ከአዲሱ የኢትዮጵያ መንግሥት የመጀመሪያው ሥራ ለኑሮ ውድነት መፍትሔ መስጠት መኾን አለበት

ሸገር ዳቦ
በተለይ በተለይ የግብይት ሥርዓቱ እንዲስተካከል ማድረግ፣ በእከክልኝ ልከክልህ ባለሥልጣናት ከአንዳንድ ነጋዴዎች ጋር በመመሳጠር የሚፈጥሩትን ያልተገባ ተግባር መቁረጥ እና ገበያውን መቆጣጠር ያስፈልጋል
ኢትዮጵያ ዛሬ (ርዕሰ አንቀጽ) - ኢትዮጵያ በብርቱ ፈተናዎች ውስጥ አልፋለች፤ በታሪኳ ገጠሟት ተብሎ ሊጠቀሱ ከሚችሉ ከባድ ፈተናዎች ውስጥ ያሳለፍናቸው ጥቂት ዓመታት ተጠቃሽ ናቸው።
ታሪካዊ ጠላቶቻችን ከሌላው ጊዜ በተለየ እየፈተኑንና እያስፈተኑን ነው። ባልተገራ የፖለቲካ አመለካከትና ዘረኝነት በወለደው እብደት በአገር ውስጥ የታየው ትርምስ የዚህችን አገር ሕልውና በእጅጉ የተፈታተነበትም ወቅት ነው።
ብርቱ ልፋትን የሚጠይቁ ችግሮች አሉ። አገሪቱ ከፈተና አልወጣችም። በዚህ የተመሰቃቀለው ፖለቲካ ስንክሳር የዜጐች ደም ፈሷል። ለሌሎች የምትተርፍ አገር የራስዋ ልጆች በሚፈጥሩት ሳንካ ዜጐቿን አጥግባ ለማኖር ብዙ እንቅፋቶች እየገጠሟትም ነው። የፖለቲካ ልሂቃን በሚፈጥሩት ውዥንብር ፖለቲካችን ጐምዛዛ ኾኖ የዚህችን አገር አበሳ አብዝቶ ይህንን ለማንፃት ብዙ ዋጋ እየተከፈለ ነው።
በተለይ ዘር ተኮር ፖለቲካው ትልቋን አገር አኮስሷታል። ከዚህ አደገኛ ሁኔታ ለመውጣት እየተደረጉ ያሉ ርብርቦችም አሁንም ገና ብዙ ልፋት የሚጠይቁ ናቸው።የተረጋጋችና ሰላማዊ አገር ለመፍጠር እንዲሁም ኢኮኖሚውን ወደፊት ለማስፈንጠር ከገባንበት አዙሪት መውጣት ግድ ይለናል። ይህንን ለማድረግ ደግሞ የአገራችን ሰላምና ደኅንነት መጠበቅ አለበት። በረባው ባልረባው የሚፈሰውን የዜጐች ደም ማስከበር ቀዳሚ ተግባር ማድረግ ያሻል። ለዚህም የተረጋጋና ሕዝብ የመረጠው መንግሥት ያሻል። ከአገርና ከሕዝብ ይልቅ የግል ፍላጐታቸውን ለማራመድ የሚሹ አካላትን በቃችሁ በማለት ለነገው ትውልድ መልካም ነገር ማውረስ የሚችል ጠንካራ መንግሥት ያስፈልገናል። ይህ ግን በምኞት አይመጣም በጋራ መቆምን መተሳሰብና መተባበርን ይጠይቃል።
ኢትዮጵያውያን ከዚህች ኢትዮጵያ ከምንላት አገር ውጭ ሌላ አገር የለንምና አገሬ ብለን ካልሠራንባት፣ ተቻችለን ካልኖርባት፣ ያላትን ሀብት በአግባቡ ጥቅም ላይ እንዲውል ካላደረግን፤ ነገም የሚጠብቀን ፍዳ ነው። ከፖለቲካው ባሻገር ወደ ነገ ለመራመድ ጠንካራ ኢኮኖሚ ሊኖረን ይገባል።
ለዘመናት ሲንከባለል የመጣውን የአገራችንን ችግር ለመቅረፍ ዛሬም ካለንበት ፍዳ ለመላቀቅ ያለንን አቅም ተጠቅመን ቢያንስ ለዜጐች የሥራ እድል ፈጥሮ፤ ጠግቦ የሚያድረውን ለማብዛት ደግሞ የተረጋጋች አገርና የዴሞክራሲያዊ ሥርዓት ግንባታ ትልቅ ቦታ አለው።
በዚህ ረገድ የተዋጣላት አገረ መንግሥት ለመገንባት እጅግ ብዙ የሚቀረን ቢኾንም፤ ወደዚያ ለመጓዝ ግን የዛሬ እርምጃችን ወሳኝ ነው።
