መቶ ሚሊዮን ህዝብ ያላት የሰው ድሃ ሀገር ኢትዮጵያ
ይገረም ዓለሙ
በ1982 ዓ.ም. ኢትዮጵያ ወዴት እየሄደች እንደሆነ አይደለም የት ላይ እንዳለች አንኳን መናገር በማይቻልበት ወቅት፤ ከአንድ ባልንጀራየ ጋር እየሄድን፤ እኔ ከማላውቀው የእርሱ ጓደኛ ጋር መንገድ አገናኘን። እናም ሠላምታ ተለዋውጠው፤ ታዲያስ እንዴት ነህ፣ እንዴት ናችሁ ሲለው፤ ምን እባክህ ሰውም አለን ሰውም የለንም ሲል መለሰለት።
ሁለቱ ተለያይተው እኛ መንገድ እንደጀመርን፤ ምንድን ነው ያለው ስል ባልንጀራየን ጠየኩት። እባክህ እሱ አመሉ ነው፣ ከርሱ ጋር ስናወራ ጓደኞቹ ሁሉ እንደተቸገርን ነው፤ በቀጥታ መናገር አይሆንለትም አለኝ። ምንድን ነው ሥራው ስል ጥያቄ አከልኩ፤ ሥራው ወታደራዊ ካድሬ፣ ትውልዱ ጎንደሬ፣ ፖለቲካውን በጎንደር አማርኛ እየመሰጠረ ነው የሚያስቸግረን በማለት ባላንጀራየም እንደመራቀቅ እያደረገው መለሰልኝ። “ሰው አለን ሰው የለንም” የሚለውን አባባል ምንነት ለመረዳት ከባልንጀራየ ጋር ብዙ አውርተንበታል፤ ብቻየንም ብዙ ግዜ አውጥቼ አውርጄዋለሁ።
ይህ በሆነ አስር ዓመት ግድም ፕ/ር መስፍን ወልደማሪያም በጦቢያ መጽሔት ላይ ኢትዮጵያ የሰው ድሀ ካልሆነች ታዲያ የምን ድሃ ልትሆን ነው የሚል ጽሁፍ አስነበቡን። ይህም ከሆነ አስር ዓመት ግድም (አጋጣሚው ሊገርም ይችላል) ፕ/ር መስፍንን አግኝቻቸው ከላይ የጠቀስኩትን ጽሁፋቸውን አስታውሼ ከ90 ሚሊዮን ህዝብ በላይ ያላት፣ በተለያዩ የዓለም ሀገራት በተለያዩ የሙያ ዘርፎች ተሰማርተው የሚሠሩ አንቱ የተባሉ ልጆች ያሏት በማለት ብዙ ነገር ዘረዘርኩና፤ እንዴት የሰው ድሃ ትባላለች ስል ጠየኳቸው። በጥሞና አዳምጠው በርጋታ የሰጡኝ ማብራሪያ ረዥምና አጥጋቢ ነበር። ከግዜው ርዝመት አንጻር ማስታወስ ቢገደኝም፤ አንኳር ነጥቡ እነዚህ የምትላቸው ሰዎች ለራሳቸው ኖረው ሊሆን ይችላል፤ ላስተማራቸው ሀገርና ህዝብ ምን ሠርተዋል? ከአገዛዝ አላቀውታል? ከድህነት አውጥተውታል? ሰው በሚፈለግበት ግዜና ቦታ ካልተገኘ መኖሩ ብቻ ለሀገር ምን ይጠቅማል የሚል ነበር።
የርሳቸውን ማብራሪያ እያዳመጥኩ አስር ዓመት ያህል ወደ ኋላ ተመልሼ “ሰው አለን ሰው የለንም” ያለውን የወዳጄን ወዳጅ አስታወስኩት። የአባባሉ ምንነትና እንደዛ ለማለት ያበቃውም ምክንያት በፕ/ር ንግግር ውስጥ ግልጽ ብሎ ታየኝ። በቁጥር ብዙ ሰው አለ፤ በቁም ነገር መድረክ በተግባሩ መስክ ግን … ማለቱ ነበር፤ የሰው ድሀ ማለት ይህ አይደል ታዲያ።
ብቸኛው ፓርቲ ኢሠፓ ከሲቭልም ሆነ ወታደራዊ ማዕረጋቸው የሚቀድመውን ጓድ መጠሪያቸው ያደረጉ ብዙ እጅግ ብዙ አባላት ነበሩት። ነገር ግን አባሉ በቁጥር በዝቶ ቁም ነገር ያለው ግን አንሶ አይደለም ሀገሪቱን ሲያንቆለጳጵሱዋቸው የነበሩትን መሪ ከስደት፤ ፓርቲውን ከሞት፤ ራሳቸውን ከውርደት መታደግ ሳይችሉ ቀሩ።
