር ሎሚ - የባህር ቄጠማ

ውብ ቆንጆ ውብ ንግሥት - የእኔ ሞናሊዛ

ልቤ ክንፍ አወጣ - ለፍቅርሽ ተገዛ።

 

ነሽ ወይ የወሎ ልጅ - የትግራይ ወለላ

የዳህላክ ደማም - የከረን የአስመራ

የመንዝወርቅ ነሽ ወይ - የባሌ የአዶላ

የጎንደር ወይንእሸት - የጆቲ የጦና

የጋምቤላዋ አልማዝ - የጅማ የአዋሣ

የአፋር የኦጋዴን - የዱፍቲ የመርሳ

የወልቃይት እንቁ - የሸበል በረንታ

ልቤ ባንች ፍቅር - እጅጉን ተረታ።

 

ለካስ ያ ባልሽ ነው - ጢቅ ሲል ያየሁት

በሰው ፊት የተፋው - ነውርን ነውር ንቆት።

 

ያ ቁመተ ደሃ - ፀባዬ ዲያብሎስ

አፍንጫ ጐራዳ - ትከሻ አልባ ሞገስ

ዓይኖቹ ሸውራራ - የማያስተውሉ

ጆሮዎቹ ድፍን - ወሬ እማያጣሩ

ጥርሶቹ ዘርዛራ - ሚስጥር አይቋጥሩ

ግብሩ የሳጥናኤል - በሀገር የተጠላ

ሼኽ የማያቀርበው - ካኅን ወይ ደብተራ

መነኩሴ እሚገድል - አምላኩን ሳይፈራ

ከእናቱ እሚቀማ - ለደሃ የማይራራ

እራሰ መላጣ - ባለጉፋያ ፂም

እኔ አንችን ቢያደርገኝ - አብሬው አላድርም።

 

አይ ዘመን አይ ጊዜ - ወይ ስምንተኛው ሺ

ሚስቱን ከወንድሙ - ይኸው ተጋራሽ

አንገትን ውሽማ - ባል ዳሌ ተካፍሎ

እንዲህ ያለ ትዳር - አሳየኝ ዘንድሮ።

 

አምላክ የመረጠው - የሥላሴ ነብይ

ያሳየውን ነገር - ያኔ ሲተነብይ

 

“እንዲህ ወደ ራስሽ - ራስ ውጋት ይዞ

ለመዳን ሲያስቸግር - ሲያስጨንቅ ሰቅዞ

ጩኸት ታበዣለሽ - እግዜሩን ልመና

እጅሽን ዘርግተሽ - ለምህረቱ መና”

 

የነብዩ ትንቢት - ሊፈፀም ነውና

ራስ ምታት ባልሽ - ውጋቱ ውሽማ

አንችኑ ሲጋሩ - በዓለም ላይ ተሰማ።

 

መቸም ያንች ነገር - ታሪክሽ ቢወራ

እንኳን የእኔ ቢጤው - የማያውቅ ምርመራ

ተነግሮ የማያልቅ - የሚያስገርም ሥራ።

 

ታቻምና ያን ጊዜ - የገና ዕለት ማታ

ሰው በዓል ሊያከብር - ነጋሪት ሲመታ

ፍሪዳው ሲታረድ - ቅርጫው ሲሰናዳ

ውሽማሽ እንደ ቦምብ - ነገር አፈነዳ

ከከንፈርሽ ወርዶ - ደረትሽን ሻተና

አምባ ጓሮ ፈጥሮ - ጃሎ ሸለለና

ቀውጥ ሆነ ሰፈሩ - ራስሽ ታመመ

ሁለተኛ ጊዜ - ያኔም ተደገመ።

 

ከንፈርን ውሽማ - ዳሌን ባል ተካፍሎ

አምላክ ጉድ አሳየን - በዓይናችን ዘንድሮ

ከእንዲህ ያለ ነገር - ከእንዲህ ያለ ጉድ

ሚስቱን ከውሽማ - ከሚካፈል ወንድ

ምን ጉዳይ ኖሮሽ ነው - ከባልሽ ያለሽው

ውርደት ከዚህ በላይ - ምን ሲያመጣ አየሽው?

