”ደሸት” የብርሃን እውነት! (ወለላዬ)
ወለላዬ ከስዊድን
(ግጥሙን በፒዲኤፍ ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!፤ ወይንም በፎቶ መልክ የተቀናበረውን ለማንበብ እዚህ ይጫኑ!)
”ደሸት” የብርሃን እውነት!
የማጂ፣ የጂማ፣ የመንዲ፣ የመደባይ አባት
የማራ፣ የዥማ፣ የገንቲ፣ የአሬቲ ... አያት
የአማራው፣ የኦሮሞው፣ ... የዘር ግንድ አውራ
የመተሳሰሪያ እውነተኛ ምንጭ አሻራ!
”ደሸት” ኢፋ ዹጋ ፍጥረተ ማለዳ
የዘር ሀረግ ገመድ ምስጢራዊ ጓዳ
አባ ቃሉ
አባ ውሉ
አያ ፍቅሩ
ትስስሩ
ዘረ ሸጋ
ኢፋ ዹጋ
መሆንህን አምኖ አማራ ኦሮሞ
ስምህን በስሙ አትሞ
”ደ”ን ደግ ብሎ አንብቦ
”ሸ”ን ሸበበ ብሎት አንግቦ
”ት”ን ትስስር ይለዋል ውልደቱን ከትቦ
”ደሸት” የዘር ምንጩ
አባ እቅጩ
ስመ ክብሩ
ውስጠ ምስጢሩ
”ደሸት” የብርሃን እውነት! (ኢፋ ዹጋ!)
ዘሩን ሲያበዛ ሲዘረጋ
ማጂ፣ ጂማ፣ መንዲ፣ መደባይ
ብሎ ሰይሞ የዘር ሲሳይ
መደባይ ስሙን ከስሙ መዞ
ኦሮሞ ብሎ መጠሪያ ይዞ
በደሸት አያትነት ሲኮራ
የጂማ ልጅ ማራ
”አ - ማራ” ወይም ”ሃ - ማራ”
ብሎ ራሱን ጠራ
”ማራ” የሱባ ቃል ትርጉሙን
ማ - ማለት እውነት መሆኑን
ራ - ትርጉሙ ብርሃን መያዙን
አረጋግጦ ተቀብሏል
”ማራ” እውነትና ብርሃን ነው ብሏል
እንዲህ ነው የዘር ግንዱ
እንዲህ ነው አወራረዱ
እንግዲህ አማራን ከኦሮሞ፤ ኦሮሞን ከአማራ
በየትኛውም ቦታ በማንኛውም ስፍራ
ማንም አይችል ሊበታትን ሊለያየው
ደሸት የብርሃን እውነት (ኢፋ ዹጋ) ነው።
***********
ደሸት ”የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ” በተባለው መጽሐፍ ላይ የኢትዮጵያ ነገዶች አባት መሆኑ ተጽፏል።
ማስታወሻ:-
ለመጽሐፉ ደራሲ ለፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ
መታሰቢያ:-
ለደራሲው ጽሑፍ መነሻ ለሆኑት መሪራስ አማን በላይ