ማነህ ባለሳምንት? የ“መሪ” ወርተራ
አስፋ ጫቦ
እንደመግቢያ
የኦርቶዶክሶች ማኅበር ቤት ወር ተረኛውን ለመመደብ ዳቦ ከተቆረሰና መውጫ ሲቃረብ ሙሴው ይነሳና፤
ማነህ ባለሳምንት?
ያስጠምድህ ባስራ ስምንት
እኔ ነኝ የምትል የቅዱስ ገብርኤል ወዳጅ ይላል።
ገብርኤሉ እንደማኅበራቸው ታቦት ሥም ይቅያየራል። ተራኛው ይቆምና የሚባለውን ብሎ ጽዋውን ይረከባል። ይህ እውደት በየወሩ ቋሚና ቀጣይ ነው። ከልጅነቴ ያስታወስኩት ነው። እዚህም፤
ማነህ ባለሳምንት?
እኔ ነኝ የምትል ሴራ ወዳጅ ማለት የሚቻል ይመስለኛል።
ማኅበሩ ወርሐዊ ነውና በየወሩ ተረኛው ደጋሽ ቤት ይሔዳል። በፓርቲዎች ውስጥ ያለው ሹምሸር የዚህ አይነት ባሕርይ የሚያጣ አይመስለኝም። ግቡ፤ መንፈሳዊነቱ፣ ዓለማዊነቱ፣ ሰላማዊነቱና ሴራነቱ እንደተጠበቀ ሆኖ ነው።
የምጽፈውን የምጽፈው ብልጭ ሲልብኝ ወይም ሲልልኝ ነው። አብዛኛው! እንጅ ይህንን እጽፋለሁ፤ በዚህ ጉዳይ ላይ እጽፋለሁ የሚል ዕቅድ ኖሮኝ የሚያውቅ አይመስለኝም። ግብታዊነት የሚሉት ሥር የምመደብ ይመስለኛል። ይህም የተጻፈው በዚሁ አይነት ነው።
ማኅበራዊ ገጽታዎች በተለይም Facebook ትልቅ ትምህርት ቤት ሆኖኛል። አገር ተሰብሶቦ ሲያወጋ የሚያድረውንና የሚውለውን ማዳመጥ፣ አንዳንዴም በወጉ ውስጥ ወጣ-ገባ ይመጣል። Facebook ከገባሁ/ከተቀላቅልኹ ሁለት ዓመት ሁኖኛልና። ”እንኳን ደስ ያለህ!” መልዕከት አንድ ቀን ይህንኑ ከFacebook አግኝቼ ሳኩኝ። እኔ የማላስታውሰውን አስታውሶ የሚነገርኝ “ወዳጅ”ም አለኝ ማለት ነው።
አገር ተሰብስቦ ያወጋል ብያለህ። አገር ደግሞ ሰፊ ነውና ብዙ ነገር ያቅፋል። ከዚህ ውስጥ ጥሩ፤ መጥፎ፤ አስጸያፊም አለ። ፈርንጅ The Good, The Bad, and the Ugly እንዲል! “ሆድ ከአገር ይስፋል!” ብሎ መጓዝ ነው። ወይ እንደፈረንጆቹ “ልዩነታችን ለዘለዓለም ይኑር!” (Vive la difference!) ብሎ መቀጠል! ነው።
እንግዲህ ”የሃሳብ ልዩነት” ሲባል “ጤናማ ልዩነት!” ማለቴ እንጅ አጸያፊውም “ለዘለ ዓለም ይኑር!” ማለት አይመስለኝም! እንደኔ እንደኔ አስጸያፊው አንድም ቀን አይደር! የFacebook ነገር ጥሩ ነው። አስጸያፊው ተመክሮ ተዘክሮ የማይመለስ ከሆነ ለማሰናበት 30 ሴኮንድ በቂ ነው ነው። ”ከዚች ሴኮንድ ጀምሮ ‘ወዳጄ’ አይደለሽም፤ አይደለህም!” ማለት ይቻላል። “Unfriend!” ይለዋል። “ተፋቱ!” ማለት ነው። በዚሁ መሠረት መክሬ- ዘክሬ እምቢ ያሉኝን ጥቂት “ፈተቼ” የለቀቅኳቸው አሉ።