 

ሰማሁ እንዳስተኛሽ - ከግብፁ ነጋዴ

ከአሜሪካው ቱጃር - ከሱዳን መደዴ

ከቻይና ቃልቻ - ከየመን አዝማሪ

ከዓረብ አንዳውላ - ከአውሮጳ አመንዛሪ

ይህ ባልሽ ይቅርብሽ - ፊትሽን አዙሪ።

 

እንደኔ እንደኔማ - ልቤ እንደሚወደው

እግዜሩ ፀሎቴን - ወደ ላይ ቢያሰርገው

እኔም ጉልበት ኖሮኝ - መውዜሩን ገዝቸው

ወይ በሽማግሌ - በሀገር አስፈርጄ

አንችን ከዚህ ባልሽ - ነጥቄ ወስጄ

ማየት ነው የምሻ - አንች ሆነሽ በጄ።

 

ወይ ዘማድ አዝማዱ - አንድ ላይ ተነስቶ

ያንን እኩይ ባልሽን - ልኩን አሳይቶ

ውሽማሽ ውንድሙን - በሚገባ ቀጥቶ

ይችል እንደሆነ - ዓይንሽን ሊያሣየኝ

ፍችውና ላግባሽ - ጥለሽው ነይልኝ።


 

ዳግማዊ ዳዊት

ሐምሌ 2001 ዓ.ም.

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.   

ዳግማዊ ዓይኑ ይጥፋ

ደሳለኝ በርሄ - መልስ ለገጣሚ ዳግማዊ ዳዊት

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.  

 

ነውጠኛ ነፍጠኛ ዳግማዊ ዓለመኛ

ነፍሰ ገዳይ ጨካኝ ዘራፊ ቀማኛ

ደግሞ “ፍችው” ይላል ይፈታና ቤቱ

የትናንት ጭካኔው የዛሬም ድፍረቱ።

 

ትናንት ብቻ በላ ዛሬም ቅሚያ አማረው

ይህ ዳግማዊ ዳዊት ፍጥረቱ ከምን ነው?

ከሲዖል አምልጦ ከሳጥናኤል መንደር

ወይስ ከናዚ ካምፕ ከሂትለር ሰፈር

መልካሙን የማያይ ከጥፋቱ በቀር።

 

አንዴ “ጮክ በል” ይላል ጮሆ ይለፍፋል

“ፍችውና ላግባሽ” ይላል ከጥሩ ባል

“ዛሬን አልኖርኩትም” እያለ ያለቅሳል።

 

እርሱ ለሴስነ መጮህ ስላማረው

መንግሥት የሚናጋ ምነው የመሰለው?

ይመኛታል እንጂ በህልም ይቃዣታል

ቆንጆዋን እመቤት በየት ያገኛታል?

አይኖራትም ዛሬን ልክ እንደትናንቱ

የነፍጠኛ ሥርዓት አክትሟል የጥንቱ።

 

ማንስ ከለከለው በሠላም ለመኖር

አልማር አለ እንጂ ከአባሻውል ሰፈር

ማየት ነው ሚስጥሩን የኃይሉን ግንባታ

የትም አያደርስም የእናንተ ጋጋታ

ጥፋት ነህ ዳግማዊ የማታ የማታ።

 

ሀገር እንድትለማ እውቀት እንዲስፋፋ

ዘላቂ እንዲሆንም የህዝባችን ተስፋ

ደግ የማይታየው ያ ቀቢፀ-ተስፋ

ማየት የተሳነው መልካሙ ሲፋፋ

ይህ ዳግማዊ ዳዊት ሁለት ዓይኑ ይጥፋ።


 

ደሳለኝ በርሄ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.   

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