ለወያኔ ዕድሜ ማራዘሚያ በተዘጋጀ መድረክ ተቀዋሚዎች ምን ይሠራሉ?
ይገረም አለሙ

የፖለቲካ ድርጅት የመገናኛ ብዙኃን ባለቤት እንዳይሆን የሚከለክለውን ሕግ በመተላለፍ ወያኔ ያቋቋመው ፋና ሰሞኑን አንድ የውይይት መድረክ አዘጋጅቶ ነበር። ውይይቱን በቀጥታ ስርጭት ሳይሆን ለእኛ ይገባቸዋል ብለው የመጠኑልንን አቀናብረው አስተላልፈውልን ተመልክተነዋል። ጽሁፍ አቅራቢዎቹ ተወክለው ይሁን ወክለው ባይታወቅም ከምሁራን ከባለሀብት ከተቀዋሚና ከኢህአዴግ ተብለው ነው የቀረቡት።
ከኢህአዴግ አቶ በረከት ከተቀዋሚ አቶ ልደቱ። ዶ/ር መረራንና ኢ/ር ይልቃልን ጨምሮም ጥቂት የፓርቲ ሰዎችንም በአዳራሹ ተመልክተናል። የባለሀብቶች ተወካይ የተባሉት ጽሁፍ አቅራቢ ለመድረኩ መዘጋጀት ምክንያት በሆነው ህዝባዊ አመጽ ለተገደሉት ኀዘናቸውን በመግለጽ ብቸኛ ሰው ሆነዋል። ከዚህም ሌላ "ኢህአዴጎች መታደስ ሳይሆን ፈርሶ መሠራት ነው ያለባችሁ" በማለት ፖለቲከኞቹ ያልደፈሩትን ተናግረዋል። አቦ እግዜአብሔር ይባርክዎት።
ተቃዋሚ ፖለቲከኞች በሀገራዊ ጉዳይ ላይ ምክክር በሚደረግበት በማናቸውም መድረክ ተጋብዘው አይደለም ራሳቸው ጠይቀው ሊገኙ እንደሚገባ አምናለሁ። ነገር ግን በተለያየ ግዜ የወያኔን ግብዣ ፋይዳ ቢስ እያሉ አለመቀበላቸውን ሲነገሩን የነበሩ ሰዎች የህወሓትን ህልውና ለመታደግ በተዘጋጀ በዚህ መድረክ ላይ መታየታቸው ለምን አሰኝቷል።
በዚህ መድረክ መገኘት ያለባቸው ሰዎች ወያኔ በጥገናዊ ለውጥና በጥልቅ ተሃድሶ ራሱን አርሞ በሥልጣኑ እንዲቀጥል የሚሹና፤ ምክር ሰምቶ የሚታዘዝለትንም መድኃኒት ወስዶ ለህዝብ ጥያቄ ተገቢና ትክክለኛ መልስ መስጠት ይችላል ብለው የሚያምኑና ምክር ለመለገስና መድኃኒት ለማዘዝ የተዘጋጁ መሆን አለባቸው።
ከዚህ አንጻር የተቀዋሚ ተወካይ በሚል ሽፋን ጽሁፍ ለማቅረብ የበቃው አቶ ልደቱ ተገቢ ቦታው ላይ ነው የተገኘው እላለሁ። ከተሰብሳቢው በኩል ሆነው ሲናገሩ ያየናቸው ዶ/ር መረራና ኢ/ር ይልቃል ግን ያለቦታቸው ነው የተገኙት ብየ ስላመንኩ፤ ለምን የሚል ጥያቄ አነሳለሁ። ከስሜት ሳይሆን ከምክንያት ተነስተን መድረኩ የሚገባቸውንና ያለ ቦታቸው የተገኙትን ለይቶ ማወቅና የመገኘታቸውን እንዴትነት መረዳት የህዝቡን ትግል ቀጣይ ተግዳሮቶች ለመለየት የሚያስችል ይሆናል።
አቶ ልደቱ፤