የአሁኑ ጉዳይ
Facebook ከገጠምኩ ሁለት ዓመት ሆኖኛል ብያለሁ። ትምህርት ቤትም ሆኖኛል ብያለሁ። ከልቤ ነው! 5,000 ወዳጆች (Friends) አሉኝ! ብዙዎች ወዳጅ ሊሆኑ ጠይቀውኝ በFacebook “ያለህ ይበቃል!’ ስለተባልኩ አልጨመርኳቸውምና በዚህ አጋጣሚ ይቅርታ እጠይቃለሁ። ወዳጆቼ በአብዛኛው ወጣቶች ናቸው። በአብዛኛው ያሰኜኝን እንደነፕሮፌሰር መስፍን ወልደማርያም ያሉ አዛውንቶችም ስለአሉበት ነው።
የዚህ የኔ “ወጣት ወዳጆቼ” ነገር ይገርመኛል። ሁሉም ማለት ይቻላል “አንተና ጋሼ አሰፋ!” ነው የሚሉኝ። ልጆቼ አድርጌ ነው የምወስደው! ልጆቼም የልጅ-ልጆቼም “አንተ” ስለሚሉኝ!። እነሱ “አሴ!” ነው የሚሉኝ። እዚህም አሴ የሚሉኝ ጥቂት አሉ። አንድ አገር ሙሉ፤ ዓለም ሙሉ ቤተሰብ ያለኝ መስሎ ይሰማኛል! ደስ ደስም ይለኛል!። ጥያቄ ይጠይቁኛል። መልስም እሰጣለሁ። “ይህን አድርግ/አታድርግ”ም ይመክሩኛል። አንዳንዴ ውይይታቸውም ጫወታቸውም ውስጥ እገባለሁ። ሰሞኑን በተለየም ልደቱ አያሌውን ባንድ በኩል ሰማያዊ ፓርቲ በሌላው አድረገው ሲወያዩ ገባሁና አስተያየት ሰጠሁ።
የመጀመሪያው አስተያየት ይኸውና።
እኔ ከብዛታቸውም ይሁን የሚሉት በደንብ ስለማይገባኝ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ፓርቲዎች ላይ ምንም ከማለት ተቆጥቤ ኖርኩ። የዛሬ ሁለት ይሁን ሦስት ወር በፊት ዶክተር መረራ ጉዲናና የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር እዚህ አሜሪካ መሆናቸውን ሰማሁን ለሁለቱም ደወልኩላቸው። መረራን አውቀዋለሁ። ይልቃልን አላውቀውም። ሁለቴ መሰለኝ ያነጋገርኩት። ማነጋገር ከማለት ያዳመጥኩት ማለት ይሻላል። ብስለቱ፤ ጥልቀቱና እርጋታው በጣም ገርሞኝ በርታ! ተባረክ! አልኩት። ለለላምታና በርቱ ለማለት ብቻ ነበር የደወልኩት። ወዲያውኑ ወረደ ይበሉ፤ ተሻረ ወይም ተባረረ የሚል ሰምቼ “አይ የኛ ነገር!” ብዬ አዘንኩ።
አሁን ከኢዴፓ ጋር የሚባለው በሙሉ አይገባኝም። ዝርዘር መረጃ ስለሌለኝና ምናልባትም እንዳይኖረኝ ስለፈለኩም ሊሆን ይችላል። የማይሆን ነገር በሰማሁ ቁጥር ለጥቂት ደቂቃዎችም ቢሆን ያመኛል። ውስጤን!
ኢደፓ ልደቱ ያለበት ከሆነ ባለፈው አንድ ስብሰባ ላይ ልደቱ ሲናገር የሰማሁን የመንግሥት ወኪል ወይ ቃልአቀባይ የሚመስል ጠረን ነበረው ልበል?
እኔ ምን አውቃለሁ!
