ዘምንሊክ ከሲድኒ
ኔልሰን ማንዴላ Nelson Mandela
ዋ ማንዴላ!
ዋ ማዲባ!
ይቺን ፀሐይ ማን ነገረህ
ከጨለማ ውስጥ በቅለህ
ከድጥ ወደ ማጥ ብትዳክር
ብርሃን በልብህ አሳድረህ
"እንካቹ!" ብትል ብትጮህ
ሰሚ ተነፍጎህ
አንድ ቀን እንደሚነጋ
በደልና ግፍ ማክተሚያ እንዳለው ስትዘክር፤

ለተጨቆነ እንዲበራ

ቃል ተጋብተህ እስክትሞት እንደምትዳክር።
ንገረኝ ማዲባ
ጥርኽልኝ ማንዴላ
ማን ነገረህ እንዲህ እንዲነጋ?
ግዙፉን ያፓርታይድ ዱላ
ሳትሰለች ቅንጣት ሳትፈራ

ቢወርድብህ

በወጣት ዘመን ቢቸክህ፤

እግርህ በግረሙቅ ታብቶ

እኩል ዕድሜህን ቀምቶ

በግዞት ቢጠበጥብህ
የልብህ ብርሃን በራ እንጅ
መች ተረታህ ለፈረንጅ።
ይቺን ቀን ፀሐይ እንድትፈካ ለጭቁኖቹ
እንድትበራ ማን ሹክ ብሎህ ይሆን ምስራቹን?
ዋ ማዲባ!
ዋ ማንዴላ!
የሰባዊነት ትሩጁማኑን ባንታየን


ቢተቹህ ቢንቁህ
ሰላማዊ ትግልህን ቢያንጓጉጡህ
የልብህን ብርሃን መች አወቁ?

ትግልህ አፋፍ ላይ ደርሶ

ሰላም ለህዝብህ አንግሶ

ሥልጣን በጅህ ሲገባ

ያቺን የልጅነትህን ብርሃን

በመካያው ላለም ብታሰፍን፤
ጥቁር የሰላም ፀር ይመስል
ዓለም በራድ ቆዝሞ -

በደም መቃባት በበቀል
ዛሬ- ነገ ፈነዳ ብሎ -

በሰቅቀን ተብሰክስኮ
ጉድ ለማየት ሲያደባ
ተቃቅፈህ ጸናህ ከዴክለርክ፤
ሰላም መስፈኑን አበሰርክ።

ዋ ማንዴላ!

ዋ ማዲባ!

እንዴት ይሆን

የገባህ ፍቅር

እንዴት ይሆን

የገባህ መላ

ዋ /ን/ ማን ማንዴላ!!!
እነንቶኔ
አንሰው አንሰው
ከዘር ወርደው
ብሔር ከጎሣ ሰፍረው
ሰፍረው
ቁ-ል-ቁ-ል
ደ-ቅ-ቀ-ው
ተ-በ-ጣ-ጥ-ሰ-ው
በሥልጡን ዘመን
ፊት ገ-ጥ-ጠ-ው
ገዢ ነን ብለው
ካገር ከህዝብ ተስፈንጥረው
እንደማይጸግብ መጋዣ -
የህዝቤን ደም መ-ጥ-ጠ-ው፡
መ'ጠው፡
አሳፈሩን በመሪ ስም ስናያቸው፡
ማይችሉት መንበር ላይ ሲንቧቸሩ ብናያቸው።

አንተ ግና

የበቀል ፍሬ እንዳይረባ

ባስደናቂ ፍቅር አስተጋባህ፤
ዋ ማንዴላ! ዋ ማዲባ!
የሰላም የፍቅር ሐውልት
የጥቁር ብልህ ተምሳሌት ።
----------//-------------
ዘምንሊክ
ከሲድኒ፣ ዲሴምበር 6፣ 2013 እ.ኤ.አ.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