የደሴ ህዝብ - ተረኛው የመስዋዕትነት ጠቦት? (መሣፍንት)
መሣፍንት ዘፈረንሣይ ለጋሲዮን (አዲስ አበባ) ( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ) ሐምሌ 2001 ዓ.ም.
ከሣምንታት በፊት ያደመጥኩት አንድ ዜና በርካታ ነገሮችን ወደ አዕምሮዬ እያመላለሰና ከዚህ በፊት ተሰምቶኝ የማያውቅ ስሜት በውስጤ እየፈጠረ ፋታ ሲነሳኝ ይህችን ወረቀት ጫጭሬ የተሰማኝን ለወገኖቼ ባካፍልስ ብዬ አሰብኩና ብዕሬን አነሳሁ።
ዜናውን አብረን አድምጠነዋል፤ የኔኑ መሰል ስሜት በውስጣችሁ የፈጠረባችሁ በቁጥር ቀላል እንደማትሆኑ ግምቴ ነው። ፈልጌው ሳይሆን ፈልጎኝ የመጣው ወሬ የቤተሰቤን ታሪክ፣ የግል የሕይወት ልምዴን፣ ሁሌም የምናፍቀውን የወላጆቼን የትውልድ ስፍራ፣ የክርስትያንና የሙስሊም ዘመዶቼን አብሮ የመኖር ዘይቤ፣ ከሁሉም በላይ ደግሞ የአብሮ አደጌን የሰይድን ወንድምነት እያስታወሰኝ በጊዜም በቦታም ሩቅ ይዞኝ ነጎደ።
ተወልጄ ያደኩት አሁን በምኖርባት በአዲስ አበባ ከተማ ቢሆንም ወላጆቼ ስለፈለቁባት ስለወሎ ሰው ፊት ይዤ የምቀርበው እውቀት አላጣም። ለመጀመሪያ ጊዜ ወደ ወሎ የሄድኩት ዕድሜዬ 16 ዓመት ሲደርስ ቢሆንም፤ በየጊዜው ከወደዛው ብቅ እያሉ ከሚጎበኙን ዘመዶቻችን ጋር አብሮ እየመጣ ሲያውደኝ ከኖረው የአካባቢው ህዝብ ፍቅር እንዲሁም አብሮ የመኖር መዓዛ እየተማረኩ አድጌአለሁ።
ወላጆቼ ክርስትያኖች ናቸው፤ ነገር ግን ሐረጋቸው ወደ ኋላ ቢቆጠር ብዙም ራቅ ሳይባል ሙስሊሞች ይገኙባቸዋል። ጿሚና ፀሎተኛ የነበሩት ክርስትያኑ አያቴ አባቴን የወለዱት ሙስሊም ወላጆች ከነበሯት ባለቤታቸው ነው። አባቴ የክርስትና እምነት ተከታይ ሆኖ ቢያድግም፤ ይህ ከሙስሊም ዘመዶቹ ጋር አብሮ ለመኖር እንቅፋት ሆኖበት አያውቅም። ቤተክርስትያን ሳሚዋ እናቴ ሙስሊም ዘመድ አዝማዶቿ ሊጎበኟት ከወሎ ወደ መሀል ሀገር ሲመጡ ጠብ እርግፍ እያለች የኃይማኖታቸውን ሥርዓት በማክበር የክርስትያን ምግብ ባልነካው ዕቃ ምግባቸውን አዘጋጅታ፣ ለፀሎት የሚሰግዱበትን ስጋጃ አነጣጥፋ እንዲሁም ዱዓ ለማድረግ የሚያስፈልጋቸውን ሁሉ አቀራርባ ስትቀበላቸው እያየሁ አድጌአለሁ። የእናቴ የቅርብ ዘመድ የሆነው ሰይድ ትምህርቱን እኛ ጋር ተቀምጦ ሲከታተል የእስልምናም ሆነ የክርስትና በዓላት በመጡ ቁጥር ለእርሱም ለኛም እንደየእምነታችን የሚታረደው ታርዶ በዓላቱን በጋራ እየበላን እየጠጣን በማክበር ለዓመታት አብረን ኖረናል።