ሁለተኛም አስተያየት ሰጥቻለሁ። በሁለተኛው እኔን በግልም የሚነካ ተነስቶ ስለነበረ ነው። ይኸውና፤
በዚህ ዙሪያ የሚደረገውን ውይይት፤ በተለየም የጋላታ ጋሞና የኤደን መኮንን ተስማምቶኛል! ”የሠለጠነ ውይይት ወይም የሃሳብ መለዋዋጥ” (Civilized Discourse) መስሎ ታይቶኛል።
ከዚያ በፊት ግን ስለእኔ መጀመሪያ ከደርግ ጋር የነበረው ግንኙነት! እኔ የነበረኝ ግንኙነት ያ “የኢትዮጵያ ሕዝብ አብዮት ነው!” ብዬ ሙሉ ለሙሉ አምኜበት ነው። ነውም!! የኢትዮጵያን ሕዝብ ከዘመናት ባርነት ነጻ አውጥቷል። ኢትዮጵያን ሪፐብሊክ አድርጓል። ከዚያ በኋላ በዋናነት በአመራር፤ በተለይም በመንግሥቱ ምክንያት አሰቃቂና አሳዛኝ በደል በኢትዮጵያ ሕዝብ፤ በተለይም በወጣቱ ላይ ተፈጽሟል። ለዚያም ተጠያቂ ናቸው የተባሉት ዋጋውን በእስራት ከፍለዋል። ፋይሉ አንድ ቀን አንድ ቦታ መዘጋት ያለበት ይመስለኛል። ያለበለዚያ ሁሌ ሙሾ ያወርድና እንደሁ የአሁኑን ያስተናል ብዬ እፈራለሁ።
በተለየ እኔን በሚመለከት! ከተወሰነ ቀን በኋላ ድጋፌን አቆምኩ። ይህንኑ “የኢትዮጵያ አብዮት ከየት ወዴት? ትላንት፤ ዛሬና ነገ!” የሚል ወደ 30 ገጽ የሚደርስ ጽፌ አሰራጨሁ። ነጻነት ቅጽ 1 ቁጥር 1! ለዚያም ወደ 11 ዓመት ታሰርኩ። ያ ፋይሉን የሚዘጋልኝ መሰለኝ።
ልደቱን በሚመለከት በ97 ምርጫ ሰበብ በሚደረገው ሁካታ ምክንያት email ሁሉ ተለዋውጫለሁ። እስቲ ለምትከሱቱ ማስረጃ አቅረቡ? ብዬም የጻፍኩ ይመስለኛል። ስለዚህ የልደቱን ጉዳይ የማየው በጅምላ መልክ አይደለም ለማለት ነው።
ያኛውን ወይም ይህኛውን ድርጅት ለምን አትደግፍም? ለተባለው ሲመች “አንተም ተው! አንቺም ተይ!” የሚል ሽማግሌ ያስፈልጋል በሚል ምክንያት ይመስለኛል።
ይህ “የሠለጠነ ውይይት” ጥሩ ነው፣ አድማሱን ሰፋ ብታደርጉት ጥሩ ይመስለኛል። ሰፋ ማድረግ ማለት ይህ እርስ - በርስ መባላት በ97 ምርጫ ጊዜም ሆነ በደርግ ዘመን ያደረገውን አይቶ ዘለቄታው ምን ይመስላል? የሚል አንጻር መጨመር ማለት ነው።
ስለ ልደቱ አሁን የሰጠሁት አስተያየት በውይይቱ ላይ የሰጠውን አስተያየት ጠረኑን ስለ አልወደድኩት ነው። “መስሎ መታየት” ሌላ ትርጉም መስጠቱ ያለ ነውና! Pereception is Reality የሚሉት!