አቶ ልደቱ ከተቀዋሚ ፓርቲ ተብሎ ከመነገሩ በቀር ተቃዋሚዎችን አይደለም አባል የሆነበትን ኢዴፓን ስለመወከሉ አልተገለጸምና አነጋጋሪ ሆኖ የሰነበተው ንግግሩ የግል አቋሙ ይሁን የኢዴፓ አልታወቀም። ፓርቲውም አላስተባበለም። የተገኘው በግሉም ይሁን በኢዴፓ መድረኩ የሚመጥነው ነውና በተገቢው ቦታ ነው የተገኘው። ይህን ደግሞ ከተመደበለት በላይ 10 ደቂቃ አስጨምሮ ለ40 ደቂቃ ባሰማው ንግግሩ ያረጋገጠው ነው። አቶ ልደቱ በብዙ መንገድ ወያኔን አድንቆና አጀግኖ የህዝቡን ትግል አናንቆና ወያኔን በሚገባው ቋንቋ ማነጋገር የሚሉ ወገኖችን አክራሪዎች እያለ በዘለፈበት ንግግሩ፤ አስቀድሞ ለሚያውቁተ የበለጠ ማረጋገጫ ሰጥቷል። እስካሁን ላላወቁትና በተለይ ከምርጫ 97 ወዲህ ለአቅመ ፖለቲካ ለደረሱት ወጣቶች ደግሞ ራሱን በግልጽ አሳይቷል። ወያኔዎች በዛ መድረክ ሲያቀርቡት ማንነቱን ተረድተውና ፍላጎቱን አጢነው ይሁን ወይም ለመድረኩ እንዲስማማ አዘጋጅተውት ባይታወቅም፤ የልደቱ አድራጎት ግን ለእነርሱም ሆነ ለራሱ የሚጠቅም አይመስለኝም። የእነርሱ ፍላጎት ሊጠቅሙትና ሊጠቀሙበት ሳይሆን፤ ለመጨረሻ ሊገድሉት ከሆነ ግን የሚሳካላቸው ይመስለኛል።
ትናንት ዛሬ አይደለም በሚል እሳቤ ልደቱ ካደረሰውም ከደረሰበትም ተምሮ ይሆናል የሚል እንጥፍጣፊ አዘኔታና ተስፋ የነበራቸው ሰዎች ሁሉ፤ አንቅረው እንዲተፉት ያደረገ መድረክ በመሆኑ፤ ለምን በተቃዋሚ ካባ ቀረብክ እንጂ ለምን እዛ መድረክ ተገኘህ፣ እንዴትስ እንዲህ ለመናገር ደፈርክ ልንለው አይቻለንም። ወያኔ የራሱ ሰዎች እየጠሉትና እየከዱት ባለበት ሰዓት ህዝብ የጠላኝ እውነቱን ሳያውቅ ነው የሚለው አቶ ልደቱ፤ ከወያኔ ጋር ይበልጥ ለመጣበቅ ይህን ያህል መሄዱ ምን ለማግኘት አስቦ ወይንም ምን ቃል ተገብቶለት እንደሆነ ወደ ፊት የሚታይ ይሆናል።
ዶ/ር መረራ
ዶ/ር መረራ የኦፌኮና የመድረክ መሪ ቢሆኑም፤ በዛ መድረክ የተገኙት በየትኛው ፓርቲ ውክልና እንደሆነ ግን አልተነገረም። በተለይ እንደ ኦፌኮ ሊቀመንበርነታቸው በዛ መድረክ ላይ መገኘት ቦታቸው ነው ወይ የሚል ጥያቄ አንስቶ በቂ ምክንያት ካላቸው እንዲነግሩን፤ አለበለዛም የተገኙት አለቦታቸው እንደነበር አምነው ለወደፊቱ እንዲታረሙ መንገር ያስፈልጋል። የወዳጅን ስህተት እየሸፋፈኑ ማለፍ ወይንም አትንኩት ብሎ በተከላካይነት መሰለፍ ሰውየውን ጭምር ነው የሚጎዳው።
ከገዳይ አስገዳዮች ጋር በአንድ መድረክ፤