ወደ ወላጆቼ የትውልድ ስፍራ ለመሄድ ዕድል ባገኘሁ ጊዜ ወላጆቼ እቤታችን ያየሁትን አብሮ የመኖር ባህል ምንጭ ወሎ ውስጥ አገኘሁት። ወደ ወሎ በተለይም ደግሞ ወደ ደሴ በየምክንያቱ ሳቀና እዛ ያሉትን ሙስሊሞቹን ዘመዶቼን ለአፍታ እንኳን ቢሆን ሳላያቸው አልመለስም። የሰይድ እናት እንዲሁም እህትና ወንድምቹ “መሳፍንቴዋ” እያሉ በፍቅራቸው እየጠሩኝ፣ አንገቴ ላይ ተጠምጥመው በስስት ዓይናቸው እያዩኝ፣ እያነቡ ተቀብለውና አስተናግደው እያነቡ ሲሸኙኝ፤ “ምነው እዚህ የምቆይበት ጊዜ እንደዓመት በረዘመልኝ” ብዬ ከመመኘት በቀር ኃይማኖታችን ለየቅል መሆኑን ለአፍታ እንኳን አስቤው አላውቅም፤ እነሱም እንደኔው።
ይህ የማወጋችሁ የቤተሰቤ ታሪክ ባጭሩ የወሎ ህዝብ ታሪክ ነው። ሀገራችንን ገላጭ የሆነው የኃይማኖቶች መከባበርና መቻቻል ጎልቶ ከሚታይባቸው ቦታዎች መካከል ወሎ ግንባር ቀደሙ ነው። ወሎ ውስጥ ሙስሊሙን ከክርስትያኑ፣ ክርስትያኑንም ከሙስሊሙ በስምም ሆነ በግብር ለመለየት አስቸጋሪ ነው። ይህን የመሰለ አስደናቂ ትስስር ያለው የደሴው ወገኔ በመሬት ጉዳይ በተቀባባ ሸር ለወያኔ መርዛማ ሴራ መታጨቱን ያረዳኝን ዜና ስሰማ ነው እንግዲህ ያ ድብልቅልቅ ያለ ስሜት በውስጤ የተፈጠረው። ግና ብዙም ሳልቆይ በአንደኛው ጆሮዬ የገባውን ይህን ወሬ በውስጤ ተመቻችቶ ሳይቀመጥ ባጫወትኳችሁ ታሪኬ በመምራት መንገድ መንገዱን እያሳየሁት “እኔ ግድም ድርሽ እንዳትል” ብዬ በሌላኛው ጆሮዬ አስወጣሁት።
ኢትዮጵያችን በአብዛኛው የምትታወቀው በየጊዜያቱ በሚፈራረቁባት ሰው-ሠራሽና የተፈጥሮ ችግሮች ቢሆንም ጥቂት የማይባሉና የብዙዎችን ቀልብ የሚስቡ በጎ ገፅታዎችንም ታድላለች። ከነዚህ መካከል በቀዳሚነት ሊጠቀስ የሚችለው በህዝቦቿ መካከል የሚታየው የመቻቻልና አብሮ የመኖር ባህል ነው።
ሀገራችንን ለ19 ዓመታት እንደመዥገር የተጣበቀባት የወያኔ መንግሥት ከምንም ነገር በላይ በሚሳሳለት ሥልጣኑ ላይ ለመቆየት፤ በመልካም ገፅታዎቹ ኮርቶና ደምቆ የሚኖረውን ህዝብ በዘር፣ በጎሣ፣ በኃይማኖት፣ በፆታ፣ በዕድሜና በሌሎችም ሰበባ ሰበቦች ለመለያየት ያልሠራው ድራማ የለም። ለ19 ዓመታት እንዳየነው ወያኔ እንደ እርጉዝ ቀን እየቆጠረ ለመለያያ ካዘጋጃቸው ካርዶቹ መሃል አንዱን መዘዝ አድርጎ በህዝብ ውስጥ እንደ እባብ በደረቱ ተስቦ እየገባ የፖለቲካ ቁማሩን ሲቆምር ቆይቷል። በተለያዩ የሀገሪቱ ክፍሎች ህዝብን በደምና በአጥንት አለያይቶ ለማጫረስ እንደሚሞክረው ሁሉ፤ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በሙስሊሙና በክርስትያኑ መሃል ለዘመናት ሰፍኖ የቆየውን ሠላምና አንድነት በመናድ ህዝቡን በታትኖ ሥልጣንን ከራሱ ጋር እንደጠጉርና ማበጠሪያ አስተሳስሮ ለመኖር የልዩነት መርዙውን እየረጨ ጠብ ለመጫር ይዶልታል። በሚፈጥራቸው ግርግሮችም ንፁኀንን ይጨፈጭፋል።