እዚህ ከላይ በለጠፍኩት “... እኔ ከብዛታቸውም ይሁን የሚሉት በደንብ ስለማይገባኝ ኢትዮጵያ ውስጥ ያሉት ፓርቲዎች ላይ ምንም ከማለት ተቆጥቤ ኖርኩ። የዛሬ ሁለት ይሁን ሦስት ወር በፊት ዶክተር መረራ ጉዲናና የሰማያዊ ፓርቲ ሊቀ መንበር እዚህ አሜሪካ መሆናቸውን ሰማሁን ለሁለቱም ደወልኩላቸው። መረራን አውቀዋለሁ። ይልቃልን አላውቀውም ...” በሚለው ልጀምር መሰለኝ።
ልወቅ እንኳ ብል ለማወቅ የሚያስቸግር ይመስለኛል። “ዘጠና የፖለቲካ ፓርቲዎች ተመሥርተዋል ይሁን ተፈልፍለዋል” የሚል ነገር ያነበብኩ ይመስለኛል። በጥንቃቄ ነው ያማበነው! ጥንቃቄው ለአገሬ ብቻ አይመስለኝም። ለጤንነቴም ጭምር ይመስለኛል። ጠለቅ ብየ ለማወቅ ብፈልግ፤ የሚጠለቅበት ጥልቀት አለው ብለን ብንገምት እንኳ፤ መንፈሴን የሚረብሸው ይመስለኛል።
ለመሆኑ ምኑ ነው መንፈስ የሚመረብሸው? ወይም ሊረብሽ የሚችለው? ጥሩ ጥያቄ ነው! ዘጠና ፓርቲዎች ተመሠረቱ ተባለ። ለዘጠና ፓርቲ የሚሆን የፖለቲካ ጽንሰሃሳብ (Theory) ከየት ሊመጣ ነው? ሁሌም፤ አሁንም ያለው የፖለቲካ አስተሳሰብ የቀኝ ፖለቲካ፤ የመሀል ፖለቲካና የግራ ፖለቲካ ነው። እርግጥ “ጽነፈኞች” (Extrimists) የሚባሉ የግራም የቀኝም አሉ። ጽንፈኞች ቁጥራቸውም ተሰሚነታቸውም ከቁጥር የማይገባ ስለሆነ “ጤና-ያጡ ግለሰቦች መሰባሰቢያ” ተደርጎ ይወሰድና የሚያተኮርበት የለም። የሚተኮርበትም አይደለም። እርግጥ ዛሬ ያለፈ በደል ክምር ገንፍሎ፤ የኃይማኖት ሸፋን ሁሉ ወስዶ አስፈሪ ሆኗል። ያም ቢሆን ያው ጽንፈኛ ናቸው። አሁን በፈነዳው የሕዝብ ቁጣ ሳቢያ፤ ዛሬ ኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ “ጽንፍና መሀል” መለየት አጉልቶ የሚያሳይ መነጽር ሳያስፈልግ የሚቀር አይመስለኝም። አንዱ ይህ ይመስለኛል ገሸሽ እንድል ያደረገኝ። “ዘጠና ድርጅቶች” የሚባል ነገር ሊኖር አይችልምኮ! የለምኮ! አይገባምኮ! “በአንድ አፍ ተነጋገሩ ወይም መነጋገር ትችላላችህ!” ብሎ፤ መክሮ፤ ገስጾ፤ ተማጽኖ ማቀራረብ ለኔም ሆነ እንደኔ ላለው ተራ ተርታ ሰው (The average person) ከባድ የቤት ሥራ ይመስለኛል።
ሌላው የታየኝ ችግር “እሽ ዘጠና ሁኑ! ለመሆኑ ልታሳፍሩን የምትፈልጉት አህያ፤ በቅሎ፤ ፈረስ፤ ጋሪ፤ ታክሲ፤ አውቶቡስ፤ ባቡር፤ አውሮፕላን ወይም መርከብ የትና ወዴት ሊወስደን፣ ሊያደርስን ነው?” የሚለው ጥያቄ ግልጽ አይደለም። ለኔ አይደለም! ዓላማችን፤ ግባችን፤ አድማሳችን የማያሻማ የተማረ የተመራመረውም ሆነ ከተሜው፤ ገጠሬው ወጣት ሽማግሌ አስተርጓሚ ሳይፈልግ መረዳት የሚገባው መሆን አለበት። መልዕክቴ ግልጽ ካልሆነ የሰሚው፤ የአድማጩ ችግር አይመስለኝም። የተናጋሪው፣ የአቅራቢው እንጅ።
