አቦይ ዘባረቁ? ሰምሃልስ?
እንግዳ ታደሰ ከኖርዌይ
ያንን ገለባ ልጅ ከደጅ የወደቀው
አድራሻህ ወዴት ነው ብለህ አትጠይቀው
የነገው ነፋስ ነው መንገዱን የሚያውቀው።
በዕውቀቱ ስዩም
ጥቅምት 5 ቀን 2009 ዓ.ም. የሸራተን አዲስ የላሊበላ አዳራሽ ቲያትር ቤት መጋረጃ ለተደራሾች ተገለጠ። ሁለት መቶ ሃምሳ ታዳሚዎችን ባጨናነቀ ሁኔታ የትያትር ቤቱ አዳራሽ ሞልቶ ነበር። ”በዲሞክራሲያዊ ግንባታ ችግሮች ላይ የተሰነዘሩ ምልከታዎች” በሚል መርሃ ቃል በአቶ በረከት ሰምዖን መርሃኤ ተውኔት አዘጋጅነት፣ በልደቱ ተዋኝነት የተካሄደ ስብሰባ። አዳራሹን ያለስሙ ቲያትር ቤት ያልኩት ጠፍቶኝ አይደለም። ከወሎዋ ላሊበላ ምድር፣ እስከ ሸራተኑ የላሊበላ አዳራሽ ድረስ እነኝህ ሁለት ሰዎች እንዴት እየተደጋገፉ እንደሚያቄሉን ስለገረመኝ ነው ቲያትር ቤት ያልኩት።
ይህ ጽሁፍ በአቶ ልደቱ ተደጋጋሚ የአልጋ መውደቅ ኃጢያት ላይ ጊዜውን አያጠፋም። እሱን ለነብስ አባቱ ትተንላቸዋል፤ ነብስ አባት ካለው። እንዲሁ ግን ምንም ሳልል እንዳላልፈው የሚመጥነውን ግጥም ከበዕውቀቱ የግጥም መድበል ላይ አገኘሁ። ከመግቢያዬ ላይ የተጻፈውን። ልደቱ ዕድሜ ሰጥቶት ነገ ሌላ መንግሥት ቢመጣም ንፋሱ ገፍቶት ሲያመጣው አዲስ ተዋናይ ሆኖ ከመምጣት ምንም የሚያግደው ህሊና የለውም። ሼም የለሽ ነው የሚሉት አራዶች።
ወደ አቶ በረከት ልምጣ
አንድ የሶቭየት ሕብረት ቀልድ ትዝ አለኝ። በጎርቫቾቭ አማካኝነት በወጣ ጥብቅ አዋጅ መሰረት፣ ቮድካ እንደልብ በሶቭየት ከተማ ባለመገኘቱ፣ ህዝቡ የመንግሥት ማከፋፈያ ደጃፍ ላይ ተሰልፎ ለመግዛት ተራ ይጠባበቃል። አንድ ጀብራሬ የሶቭየት ዜጋ የሰልፉን ጥምጥም በዓይኑ ቃኝቶ እንዲህ በዋዛ እንደማይደርስበት በንዴት ከተረዳ በኋላ፤ ከሰልፉ ውስጥ ጮኾ በመውጣት በምንም አይነት ይህን ሰልፍ አልከተልም ጎርቫቾቭ የሚባለውን ሰው ባገኝ እገለዋለሁ እያለ በቀጥታ ወደ ክሬምሊን ቤተ መንግሥት አመራ። ከ40 ደቂቃ በኋላ ይህ ሰው ተመልሶ ቀድሞ ተሰልፎበት ወደነበረበት ቦታ እየተወራጨ ሲመጣ፣ ሰልፉ ላይ የነበሩት ሰዎች በአንድ ድምጽ ገደልከው? የታባቱ ገላገልከን? ይሉት ጀመር። ምን እገለዋለሁ! ክሬምሊን ቤተ መንግሥት ስደርስ፣ ጎርቫቾቭን ሊገድሉ የተሰለፉ ሰዎች ሰልፍ ከዚህ ሰልፍ እጥፍ ስለሚበልጥ ይኽኛው ሰልፍ ይሻላል ብየ ተመለስኩ ይላቸዋል።
