የዳግማዊ እና የደሳለኝ ሙግት በግጥም (ክፍል ፪)
ባለፈው ጊዜ ገጣሚ ዳግማዊ ዳዊት “ፍቺውና ላግባሽ” በሚል ርዕስ ለገጠመው ግጥም፤ ገጣሚ ደሳለኝ በርሄ “ዳግማዊ ዓይኑ ይጥፋ” በሚል ምላሽ መስጠቱን ማስነበባችን ይታወሳል። በዚህ ክፍል ፪ ብለን በሰየምነው የግጥም ሙግታቸው ደግሞ፤ ዳግማዊ “መሪዬን ተኩልኝ” ሲል ምላሽ የሰጠ ሲሆን፣ ደሳለኝ ደግሞ “አውቆ የተኛ” በማለት አፀፋውን መልሷል። የሁለቱን ተሟጋቾች ግጥም ታነቡ ዘንድ እንጋብዛለን። መልካም ንባብ!!! (የመጀመሪያውን ሙግት ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!)
መሪዬን ተኩልኝ ዳግማዊ ዳዊት አንድ ምስኪን ደሃ - ማየት የተሳነኝ ቀኑና ሌሊቱ - አብሮ ዶልቶብኝ የእናቴን ገጽታ - አባቴን ምስሉን ክዋክብትን ሳላይ - ጠፈሩን ሰማዩን ባህርና ኃይቁን - ጋራ ተራራውን ኒያላ ዋልያ - ፍንጠዛ እምቦሳውን የቆንጆን ፈገግታ - የዓይኗ ነፀብራቁን የጀግና ፉከራ - ፈሪ መርበትበቱን አዛን አላየሁም - ፀሎትና ጽዋ ቁርዓን አላነበብኩ - ወንጌል ጾመ ድጓ ጨረቃን ሳላውቃት - ፀሐይን ሳልሞቃት ዓለምን እንደ ዓለም - ፈፅሞ ሳላውቃት ግርም ሳይለኝ - ዓይኔ ሁሉን ዓይቶ የማየት ምንነት - ከእኔነቴ ጠፍቶ ይኸው እኖራለሁ - ዕድል እንደሰጠኝ ማየት የሚሉትን - አላግባቡ ነፍጎኝ።
አውቃለሁ አምናለሁ - ክርክር አልገባ አልሞክርም እኔ - የለ እሰጥ አገባ ዕድል እኔን ብቻ - ማየት አልነፈገ አድልዎ እየፈፀመ - ልብን እያዛገ ህሊናን በምኞት - ዘልቆ እያማለለ አካልን በጽኑ - ልብ እያቆሰለ ትናንትም ነበረ - ይኸው ዛሬም አለ የእኔማ እሮሮዬ - ኀዘኔ ለቅሶዬ ደስ ባይለኝ ነው - በዛሬ መሪዬ።
ሆሜርን ከግሪክ - ሳምሶንን ከእስራኤል የአላባማዋ እምቡጥ - ውቧን ሄለን ኬለር አንድ ያደረጋቸው - ያመሳሰላቸው ሰው መሆናቸው ነው - ብዬ እንዳልላቸው ከመንጋው ካሉበት - ከተደበቁበት ነጥረው ተስፈንጥረው - ጎልተው የታዩበት ልዩ ምልክቱን - ምስጢሩን ሳጤነው ጥሩ መሪ ማግኘት - ሆኖ ነው እማገኘው።
ሆሜር ጥሩ ገጥሟል - ግሪክ ጠጅ ጥሎ ሄለን ቀጭን ፈታይ - ብዕረ አመልማሎ ሳምሶን ግዳይ ጣለ - አዕማዱን ታግሎ ህሊና ዓይን አወጣ - ልብ በር ከፈተ ዓይነስውር ጃሎ - ጀግና ድልን ሻተ ወንዱ ደም መለሰ - ጠላት ተከተተ።
የአላባማ ፀሐይ - የአሜሪካ አበቦች የእስራኤል ኮረዶች - የግሪክ ፀዳሎች ፍጡረ ሥላሴ - ወይም አማልክቶች ሁሉም በዚህ ምድር - የሚርመሰመሰው በላይኛው ሰማይ - በአክናፍ የሚከንፈው በህዋው በጠፈር - ተንጣሎ እሚታየው ውበቱ ቢገለጥ - በሄለን በሆሜር የሰሙትን እንጂ - ያዩትን አልነበር ክታቡና አክታቡ - ስንኝ ቢደረደር ልብም ሃሴት ቢያደርግ - ህሊና ቢዘምር ምስጢሩ ቢደንቀን - ያስረከቡን ነገር ይሄ ከየት መጣ - ብለው ቢጠይቁ የእውቀቱን መስመር - መምጫውን እንዲያውቁ ሃሳብ ተፀንሶ - ተወልዶም ያየነው መሪው ለመምራቱ - ብቁ ሆነና ነው።