ሌላው ድፍን አገር የሚያውቀው ላይ ከሚገባው በላይ ትኩረት የሚሰጠው ይመስለኛል። ወያኔ በሉት ኢሕአዴግ እቡይ መሆኑ የአደባባይ ሚስጥር ነው። ዛሬ ሳይሆን ሕዝቡ ከግንቦት 1983 ጀምሮ የሚያውቀው ነው። እዚያ ላይ ብርቱ ጊዜ የሚባክን ይመስለኛል።
ከዚህ ጋር አብሮ የሚሔደው ክስና ውቅስ፤ ዛሬም ያልተቋጨው “ይኸኛው ወያኔ ሰርጎና አስርጎ ያስገባው ግለሰብ ነው፤ ድርጀት ነው” የሚለው ጣት መቀሰር ነው። የአስርጎ ማስገባት ነገር ዓለም አቀፋዊ መሆኑንም ባላውቅም በየአገሩ የነበረ፣ ያለ፤ የሚኖር ነው። እዚህ አሜሪካም አለ። በቅርቡ እንግሊዝ አገር በዚሁ ጉዳይ የሌበርና የኮንሰርቫቲቭ ፓርቲ ይሁን ሌላ ሲካሰሱ ነበር። ይልቅስ የሚደንቀው ወያኔ ሰርጎ ወይም አስርጎ ባያስገባ ነው። “ወያኔ እንዲህ አድርጎ እንዲህ ሆንን” ማለት ወያኔ በፖለቲካ ጥበብ፤ ተክኒክና ታክቲክ ይበልጠናል፤ በልጦናል ብሎ እንደማመን ይመስለኛል። ቡሐቃዋን በቅጡ አትከድንምና ሁሌ በድመቷ ወይም ውሻው ላይ እንደምታማርረው የቤት እመቤት የሚመስል ነገር ያለው ይመስለኛል። በሩን ሊዘጋ የሚችለውን ያክል መዝጋት ነው። ካልተቻለ በዚያም ይሁን በዚያ ለዚህ የጨዋታ ሜዳ ብቁ ሆኖ አለመገኘትንም የሚጠቁም ይመስለኛል። ”ለተቀማጭ ሰማይ ቅርቡ ነው!”ንም አውቃለሁ።
ሴራው
የ1997 አገር አቀፍ ምርጫ ውጤትና ያንን ተከትሎ ተቃዋሚ ፓርቲ ነን የሚሉት ያደረጉት አልገባኝም። ሊገባኝ የሚችልም አይመስለኝም። ያንን በሚመለከት በወቅቱ ተዋናኝ ከነበሩት አንዱን የተቃዋሚ ድርጅት መሪ በስልክ ለማነጋግር ሞክሬ መልስ አላገኘሁም። የሚመስል መልስ አላገኘሁም ማለት የሚሻል ይመስለኛል። ምርጫውን አሸነፉኮ! በአገር አቀፍ ደረጃ ከ200 በላይ መቀመጫ ያገኙ ይመስለኛል። ያም ይቅር አዲስ አበባን፤ የኢትዮጵያን ዋና ከተማ፤ የአፍሪቃን ዋና ከተማ፤ የተባበሩት መንግሥታትን ዋና ከተማን ሙሉ ለሙሉ አሸነፉኮ! ገቢናው መሪው፣ ሹፌሩ (The Driver’s Seat) ያለውኮ አዲስ አበባ ከተማ ነው! ለኔ ማመን የተሳነኝ ድል ነበር።
