መጽሔታቸው ግን እንደታሰረ ነው

Ethiopia Zare (ኀሙስ ሚያዝያ 30 ቀን 2000 ዓ.ም. May 08, 2008)፦ ባለፈው ቅዳሜ የዓለም የፕሬስ ቀን ተከብሮ በዋለበት ዕለት ፖሊስ አስሯቸው የነበሩት አራት የዕንቁ መጽሔት ጋዜጠኞች እና ባልደረቦች ትናንት ከሰዓት ረፋዱ ላይ በዋስ መለቀቃቸውን ሪፖርተራችን ከአዲስ አበባ ዘገበ።

 

የዕንቁ መጽሔት አሣታሚና ምክትል ዋና አዘጋጅ አቶ አለማየሁ ማኅተመ ወርቅ፣ ባልደረቦቹ አቶ ሠለሞን መኮንንና አቶ ሲሳይ ወርቁ እንዲሁም አቶ ኢሳያስ የተባለው የታክሲ ሾፌር ጭምር ቅዳሜ ሚያዝያ 24 ቀን 2000 ዓ.ም. ከምሽቱ 4፡30 ሰዓት አካባቢ የዕንቁ መጽሔትን አስር ሺህ ቅጂ ሕትመት በብራና ማተሚያ ቤት ከተጠናቀቀ በኋላ በሚኒባስ ታክሲ ለመውሰድ ወደ ማተሚያ ቤቱ ሲሄዱ ፖሊስ ቁጥጥር ስር አውሏቸው ነበር።

 

ማክሰኞ ዕለት ፖሊስ በአዲስ አበባ ከተማ የመጀመሪያ ፍርድ ቤት ልደታ ክፍለ ከተማ ምድብ ችሎት አራቱንም አቅርቧቸው የ14 ቀናት ጊዜ ቀጠሮ ጠይቆ ፍርድ ቤቱ ከፈቀደለት በኋላ ለግንቦት 11 ቀን 2000 ዓ.ም. ተለዋጭ ቀጠሮ ተሰጥቶ እንደነበር ታውቋል።

 

በትናንትናው ዕለት ከሰዓት በኋላ ረፋዱ ላይ ፖሊስ ዋስትና ፈቅዶላቸው አራቱም የተፈቱ ሲሆን፣ ያሳተሙት መጽሔት ግን ሳይለቀቅላቸው ቀርቶ ለዛሬ ቀጠሮ ተሰጥቷቸው ነበር። ዛሬ ከሰዓት በኋላ ገበያ ላይ ያልዋለውን መጽሔታቸውን ለማምጣት ፖሊስ ጋር ሲሄዱ፤ “በፍርድ ቤት የተያዘ ጉዳይ ስለሆነ” በሚል ሰበብ ሳይለቀቅላቸው መቅረቱን የኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ ባረደገው ለማረጋገጥ ችሏል።

 

ዕንቁ መጽሔት በአለማየሁ አሳታሚ ድርጅት ስር እየታተመ የሚወጣ በኪነጥበብ ዙሪያ የሚያተኩር ወርሃዊ መጽሔት ነው። መጽሔቱ ከነአዘጋጆቹና የአሳታሚው ባልደረቦች ቅዳሜ ዕለት በፖሊስ የተያዙት በማግስቱ እሁድ ለገበያ ይቀርብ ስለነበር ለየክፍለሀገራቱና ለአዲስ አበባ የጋዜጣ አከፋፋዮች ከመድረሱ በፊትና ከማተሚያ ቤቱ ከመውጣቱ በፊት ነው። በዚህም ምክንያት እስከዛሬው ዕለት ድረስ ገበያ ላይ ሳይውል ቀርቷል።

 

መጽሔቱ በፊት ሽፋኑ (ከቨር ሰቶሪው) እና በውስጡ የያዛቸው መጣጥፍ በእስር ላይ ያለውን አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁንን የሚመለከቱና ሌሎችንም እንደሆነ ለማወቅ ተችሏል። አርቲስት ቴዎድሮስ ካሳሁን (ቴዲ አፍሮ) የዋስ መብቱን ተከልክሎ በቃሊቲ እስር ላይ የሚገኝ መሆኑንና በቅርቡም ጨለማ ቤት እንደታሰረ በኢትዮጵያ ዛሬ ድረ ገጽ መዘገባችን አይዘነጋም።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