ከዚህ አንጻር እንደ አገር አሁን ላይ አንድ እድል ተገኝቷል ማለት ይቻላል። አገራችን በአሁኑ ወቅት ካለችበት አዙሪት ለመላቀቅ እንደ አንድ እድልና ጅማሮ የምንወስደው ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ የዛሬ ሳምንት ሰኞ ሰኔ 14 ቀን 2013 ዓ.ም. የተደረገው አገራዊ ምርጫ ነው።
እስከ ችግሮቹም ቢኾን ይህ ምርጫ በተሻለ ሁኔታ ዝግጅት ተደርጐበትና ሒደቱም የጐላ ችግር ሳይታይበት ተከናውኗል። ስለዚህ ይህ ምርጫ በተሻለ ሁኔታ መከናወኑ ወይም እንዲከናወን በሁሉም ወገን የተደረገው ርብርብ የሚያሳየን፤ እንደአገር ብዙዎቹን ችግሮቻችን ለመፍታት እንችላለን በሚል ጭምር ነው። ባለፉት ሦስት ዓመታት ያየናቸውን ለጆሮ የሚከብዱ አሰቃቂ ድርጊቶችን ሳይቀር መፍትሔ ሊያበጅ እንደሚችል ተስፋ በማድረግ ጭምር ነው። በምርጫ ሒደቱ እንዳየነው ሕዝብ በሰላማዊ መንገድ ድምፅ ሰጥቷል። በምርጫው የተሳተፉ የፖለቲካ ፓርቲዎች እስከ ዛሬ በአገሪቱ ታሪክ ባልታየ ሁኔታ ሰከን ብለው ምርጫው በአግባቡ እንዲካሔድ የበኩላቸውን አድርገዋል። ምርጫው ተዓማኒነት እንዲኖረው በአዲስ መልክ የተደራጀው የኢትዮጵያ ምርጫ ቦርድም አዳዲስ ታሪኮች አጽፏል። ስለዚህ እስከዛሬ ከተካሔዱት ምርጫዎች የተሻለ ምርጫ የተካሔደበት የዘንድሮ ምርጫ አሸናፊ ግን ከፊት ለፊቱ የሚጠብቀው ሥራ እንዲህ ቀላል አይኾንም።
አሁን የሚታዩ ፖለቲካዊ ምስቅልቅሎችን ከማስተካከል፤ ብሎም አገር እንደ አገር እንድትቀጥል እስከ ዛሬው ጉዞዋችን በተለየ መሥራትን ይጠይቀዋል። አዲሱ መንግሥት ኃላፊነቱን ከተረከበበት ከመጀመሪያው ቀን ጀምሮ በብርቱ ሊሠራበት ከሚገባቸው ጉዳዮች መካከል አንዱ ደግሞ በአሁኑ ወቅት እጅግ አንገብጋቢ የኾነውን የኑሮ ውድነት መላ እንዲኖረው ማድረግ ነው። ዛሬ የዋጋ ንረቱ 20 በመቶ ደርሷል። ይህ በኢትዮጵያ ታሪክ ያልታየ ነው። ከምሥራቅ አፍሪካ አገሮች አንጻር ሲታይ፤ የኢትዮጵያ የዋጋ ንረት አስደንጋጭ ነው። አብዛኛዎቹ የአካባቢው አገሮች የዋጋ ንረት ከአምስት በመቶ በታች ነው። ይህ ሲታይ በኢትዮጵያ በዚህ ጉዳይ ላይ በርትቶ መሥራት ቀዳሚ ተግባር መኾኑ ግድ ነው።
በዚህ ምርጫ ማንም ይመረጥ ማንም አዲስ የሚመሠረተው መንግሥት በጠረጴዛው ላይ ማስቀመጥ ያለበት የመጀመሪያው አጀንዳ ይህንን የኑሮ ውድነት ለማቃለል የሚያስችል ፖሊሲ ቀርፆ መተግበር ነው። ዛሬ በኢትዮጵያ በየትኛውም ክፍል ያለው የኑሮ ውድነት ሕዝብን እያማረረ ነው። በፍጥነት እያደገ ላለው የዋጋ ንረት ምክንያቱ ብዙ ቢኾንም፤ ይህንን ሥር እየሰደደና ዜጐችን እየፈተነ ያለ ጉዳይ በብልሃት መፍትሔ መስጠት የአዲሱ መንግሥት ቀዳሚ ተግባር መኾን አለበት የምንለውም ያለምክንያት አይደለም።
