እኔም አለኝ ሕልም

ከወለላዬ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )

(በፒ.ዲ.ኤፍ. አስነብበኝ) 

ሿሚና ሻሪ እያለ እግዚአብሔር፤

ማለት ከንቱ ነው ነጭና ጥቁር።

ትልቅ ነው ትንሽ ማለትም አይበጅ፤

ለሚወሰነው ሁሉ በሱ እጅ።

 

ይህን እንተው ለባለቤቱ፤

ምን ያገባናል በገዛ ሀብቱ።

ትልቁን ሀገር ኃያል ከተማ፤

ተቆጣጠረው ይሄው ኦባማ።

ማርቲን ሉተር ኪንግ ሕልምህ ደረሰ፤

አሜሪካን ላይ ጥቁር ነገሠ።

ኃይሌ በሩጫ ሲያሸንፍ ከርሞ፤

ታይሰን በቡጢ ሲያሸንፍ ከርሞ፤

ሁሉን በለጠ ኦባማ ደግሞ።

 

ድናለች በቃ ዓለም ከጥፋት፤

እያሳየ ነው እግዜር ታምራት።

ከንግዲህ በእውነት ፍርድ ይበየናል፤

ሀገር ከስቃይ ከራብ ይድናል።

ከንግዲህ አይኖርም ገደላ - አፈና፤

ሠላም ይወርዳል፣ ይገኛል ጤና።

ከንግዲህ አይኖርም ሀገር ወረራ፤

በየትም ቦታ በየትም ሥፍራ።

ሀገራችንም ሠላም ተገኝቶ፤

ህዝብ የመረጠው ሥልጣን ላይ ወጥቶ፤

ሕመምተኛዋን ኢትዮጵያን ሲያክም፤

አይቻለሁኝ እኔም አለኝ ሕልም።

 

የክፉ ሰዎች ጠንካራ መዳፍ፤

አይቻለሁኝ ደክሞ ሲታጠፍ።

አይቻለሁኝ ከንቱ ክብራቸው፤

የሰበሰቡት የግፍ ሀብታቸው

ምንም ላይጠቅም ምንም ላይረባ፤

ንፋስ ሲያቦነው እንደገለባ።

ከተዘጋበት የእስር ኑሮ፤

ህዝብ ሲወጣ በራፉን ሰብሮ

ነፃነትና ክብሩን ሲጠብቅ፤

ባገሩ ሲኖር ሳይሸማቀቅ።

አይቻለሁኝ ሕልሜ ነግሮኛል፤

አያድርም ውሎ ግልጽ ታይቶኛል።

 

የተሰደደው በፍትህ እጦት፤

የተሰደደው ነፃነት ጠምቶት፤

የተሰደደው ራብ ገሽልጦት፤

ሀገሩ ገብቶ የሚኖርበት።

ጊዜው መድረሱን አይቻለሁኝ፤

ለዚህ ምስክር እኔ እራሴ ነኝ።

 

ብዙም አይቆይም ይደርሳል ሕልሜ፤

በነፃነት ቀን ከሰው ጋር ቆሜ።

ደስታ ፈንቅሎን አብረን ስናለቅስ፤

አይቻለሁኝ እንባችን ሲፈስ።

የመጨረሻው የዛን ቀን ለቅሶ፤

ግፍን ግፈኛን ይዞ አግበስብሶ

ገደል ሲከተው እስከዘላለም፤

ፍቅር አንድነት ሲመጣ ሠላም፤

አይቻለሁኝ እኔም አለኝ ሕልም።


 

ከወለላዬ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )

ጥቅምት 28 ቀን 2001 ዓ.ም. (November 7, 2008)

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!