ግርማ ካሣ

ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በቃሊቲ እሥር ቤት እያለች መራራ ስቃይ እንደደረሰባት ሳትደብቅ ደጋግማ ገልጻለች። የቀድሞ የአዲስ ነገር ጋዜጠኛ፣ አብይ ተክለማሪያም፣ የናዚ ጀርመንን ታሪክ በማስታወስ “Verschärfte Vernehmung” (silent Torture) በማለት ለማስረዳት እንደሞከረው፣ አሰቃቂ የስነ ልቦና ቶርቸር እንደተፈጸመባት የሚያከራክርና የሚያወዛግብ አደለም።1

 

የወ/ት ብርቱካን አፈታት ሁኔታን በተመለከተ ደግም፣ በሕግ ፣ በሞራልና በፖለቲካ አንጻር ተቀባይነት እንደሌለው፣ የአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ የፍልስፍና መምህረ የሆኑት ዶር ዳኛቸው አሰፋ፣ ታሪክ እና ሕግን በማጣቀስ ለአዲስ አድማስ ጋዜጠኛ ጽዮን ግርማ በሰጡት አስተያየት ግሩም በሆነ መልኩ በሚገባ አስረድተዋል።2

 

ስለዚህ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በቃሊቲ እሥር ቤት ባሳለፈችው የመከራና የሰቆቃ ኑሮ እና የአፈታቷን ሁኔታ በተመለከተ ብዙም የምለው አይኖረኝም። (የአብይ ተክለማሪያምን እና የጽዮን ግርማን ጽሑፍ ማንበቡ የሚበቃ ይመስለኛል)

 

የዛሬው ጽሑፌ ዓላማ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ምን ማድረግ እንዳለባት የሚገልጽ አንዳንድ የሚሰጡ አላስፈላጊ አስተያየቶች ላይ ጠቃሚ የምላቸውን ትችቶን ለማቅረብ ነው።

 

በቅርቡ አቶ ይልማ በቀለ ያቀረቡልን አንድ ጽሑፍ አለ። ጽሑፉ በአብዛኛው እውነትን የሚያንጸባርቅና ጠቃሚ የሆነ ጽሑፍ አድርጌ ነው የምወስደው። ነገር ግን ማጠቃለያቸው ላይ ትንሽ የማልስማማባቸው ነጥቦችን አንስተዋል። አቶ ይልማ በቀለ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ እረፍት እንደሚያስፈልጋት፣ የአዕምሮ ጤንነቷ ጥሩ ላይሆን እንደሚችል ገልጸው፤ “ከእርሷ ምንም ነገር አሁን መፈለግ የለብንም፤ ነገር ግን በራሷ ጊዜና በራሷ መንገድ ሁሉን እንድትመረምር ጊዜ ልንሰጣት ይገባል” ይላሉ። የተጠቀሙት እንግሊዘኛ ልጠቀምና “She is in a fragile state of mind” ነበር ያሉት።3

 

እዚህ ላይ አቶ ይልማ እውነታቸው ሊሆን ይችላል። ብዙ ሰው ስለሚደውል፣ ተጨማሪ መጨናነቅ አልፈጥርም በሚል፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳን ደውዬ ገና አላነጋገርኳትም። ነገር ግን ለተለያዩ ጋዜጠኞች የሰጠችውን ቃለ መጥይቆችን አዳምጫለሁ፤ አንብቤያለሁም። (ከአውራምባ ታይምስ ጋር ወ/ት ብርቱካን ያደረጉትን ቃለ ምልልስ አይነት ማየት ይቻላል)

 

ከዚህም በተጨማሪ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ለህዝብ የጻፈችው ግልጽ ደብዳቤ አለ። በደብዳቤዋ ትንሽ እረፍት እንደምትወስድ አሳወቃለች። “ላለፉት ሃያ አንድ ወራት ከመላው ዓለም ተለይቼ በእሥር የቆየሁ እንደ መሆኔ መጠን፣ የሀገራችንን የፖለቲካ ሁኔታም ሆነ የፓርቲዬን እንቅስቃሴ የሚገኝበትን ደረጃ ለማጤን እና ከዚህ በኋላ የእኔ አስተዋጽዖ ምን ሊሆን እንደሚገባ ለመመልከት የራሴን ጊዜ ለመውሰድ የወሰንኹ መሆኑን በአክብሮት አስታውቃለኹ” ስትል ነበር ደብዳቤዋን የቋጨችው።

