ተሻገር በላይ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

"... ሕገወጦችን ከምርጫ በኋላ እንከሳለን ..." የሚለው ንግግር የህዝባዊ ወያኔ ሓርነት ትግራይ ሊቀመንበር፣ የኢህአዲግ ሊቀመንበር፣ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስቴር እና የጦር ኃይሎች ጠቅላይ አዛዥ የሆኑት አቶ መለስ ዜናዊ ሰሞኑን ከተናገሩት ውስጥ የተወሰደ ነው። ይህ አባባላቸው አዲስ ሆኖብኝ ሳይሆን ከምርጫ ሂደት ጋር ሲታይ አግባብ የሌለው መሆኑን ወዳጆቻቸውና ደጋፊዎቻቸው ማየት ቢችሉ ብዬ ነው።

 

(ማስታወሻ አቶ መለስ ዜናዊን ክቡር ጠቅላይ ሚኒስቴሩ እያልኩ የጻፍኩበት ምክንያት ለእርሳቸው ባለኝ ክብር ሳይሆን ለቦታው በምሰጠው ከበሬታ የተነሳ ነው። በታሪክ አጋጣሚ የምንወዳት ታላቅ ሀገር መሪ ሆነዋልና አንቱ ልላቸው ወስኛለሁ። ይህንን ስል የሚሠሩት ሥራና ሀገራቸውን ለሚወዱ ኢትዮጵያውያን ያላቸውን ጥላቻ ባለማወቅና ያ ሥራቸውም ከኢትዮጵያውያኑ ጥላቻ እንዳተረፉ በመርሳት አለመሆኑን አንባቢ እንዲረዳልኝ እፈልጋለሁ። አንዳንዴ ሰው “አንቱ” እየተባለ ይሰደብ የለ!)

 

ይህ ከላይ የተጠቀሰው "የክቡር" ጠቅላይ ሚኒስትሩ አባባል ከምርጫ በፊት የተነገረ በመሆኑ የምርጫውን ውጤት በቅድሚያ ያሳያል። አባባላቸው ፓርቲያቸው የ2002 ምርጫን ተከትሎ ኢትዮጵያን የመምራት ኃላፊነትን እንደሚረከብ በቅድሚያ ያረጋገጠ ነው። የምርጫን ትክክለኛ አካሄድ የተቀበሉ ቢሆን ኑሮ ይህን ለማለት አይደፍሩም ወይም ደግሞ አባባላቸውን ያስተካክሉ ነበር። ጠቅላይ ሚኒስትሩ በሥልጣን እንደሚቆዩና ለዚህም የታያቸውን ሁሉ ማድረግ እንደሚፈልጉና እንደሚችሉ ነው የሚገልጹልን።

 

አቶ መለስ ይህን መሰል ንግግር በየጊዜው ይናገራሉ። ሁላችንም እንደምናስታውሰው ከምርጫ 97 በፊት የኢህአዲግ ደጋፊዎች በአዲስ አበባ ባካሄዱት የድጋፍ ሰልፍ ላይ ኢህአዲግ ያን ያክል ደጋፊ እያለው ምርጫ ማጭበርበር እንደማያስፈልገው ገልጸው ነበር። አነጋገራቸውም ያሰቡትን በግልጽ ያወጣ ነበር። አቶ መለስ በምርጫ 97 የተፈጠረውን ያውቁታልና "ውጤቱ እንዴት ነበር?" ለሚለው ጥያቄ ራሳቸው ለራሳቸው መልስ እንዲሰጡበት አሳስባቸዋለሁ። ታዲያ አሁንም ማሸነፍን ወስነው ወደ ምርጫ መሄድ ምን ምርጫ ያስብለዋል?