ከምርጫ በኋላ በአብዛኛው አወዛጋቢ ጥያቄ ይነሳል። የትም ሁሌም ያለ ጥያቄ ነው። ውዝግቡን ለመፍታትም የታወቀና የተረጋገጠ የሌሎች አገሮች ተሞክሮም አለ። የኢትዮጵያ ተቃዋሚ ፓርቲዎች ያንን የተጠራቀመ ልምድ አልተጠቀሙበትም። ሊጠቀሙ አልፈለጉም ወይም ከነአካቴው አያውቁትም ማለትም የሚያስችል ይመስላል። የሚያማርሩበት ነገር እንኳ ቢኖር፤ በኔ አስተያየት፣ ይህን ያክል የሚያማርር ነጥብ የነበር አልመስለኝም፤ የታወቀው ”ብልጥ ልጅ የሰጡትን እየበላ ያለቅሳል!” የሚለው መመሪያ እንደ ሀ ሁ መታወቅ የነበረበት ይመስለኛል። የወሰዱት አማራጭ ትላንትና የመረጣቸውን ሕዝብ “እስቲ ፓርላማ እንግባ አንግባ!?” ምን ይመስላችኋል!?” ብለን እንጠይቅ የሚል ነበር። ውጤቱ “የቆጡን አወርድ ብላ የብብቷን ጣለች!” ሆነ። በብዙ መቶ የሚቆጠር ሕዝብ ለሞት ተዳረገ። መሪዎቹ የተባሉት ከርቼሌ ወረዱ። “አስታራቂ ሽማግሌ!” የሚባሉ ከመለስ ዜናዊ ፋብሪካ ተፈለፈሉ። መሪዎቹ መለስ ዜናዊን ይቅርታ ጠይቀው ተፈቱ። ያ የኢትዮጵያ ሕዝብ ያንን ሁሉ ጥይትና ዱላ ችሎ ተዓምር በሚመስል መንገደ ያገኘው ድል ከንቱ ሆነ። ለዚህ አይነት ክህደት እንኳን ባይባል አላአዋቂ ሥራ ተጠያቂ፤ ተጠያቂው(ዎች) ማነው? እነማናቸው? የሚለው መልስ ያገኘ አይመስልም። ከሆነም እኔ አልሰማሁም። አንድ አርግጠኛ ነገር አለ። ወያኔ ዘላቂ ትምህርት፣ ”ይህችን ስህተት አንደግማትም!” የሚል ትምህርት አግኝቶ ተግባራዊ አድርጓል። የምርጫውን በር ዘግቶ ቁልፉን ወረወረው! የተቀረነው የተማርንበት አይመስለኝም።
ሌላ ተያያዥ ጥያቄ መጠየቅም የምንችል ይመስለኛል። ወያኔ የተማረበት የሚመስለውን ዞር ብለው ሲያዩት ጊዚያዊ ይመስላል። ባሰበት እንጅ አልተማረበትም። ዛሬ የውስጥ አዋቂዎች ነን የሚሉ እንደሚነግሩኝ (ለነገሩ የማናውቀው ውስጥ ያለ ይመስል) “ብትፈልግ ወያኔ፤ ብትፈልግ ኢሕአዴግ በለው የሚባል ነገር የለም። ተከስክሷል! ጥላው ነው ያለ የሚያስመስለው። እያንዳንዱ የኢሕአዴግ አካል አምሳል ነኝ ተብዬው ውስጡ ሦስት ወይም አራት ቦታ ተፈረካክሶ ያለመልሕቅ ይዋዥቃል” ነው የሚሉኝ። በእርግጠኝነት ያላቸው ነገር ቢኖር አፈሙዙ ነው። ተቃዋሚ ድርጅቶች የሚባሉት ያው የዛሬ ስንት ዓመት ሲሠሩት የነበረውን ያንን የውስጥ አድማ እንበለው ሴራ ቀጥለውበታል። ትላንትን ዛሬ አድርገውታል። ይህ፤ ለዚህ መነሻ የሆነኝ የኢዴፓና የሰማያዊ ፓርቲ በአደባባይ መናቆር ትላንት አሁንም ትላንት ሳይሆን ዛሬ መሆኑን የሚያሳይ ይመስለኛል።