ወያኔ በኃይማኖት ሰበብ የማበጣበጥ ሥራ እንዲሠሩለት የሚያደራጃቸውን ቡድኖች በማር የለወሰውን ሬት አስይዞ በህዝብ መሃል እየለቀቀ በተለያዩ መንገዶች ብጥብጥን ይጭራል። አንዱን መስሎ የሌላውን እምነትና ተከታዮችን በማንቋሸሽና በመዝለፍ፣ በአምልኮ ስፍራዎችና ህዝብ በብዛት በሚገኝባቸው ቦታዎች የእምነት መፈክሮችን በማሰማት፣ ለአንዱ የሚገባውን መሬትም ሆነ ሌሎች ነገሮች ለሌላኛው በመስጠትና ሌሎች መሰል ሴራዎችን በመሸረብ የኃይማኖቶቹን ተከታዮች ቁጣና ንዴት ውስጥ እየከተተ ወደ አለመግባባትና ጠብ በመምራት ህዝብን በህዝብ ላይ ለማነሳሳት ያሴራል። በእምነቶቹ ተከታዮች መካከል የማግለል አስተሳሰብና አመለካከት የሚያሰርፁ ኃይሎች እንዲሠርጉ በማድረግ ተቻችሎ የኖረውን ህዝብ ሆድ እያሻከረ ሊያባላው ይሸርባል።
እነዚህንና መሰል ተግባራትን በማቀነባበር በህዝብ መሃል እሳቱን ከለኮሰ በኋላ ቅልብ እና አልሞ-ተኳሽ ሠራዊቱን ሴራውን ወደሸረበበት ስፍራ እየላከ ንፁኀንን አስቀጥቅጦና አስገድሎ ሲያበቃ የአዞ እንባውን በማንባት “ድርጊቱን የፈፀሙት የፖለቲካ ሴራ ያላቸው የጥፋት ኃይሎች ናቸው” እያለ እንደ ጲላጦስ እጁን በአደባባይ ይታጠባል። ባለፉት ጥቂት ዓመታት ይህንኑ መርዙን ለመርጨት ከሞከረባቸውና ሙስሊሞችና ክርስትያኖች ተቻችለው ከሚኖሩባቸው ቦታዎች መካከል ለአብነት ሐረርን፣ ጅማን እንዲሁም አዲስ አበባን መጥቀስ ይቻላል።
ነገር ሳላበዛ ከላይ የጠቀስኩትን ርካሽ የወያኔ አካሄድ ቁልጭ አድርጎ የሚያሳይ አንድ የማስታውሰውን ታሪክ አጫውቻችሁ ልለፍ። ጊዜው የ97 ምርጫ መዘዝ ናላውን ያዞረው ወያኔ፤ የቅንጅት መሪዎችን በግፍ እስር ቤት ያጎረበትና ያንንም ተከትሎ ህዝቡ በድብቅም በግልጽም ተቃውሞውን እያሰማ በነበረበት ወቅት ነው። በተለይ በከፍተኛ ትምህርት ተቋማት አካባቢ ከፍተኛ የጭንቀት ድባብ የረበበት ጊዜ። ወያኔ በዚህ ወቅት የህዝቡን የትኩረት አቅጣጫ ለማስቀየርና ራሱ የነዛውን የዘር መርዝ ተቋቁሞ አንድ ሆኖ የተነሳውን ህዝብ ለመከፋፈል እንደለመደው ለክፉ ቀን የሚጠቀምባትን የኃይማኖት ካርድ መዘዝ አድርጎ ቁማሩን ለመጫወት ሞክሮ ነበር።
የሴራው አቀናባሪዎች በጅማ ዩኒቨርሲቲ “አንድ ተማሪ ቅዱስ ቁርዓንን ቀዶ ለመጸዳጃነት ተጠቀመ” የሚል የበሬ ወለደ ወሬ በዩኒቨርሲቲው ተማሪዎች መካከል እንዲናፈስ ያደርጋሉ። አጀንዳው የተፈለገው ወዲህ ነበርና ወሬውን በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ ውስጥም በትጋት አሰራጭተውት በቀጣዩ ቀን ሙስሊም ተማሪዎች ይህንን በማውገዝ ሰልፍ እንዲወጡ ያደርጋል። በዚህም ምክንያት ጉዳዩን ከምንጩ ያልተረዱ ሙስሊም ተማሪዎች ክፉኛ ተቆጡ፣ የትምህርት ሂደቱም ተስተጓጎለ። በወቅቱ በመገረም እጄን በአፌ ላይ አድርጌ የተመለከትኩት ሌላ ክስተትም ነበር። እኔ በነበርኩበት በአዲስ አበባ ዩኒቨርሲቲ አንድ ዲፓርትመንት ውስጥ ትሠራ የነበረች ወያኔ የአስተዳደር ሠራተኛ ከተማሪዎቹ ጋር ሰልፍ ውስጥ ተቀላቅላ በዓይኔ በብረቱ ተመለከትኳት።
