አበበ ገላው እና ሊባክኑ የማይገቡ አጋጣሚዎች (ዳዊት ንዳ)
ዳዊት ንዳ
ባለፋው ዓመት ወጣቱ ቱኒዚያዊ ሞሃመድ ቦዚዝ ራሱ ላይ ቤንዚን አርከፍክፎ ሲያቃጥል የቤን አሊ ሥርዓት ያደርስበት የነበረውን ጭቆና በመቃውም እንጂ ሓውልት ሊያስቆም የሚችል ተግባር ለመፈጸም አልነበርም። የርሱ ራስን ማቃጠል የነጋዳፊ መጨረሻ መጀመሪያ ይሆናል ብሎም አልነበረም።
ነገር ግን ምሬቱ ምሬታቸው፣ በሶቱ ብሶታቸው፣ ስቃዩ ስቃያችው የሆነ የሃገሩ ልጆቸ ተቃውሞውን ተቀብለው አለምን ጉድ ያስኘ ለውጥ በሃገራቸው ከማምጣት አልፈው የለውጥ ትኩሳቱን ወደጎረቤት ሃገርና ወደ መካከለኛ ምስራቅ በማዛመት የብዙ አምባገነኖችን ውድቀት አሳይተውናል። እስካሁንም ለለውጥ የሚከፈለውን መራራ ክፍያ እየከፈሉ እምቢኝ ለአምባገነን ያሉ ብዙዎቹ ናቸው።
ከሁለት ቀናት በፊት በዋሽንግተን ዲሲ ጠቅላይ ሚኒስትር መለስ በተለመደው እብሪት ደረታቸውን ነፍተው ስለ ኢኮኖሚ እድገት አስፈላጊነት ሲመጻደቁ ጋዜጠኛ አበበ በለው ሁላችንም ባስደመመ ጀግንነት የርሱንና የሁላችንም ብሶት ይሆነውን የመለስን አገዛዝ ጭቆና በአደባባይ ጮክ ብሎ ተናግሯል። ይህ ጩኀትም እነ ኦባማን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር ያላቸውን ግንኙነት ድጋሚ እንዲያስቡበት ያደርጋቸዋል ብዬ ተስፋ አደርጋለሁ።
ይህ የአበበ ቁጣና ጩኀት በኛ ፊት ክብር ሞገስና ለማግኘት ያደረገው አይደለም። የደረሰበትን ስቃይ፣መከራ፣ ጭቆና ነው የተቃወመው። የአበበን ጩኃት በዙሌሎች ኢትዮጵያውያኖች ጮኀውታል። በቅርቡ እንኳን እነእስክንድር፣ አንዷለም፣ ርእዮት፣ ውብሽት ጮኀውታል። ራሱ አበበ ኢሳት ላይ ከሲሳይ አጌና ጋር ባደረገው ቃለ መጠይቅ እንዳለው ባገኘው አጋጣሚ የመለስን አስከፊ ጭቆና ሊያጋልጥ እንደሞከረ እና ሌሎቻችንም የርሱን አርኣያ እንድንከተል ጥሪ አቅርቧል።
ከላይ ለመግለጽ እንደሞከርኩት እስከዛሬ የተጮሁትን ጩኀቶች ሁላችንም የአንድ ሳምንት መወያያ ርእስ ከማድረግ ውጭ መልእክቱ ገብቶን የጀግኖቻችንን ቁጣ መልስን ስንቆጣ የታየንበት አጋጣሚ አልታየም። ቱኒዝያዊው ሰማእት ቦዚዝ ስሙ ገኖ ሊቅ ደቂቃኑ ያወቀው በሌሎች የሃገሩ ልጆች ብርቱ ትግልና መሰዋእትነት መሆኑን መዘንጋት የለብንም። አቤ፣ እስክንድር፣ ርእዮት፣ውብሸት፣ተመስገን ጀግኖቻችን ሆነው እንዲቀጥሉ ማድረግ የምንችለው ቁጣቸውን ቁጣችን፣ ብሶታቸውን ብሶታችን፣ ጩኃታችውን ጩኃታችን ማድረግ ስንችልና የጀመሩትን አርኣያነት ስንቀጥልበት ብቻ ነው። አሊያ ግን እንደ እስካሁኑ ጀግኖቻችን የወቅቱ ርእስ ብቻ ሆነው እንዳይቀሩ እሰጋለሁ።
ዳዊት ንዳ
Silver Spring, MD
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.



