ክንፉ አሰፋ

Semehal Meles

የአፈና ግዜ አዋጁን ተከትሎ፤ የህወሓቱ ፋና ብሮድካስቲንግ በወቅታዊ ጉዳዮች ዙሪያ ያስተናገደው "የውይይት መድረክ" አዳዲስ ኩምክናዎችን ይዟል። ልደቱ አያሌውን በመሪ ተዋናይነት ያሳተፈውን ይህን አዲስ የበረከት ስምዖን ድራማ ብዙም ሰው አላየውም። ህዝቡ ፋና ሚባል ነገር እንደሬት መርሮታል። ገሚሶች ደግሞ በ"ቃና"ው "ጥቁር ፍቅር" ድራማ ተጠምደዋል። በዚህ ድራማ ልደቱ አያሌው መሪ ገጸ-ባህሪይ ተላብሶ ይተውን እንጂ፤ እንደወትሮው ቀልብ ሊስብ አልቻለም። በኢትዮጵያ ታሪክ ወያኔ መድብለ ፖርቲን የፈቀደ ድርጅት እንደሆነ በሙሉ አፉ ሲናገር እሱ አላፈረም። ከሱ ይልቅ የተሸማቀቁት እነ በረከት እና ስብሃት ናቸው። በልባቸው አበስኩ ገበርኩ እያሉ ... ጌታዎቹ ኀዘን ሲሰማቸው እሱ ያለቅሳል። በዚህ አቋሙ ከሦስተኛው መንገድ ወደ አንደኛው የተሸጋገረ ይመስላል ልደቱ። ለነገሩ እንጂ፤ ለሱ መገለባበጥ አዲስ ጉዳይ አይደለም!

ልደቱ አያሌው ከተቃዋሚ ፓርቲ መሪነት ወደ ልማታዊ ባለሀብት እንደገባ ነበር የምናውቀው - የሀብቱ ምንጩ ግልጽ ባይሆንም። እንደ ፕ/ር ኤፍሬም ይሳቅ የህወሓት የመከራ ጊዜ ደራሽ እና አስተንፋሽ ለመሆን መጣሩ አይደንቅም። ህዝባዊ አመጹን ማውገዙ ግን ከኃይለኛ ማዕበል ጋር አላትሞታል። "ጥናታዊ ጽሁፍ" ያቀረበው የአስታራቂነትን ሚና ለመጫወት ከሆነም ማስታረቅ፣ የተበደለን ህዝብ እየኮነኑ አይደለም። ህወሓት ህዝብን በጅምላ ገድሏል። አንዴ የተገደለውን ህዝብ ደግሞ መግደል ምን ይሉታል? መጨረሻውን ፈጣሪ ያሳምርለት።

የዚህ ውይይት ዓላማ ግልጽ ነው። ችግሩን ከመፍታት ይልቅ በግብጽ እና ሻዕቢያ ላይ ጣት ማውጣቱ ያዋጣቸው አልመሰለም። ስለዚህ የተወጠረውን ለማስተንፈስ፣ የተለመደ አቅጣጫ ማስቀየስ፣ እና ህዝብን ለማዘናጋት መሞከር ከመጣር አልተኙም። በውይይቱ የተገኙትም አይነተ ብዙ ናቸው። ጉዳዩ የገባቸው፣ ጉዳዩ ያልገባቸው እና ግራ የገባቸው ሰዎች ተሳትፈዋል።

ኃይሌ ገብረሥላሴ እና ሳምሶን ማሞ የነበረከት ደባ በደንብ ከገባቸው ተሳታፊዎች ዋነኞቹ ናቸው። የኢትዮጵያ ችግር በውይይቱ እጅግ ተጋንኖ እንደቀረበ በቀልድ እያዋዛ ተናገረ ኃይሌ። አንዴ ተኑሮ ለሚታለፍባት ዓለም እንዲህ አጎብዳጅ መሆን ለምን እንዳስፈለገ አይገባኝም። የማያልፍ ነገር የለም። ይህ ሥርዓትም በእርግጠኝነት ያልፋል። እንደ ኃይሌ እና ቀነኒሳ ያሉ አድርባዮች ይህን ያከበራቸውን ህዝብ ነገ እንዴት ቀና ብለው እንደሚመለከቱት ወደፊት የምናየው ይሆናል። በፈጣሪ አምሳል የተሠራን ሰው አትግደሉ ብሎ የመናገር ሞራል ከሌላቸው፣ ዝምታም እኮ መፍትሄ እንኳን ባይሆን አማራጭ ነበር። ዝምታ ወርቅ ነው። እነሱ ግን እንደበቀቀን ህወሓቶች የሚሉትን የ"መልካም መስተዳደር" አሲዮ ቤሌማ ደጋግመው ይዘፍኑልናል።