እኔም ዓይነስውር - የዛሬው ሆሜር ሳምሶን ነኝ እኔማ - ወንድመ ኬለር ጉዞዬ አስቸጋሪ - ከመሆን በቀር እመዘገብ ነበር - በታሪክ መዝገብ መሪዬ ባይጨክን - ክፋት ባያስብ።
እናንተ ወገኖቼ - የአጥንቴ ፍላጮች አዛኝ እህቶቼ - ልበ ደጋ ደጎች መሪዬን ተኩልኝ - በሉ አስወግዱልኝ የዛሬ ኑሮዬን - አያበላሽብኝ የነገ ተስፋዬን - አያጨልምብኝ።
ዳግማዊ ዳዊት ነሐሴ 2001 This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. | አውቆ የተኛ ደሳለኝ በርሄ አውቆ የተኛ ልግመኛ ፀረ-ሠላም አድመኛ ዓይነ-ሥውር ልበ-ብርሃን ልበ-ስውር ዘመነ-ጭፍን መልካም ከማያስተውል ልብ ይሻል የለ ዓይነ-ግብ።
ጠብ ይሻል አሉ ዳግማዊ ብሔረ-ሲኦላዊ ታወረ አሉኝ ላለማየት ልቦናውን ሸፍኖት ደግነቱን ነፍጎት ሠላም ከውስጡ ጠፍታ ተፈጥሮበት ሁካታ ይቃዣል አለኝ በፀና ዛሬም እንደገና እንዴት ብዬ ልንገረው እሱን የመረጠ ጥፋትን የሠላም ጠላትን እንዴት ልቀስቅስው እርሱን አውቆ የተኛውን።
የሚሰማቸው ካሉት ንገሯቸው ይንገሩት ድህነት መሰይጠኑን የሀገር ዕድገት ማገዱን የእኛን ውጊያ መፈለጉን
ጠላታችን ለእኛ ድህነት የምንዋጋው ዕለት ተዕለት ዳግማዊ የማያወቀው መስማት ያልፈልገው ማየት የተሳነው ጠላታችን ድህነት ነው።
ማን ይፈልጋል ዳግማዊን ይጋግር እንጀራውን - የህልሙን ይጋልብ እራሱን - የምኞቱን የጥፋት ፈረሱን እኛስ ተጉዘናል ወደፊት ከዚህ በኋላ ወዴት።
አንተ ትናንትን ናፍቀህ ዛሬ ታወርኩ ትላለህ ልፀልይህ አስቤ ከልቤ ጀመርኩ ፀሎቱን እውነቱን
ደግሞ ተውኩት ፀሎቱን አየውህና በህሊናዬ ክፋትህን ከደግ ከፍዬ ባሰላስለው ውጤቱን የፀሎቴን ተነሳሁ ትቸው መማለዴን ነቅፌ ድርጊቴን ሰው እንዴት ለአንተ ይፀልያል ለፈረሰ-ሳጥናኤል ጥፋት ለሚመኝ ለሀገር ሐውርያ-ዲያብሎስ ግብረ ነውር።
አብረን እንሥራ እንደግ ብዬ ብልህ ሁን ደግ ዛሬም ተመልሰህ ጥሬ እኔስ በቃኸኝ ዛሬ ላልመልስህ መክሬ ለታወረው ልብህ መሪም አያስፈልግህ ዓይነ-ስውርን ይመሯል ልበ-ስውር ግን ያስቸግራል እንዴት አድጎስ ይመራል?
በል አንተም አንቀላፋ በልብህ የለ ተስፋ ግና አንድ ልበልህ የሆነውን ልንገርህ ደግሞ ካልደነቆርህ
አዝማሪ ሰማሁ ሲዘምር በትግራይ በጎንደር “ሥልጡን መሪ” ብሎ ሲል መንበር ከሰሜን ስትወጣ ሥልጣኔ ይኸው መጣ።
ሰማኸኝ ወይ ወንድም ጥፋተ-ዳግም ቸር ተመኝ እንጂ ቸሩን የሚበጀውን ደጉን እንድታይ እውነቱን የሀገር ዕድገቷን ተወው እባክህን አውቆ መተኛቱን።
ደሳለኝ በርሄ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. |