እንዳልኩት እኔ የአሁኑን ድርጅቶችም ሆነ መሪዎቻቸውን አብዛኞቹን አላውቃቸውም። ዶክተር መረራ ጉዲናን አውቀዋለሁ። ቢያስሩት “ኧረ እባካችህ ፍቱት!” ብዬም ጽፌያለህ። ዶክተር በየነ ጴጥሮስን ትንሽ የማውቀው በአብዛኛው የማላወቀው ይመስለኛል። የዶክተር በየነ ስም ሲነሳ ሱሳን ሳረንደንን (Susan Sarndon 1995) ያስታውሰኛል። የዛሬ ስንት ዓመት (1995) Dead Man Walking የሚል ፊልም ውስጥ ዋንኛዋ ተዋናይ ነበረች። “በቁሙ የሞተ!” እንደማለት ነው። በቁሙ ሞቶም ሙቱ ሰውም ግና ነፍሱ አልወጣታችምና ፊልሙ ውስጥ ይታያል። እውነተኛ ታሪክ ላይ የተመሠረተ ፊልም ነበር። ዶክተር በየነን የሚመሳሰልብኝ ያንን ሁሉ ድርጀት፤ በተለይም የደቡብን ሕብረት ቀብሮ፤ አባላቱን አሳዶ ዛሬም እዚያው መኖሩ ነው። ልጅ ሆኜ ጨንቻ መሰለኝ የሰማሁትን የልጆች ዘፈንም አስታወሰኝ። ”እዚያ ነሽ ዛሬም እዚያው ነሽ? አስሮ የሚገርፍሽ ዘመድም ያለሽ ዛሬም እዚያ ነሽ!” ይሉ ነበር። ከዚህ ሌላ እንጂንየር ይልቃልን በስልክ ሁለቴ አነጋግሬአለሁ። ብርቱካን ሚደቅሳን አሁንም አነጋግራታለሁ። በጥሞና እንደተሳታፊ፤ እንደሕግ ባለሙያም ያኔ የሆነውን፣ ለእስራትና ለስደት ያበቃትን ከሁለት ዓመት በፊት አውግታኛለች። ከልጆቼ እንደአንዷ አያታለሁ። ልደቱን በካል አላውቀውም። የዛሬ ስንት ዓመት (March 8, 2006) ምርጫው ውስጥና ውጭ ስለሆነው ነገር የጻፈውን መጽሐፍ አንብቤ፤ ወድጀው፤ Email አድርጌለታለሁ መልስም (03/27/2006) ሰጥቶኛል። እውቀቴ ይህችው ነች!
የአሁኑ ውዝግብ ዘመነ ደርግን ያስታውሰኛል። በየቀኑም ባይሆን በየሳምንቱ አዲስ ድርጅት ወይም ስንጣቂ ተመሥርቶ ወረቀት ይበትንና ያንን አገኘው ነበር። የሚደራጅ ሳይሆን የሚፈለፈሉ የሚመስል ነገር ነበረውና “ማለቂያ የለውም እንዴ!” የሚያሰኝ ነገር ነበረው። እንዳያልቅ የለምና እንዳይሆን ኹኖ አለቀ። ከዚያ ዘመን ዛሬም ቢሆን፣ አልፎ አልፎ፣ “አለና!” የሚሉና ሙሾ የሚያወርዱ “በቁሙ የሞቱ!” አያለሁ፤ እሰማለሁም። እኔ የማስታውሰው የመጨረሻው “የሰንጥቅ” ደርጅት መሥራች ዶክተር አለሙ አበበ መስለኝ። “ቀይ ባንዲራ!” ነው ያለው? የመኢሶን ግንባር ተዋናይ ነበርና፤ መኢሶን ላይ ጀንበር ሲያዘቀዝቅ ሲ አይቶ መሰለኝ ቀይ ባንዲራ ያነሳው። ለሱም አልበጀውምና ከርቸሌ ወረደ።
ለምናውቀውም ለማናውቀውም ዝርዝሩ ብዙ ነውና አልገባበትም። ብፈልግም የምችል አይመስለኝም። አልበርት አይንስታይን (Albert Eienstein) ብሏል ያሉትን እደግማለሁ። ”ያንኑ እየመላለስ ግን ከቅድሙ የተለየ ወጤት አገኛለሁ ብሎ የሚያምን እብድ ብቻ ነው!” የኛም ሰው ይህንኑ ይላል። “አብዷል እንዴ! አብዳለች እንዴ!” ይህንን የሚሉት ተመክሮም ተዘክሮም የማይመለስ ሰው ሲያገኙ ነው።