ባሳለፍነው አንድ ዓመት በኦሮምያ ከአንድ ሺ በላይ ሰላማዊ ዜጎች መገደላቸውን በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ መታሰራቸውንና ለአካል ጉዳት መዳረጋቸውን ከራሳቸው ፓርቲ ሲወጡ ከነበሩ መግለጫዎች ሰምተናል። ያ አልበቃ ብሎ ሌላ ግድያ፣ ሌላ እስር፣ ሌላ ማሰቃየት ለመፈጸም የአስቸኳይ ግዜ አዋጅ ታውጇል። ለዶ/ር መረራ በእንዲህ አይነቱ መድረክ መገኘት ግድያና እስራቱ መቆምና ያለፈው በገለልተኛ እንዲጣራ ስምምነት ላይ መደረስ ነበረበት። ነገር ግን ይህ ሊሆን ቀርቶ የተ.መ.ድ የሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ጉዳዩን ለማጣራት ላቀረበው ጥያቄ አዎንታዊ ምላሽ ተነፍጎት ባለበት ወቅት ያውም ለህወሓት ትንሳኤ ሊመክር በተጠራ መድረክ፤ የዶ/ር መረራ መገኘት ምን ለመፈየድ ነው? ሺዎች ኦሮሞዎችን ከገደሉና ካስገደሉ ሰዎች ጋርስ ምሳ አብረው መብላታቸውን በመገናኛ ብዙኃን መናገራቸውስ ምግቡ እንዴት ቢዋጥላቸው ነው? ይሄ መቼም ዲፕሎማሲም ዴሞክራሲም ሊባል የሚችል አይመስለኝም።
ጥያቄአችን የሥርዓት ለውጥ ነው።
የሥርዓት ለውጥ እየጠየቀ ያለውን የህዝብ ትግል፤ የዶ/ር መረራ ፓርቲ ባይመራውም እወክለዋለሁ የሚለው ህዝብ ጥያቄ ነውና መደገፉ ግድ ነው። የፖለቲካ ሣይንስ መምህሩ ወያኔ በሥልጣን ላይ እያለ የሥርዓት ለውጥ ተግባራዊ የሚሆንበት መንገድም ዘዴም አለ ካላሉ በስተቀር፤ ከሥልጣን መልቀቅ የሚጠይቅ ነው። ታዲያ የሥርዓት ለውጥ እየጠየቁ ለወያኔ ዕድሜ ማራዘሚያ መድኃኒት ፍለጋ በተጠራ መድረክ ላይ መገኘት ምን ይሉታል?
ወያኔ አፍ እንጂ ጆሮ የለውም
ዶ/ር መረራ ከሚታወቁባቸው ንግግሮች አንዱ “ወያኔ አፍ እንጂ ጆሮ የለውም” የሚለው ነው። ታዲያ ወያኔ የሚናገር እንጂ የሚሰማ ካልሆነ ርሳቸው በዛ መድረክ የተገኙት ወያኔን ለመስማት ነው? ወይንስ በራሱ መድረክ ሲሆን ጆሮ ይኖረዋል ብለው ወይንም የህዝቡ ቁጣ ጆሮ እንዲኖረው አድርጎታል ብለው አምነው ለጥገናዊ ለውጡ ሃሳብ ለመለገስ። ከላይ ባነሳኋቸውም ሆኑ በሌሎች ምክንያቶች የዶ/ር መረራ በፋና መድረክ መገኘትን ተገቢ የሚያደርግ ምክንያት አላገኘሁምና አለቦታቸው ነው የተገኙት እላለሁ። ምክንያት ካላቸው ማስረዳት፤ ከሌላቸው ደግሞ ነገም ሚሆነው አይታወቅምና ተመሳሳይ ነገር በመሥራት ለወያኔ ምርኩዝ የሚሆንና ትግሉን የሚጎዳ ተግባር ከመፈጸም ሊታቀቡ ይገባል። አናለባብስ!
