ስብሐት ለጨለማ

መስፍን ወልደማርያም (እንጉርጉሮ) - 1967 ( Read on PDF )

ስብሐት ለጨለማ፤ ለብርሃን ዋዜማ!

ጨለማ! የስርቆሽ ውድማ! የግብዝ ከተማ!

ጨለማ! የክፋት፤ የተንኮል፤ የጭካኔ አለኝታ!

የወንጀል ነፃነት! የኃጢአት ደስታ!

ይጠየቅ ሰው ሁሉ፤ እውነቱን ይናገር፤ የሚናገር ቢኖር፤

ብርሃን ነው ጨለማ ሰውን የሚያሳፍር?

ጨለማን ይጠላል ሰው ጨዋ ለመባል፤

ብርሃን ሲያሸማቅቅ አያውቀው ይመስል!

 

ጨልም! ጨልም! ድፍን ብለህ ጨልም!

ዓይኖቻችን ይጥፉ፤ አያዩም፤ አይጠቅሙም።

ውሾቹ ይጩሁ፤ ጅቦቹ ያጉዋሩ፤

የሌሊትም ወፎች በራስ ላይ ይዙሩ፤

አራዊት ይንጫጩ፤ አጋንንት ይጋጩ፤

የብርሃንም ጨዎች በጣር ይወራጩ፤

ዛሮችም ይጋልቡ ፈረሶቻቸውን፤

ሁሉም ይኮላተፍ የዛር ፈረስ ይሁን፤

ድብልቅልቁ ይውጣ ሰው ሰውን አይለካው፤

የራሱን ሰውነት መጠኑን እስቲያውቀው።

 

ጨልም! ጨልም! ድፍን ብለህ ጨልም!

ዓይኖቻችን ይጥፉ፤ አያዩም፤ አይጠቅሙም።

ሰውረን ጨለማ አድነን ከብርሃን፤

ምስጢር እንዲጠበቅ ገበና እንዲሸፈን፤

ብርሃኑ ይጨልም! ጨለማውም ይድመቅ!

ፀሐይዋ ትሰበር! ምሰሶዋ ይውደቅ!

ጨረቃዋ ትጥፋ! ኮከቦች ይርገፉ!

ጨለማውን ለብሰው መሬት ይነጠፉ!

ሰማዩ ይቀደድ! ይጣራ፤ ዶፍ ይውረድ!

ይጥፋ የሚማገድ፤ የነደደው ይብረድ!

 

ጨልም! ጨልም! ድፍን ብለህ ጨልም!

ዓይኖቻችን ይጥፉ፤ አያዩም፤ አይጠቅሙም።

ለመጋለጥና ለማጋለጥ ብቻ ከጠቀመ ብርሃን፤

ከነምቹ ይጥፋ! አልበጀንም ዋመን።

አይቶ የማይገምት፤ ታይቶ የሚገመት፤

የጨለማ ሰው ነው የቀን አሻንጉሊት!

አንዱ አንዱን ሳያውቀው በርግጥ እያወቀው፤

አንዱ አንዱን ሳያውቀው በርግጥ እያወቀው፤

በብርሃን ደግነት፤ በጨለማ ክፋት፤

ቁም ነገር የሌለው ዕለት በለት ስደት።

 

ጨልም! ጨልም! ድፍን ብለህ ጨልም!

ዓይኖቻችን ይጥፉ፤ አያዩም፤ አይጠቅሙም።

መንታ መንታውን ነው ጭካኔ እሚወልደው፤

አንደኛው መከታው አንደኛው ጠሩ ነው።

ንዴት በሌለበት ምን ማለት ነው ትዕግስት?

ፍርሃት በሌለበት አለ ወይ ጀግንነት?

ክብርን የማያውቁ

እንዴት ውርደት ናቁ?

ድህነት በመሬት ጭራሽ ባይፈጠር፤

ጌትነት ምን በልቶ ይጠበድል ነበር?

 

ጨልም! ጨልም! ድፍን ብለህ ጨልም!

ዓይኖቻችን ይጥፉ፤ አያዩም፤ አይጠቅሙም።

ጨለማ አስረግዞ ጨለማ ሳይወልደው፤

ብርሃን የት ይገኛል ጨለማ እሚገልጠው?

ጨክን ጨለማችን ጭላንጭሉን አጥፋው፤

ብርሃን ከኛ ይፍለቅ፤ በውሉ ስንሻው።

ውበት ስሙ ይጥፋ፤ እኛ እስትንፈጥረው፤

እውነት ያንቀላፋ እስትንቀሰቅሰው።

በርታ ጨለማችን፤ ተጨነቅ! ተጠበብ!

አምጥና ውለድ ለቁም ነገር ጥበብ።

 

ጨልም! ጨልም! ድፍን ብለህ ጨልም!

ዓይኖቻችን ይጥፉ! አያዩም፤ አይጠቅሙም።

የግዜር ሕያው ትንፋሽ ካለ በውስጣችን፤

አስረግዘን ብርሃን ጨለማው አውራችን።

የተዳፈነውን በቀኑ ለኩሰው፤

እሳት በሳት ነጥሮ እሳት እንዲሆን ሰው።

ጨለማ ያስታርቀው የብርሃንን ጠላት፤

ጨለማና ብርሃን ሰውን አይክፈሉት።

በብርሃን ያየነው ሲጨልም ከጠፋ፤

ይጨልም ጨርሶ፡- ጨለማ ምን ከፋ!

ስብሐት ለጨለማ! ይጨልም! ይጨልም!

ዓይኖቻችን ይጥፉ አያዩም፤ አይጠቅሙም።

 

መስፍን ወልደማርያም

(እንጉርጉሮ) - 1967

 

 

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