ሳምሶን ማሞ ሲናገር የክበበው ገዳን አዲስ ቀልድ ያስታውሳል።

በአሜሪካ ሀገር ዋይት ሃውስ በር ላይ ቆመህ "ኦባማ ይውረድ" እያልክ ብትውል የሚነካህ የለም። ሲባል የሰማው ክበበው ገዳ፤ እኛስ ሀገር ቢሆን አራት ኪሎ ቤተ መንግሥት በር ላይ ቆመህ "ኦባማ ይውረድ!" እያልክ ብትጮህ ማን ይነካሃል? ብሎ ነበር ክበበው ገዳ።

"እኔ አቶ በረከት ስምዖን ቢሮ ገብቼ እንደፈለኩ ተሳድቤ እወጣለሁ። ይህንን ያህል ነፃነት አለ።" ይለናል፤ ይህ የሥርዓቱ ተደጋፊ ሳምሶን ማሞ። አዎ! ይህ ሰው ይሳደባል። አቶ በረከትን ቢሮ ድረስ ሄዶ ተሳድቦ ቢሆን ኖሮ ግን 34 ጥርሶቹን አናያቸውም ነበር። ደፋሩ ሳምሶን ባለፈው ሣምንትም በዚሁ መድረክ ላይ ቀርቦ ህዝብን በጅምላ ተሳድቧል። አቶ በረከትን ሊሳደብ እንደማይችል ግን ሕጻን ልጅም ይገምታል። የሚደንቀው ታዲያ በስድብ እና በመብት መካከል ያለውን ልዩነት እንኳን አጥርቶ የማያውቅ ይህ ሰው፤ መድረኩን ይዞት ሲቀልድ ማየቱ ነው። እርግጥ ነው። ዝሆን ላይ የሚጮህ ሞኝ ውሻ ብቻ ነው። ሆድ ከፊት ለመሰለፍ አይፈራም ይሉ የለ አፍሪካውያን።

ህዝብ መሬት ላይ ነው። እነሱ ሰማይ ላይ። መሬት ላይ የተኛ ግዜው እስኪያልፍ ሊረጋገጥ ይችላል። መሬት ላይ የተኛ እወድቃለሁ ብሎ አይሰጋም። ዛሬ ሰማይ ላይ ያሉት ግን እዚያው አይቀሩም። ነገ መውረዳቸው የተፈጥሮም ሕግ ነው።

የመለስ ዜናዊ ልጅ ሰመሃል መለስ ግራ የተጋባች ተሳታፊ ትመስላለች። ግን አጠር ብላ የረዘመች መልዕክት አላት። በህወሓት ውስጥ ያለውን የሥልጣን ሽኩቻ ብቻ ሹክ ብላ አላለፈችም። ሥልጣንችሁን ላለማስነካት ከምትንደፋደፉ ሥልጣኑን ለኛ ስጡን ብላለች።

አባትዋ ከማለፉ በፊት ስለመተካካት ብዙ ተናግሮ ነበር። ሰመሃል ይህንኑ ቃል እንደ ፈጣሪ ቃል አምና ተቀብላለች። ይህ ብቻ አይደለም። የህወሓት ሥልጣን እንደ ርስትና ጉልት በውርስ እየተላለፈ ይቆያል ተብሎም ተነግሯታል። ጸጉርዋን የሽፍታ አስመስላ ሥልጣኑን ከነበረከት ለመቀበል ብዙ የጠበቀች ነው የሚመስለው። በዚያ ሰሞን ጠመንጃ ይዛ የተኩስ ልምምድ ስታደርግ የተነሳችው ፎቶም ተለቆ ነበር። ይህም በህወሓት መመዘኛ ከርክክብ ቅድመ ሁኔታዎቹ አንዱ መሆኑ ነው።

የመተካካት እና የቅብብሎሹ ወሬ ከአቶ መለስ ጋር ተቀብሮ በጥልቅ ተሃድሶ አዲስ ዜማ መተካቱን ግን ሰመሃል የሰማች አይመስልም። ይህች ወጣት ስብሰባው ላይ የተሳተፈችው የእናቷ አዜብ ጎላን ሐሜት ይዛ ነው የሚለው ንግግራቸው የሚያስኬድ ቢሆንም፤ መልዕክትዋ ግን ግልጽ ነው። እስዋም ገና የለውጥ ሳይሆን የጥገና መፍትሔ ላይ ናት።