አሁን ያሉት ድርጅቶች ከሌላው ዓለም ተሞክሮ አለመማመር ብቻ ሳይሆን፤ ባለፈው 50 ዓመታት በኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ከሆነውም አልተማሩም። ከሌላው ስህተት አለመማር ብቻ ሳይሆን ተትላንት ጥዋት ራሳቸው ከሠሩትም የተማሩ አልመስለኝም። አንድ ሌላነገር፤ ከወጣንበት፤ ከመጣንበት፣ የተሻለ ቀንም እናመጣልሃለን ከምንለው ከኢትዮጵያ ሕዝብ የአኗኗርና የአደረጃጀት ታሪክም የምንማር አልመሰለኝም። ኢትዮጵያ ውስጥ ለምሳሌ ያክል እቁብና እድርን እንውሰድ። የአንድ እቁብ ወይም እድር ዳኛ “እባክችሁ ደክሞኛልና ሌላ ዳኛ እንፈልግ!” ብሎ ለምኖ ነው ከዳኝነቱ የሚነሳው። ከሥልጣኑ ማለት ነው!! ከዚህ የምንማረው ቢኖር ጀማው፤ የእድሩ ወይም የእቁቡ አባላት በዳኛቸው ላይ ሙሉ እምነት አላቸው ማለት ነው። ይህንን ማለት ደግሞ መጀመሪያውኑ የሚሆናቸውን፤ የሚያዘልቃቸውን ሰው አይተውና፤ ለየተው መርጠው ነበር ማለት ነው።
ይህ በየሳምንቱ የፖለቲካ ድርጅት መሪ መለዋወጥ የሚያመጣው ሌላም ችግር ያለው ይመስለኛል። የድርጅቱን ተቀባይነት ያሳጣል። አንድ የሕዝብ ስበሰባ ላይ ባለፈው ሰኞ አሰፋ መሪ ነኝ ብሎ መጥቶ፤ የአሁኑ ሰኞ ከበደ መሪ ነኝ ብሎ ቢመጣ፤ ሕዝቡ ግራ የሚጋባ ይመስለኛል። “ስምህን ማን አልከኝ? ያ አሰፋ የተባለው ሰውዬ አልነበር አለቃችሁ?” የሚልና የመሳሰሉ ጥያቄ ያስነሳል። የመሪና የድርጀት ስም አብሮ አጣምሮ ማየትና ማወቅ አለ። Name Recoginition የሚሉት ነው። ይህ በተለዋወጠ ቁጥር ሕዝቡ፤ ደጋፊ የሆነውም ያልሆነውም ይህንን ነገር “የልጅ ጫወታ አደረጉት እንዴ?” ማለቱ የማይቀር ነው። እኔም እላለሁና!
የኦርቶዶክሱ ካሕን ሲያሳርግ በሚለው ልቋጭ መሰለኝ። ”ዘሀለፈ ሥርየት ወለዘይመጽእ እቅበት!” ይላል። “ላለፈው ምህረትን ለመጪው መቆጠብን ይስጣችሁ!” ማለት ነው። መቆጠብ ማለት ደግሞ ያንኑ አለመደጋገም ማለት ነው።
ካህናቱ “ገዝቻለሁ!” የሚሉትም አላቸው። ይህ የሚሆነው ተመክሮ ተዘክሮ አልመለስ ያለውን ዳግም እዚያች ቦታ/ድርጊት ድርሽ እንዳትል ብሎ ቁልፍ መቆለፍ ማለት ነው። መጽሐፉ ውስጥ “ያሰራችሁት የታሰረ፣ የፈታችሁት የተፈታ ይሁን!” የሚል ሥልጣን ተሰጥቷቸዋልና ነው።
አወይ ያ ሥልጣን ቢኖረኝ!



