የፓርላማ ድንፋታ - በዲሲ ተረታ!

ጌታቸው አበራ

(መታሰቢያነቷ፦ የሚሊዮኖችን የብሶት ድምጽ በድፍረት ላስተጋባው የኢትዮጵያ ልጅ፣ ለአበበ ገላው እና አምባገነኑ መለስ ዜናዊ ለደነገጠባት ለዚያች ዕለት ይሁን።)

(ግጥሙን በፒ.ዲ.ኤፍ. አስነብበኝ!)

ሁለት አሥርት ሙሉ “ያለኔ ማን” ያለ፣

ከራሱ “ራሶች” ጋር ፓርላማ የፎለለ፣

ቢባል ... ቢባል ... ቢጻፍ ... አልሰማ ቢል ከቶ፣

አበበ ነገረው፤ በ”ማዕረጉ” ጠርቶ።

 

(ራሱን ላዋረደ ክብሩን ለናቀ ሰው፣

“ዲክታተር” የሚለው “ማዕረጉ” ሲያንሰው ነው።)

በብረት ተከቦ — ራሱን አጉል ክቦ፣

በውዳሴ ዜማ — ባጎንባሽ ታጅቦ፣

አገር ያዋረደ፣ ሕዝብን ያሳደደ ...

ሰው መሳይ በሸንጎ፣

እማያቁት አገር “ቁርበት አስነጥፎ” ሊበላ ፈልጎ፣

“ፐርሰንቱን” ሲጠቅስ ሃሳዊው መሲህ ሊቅ፣

ፓርላማ ያለ መስሎት ጭብጨባ ሲጠብቅ፣

ሲሸሽ የኖረውን፣ ሰምቶ እማያውቀውን፣

እስኪሰበር ቅስሙ አገኘው ዋጋውን።

መለስ ሳይቸግረው አሸባሪ ብሎ አስቀድሞ ከሶ፣

በሽንጎ አሸበረው ያ! አበበ ገላው ቃላቱን ተኩሶ!

የኢትዮጵያ ልጆች ሁሌም ባለዝና፣

ይህ ታሪካዊ ስም ክቡር ነው ገናና፤

በሮም፣ በቶኪዮ እንዳኮራን ጀግና፣

ዋሽንግተን ዲሲም አበበ እንደገና!

አቤ! በተግባርህ፣ ያገር ወዳድ አንጀት ቅቤ ጠጣ ራሰ፣

የኢትዮጵያ ጠላት ደበነ፣ ኮሰሰ ...፣

ዳግም የትግል መንፈስ በብርቱ ታደሰ፣

የኢሳት ዝና ገድል ላለም ተዳረሰ፣

ለውለታህ ክብር እነሆ ምስጋና!

የነጻነት ድምጹ አበበ ነህና!


ግንቦት 2004 ዓ/ም (ሜይ 2012)

 

ጌታቸው አበራ

(ከምድረ-አፍሪቃ)

ማስታወሻ እሚገርመው ነገር፣ አበበ ገላው በዚያች ቅፅበት የተናገረው እውነታ፣ ኢትዮጵያ ውስጥ ቢሆን ኖሮ፣ ሊደርስበት ከሚችል አሰቃቂ ድብደባና ሰቆቃ በአጋጣሚ ህይወቱ ልትተርፍ ብትችል እንኳን፣ በወያኔ “ፍርድ” ቤት ከዕድሜ ልክ እስከ ሞት የሚያስቀጣው እነደነበር የሚጠራጠር ያለ አይመስለኝም። ግና በነጻይቱ አሜሪካ ምድር፣ በኢሳት ዘገባዎች እንደሰማነው ከሆነ፣ ከጥቂት ደቂቃዎች የፖሊስ ጥያቄ በኋላ፣ አቤ ወደ ቤቱ ሄዶ፣ ያቺን ምሽት በነጻነት የሰላም እንቅልፉን ሲለጥጥ ነው ያሳለፈው። (ምናልባትም በህልሙም ቀን የከወነውን አኩሪ ተግባር እየመላለሰ እያየ ደስ የሚል ሌሊት አሳልፎ ይሆናል)።

ነጻነት ለዘላለም ትኑር!! እኛም በዚሁ ጠንካራ መንፈስ ነጻይቱን ኢትዮጵያን ለመገንባት በያለንበት እንትጋ!

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