 

የራሴን ጊዜ መውሰድ አለብኝ ያለችው ሕክምና ያስፈልገኛል ብላ አይደለም። እስከ አሁን እንደሰማናትና በአገር ቤት ያይዋት ወገኖች እንደተናገሩት ከሆነ፣ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ፣ ምስጋና ለእግዚአብሔር ይድረሰውና፣ በጣም ጥሩ ጤንነት ላይ ነው የምትገኘው። ወ/ሮ ላቀች ደገፋ፣ የአንድነት ፓርቲ አመራር አባልና የሴቶች ጉዳይ ኃላፊ ሲናገሩ “ልክ ከመታሰሯ በፊት የነበረችዋን ብርቱካንን ነው ያገኘኋት” ነበር ያሉት ብርቱካን ለመጀመሪያ ጊዜ ካገኟት በኋላ በሰጡት አስተያየት።

 

ወ/ት ብርቱካን ጊዜ መውሰድ አለብኝ ያለችው በሀገራችን ያለውን የፖለቲካ ሁኔታ ለማጤን፣ የአንድነት ፓርቲ ምን ደረጃ ላይ እንዳለ ለመመርመር ከእናቷና ከልጇ ጋር ለማሳለፍ ስትል ነው። ሌላ ታሪክ፤ ሌላ ምርምር በሌሎቻችን ዘንድ ብዙ የሚያስፈልግ አይመስለኝም።

 

ደጋፊዎች ለወ/ት ብርቱካን ጊዜ እንዲሰጧት አቶ ይልማ ያሳሰቡና ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ለሕክምና ወደ ውጭ ሀገር እንድትወጣ ሲመክሩ “ከሁሉም የሚበጀው መድኃኒት፣ ለርሷ ወደ ውጭ ሀገር ወጥታ የፕሮፌሽናል እርዳታ ብታገኝ ነው” ነበር ያሉት።

 

እርግጥ ነው ሕክምና ወ/ት ብርቱካን ካስፈለጋት በውጭ ሀገር የተሻለ ሕክምና ይኖራል። ነገር ግን አሁንም ከፈረሱ በፊት ጋሪውን ማስቀደም የለብንም። ወ/ት ብርቱካን ታምሜያለሁ ሳትል ሕክምና ያስፈልግሻል ማለት ስህተት ይመስለኛል። ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የሚበጃትን እርሷ ናት የምታወቀው። ሕክምና ያስፈልጋት አያስፈልጋት፣ ሕክምና ካስፈለጋት ደግሞ ሀገር ውስጥ መታከም ትፈልግ ወይንም ከሀገር ውጭ፣ እርሷ የምትወስነው ጉዳይ ይመስለኛል። በዚህ ጉዳይ ብዙ ገፍተን ቴዎሬቲካል ባንሆንና ገፍተን ባንሄድ መልካም ይሆናል ብዬ አስባለሁ።

 

ሌላው የአቶ ይልማ ጽሑፍ ላይ ሳነበው ትንሽ ግር ያለኝ ሌላ ነገር ቢኖር፤ ዶ/ር ብርሃኑ ነጋን መጥቀሳቸው ነው። የዶ/ር ብርሃኑ ጉዳይ ከወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ጋር ምን እንዳገናኘው ሊገባኝ አልቻለም። ዶ/ር ብርሃኑ እንዲሁም ሌሎች እንደነ አቶ ሙሉነህ እዮዔል ያሉ የተከበሩ ወገኖቻችን፣ የቅንጅት አመራር የነበሩ ጊዜ ምን አይነት አኩሪ ገድል እንደፈጸሙ ሁላችንም የምናወቀው ነው።

 