ኢሠፓ ያልነበሩ እንደውም ኢሠፓን ተቃውመው መንግሥቱን አውግዘው ሲታገሉ የነበሩ ባይታገሉም ሥርዓቱን ይቃወሙ ዴሞክራሲን ይመኙ የነበሩ በቁጥር ብዙ ነበሩ። ግና ቁም ነገራቸው ሚዛን የሚደፋ የተግባር ሰውነታቸው እስከመስዋዕትነት የደረሰ ጥቂቶች ሆኑና ኢትዮጵያ ሰው እያላት የሰው ድሃ ሆነችና ከወታደራዊ አገዛዝ ወደ ተጋዳላዮች አገዛዝ ለመሸጋገር በቃች።
ዘመነ ወያኔንም ስናይ ከመነሻው ጀምሮ ወያኔን የሚቃወመው፣ ስለ ለውጥ የሚደሰኩረው፣ ስለ ዴሞክራሲ የሚሰብከው፣ ወዘተ ቁጥሩ የትየለሌ ነው። ግና ከቁም ነገሩ መድረክ ከተግባሩ ስፍራ የሚገኙት ጥቂት በጣም ጥቂት ሆኑና ወያኔ ማን አለኝ ከልካይ እያለ ያሻውን እየፈጸመ ሃያ አራት ዓመታት ለመግዛት ቻለ። ሌላው ቀርቶ በቅርቡ ኢሳትና ቪዥን ኢትዮጵያ በጋራ ባዘጋጁት የውይይት መድረክ ላይ የመወያያ ጽሁፍ ያቀረቡትን በተለያየ የሙያና የእውቀት ዘርፍ ከጫፍ የደረሱ ምሁራንን የተመለከተ የእነርሱ መሰሎች ሀገር ኢትዮጵያ እንዲህ በአገዛዝ ስትማቅቅ፤ ከዴሞክራሲ ጋር ሆድና ጀርባ ሆና ስትኖር፣ ህዝቡ በየግዜው በረሃብ አለንጋ ሲገረፍ ሰው እያላት ሰው ያጣች ሀገር አያሰኝም ትላላችሁ!
የኢትዮጵያ የሰው ድህነት በወያኔም ውስጥ በገሀድ ይታያል። በተለያየ መንገድ የድርጅቱ አባልም ደጋፊም የሆኑ አባልና ደጋፊም ባይሆኑ ደግሞ የማይቃወሙ በተለያየ የእውቀትና የሙያ መስክ ላይ የሚገኙ በውጪም በውስጥ ብዙ ዜጎች አሉ። ነገር ግን እነርሱም ቁጥራቸው እንጂ ቁም ነገራቸው የሚታይ ባለመሆኑ ድርጅታቸው በሀገርና በህዝብ ላይ የሚያደርሰውን ጥፋት ማስቆም ቀርቶ አንድ መለስ ያለእኔ ማን አለ ብለው ፓርቲም መንግሥትም ግለሰብም ሆነው ናውዘው ለሞት ሲበቁ ሊታደጉዋቸው አልቻሉም።
ይህም ብቻ አይደለም ከአስር ዓመት በፊት ከአምስት ሚሊዮን በላይ አባላት አሉኝ ያለ ድርጅት በቁጥር እንጂ በቁም ነገር (ከሱ ፍላጎት አንጻር) ሚዛን የሚደፋ ሰው አጥቶ ከቦታ ቦታ የሚያገላብጣቸው የተወሰኑ ሰዎችን ነው። ሴቶችማ ለቁጥርም የሉ። የአሁኑ አፈ ጉባኤ አባ ዱላ ገመዳ አንዴ ጀነራል፣ አንዴ አቶ እየተባሉ ስንት ቦታ እንደተገለባበጡ ማስታወሱ ብቻ ለዚህ በቂ ይመስለኛል።
የትውልድ ድርሻውንና የዜግነት ግዴታውን ቅንጣት ሳይከውን በሥልጣኔ ስም ሰይጥኖ ወደ ላይ አንጋጦ ትናንትን የማውገዝ ድፍረት በተላበሰው ትውልድ የሚነቀፉ የሚዘለፉት አባቶቻችን በቁጥር ጥቂት ሆነው ከነዛው መካከል ግን የቁም ነገር ሰዎች ብዙም ብርቱም የነበሩ በመሆናቸው ነበር በዙሪያችን ያሉ ሀገሮች በቅኝ ግዛት ሲማቅቁ ኢትዮጵያ በነጻነት የዘለቀችው፤ ዳር ድንበሯን አስከብራ የባህር በሯን አስጠብቃ ለመኖር የቻለችው። ለዓለም ጥቁር ህዝቦች የነጻነት ተምሳሌት ሆና የኖረችው።
