ሶምራን

ከ’ንግዲህ አልዘፍንም ዘፈኑም አስጠላኝ

ግጥምና ቅኝቱ ደስታ መቼ ሰጠኝ

ዘር እየለያየ ማዘመር ሲመጣ

ሕመሜ ስቃዬ ከቅኝቱ ወጣ

ኢሬቻን አክብሬ ስቄም አልገባሁ

ደመራን አከብሬ ስቄም አልገባሁ

አረፋን አክብሬ ስቄም አልገባሁ

ወንድሜ በወንድም ተረግጦ እያየሁ

ጥምቀት ሆኗል ብየ እስክስታም አልመታ

መንፈሴ ተጎድቷል አይችልም እልልታ

ተፈሰከ ብየ ጾም ጸሎቴ ሥግር

ባማኝን ታማኝ ሥራ ሳመሳክር

ደስታ አላገኘሁም ልቤ የለው ፍሰሀ

መሪር ነው ኀዘኔ ሁሌ የደስታ ድሀ

እንባዬ ሳይደርቅ ኀዘኔ ሳይሰክን

ጉድ ይበል ዓለሙ ደረበብኝ ኀዘን

ለድሀ የሚያለቅስ ዓይን እንባ ቢኖርም

ኀዘኑን የሚከፍል ትልቅ ሰው አልኖርም

ቢኖርም መልካም ሰው ያለውን የሚቸር

ሰው ከሰው ሲከጅል በጣም ነው የሚመር

የቆሼ ወንድሞቼ ውርደቴን አይሹ

ትቢያ አፈር ለበስኩ ሳይቻለኝ መሸሹ

ኢድና ፋሲካው ቀን ቆጥሮ ቢመጣ

ሰው ኀዘን ላይ እንጂ መች ደስታ ላይ ወጣ

ዘር በዘር ተማታ አስታራቂ አሹፎ

ያስታራቂ ጠላት አንዱ ባንዱ ጠልፎ

ወይ ምሥራቅ አፍሪካ አወይ ያፍሪካ ቀንድ

ማን ይደሰት ይሆን መሬቱ ሲቀደድ

አይጠቀም በመርፌ አይሰፋ በክር

ቀዳጁ ከላይ ነው ጠቃሚው ከሥር

እንግዲህ ለዘፈን ወኔ ከየት ይምጣ

እንግዲህ ለስክስታ ወኔ ከየት ይምጣ

እንግዲህ ለልልታ ወኔ ከየት ይምጣ

ልብ የሚፈልገው ቅኝቱ ከታጣ

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!