መርሃኤ ተውኔት በረከት ስምዖንም ባስመዘገብነው የኢኮኖሚ ዕድገትና፣ የዲሞክራሲ ባህል መጎልበት የተነሳ የህዝባችን ንቃተ ህሊና በማደጉ የተፈጠረ ተቃውሞ እንጂ፣ ህዝባችን ፌዴራላዊ አስተዳደራችንን በመቃወም ያደረገው ህዝባዊ አመጽ ቤተመንግሥቱን ለመናድ አልነበረም። ስለዚህ እንደ ጀብራሬው የቮድካ ሰልፈኛ ቅጥፈት ከዚያኛው ሰልፍ ይኽኛው ይቀላል አይነት የመሸወጃ ቲያትሩን የዚያ ሁሉ አመጽ ልማታችን ያመጣው ዕድገት ነው በሚል ምንተ-እፍረት ባጣ የፖለቲካ ተራክቦ ብልግና ስብሰባውን መርቷል። በዚህ የበረከትና የልደቱ ቲያትራዊ ጨዋታ ላይ የEMF ድረገጽ አዘጋጅና አምደኛ አቶ ክንፉ አሰፋ የሄደበትን ትንታኔ አንብቤአለሁ። በአብዛኛው አቶ ክንፉ ያነሳቸውን ነጥቦች ብጋራም በአንዳንዶቹ ተሳታፊ ሰዎች ላይ ግን ልዩነት አለኝ።
- የሸራተኑ ጉባዔ እንዴትና ለምን ዓላማ ተዘጋጀ?
- በአባ ዱላ አማካኝነት ይህ ጉባዔ ለምን በገሃድ እንዲከፈት ተፈለገ?
- ጉባዔው ሲዘጋጅ ታዳሚና አድማቂ ሆነው የተመረጡት ሰዎች፣ በምን መስፈርት ተመረጡ?
- ፕሮፌሠር መረራና ኢንጅነር ይልቃል በግል ነው የተጋበዙት ወይስ የሚመሩትን ፓርቲ ወክለው?
- አቦይ ዘባርቀው ነው ወይስ ሆን ብለው መረራና ይልቃል ጓደኛሞች እንጂ ፓርቲ የላቸውም ያሉት?
- ታውቆና ታስቦበት ነው ከመጀመሪያው ተርታ ሰልፍ ላይ አቦይ ወንበር ያልተሰጣቸው?
- ሰምሃልስ እንደተረሳ የቤት ልጅ ከመጨረሻው ረድፍ ላይ ለምን ተወረወረች?
ብዙ ጥያቄዎችን የዕለቱን የስብሰባ አዳራሽ ድባብ በመመልከት መጠየቅና ግምቶችን መስጠት ይቻላል። ገራሚው ጉዳይ ግን ”ተከልከይ ባዋጅን” አሽሞንሙኖ ባወጀበት ማግስት፣ በዲሞክራሲያዊ ግንባታ ችግሮች ላይ የተሰነዘሩ ምልከታዎች በሚል ባዶና ቱሻ መፈክር ውስጥ የተገኙት ጎምቱ ተቃዋሚዎች፣ በተበላ ዕቁብ ውስጥ አድማቂ ሆነው መገኘታቸው ነው አጠያያቂው። ቢያንስ እነኝህ ሁለት ሰዎች በዚህ ጉባዔ ላይ እንዲገኙ ሲመረጡ፣ የዕለቱን ጉባዔ የወደቁ ሰማዕቶችን በማሰብ በህሊና ጸሎት ጉባዔው እንዲጀመር ያለማድረጋቸው፣ ለሀገሪቱ መጻኢ ሁኔታ ለሰላምና መረጋጋት ሲባል የታሰሩ የህሊና እሰረኞች ነጻ እንዲወጡ እንኳ ሳይጠይቁ፤ በረከት ቀድሞ ሊጫወትባቸው ባዘጋጀው የዲሞክራሲ ዕድገታችን ያመጣው ቁጣ ነው ጨዋታ ተጠልፈው፤ ያላቸውን ካርታ ተኩሰውና ጨርሰው በተቃዋሚነት ጨዋታ ለአሜሪካ ምክር ቤትና ለአውሮፓ ሕብረት ፓርላማ ለሚቀርብ ካሜራ ገጭ የሳሎን ቤት ጨዋታ ተበልጠው ሩጫቸውን ጨርሰዋል።
