ታላቁ የነፃነት አባት ኔልሰን ማንዴላ አረፉ (1918-2013)
የዓለማችን ታላቁ የፀረ-አፓርታይድ መሪ
Ethiopia Zare (ሐሙስ ሕዳር 26 ቀን 2006 ዓ.ም. Dec 5, 2013)፦ አፓርታይድን ከምድረ ደቡብ አፍሪካ እስከመጨረሻው ለመገርሰስ በተደረገው ታላቅ ተጋድሎ በዋንኛነት ተጠቃሽ የነበሩትና የሰላም አባት በመባል ዓለም አቀፋዊ ሽልማቶችን የተጎናጸፉት የደቡባዊት አፍሪካ የነፃነት አባት ኔልሰን ማንዴላ አረፉ።
የ95 ዓመቱ አዛውንት ለ27 ዓመታት በተጣሉበት እስር ቤት ውስጥ ባጋጠማቸው የሳምባ በሽታ ምክንያት ለዓመታት በሆስፒታል ሲመላለሱ እንደነበር የሚታወቅ ሲሆን፤ ባላፉት ጥቂት ወራቶች ብቻ በተደጋጋሚ ሆስፒታል ውስጥ በሐኪሞቻቸው ክትትል ይደረግባቸው እንደነበር ይታወሳል።
የመጀመሪያው የደቡብ አፍሪካ ጥቁር መሪ የሆኑትና የአፓርታይድ ባላንጣዎቻቸውን ምህረት በመስጠት ሀገራቸውንና ህዝባቸውን ከከፍተኛ እልቂት ያዳኑ መሆናቸው በታሪክ የሚታወስ ሲሆን፤ ሀገራቸው ለተያያዘችው የእድገት ጎዳና ጥርጊያ መንገድ ከፋች መሆናቸውም በታሪካቸው ይታወሳል።
ኔልሰን ማንዴላ ለሀገራቸው ነፃነት ከፍተኛ እገዛ ያበረከቱ አፍሪካዊ ሀገራት መካከል ኢትዮጵያን በመጻሕፍቶቻቸው በተደጋጋሚ በማንሳት የኩራታቸው ምንጭ መሆኗን አትተዋል።
ኔልሰን ማንዴላ ከስምንት አጋሮቻቸው ጋር የዕድሜ ልክ ውሳኔ በተጣለባቸው በጁን 12 ቀን 1964 ወቅት የሰጡት ቃል በግርድፉ እንዲህ ይነበባል።
"በህይወት ዘመኔ ለደቡብ አፍሪካ ህዝብ ነፃነት ትግል ራሴን ሰጥቻለሁ። የነጭን የበላይነት ስታገል ቆይቻለሁ። እንዲሁም ጥቁርም የበላይ ነው ብዬ አምኜ አላውቅም። የምታገለው በደቡብ አፍሪካ ዲሞክራሲና ነፃ የሆነ ማኅበረሰብ አለበትና እያንዳንዱ ግለሰብ በስምምነት የሚኖርበትና እኩል የሆኑ መብቶች የተመቻቹ እንዲሆኑ ነው። ይህን እሳቤ ነው እውን እንዲሆን የምመኘው። ለዚህ ዓላማ ስኬት እስከ መሞት ዝግጁ ነኝ።" ብለው ነበር።
ኔልሰን ማንዴላ የኢትዮጵያና የኢትዮጵያዊያን ወዳጅ መሆናቸውን በዓለም አቀፍ ደረጃ ተነባቢ በሆኑት መጻሕፍቶቻቸው የተረኩ መሆናቸው ይታወቃል። (ኢትዮጵያ እና ማንዴላ የሚለውን ቪድዮ ለመመልከት የማጫወቻ ቁልፉን ይጫኑ!)