ይድረስ ለአቶ መለስ

ከወለላዬ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)  (Read on PDF)

 «ትዕቢትና ኩራት የሞሉት አናት

ሰይፍና ጎራዴ የመቱት አንገት

አይገላገሉም እንዲህ በቀላሉ

እመሬት ላይ ወድቀው ሳይንከባለሉ።»

ከበደ ሚካኤል

 

ኢትዮጵያዊ ባህል አክብሮት ሳይቀንስ፣

ይሄ ደብዳቤዬ ይድረስ ለአቶ መለስ።

ሥልጣንን ጨብጠው ከቆነጠጡበት፣

እስከ ዛሬ ድረስ አስራ ሰባት ዓመት፣

ኢትዮጵያዊነትን ባህል ልምድ ጥሰው፣

ህዝቡን በቋንቋና በጎሣ ከፋፍለው፣

በፊርማዎ አጽድቀው አገር በመገንጠል፣

ወደብ አልባ አድርገው ባንዲራን በማቅለል፣

 

የራስዎን ጎሣ ሥልጣን በማስጨበጥ፣

የሀገሪቱን ንብረት በገፍ በመቦጥቦጥ፣

አለምንም ገደብ ይሉኝታ ፍራቻ፣

አርገውት ከርመዋል ህዝቡን መጫወቻ።

 

ይሄ ሳያንስዎ የዛሬ ሦስት ዓመት፣

ተቃዋሚን ወገን ለምርጫ በመጥራት፣

እንደአንድ ፓርቲ ገብተው ለውድድር፣

ገና ከጅምሩ ፈጥረው ብዙ ችግር፣

ተቃዋሚው ችሎ ሁሉንም በትዕግስት፣

ቅንጅት በመፍጠር አብሮ በአንድነት፣

ለህዝብ አስረድቶ ዓላማውን ነግሮ፣

ሊጥልዎት ችሏል በምርጫ አሽቀጥሮ

ያን ባለመቀበል በአምባገነንነት፣

ግንቦት ስምንት ቀን ተነስተው በእብሪት፣

ማንም እንደማይችል መቃወም መሰለፍ፣

ሕግ ደንብ አውጥተው ቀርበው በመለፍፍ፣

የፀጥታው ክፍል እንዲወስድ እርምጃ፣

አስከብበው አድረው ህዝቡን በጠብመንጃ፣

ብሎም የወጣውን ድምጻችን ይከበር፣

ግማሹን በመግደል ግማሹን በማሰር፣

ያሸነፈውንም ከየቤት በመልቀም፣

ሰብስበው በማሰር ወሕኒ በመጠርቀም፣

ባገሪቷ ያሉን ነፃ ጋዜጠኞች፣

የሰብዓዊ መብትን ተከራካሪዎች፣

አንድ ላይ አጉረው ሲያሰቃዩ ከርመው፣

በሞት እንዲቀጡ በዳኛ አስፈርደው፣

ተፅዕኖ በማድረስ ሞራል በመደፍጠጥ፣

ይቅርታ አሰኝተው ፍርዱን በመለወጥ፣

መልሰው እነሱን ጥፋተኛ አድርገው፣

ሊፈቱ ችለዋል ሕግ እራሱን ገድለው።

 

የግፍ ድርጊትዎ ከዚህ አልፎ ንሮ፣

ተደናቂው አርቲስት ወጣቱ ቴዲ አፍሮ፣

ጥፋተኛ ሆኖ ታስሮ እንዲንገላታ፣

ሲመቻችበት ክስ መርጠዋል ዝምታ

ግዴለም ተብሎ ይሄም ባይታለፍ፣

አሁን ደግሞ ሀገርን ዙርያዋን በመቅረፍ፣

የኢትዮጵያን ግዛት የኢትዮጵያን ድንበር፣

ሰተዋል አስምረው ለጎረቤት ሀገር።

 

ህዝቡም እያለቀ በረሃብ ቀጠና፣

ኢኮኖሚው አድጓል ተሻሽሏል ከአምና፣

ብለው በመናገር በአፍዎ እያወሩ፣

ይሄው ዓለም አውቋል በርትቶ ችግሩ

ደንታ ቢስብም ሆነው ለራስ በመስገብገብ፣

የኑሮው ውድነት ሊያልፍ ችሏል ገደብ

ምን እንደሚያስከትል ይሄንን ሲሰሩ፣

ይገባዎት ነበር ከታሪክ ሊማሩ፣

የተራበ ሁሉ የኋላ የኋላ፣

ታይቷል በብዙ ሀገር መሪውን ሲበላ

እርስዎን መሳዮች በግፍ የተነሱ፣

ምንግዜም አልቻሉም እጫፍ ላይ ሊደርሱ

በዚች ሀገራችን ያስከተሉት መዘዝ፣

አለው ብዙ ብልጫ ከማንንም አገዛዝ

ስለዚህ በቶሎ ነገ ዛሬ ሳይሉ፣

መጭውን ሁኔታ አይተው በጥቅሉ፣

ጥፋት በጥፋት ላይ መደራረብ ትተው፣

ከክፉ ጥላቻ ከቂም በቀል ወጥተው፣

ይቺ ባለ ታሪክ የነፃነት ሀገር፣

መላቀቅ እንድትችል ከከተቷት ችግር፣

ያጠፉትን ጥፋት በግዜ በማረም፣

ይነሱ በቶሎ ቀንዎ ሳይጨልም

አለበለዚያ ግን ይህ የያዙት እብሪት፣

ከበደ ሚካኤል ቀድመው እንደጻፉት፣

ማስከተሉ አይቀርም ጠንከር ያለ ውርደት

በአንድ ሀገር የኖረ አንድ ጨካኝ ንጉሥ፣

ሰው መሆኑን ሲስት ህዝቡን እንዳይጨርስ፣

”ንጉሥ ሆይ! ሰው ነዎት!” እያለ የሚነግረው፣

በየቀኑ አስታዋሽ አንድ ሰው ነበረው፣

እርስዎም ሰው ነዎት እንደሰው ያስቡ፣

እጅግ ነው የከፋው የመረረው ህዝቡ፣

በርሃብ አለንጋ በጠብመንጃ አፈሙዝ፣

እየቀጠቀጡ አጥብቀው በመያዝ፣

እያስከፈሉት ነው ያልበላውን ዕዳ፣

መቼም አልገጠመው ይሄን መሳይ ፍዳ

እንዲህ አስርበውት አንድ ቀን ሲነሳ፣

እስከጭፍሮችዎ አይበቁም ለምሳ።

ይሄ ደብዳቤዬ ሳይጨምር ሳይቀንስ፣

በዚሁ ሁኔታ ይድረስ ለአቶ መለስ።


 

ወለላዬ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)

(ግንቦት 24 ቀን 2000 ዓ.ም. June 1, 2008)

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