ነገ ከነገ ወዲያ መንግሥትን ሊፈታተን የሚችል ጭምር በመኾኑ ነው። በዘንድሮው ምርጫ ሕዝብ ድምፅ የሰጠው ይህንን መሠረታዊ ችግር የኾነውን የኑሮ ውድነትና ቅጥ ያጣውን የገበያ ሥርዓት ያስተካክልልኛል ብሎ በማመኑ ጭምር እንደኾነ መታወቅ አለበት። በተለይ መሠረታዊ የሚባሉ ምርቶች ላይ ያለውን ችግር ቅድሚያ ሰጥቶ መፍታት ያስፈልጋል። ለምሳሌ በተከታታይ የተመረቁ የዘይት ማምረቻዎች ወደ ሥራ መግባታቸው በትክክል ምን አስገኙልን? ብሎ መጠየቅ ያስፈልጋል። በአደባባይ በፌሽታና በድምቀት የተመረቁት እነዚህ የዘይት ማምረቻዎች ሥራ በጀመሩበት ወቅት ግን የዘይት ዋጋ በእጅጉ ተሰቅሎ የሚሸጥበት ነገር ግራ ያጋባል። ፋብሪካዎቹ አንድ ሌትር ዘይት ከ40 ብር ያነሰ አመረትን እያሉ፤ ሸማች 100 እና 125 ብር የሚገዛበት ምክንያቱ ምንድነው? ስለዚህ የገበያ ሥርዓቱ ይስተካከል ሲባል እንዲህ ያሉ ጉዳዮችን መፈተሽና መፍትሔ መስጠት ይጠይቃል። ይህ አንድ ምሳሌ ብቻ ነው በሌሎች ምርቶች ላይም በተመሳሳይ የሚታዩ አገሮች አሉ።
በአዲስ አበባ የሸገር ዳቦ ፋብሪካን በአጭር ግዜ ውስጥ ግንባታውን በመጨረስ ወደ አምራችነት ከተቀየረ በኋላ፤ በከተማው ውስጥ በተለያዩ አካባቢዎች የሸገር ዳቦ መሸጫ ሱቆች ለወጣቶች ተሰጥተው ዳቦ ለከተማው ሕዝብ ማቅረብ ጀምሮ ነበር። በአሁኑ ወቅት ግን እነዚህ ሱቆች ዳቦ ከማቅረብ ይልቅ ሻይ፣ ቡና እና ወኃ መሸጫ ኾነዋል። “ዳቦውስ?” ተብሎ ሲጠየቅ ምላሹ “ስንዴ የለም” የሚል ነው። ፋብሪካው የተገነባው በአስተማማኝ ሁኔታ የስንዴ አቅርቦቱን ሳያስተካክል ነውን? ፋብሪካው ሲቋቋም ዋንኛ ግብዓተ ምርቱ ስንዴ መኾኑ እየታወቀ እንዴት “እጥረት ስላለ ነው” ተብሎ ይባላል? መንግሥትም ኾነ የፋብሪካው ባለቤቶች ዓላማቸው የሕዝብን የዳቦ ችግር ማቅለል ከኾነና ለጊዜያዊ የፖለቲካ ጥቅም ካልኾነ፤ “የእናቴ መቀነት አሰናከለኝ”ን ምን አመጣው?
የአገሪቱ ገበያ ቅጥ አጥቷል። ኾን ተብሎና ታቅዶ በሚተወን ደባ የሚፈጠረው የኑሮ ውድነትም ብዙ ችግር ፈጥሯል። ገበያን ለማረጋጋት ተሠሩ የተባሉ ሥራዎችም ለውጥ ሲያመጡ አልታየምና ይህ የአገር በሽታ የኾነውን የዋጋ ንረት መንሥኤዎቹን ከሥር መሠረቱ በመፈተሽ ትክክለኛ መፍትሔ መስጠት አዲሱ መንግሥት የሚፈተንበት ቀዳሚ ተግባሩ መኾን አለበት። በተለይ በተለይ የግብይት ሥርዓቱ እንዲስተካከል ማድረግ፣ በእከክልኝ ልከክልህ ባለሥልጣናት ከአንዳንድ ነጋዴዎች ጋር በመመሳጠር የሚፈጥሩትን ያልተገባ ተግባር መቁረጥ እና ገበያውን መቆጣጠር ያስፈልጋል። ለዋጋ ንረት ዘላቂው መፍትሔ ግን ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ ነው። ለዚህ ደግሞ የሚያሠራ ፖሊሲ ያሻናል። ይህንን የሚያስፈጽም ጠንካራ መንግሥትም ያስፈልገናል። (ኢዛ)