ነገር ግን ስደትን ከመረጡ በኋላ አዲስ መንገድ ጀምረዋል። ግንቦት ሰባት የተሰኘውን ድርጅት አቋቁመው እንታገላለን እያሉ ነው። የሚሉንን ተቀብለን እየታገሉ ነው ብለን ብናምን እንኳ፣ የማያከራክር ነጥብ አለ። እርሱም እነ ዶ/ር ብርሃኑ ለትግሉ ሊያበረክቱት የሚችሉት ነገር፣ ውጭ ሀገር በመሆናቸው ብቻ፣ በጣም ውስን እንደሆነ ነው።

 

የመለስ አምባገነናዊ አገዛዝ ሁለት ዓላማ ይዞ ነበር በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ላይ የግፍ እርምጃ የወሰደው። አንደኛው ወ/ት ብርቱካን ተስፋ ቆርጣ ከጨዋታ ውጭ እንድትሆን ሲሆን፤ ሁለተኛው ደግሞ ከሀገር እንድትሰደድ ነው። አንድ ጠንካራ የፖለቲካ መሪ ከሀገር ለቀቀ ማለት ወታደር ያለ ጥይት ጠመንጃ ይዞ እንደሚዞር መሆኑን አቶ መለስ ጠንቅቆ ያውቃል። ይህንንም የአቶ መለስ እኩይ ዓላማ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ በሚገባ የምትስተው አይመስለኝም። የስደት የፖለቲካ ትግል አጋዥ እንጂ ወሳኝ አይደለም!

 

አቶ ይልማ ጥሩ ጥያቄ ጠይቀዋል። “ንዴቱ የት አለ? (Where is the Rage?)” ነው ያሉት። እኔ ገፍቼ እሄዳለሁ። ንዴት ብቻ አይበቃም። ንዴት ባዶውን ደም ብዛት ነው የሚያሲዘው። ነገር ግን ንዴቱ የትግል መነሳሳትንና ቁርጠኝነትን መውለድ አለበት። የትግል መነሳሳት ስል የወሬ ትግል አይደለም። የሥራ ትግል። በሀገራችን ኢትዮጵያ ለውጥ እንዲመጣ ከተፈለገ የኢትዮጵያ ህዝብ ለመብቱ ሊነሳና ሊነቃነቅ ያስፈልጋል። የኢትዮጵያ ህዝብ ለመብቱ እንዲነሳና እንዲነቃነቅ ከተፈለገ መደራጀት ያስፈልገዋል። ህዝብ ባልተደረጃበት ሁኔታ ውጤት የሚያመጣ እንቅስቃሴ ማድረግ አይቻልም። ህዝብ እንዲደረጅ ደግሞ ህዝብን የሚያደራጁ ከህዝቡ ጋር ያሉ የፖለቲካ ፓርቲዎች ያስፈልጋሉ።

 

በቅርቡ ዶ/ር ብርሃኑ በአዲስ ድምፅ ራዲዮ ኢትዮጵያውያን ለሀገራቸው ነፃነት በአንድ ላይ መሰባሰብ እንዳለባቸው ገልጸዋል። ትክክል ናቸው። ዳያስፖራው የሀገር ቤቱን ድጋፍ በመደገፍ ዙሪያ በአንድ ላይ ሊሰባሰብና ሊተባበር ይገባል። የትግሉ መሪ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ ናት። ወ/ት ብርቱካን ምን አይነት ውሳኔዎች ማሳለፍ እንዳለባት በወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ አዕምሮ ውስጥ ገብተን የተለያዩ አስተያየቶችን ከመስጠት ይልቅ፤ ወ/ት ብርቱካን ሚደቅሳ የምትመራውን ትግል ለማገዝ፣ የድርሻችንን ለማበርከት መዘጋጀት ያለብን ይመስለኛል።


ግርማ ካሣ

(This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.)

ጥቅምት 3 ቀን 2003 ዓ.ም.


1 http://addisnegeronline.com/2010/10/forget-abuse-birtukan-was-tortured/  

2 http://ethiopiazare.com/the-news/64-reportage/1492-a-report-on-birtukan-release

3 http://www.ethiopianreview.com/content/29762

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