ይህ ጉባዔ ሲዘጋጅ ታስቦበት፣ በረከት ቅድመ ሴራውን ጎዝጉዞበት እንደሆነ የሚታወቀው፣ ጉባዔው የተከፈተው በሀገሪቱ ፓርላማ አፈጉባዔ መሰረት መሆኑ ነው። ይህ ለፈረንጆች ታላቅ ምልከታ ነው። ፈረንጆች በየሀገራቸው የፓርላማ አፈጉባዔዎችን የክብር ቦታ ያውቁታል። በዚህ ጉባዔ ላይ ካሜራው በደንብ እንዲታዩ ያደረጋቸውና በተቀዋሚነት ማማ ላይ ወጥተው እንዲጎሉ ያደረጋቸው በቅርቡ በሰሜን አሜሪካ የአሜርካን ኮንግረስ አባላቶችን በቅርበት በጋር ሲያናግሩ የከረሙት እና በጋራም በአንዳንድ የአሜሪካ ግዛቶች ለኢትዮጵያውያን ስብሰባ ሲጠሩ የነበሩ ሁለቱ ተቃዋሚዎች እንደሆኑ ወያኔ ስለምታውቅ ነው። ይህን ጨዋታ ወያኔ ጠንቅቃ ስለምታውቅ ካሜራ ላይ ሞልተው እንዲታዩላት በደንብ ሠርታቸዋለች።
በሌላ በኩል ምንም እንኳ ለአባላቶች እና ደጋፊዎች ግልጽ ባይሆንም፣ ከሰሜን አሜሪካ መልስ በኢንጅነር ይልቃል ላይ ባልተገኙበት መፈንቅለ መንግሥት ተደርጎባቸው በምትካቸው አቶ የሺህዋስ አሰፋ መመረጣቸው በአደባባይ ተነግሯል። ይህን የምርጫ ሥነሥርዓት የመራው ደግሞ የምርጫ ቦርድ ጭምር እንደሆነ በግልጽ በተነገረበት ወቅት፣ እንዴት ኢንጅነር ይልቃል በዚያ ስብሰባ ላይ ተገኙ? ሰማያዊውን ወክለው እንዳንል የምርጫ ቦርዶቹ መሪዎች ፕሮፌሠር በቃና እና ዶክተር አዲሱ ባሉበት ነው ኢንጅነር ይልቃል በሰማያዊ ፓርቲ ስም ክርክር ውስጥ የገቡት። አይ! በግል ነው እንዳንል ደግሞ አቦይ ስብሃት በመረራ ላይና በይልቃል ላይ የሰነዘሩት ሂስ አንድ ነገር ያሳብቃል።
ጽሁፌን ለማጠቃለል እንደ ቀድሞው ደርግ መፈክር እኛም አልረሳናችሁም አይነት መፈክር ያረሳኋቸውን ሁለት ሰዎች ጠቅሼ ጽሁፌን ላጠቃልል።
ወደ ሰምሃል ስመጣ
ብዙዎች በሰሞኑ በፌስ ቡክ ላይ ሽንት አስፈንጥሮ ከመሽናት ፎቶ ባሻገር፣ እስከ የጆሮግንድ የጺም አወራረድ ጆንትራ ቮልታ ፎቶዎቿን ጭምር በማምጣት ሃሳቧን ሲተቹ አይቻለሁ። በኔ በኩል ሰምሃል ያጠፋችው ጥፋት አልታይ ብሎኛል፤ እንደ አቦይ ከመድረኩ ርዕስ ወጥታ! ባገኘችው ዕድል ግን ራሱ ህወሓት ያወጣውን መመሪያ ራሱ እየበላው የኋሊት እንደሄደ ያጋለጠችበት መድረክ ነው። ከመለስ አንጻር ልጅቷን ጭምር