ኢ/ር ይልቃል ጌትነት
ሰማያዊ ፓርቲ ጠቅላላ ጉባዔ አካሂጄ የሊቀመንበር ለውጥ አደርጌአለሁ ማለቱን ሰምተናልና፤ ኢ/ር ይልቃልን በሚመለከት የሚነሳው የመጀመሪያ ጥያቄ ማንን ወክሎ ነው የተገኘው የሚለው ነው። ሁለተኛው ብዙ መድረኮችን አልገኝም እያለ መሰረዙን እናውቃለንና፤ ዛሬ ምን ተገኘ የሚል ሲሆን፤ ሦስተኛው በዛ ቦታ መገኘነቱ በተለያየ ግዜና መድረክ ሲናገራቸው ከነበሩትና የፓርቲው አቋሞች ናቸው ብለን ከተቀበልናቸው ጉዳዮች ጋር የሚቃረን መሆኑ ነው። ጥቂቶቹን እንይ።
ትግሉ የነጻነት ነው፤
በምርጫ 2007 ሰሞን "ትግሉ የነጻነት ነው" እያለ ሲናገር ሰምተናል። ይህንኑ አቋሙን በማጠናከርም ካናዳ በሄደበት ወቅት "የምርጫ ፖለቲካ አብቅቶለታል" ሲል ተናግሯል። እነዚህም ሆኑ ሌሎች ንግግሮቹ የሚያሳዩት የሥርዓት ለውጥ ያስፈልጋል የሚል እምነት እንዳለው ነው። ወያኔ በሥልጣን ላይ እያለ ነጻነትን የሚያቀዳጅ የሥርዓት ለውጥ የሚገኝበትን ዘዴም ሆነ መንገድ የነገረንም ሆነ ያሳየን የለምና በእስካሁን ግንዛቤአችን የምንረዳው እነ ይልቃል የሥርዓት ለውጥ ሲሉ ወያኔ ሥልጣን መልቀቅ/ መወገድ አለበት እያሉ እንደሆነ ነው። ታዲያ ኢ/ር ይልቃል ለመገናኛ ብዙኃን ፍጆታ የሚናገረውና የሚያምነው የተለያየ ካልሆነ በስተቀር የወያኔን ዕድሜ ለማራዘም መድኃኒት ፍለጋ በተጠራ መድረክ ላይ መገኘቱ ምን ለማትረፍ እንደሆነ ግልጽ አይደለምና ምክንያት ካለው ማስረዳት፤ ካልሆነም ዳግም መሰል ድርጊት እንዳይፈጽም በተለይ ወዳጁ አድናቂው ተከታዩ ወዘተ ነን የምትሉ ልትመክሩትም ልትገስጹትም ይገባል። ህዝብ አንዴ አንቅሮ ከተፋ መመለሻ የለም።
ወያኔ የሥልጣን ዕድሜውን ለማራዘም ይጠቅማል እስካለ ድረስ መድረክ መጋበዝ አይደለም ትንሽ ትንሽ ሥልጣን እስከመስጠት ሊሄድ ይችላል። በዚህ ወቅት እየተንገዳገደ ያለውን ወያኔ ተጋግዞ ከመግፋት ይልቅ፤ በየግል ፍላጎት ምክንያት በወያኔ ድርጊት እየተታለሉም ሆነ እየማለሉ ጥያቄውን በመመለስም ሆነ ስጦታውን በመቀበል ምርኩዝ መሆን የኢትዮጵያ ህዝብ በባርነት እንዲኖር ተባባሪ መሆን ነውና ያስጠይቃል። ስለሆነም ወያኔ ከዚህ በኋላም ብዙ ነገር ሊያደርግ መቻሉን ታሳቢ በማድረግ ህዝብ በደሙ ያቀለመውን ትግል ማገዙ ቢቀር እንዲኮላሽ ተባባሪ ከመሆን መቆጠብ ይገባል። ላለፈው ክረምት ቤት ባይሠራም፤ ለመጪው ማሰብ ግን ተገቢ ነው።