ዛሬ ግን እንደ ቁጥራችን ብዛት ከቁም ነገር ያፋቱን፣ ከተግባር ያራቁን ችግሮቻችን በዝተው እኛ የሚናቁት የሚወገዙና የሚኮነኑት አባት እናቶቻችን ያቆዩንን ሀገር፣ ዳር ድንበር፣ የባህር በር፣ ወዘተ ማስከበርና መጠበቅ ሳንችል ቀረን። ከወያኔ አገዛዝ ተላቀን የምናወራለትን ዴሞክራሲ እውን ለማድረግ መስኩ ላይ መገኘት አቃተን። በእውቀት የበለጸጉ በሙያ የተካኑ በልምድ የዳበሩ አያሌ ልጆቿ በመላው ዓለም በተለይም በምዕራቡ የዓለም ክፍል ተሰማርተው እውቀት ጉልበታቸውን ለሌላ ሀገር እየሸጡ የተደላደለ ኑሮ መኖር ቢቻላቸውም እውቀታቸውም ሆነ ሙያቸው፣ ልምዳቸውም ሆነ ጉልበታቸው፣ ለሀገራቸው የሚፈይድ አልሆነም። እንዲህም ሆነና እናት ሀገር ኢትዮጵያ መቶ ሚሊዮን የሚሆን ሰው እያላት የሰው ድሃ ሆና አገዛዝ እንደተፈራረቀባት፣ ዴሞክራሲ እንደናፈቃት፣ ረሃብ ልጇን እንዳሰቃየባት ትኖራለች። ዛሬ እየሆነ ካለው በላይ የነገው ተስፋ የለሽነት ይብስ ይከፋል።
መቼ ይሆን! ኢትዮጵያ ልጆቿ ቁጥራችን ብቻ ሳይሆን ቁም ነገራችንም በዝቶ ሰው እያላት የሌላት የሰው ድሃ ከመሆን የምትወጣው? መቼ ይሆን! በዘር፣ በኃይማኖት፣ በአመለካከት ልዩነት ተለያይተው የመቶ ሚሊዮኖች እናት ግን የሰው ድሃ ያደረጉዋት ልጇቿ ከምንም ነገር በፊት እናታችን ብለው እውቀታቸውን አቀናጅተው ኃይላቸውን አስተባብረው ነጻነት የሚያቀዳጇት? መቼ ይሆን! ልጆቿ ከራስ በላይ ነፋስ አስተሳሰብ ተላቀው፣ ከመጠላለፍ አዙሪት ወጥተው፣ ከቁልቁለት ጉዞ የሚያቃኑዋትና የነበረ ዝናና ክብሯን መልሰው የሚያቀዳጁዋት? ኧረ! መቼ ይሆን! ልጆቿ ዴሞክራሲ እየተረገዘ የሚጨነገፍበትን ሲወለድም በአጭር የሚቀርበትን በሽታ ተረድተው መድኃኒትም አግኝተውለት ኢትዮጵያን ዴሞክራሲያዊት ሀገር ለማድረግ የሚበቁት? ኧረ መቼ ይሆን! ልጆቿ የመቶ ሚሊዮን ህዝብ ሀገር የሰው ድሃ የሆነችው እነርሱ ተለያይተው በመቆማቸው፤ በሥልጣን ጥም በመታወራቸው፤ ከእኔ በላይ በሚል አስተሳሰብ በመታጠራቸው፣ ለራስ እንጂ ለመጪው ትውልድ የማይጨነቁ በመሆናቸው ወዘተ … መሆኑን ተረድተው ከየራሳቸው ታርቀው፣ ርስ በርሳቸው ፍቅር መስርተው፣ እንደ ብዛታቸው ቁም ነገራቸውም ለሀገርና ለወገን ሲበጅ የሚታየው? መቼ ኧረ መቼ!
ታዋቂው የብዕር ሰው ሎሬት ጸጋዬ ገብረመድኅን ይድረስ ከእኛ ለእኛ በሚለው ተከታታይ ግጥም ውስጥ እንዲህ ብሎ ነበር።
ይድረስ ወገን ከእኛ ለኛ “እሳት አንሆን ወይ አበባ”
የነገን ራዕይ እንዳናይ፣ በሐቅ እንቅ ስንባባ
መክሊታችንም ባከነች፣ ዕድሜአችንን ስናነባ።
ፍቅር ፈርተን፣ ሠላም ፈርተን
አንድነታችንን ጠልተን፣ ተስፋችንን አጨልመን
የነፍስን አንደበት ዘጋን፣
የልጆቻንን ተስፋ፣ እምቡጥ ሕልማቸውን በላን።
ሳይነጋ እየጨለመ ነው፣ ተው ወንድሜ እንተማመን፣
ዓለም ባበደበት ዘመን፣ የብረት ምሽግ ነው ወገን።
ኢትዮጵያ ዘለዓለሚቷ፣ አንድነት ነው መድኃኒቷ
ሕብረት ነው መፍትሔው ስልቷ።