ገለታው ዘለቀ
ኔልሰን ማንዴላ Nelson Mandelaመቼም ሰው ሥጋ ነኝና ታከተኝ

እረፍት ለጎኔ ናፈቀኝ

ሩጫዬን ግን ጨርሻለሁ

እምነቴንም ጠብቄያለሁ

እነሆ ከፊቴ ...

ከሰማዩ ከላይ አባቴ
የድል አክሊል ተዘጋጅቶልኛል

 

የሰላም የፍትህና የ'ኩልነት

ደግሞ የሕግ የበላይነት

ዋንጫዎች ይጠብቁኛል

እስትንፋሴ ሳይለይ ግን አንድ ነገር ልበል ...

 

አንቺ አፍሪካ ...

እትብቴ ስወለድ የተቀበረብሽ

ዘመኔን ሁሉ የሰጠሁሽ

እናት ዓለም አዳምጪኝማ

ኑዛዜ ቃሌን ጻፊልኝማ

አዳምጪኝማ ልንገርሽ

ምክር ተግሳጼን ልስጥሽ

ብዙህ ተፈጥሮሽን

ቀስተ ደመናነትሽን

ውበትሽ አርጊው ድሪሽ

ክብርና ልዕልናሽ

አትለይው ካንገትሽ ላይ

ዘመን ሲመጣ በዘመን ላይ

አንቺ ደቡባዊት አፍሪቃዬ

እትብቴ የተቀበረብሽ እመዬ

እንደገና አንድ ነገር ላስተንክርሽ

አዳምጪኝ እማ ሆይ እባክሽ

 

ያኔ በለቅሶ ዘርን ስትዘሪ

የነፃነትን፣ የፍትህን አባት ስትጣሪ

ጩኸትሽ ከጸባኦት ገብቶ

ቅን ፈራጁን አምላክ አትግቶ

የኢያሪኮን ግንብ አፈረሰው

የግዞት ቤቱን ደረመሰው

የብረት በሩን አባተው

እግረ ሙቁንም አቀለጠው

 

ትዝ ይለኛል ...

ስወጣ እስራቴ ተፈቶልኝ

ምናቤ ተከፍቶ እንዲህ አሳየኝ

አነሆ ፀሐይ ሕጉዋን ሰብራ

የተፈጥሮ ልማዱዋን ሽራ

በደቡብ በኩል ስትወጣ

የዘንባባ ዝንጣፊ አምጥታ

አየኋትና ደስ አለኝ

ተስፋና ሃሴት ወሰደኝ

ዓይኔ በርቶልኝ አሻግሬ ሳይ

ከፀሐይ መውጪያ ወዲያ ማዶ ላይ

ከኒያ ካሳለፍናቸው ክፉ ዘመናት በላይ

ክምር የመልካም ነዶ ዘመን ተቆልሎ ባይ

የአሁኑ ዘመን ስቃይ

ሊመጣ ካለው ክብር ጋር ሲተያይ

እንደ ኢምንት ሆኖ አየሁትና

የዘንባባ ዝንጣፊ አነሳሁኝ

ሰላምና ፍትህን አወጅኩኝ

በቀልና ዘረኝነትን ኮነንኩኝ

የኩልነትን እጀታ አጥብቄ አጥብቄ ያዝኩኝ

ያ ነበር በውነት ያስደሰተኝ

በርጅና ዘመኔ ሁሉ እንደ ንስር የሚያድሰኝ

 

አንቺ ደቡባዊት አፍሪካዬ

እትብቴ የተቀበረብሽ እናትዬ

ከምድርሽ ፍሬ በልቼ

ከሖድሽ ጠበል ጠጥቼ

አድጊያለሁኝና

ምስጋናዬ ይሄውና

ያ የክረምቱ ጊዜ አልፎ

ዶፍ ዝናሙ ደመናው ሁሉ ተገፎ

እሰይ እሰይ አጨዳሽን ጀምረሻል

የመኸር ጊዜ መጥቶልሻል

አጨዳሽን እጨጂ

በርቺ ሂጂ ተራመጂ

 

ግን ደሞ ...

አንድ ነገር አትርሺ

ያን ያፓርታይድ ዘረኝነት እንዲያ አንደጠላሽው

አንገፍግፎሽ አንዘፍዝፎሽ ወዲያ እንዳልሺው

እንደዚያው እንደጠላሽው ኑሪ

በፍቅር ባቡር ብረሪ

አንዳትመለሽበት አደረሽን

ከነፍስሽ ጥይው እባክሽን

በራስሽ ላይ አንደጠላሸው

በሌላውም ላይ አታድርጊው

 

እነሆ አግዚአብሔር በሰጠኝ አገልግሎት

የፍቅርና የሰላም ክህነት

ውጉዝ ውጉዝ ከመ አርዮስ

ውጉዝ ከአፍሪካ ብያለሁ ዘረኝነትን

አምባገነንነትና ኢፍታዊነትን

አትብቀሉ በምድሪቱ

አትለምልሙ አታኩርቱ

ባለም ሁሉ በምድሪቱ

ያለም ህዝቦች ሁላችሁ

የሰው ዘር ሁሉ የሆናችሁ

ከሰላምና ከእኩልነት ገበታ ብሉና ጠጥታችሁ ርኩ

ሰላም በሰላም ላይ ፍቅር በፍቅር ላይ ተኩ

 

የናቴ ያባቴ ልጅ አፍሪካ ...

አሁን ስጋዬ ረፍት ብጤ ናፈቀው

መቼም ሰው ነውና ስጋ ነውና ታከተው

ሄዶ ሄዶ ከዚህ አይቀርምና

የተፈጥሮ ህግ አይሻርምና

እኔ እንግዲህ ሄጃለሁ

ፍቅር ሰላም አኩልነት ላለም ሁሉ አመኛለሁ

አበቃሁ ቃሌ ይሄው ነው ኑዛዜየን አድርሻለሁ

ሃብቴ ቅርሴ ያለኝ ይሄው

ኑዛዜየ ስጦታዬ እምነቴ ነው


ገለታው ዘለቀ
This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.  

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