የአደራ ድምፅ (ከትንሣዔ)
የአደራ ድምፅ
ከትንሣዔ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )
የአያት የቅድመ አያት፣ ... የዘመድ አዝማድ የቃል ውል፣
የልጅ፣ የልጅ ልጆች ራዕይ፣ ... የነገም የተስፋ ደወል፤
«ተነሱ ደም መላሾቼ!!» እያለ፣ ... በጆሮአቸው ሲያቃጭል።
መቆምያ መቀመጫ ቢነሳ፣ ... የአዛውንት የሕፃናቱ እንባ፣
የነፃነት ጥሪ አዋጅ፣ ... ከአድማስ አድማስ ሲያስተጋባ፣
የተዘጋ አንደበትህን ከፍተው፣ ... ብሶትህን ለዓለም ሊያሰሙ፣
እነሆ የአደራ ድምፅህን ይዘው፣ ... ካራቱም ማዕዘናት ተመሙ።
«ስደት ከጎንህ ላይነጥለን፣ ... ጩኸትህን ልንጮህ ተነሳን»፣
እያሉ የምሥራች ይዘው፣ ... ለአንተ ደስታ ለወያኔ መርዶን፤
የእስር ሰንሰለት በጥሰው፣ ... የስደት አጥሩን አፍርሰው፣
ከድርጅት ከፓርቲ በላይ፣ ... የሀገር ፍቅርን ተላብሰው።
የሃሳብ የልብህ እንዲወጣ፣ ... አድምጠን እነሆ ይላሉ፣
ያንተም ድምፅህ ይሰማ፣ ... ይወቁት ወሽካቶቹ ሁሉ።
በሳይበር ቅመም ተደልዛ፣ ... በድንበር አልባ ፍቅር ተቀምማ፣
ከተበተንበት የዓለም ዙሪያ፣ ... የአደራ ድምፅህን ልናሰማ።
ይኸው እጅ ለእጅ ተያይዘን፣ ... በቅጥል ስማችን ተቆለማምጠን፣
በሕብረ ህዝብነታችን ተማምነን፣ ... በኢትዮጵያዊነት አንድ ሆነን።
የእውነት ቃልህ ነጎድጓድ፣ ... የጠላትክን መንደር የሚያናውጥ፣
ህዝብ ማፈን «ጉም መዝገን» ... መሆኑን ተናግረው በቁርጥ።
«የአደራ ድምፅ» ብለው፣ ... እንዲሆን ለቃል ውልህ ማሰሪያ፣
ከጎጆ ከመንደርህ የሚደርስ፣ ... ከፈቱልህ ራድዮ ጣብያ።
እሰየው በል ተመስገን፣ ... ልጆችህ ሀሞተ ኩሩ፣
አጋር ወገንነታቸው፣ ... ሙያቸው ነውና ምስክሩ።
የእውነት መንገድ ለያዙ ልጆችህ፣ ... ስጣቸውማ ጆሮ።
የመከራ ጊዜ እንዲያጥር፣ ... መገፋታችን እንዲያበቃ፣
አንድ ሆነን እንነሳ፣ ... ለድል ለነፃነትም እንብቃ።
የኢትዮጵያ ከረንት አፌየርስ መሪዎች፣ ዕድምተኞችና ድጋፍ ሰጪዎች ይህን ታላቅ ስጦታ ለኢትዮጵያ ህዝብ በማበርከታችሁ እንኳን ደስ ያላችሁ! ይህ የጽናት ውጤት የሆነ አበረታታች ሥራ ይበልጥ ይጠናከር ዘንድ ሁሉም ኢትዮጵያዊ የድርሻውን እንዲያበረክት ጥሪ አቀርባለሁ።
እግዚአብሔር ኢትዮጵያን ይባርክ! - አሜን!!!
ከትንሣዔ (This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. )
ኅዳር 2000