እንደ ሰመሃል ነገሮችን ሳያላምጡ እየዋጡ፣ ቅዠት ሁሉ ህልም መስሎ እየታያቸው፤ ህወሓትን እንደ ንጉሣዊ ሥርዓት ለማስቀጠል የሚፈልጉ ደፋሮች ጥቂት አይደሉም።

ዶ/ር መረራ ጉዲና እና ኢንጅነር ይልቃል በዚህ ስብስብ የተሳተፉበት ምክንያት ግን አልገባኝም። ድራማውን ለማሟሟቅ ካልሆነ በስተቀር የእነሱ በዚያ መገኘት ፋይዳ አይታይም። እርግጥ ነው ሁላችንም ይህንን ውይይት እንድንመለከት ያደረገን የእነሱ መሳተፍ ነበር። ግና ከምርጫ ክርክር ግዜ የተናገሩትን ያህል እንኳን በዚህ ውይይት ሲናገሩ አልሰማንም። እነሱ እዚህ እያወሩ ባሉበት ቅጽበት ኣግአዚ ጦር በጠራራ ፀሐይ የቤት ለቤት ዘረፋ፣ አፈና እና አስገድዶ መድፈር ላይ ተሰማርቷል። ከውይይቱ በፊት - እንደ ተቃዋሚ ፓርቲ መሪ ቅድመ ሁኔታዎችን ማስቀመጥ ነበረባቸው።

ህዝብ ጥገና ወይንም ተሃድሶ ሳይሆን ለውጥ ነው የፈለገው። ህወሓት፣ የማይታደስ፣ የማይሻሻል፣ ከስህተት የማይማር እንደሆነ ብዙ ግዜ ነግረውናል። ጅምላ ግድያ እየፈጸመ ካለ ከዚህ ሥርዓት ጋር ቁጭ ብለው ዲስኩር ማድረግ ምን ሊጠቅም እንደሚችል ከእኛ በላይ እነሱ ያውቁታል። ህዝብ እና ህወሓት የማይታረቅ ቅራኔ ውስጥ በገባበት በዚህ ወሳኝ ወቅት፤ እነሱ ራሳቸው የውይይት ግዜ አብቅቷል ሲሉ የሰማን መስሎኝ ነበር። በረከት ስምዖን እና ልደቱ “ብቃት ያለው ተቃዋሚ ልንፈጥር አልቻልንም” የሚሉን ይህንን እያስተዋሉ ይሆን?

አቦይ ስብሃት እንደተባለው ቀምቅመው መድረክ ላይ ይውጡ እንጂ፣ የሚናገሩት ሁሉ ቅኔ አዘል ነበር። ሰምና ወርቅ ያለው ቅኔ። "መረራ እና ይልቃል ጓደኛሞች ናቸው። የፖለቲካ ፓርቲ አይደሉም!" ያሉት ያለምክንያት አልነበረም። ያንን ሁሉ ተናግራችሁ ስታበቁ እዚህ በኛ ጉባዔ ላይ ምን ትሠራላችሁ? ማለታቸው ይመስላል። ሆድ ያባውን ብቅል ያወጣዋል እንዲሉ፤ ህወሓት ለፍትህ እንጂ ለድርድር እና ለውይይት የሚቀርብ ሥርዓት እንዳልሆነ ነው የቅኔው ወርቅ የሚጠቁመን። የህወሓት መክሠም እና መጥፋት ምኞታቸው መሆኑን የማብሰራቸው ቅኔ ግን ሰምም ሆነ ወርቅ የለውም።

ሽማግሌው ስብሃት ቀጠሉ "እናንተ ህዝቡን አታውቁትም። እኛ እንኳን ግማሹን የኢትዮጵያ ህዝብ አናውቀውም!" ብለው አረፉ። የማያውቁትን ህዝብ ለ25 ዓመት የሙጥኝ ይዘውት ኖሯል።

"ከፊትህ የሚጠብቅህን መንገድ ለማወቅ ተመላሾቹን ጠይቅ።" ይላሉ ቻይናውያን። ላስተዋለው ትልቅ አባባል ነበር። ለተሞክሮውም የደርግ ውድቀት ብቻ በቂ ነው። እነሱ ግን ከታገሉት ደርግ በመቶ እጥፍ ብሰው ተገኙ። ወትሮውን ቁጭ ያሉበት መጥበሻ ሲግል እንደማሽላ መፈንዳት ግድ ነውና እስከመጨረሻው እስትንፋሳቸው ይናገራሉ። እኛም እንደ ኮሶ እያንገሻገሸን የሚሉትን መስማቱን አልተውንም።

... በሚቀጥለው ጽሁፌ ስለአፈና ግዜ አዋጁ እና ስለ ኣግአዚ የምለው አለኝ። እስከዚያው ቸር እንሰንብት።

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