 

ከዚህ ጋር የሚሄድ አንድ ገጠመኝ ላንሳ። ሁለት ወጣት ባልና ሚስቶች አንድ ወንድ ልጅ ወለዱና ስሙን ማን እንበለው የሚል ጥያቄ ተነሳ። በአባት፣ በእናት እና በሌሎች በጠቅላላው ሦስት አማራጮች ቀረቡ። እናት ያቀረበችው ስም እንዲሆን ከገፋፋች በኋላ ዕጣ እንዲወጣ ሃሳብ ቀረበ። የዕጣውንም ሃሳብ እናት ከተቀበለች በኋላ “ዕጣው መውጣቱን ይውጣ፤ ስሙ ግን ምንም ይሁን? ምን እኔ ያወጣሁት ነው የሚሆነው” ስትል ተናግራ ዕጣው ወጣ። ዕጣውም ሲወጣ በአጋጣሚ እናት የሰጠችው አማራጭ ስም ዕጣ ደረሰው። ዕጣውም ሲወጣ የልጁ አባት ከሁሉም በላይ ደስ አለው። ደስ የተሰኘበትም ምክንያት ሌላ ቢወጣ ሚስቱ ያለችውን በማሰብና ሊነሳ የሚችለውን አለመግባባት በመፍራት ነበር።

 

አሁንም ኢህአዲግ ከምርጫ በኋላ የሚወስደውን እርምጃ እየተናገረ ከዛተ ተወደደም ተጠላም፣ ካርድ ተጭበረበረም አልተጭበረበረም "መመረጤ" አይቀርምና እርምጃችሁን አስቡ እያለ ነው። መቸም አቶ መለስ የሚናገሩትና የሚሠሩት የተለያዬ መሆኑን ብዙ ሰው ያውቃል። ደጋፊዎችቸውም ከመፍራታቸው በስተቀር ይህን ከማንም የበለጠ ያውቃሉ ብዬ አስባለሁ። አሁን ግን ብዙ ነገር “አደርጋለሁ ምን ልታመጡ ነው?” የሚሉ ይመስላሉ። ሰሞኑን የአሜሪካን ሬዲዮ የአማርኛ አገልግሎት ታሰናክላላችሁ (Jam ታደርጋላችሁ) ተብለው ሲጠየቁ የተሟላ አቅም እንደሌላቸው ጠቁመው፤ ሙከራ እያደረጉ መሆናቸውን ገልጸዋል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ አምባገነንነትን በግልጽ የተቀበሉ ይመስላሉ። አቶ መለስ የማንነት ብዥታው የጠፋላቸው ይመስላል። እንኳን ለዚህ አበቃዎት! አምባገነንነትዎን የሚመሩት ህዝብና ደጋፊዎችዎ ካወቁ የቆዩ ቢሆንም እርስዎ አምባገነንነትዎን አውቀው በግልጽ ሲነገሩ አይቼ “እንኳን ለዚህ አበቃዎት!” ሳልል አላልፍም። የታመቀ ጉልበት ሲፈነዳ ሕያው መሆኑ ይቀራልና የአገዛዝዎትን ዕድሜ ማለቁን ለመግለጽ ብዙ ትንታኔ አያስፈልግም።

 

ምርጫ 2002ን በተመለከተ ባለፈው ሰሞን አቶ ስየ አብርሃ አሉ የተባለውን ነገር በዚህ አጋጣሚ ማንሳት እፈልጋለሁ። አቶ ስየ እርሳቸው ካልተመረጡ ምርጫው ለመጭበርበሩ ማረጋገጫ ነው ያሉት ተገቢ አይመስለኝም። አንድ ነገር ሂደቱ እንጂ ውጤት ዲሞክራሲያዊነትን የሚያሳይ አይመስለኝም። ተወዳዳሪዎችም ሂደቱ ትክክል አይደለም ብለው ካሰቡ ላለመሳተፍ ከዚሁ መወሰን እንጂ ውጤቱን አይቼ እወስናለሁ ብሎ ነገር የለም። ትግላችሁ ሂደትን ለማስተካከል መሆን አለበት ብዬ አስባለሁ።


ተሻገር በላይ

This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