አፍሪካዊው ኮከብ (አበራ ለማ)
አበራ ለማ
ጀግናው አሸለበ፣ ደከመው ተረታ
ሞት አይቀርምና፣ የማታ የማታ፤
ምን ብርቱ ቢሆኑ፣ ሺ መካች ቢሆኑ
ሰው አያልፍ አይገደፍ፣ ተዛቹ ተቀኑ፤
አፍሪካ ሆይ መጥኔ፣ አንድ ወልደሽ ላጣሽው
ተንግዴ መሸብሽ፣ በማን ትዘክሪው? በማንስ ትጠሪው?
ማንዴላ ብረቱ፣ የሮቢን ደሴቱ
የዘረኞች ዋግምት፣ የጥቁር ኩራቱ
ተንግዲህ የለህም፣ ታሪክ ነበርክና
ታሪክ ነህ ተንግዴ፣ ላትመጣ እንደገና፤
ዓለም አሸርግጂ፣ ቱቢት አስመቺና
ደረት እየመታሽ፣ "ወይ ልጄን ..." በዪና፤
አንበሳሽ ቀን ጣለው፣ ይውጣልሽ ኀዘንሽ
ሙሾሽን ደርድሪ፣ ማቅ ልበሽ እባክሽ
ማንዴ'ኮ ነው ሂያጁ፣ ሌላው እንዳይመስልሽ፤
ባፍሪካ ሰማይ ላይ፣ የበራው ኮከብ
ተወርዋሪ ነበር፣ ዐይንን የሚስብ፤
ባፍሪካ ሰማይ ላይ፣ የነጋው ጀምበር
ለወገኑ ነበር፣ ብርሃንና አድባር
ለጠላቱ ነበር፣ መራር እንደ ኮሶ
ገፍናኝ እንደንቆቆ፣ ጠላትን አድብኖ - ጠላትን አጢሶ፤
ማንዴላ አባ ቢያ፣ ደከመኝ ባይል
በቀን ተሸንፎ፣ ኑ ሸኙኝ ባይል
የኮከቡን ኮከብ፣ ማን እሱን ሊያህል?!
ባፍሪካ ሰማይ ላይ፣ የታየው ፀዳል
ጌጣችን ነበረ፣ ተመሃል ባይጎል፤
አበራ ለማ
(ኦስሎ፣ 06/12/2013 እ.ኤ.አ.፣ 01፡06 ሰዓት)