በመጥላት ሳይሆን የምንቃወማት፣ ያደረገችው ንግግር በህወሓት የሥልጣን ማማ አወጣጥ ላይ ችግር እንደገጠማት የሚያሳይ ነው። በነማን ላይ ቂም እንዳላት ያባቷ ልጅ ሳታፍር ፈርጠም ብላ ተናግራለች። እዚያ ማዶ ጭስ ይጨሳልና አጭሳም ይሁን አንጀቷ ጨሶ በቡሄ መልክ አውርዳለች። የሥልጣን ብጥብጥ ጭምር እዚያ ቤት እንዳለ የሚያሳይ ጭምር ነው። መለስ ሲሞት ይቅርታ ሲሰዋ አቦይ ስብሃት በአደባባይ ወጥተው በአሜሪካን ድምጽ ራድዮ፣ ድርጅቱ እስካለ ድረስ መለስ ሞተ! ፋጡማ መጣች የሚመጣ አደጋ የለም፣ የሚፈጠር ቫክዩምም የለም እስካሉ ድረስ፣ ለምን የተገለላችሁት የህወሓት አዛውንቶች ድርጅቱ እስካለ ድረስ ተመልሳችሁ ወደ ሥልጣን መጣችሁ? እኛ ተተኪ ወጣት ልጆቻቸው እያለን ነው ያለችው! ዋሸች እንዴ?
ጋዜጠኛ ሳምሶን ማሞ በሚመለከት
መድፊያዬን በቀድሞዋ ሶቭየት ሕብረት አምባገነን መሪ ስታሊን ላይ በተቀለደው ቀልድ ዙሪያ በማጠንጠን ወደ ሳምሶን ማሞ አለፍኩ። ስታሊን ፊልም ቤት ሄዶ! የያዘውን ዱካክ በሳቅ ካስወገደ በኋላ፤ ያን የመሰለ አስቂኝ የቲያትር ገቢርን በብቃት የተወጣውን ኮሚክ አክተር አድንቆ ሲያበቃ፤ አስጠርቶ የአድናቆቱ ማሰርያ ያደረገው ያን ድንቅ ኮሚክ አክተር አሁኑኑ ወስዳችሁ ረሽኑት በማለት ነበር። ይህ የስታሊን ትዕዛዝ ያሳዘናቸው የቲያትር ቤቱ ኃላፊዎች ቢያንስ ከላይ ከንፈሩ ላይ ልክ እንደ ስታሊን ያጎፈረውን የከንፈሩን ጺም ይላጭና ይትረፍልን ብለው ስታሊንን ቢማጸኑት፤ ይሁን! ጺሙን ላጩና ረሽኑት እንዳለው፣ ሳምሶንም የጊዜ ጉዳይ ነው እንጂ በጌታቸው ረዳ የሚተርፍ አይመስለኝም።
ሳምሶን የራሱን ተክለ ሰውነት አጉልቶ ለማሳየት ሲል፣ የበረከትን ቢሮ በስድብ እበት ለቅልቆ እንደሚወጣ ራሱን አጀግኖ ተናግሯል። በረከትን አድንቆ፤ የጌታቸው ረዳን መዋቅር አኮስሦ መናገሩ ከተሰመረው 40 ኪሎሜትር ቀይ መስመር ውስጥ ያለፈ ይመስለኛል። አዲሱ አስገዳጅ ወይም አስገዳይ አዋጅ ደግሞ ከአፍንጫው የረዘመ ”የአሊ ባባን ጫማ አይነት” የተጫማ ሰው ደብረዘይት ጁስ ቤት ላይ ካልቆመ አልፌ ቢሾፍቱ እሄዳለሁ ቢል፤ ቢያንስ ጫማው እንደ-ምድር ዘላይ ሰው ጫማ ከተሰመረው መስመር አልፎ ቢሾፍቱ/ ደብረዘይት ስለሚደርስ፤ አዲዮስ ነው። ሳምሶናችን!! በለፈለፉ በአፍ ይጥፉ ነውና፤ ከሰሞኑ የኮሚኒኬሽን ጽ/ቤትን ውሳኔ እንሰማለን።