ወያኔ ዛሬም ለተመሳሳይ ተልዕኮው ሴራውን ሸርቦ በተረኛ የመስዋዕት ጠቦትነት ወደመረጠው ወደደሴ ህዝብ ተሽሎክሉኮ ለመግባት ሞክሯል። በደሴ ሙስሊሙን ከክርስትያኑ ለማጋጨት የተመረጠው አጀንዳ መሬት ነው። ቀድሞውንም መንግሥትና ህዝብ እያወቀው በድንኳን ቤተክርስትያን ከልለው ፈጣሪያቸውን ሲያመልኩበት በነበረውና አሬራ ሰፈር አዘዋ ገደል ጫፍ በሚገኘው ስፍራ ላይ የቤተክርስትያን ሕንፃ ለመገንባት በአግባቡ ጥያቄ ላቀረቡት የክርስትና እምነት ተከታዮች ወያኔ በሎሌዎቹ በኩል “ሙስሊሞች ስለተቃወሙ ቦታው ለቤተክርስትያን ግንባታ ሊውል አይችልም” በማለት ሙስሊሞቹ ያላሉትን አሉ ብሎ ዓይን ባወጣ መልኩ ህዝቡን ለማቃቃርና ወደጠብ ለመግፋት በመሞከር እንደለመደው የቻለውን ያህል ንፁኀንን በጥይት ጨረሰ።
ሴራውን ጠንቅቆ የተረዳው ህዝብ የተላከበትን የወያኔ ቅልብ “ወግድልኝ! ሳልደርስብህ አትንካኝ” ከማለት ውጪ ሙስሊሙን ወንድሙን “መሬቴን ለምን አስከለከልከኝ?” ብሎ እሰጥ አገባ ውስጥ አልገባም። የወሎ ክርስትያንና ሙስሊም ህዝብ እንኳንስ መሬት ይገባኛል ብሎ ወያኔ የሚመኝለትን ዓይነት ጠብ ውስጥ ሊገባ ይቅርና፤ በአንድ ቤተ-አምልኮ ውስጥ ፈጣሪውን በጋራ ማመስገን የማይሳነው በደምና በፍቅር የተሳሰረ ህዝብ ነው። ይህ ህዝብ እንኳንስ ለጠብ ደርሶ በዚህ በዱርዬ መንግሥት ገላጋይነት ሊዳኝ ይቅርና፤ ተቻችሎ መኖር ላልገቸባው ለነዚህ ደናቁርት የአብሮ መኖርን ፊደል የሚያስቆጥር፤ ሳይማር ያወቀ ህዝብ ነው።
በጥምቀት በዓላት የወሎ ሙስሊም “አልሀምዲሊላህ ታቦታችን ገባ” ይላል ተብሎ የሚነገረው በቁምነገር መነጽር ሲታይ የሚኖረውን መልዕክት የሚገልፀው ይህንኑ ነው። በወሎ ፀንቶ የኖረው የክርስትያኖችና የሙስሊሞች አንድነት ተምሳሌትነቱ ስለኃይማኖት መቻቻል ብቻ ሳይሆን ስለኃይማኖት መዋሀድም ጭምር ነው። በደምና በአጥንት አንድ የሆነውን ህዝብ በኃይማኖት ልለየው ብሎ መቃዠት ስንጥቅ የሌለውን ብርጭቆ ሰባራ ነው ብሎ እንደማለት ይሆናል።
ወገኖቼ! ይህ መንግሥት በህዝብና በሀገር ላይ እየፈፀመ ያለው የግፍ መዓት “ሐረግን ሲመዙት ሐረግ ይከተለዋል” አይነት ሆኗል። ሀገራችን ኢትዮጵያ የምትታወቅባቸውና ዜጎቿ የምንኮራባቸው በጎ ገፅታዎቿ አንድ በአንድ እንደጉም በነው እንዲጠፉ እየተደረገ ነው። እንደ ብሔር ብሔረሰቦቿ ሁሉ በኃይማኖቶቿ ብዛትና በአማኞች ተቻችሎ የመኖር ባህል ደምቃ የምትታየው ኢትዮጵያችን፤ ይህ ገፅታዋ በኃይማኖት ግጭቶች ለሚታመሱ ሀገራት ትምህርት ሰጪ ሊያደርጋት ሲገባ ወያኔ ጠብመንጃ ሲፈታበት በኖረ እጁ ጥላሸት ሊቀባው ደፋ ቀና ይላል። በኃይማኖት ሰበብ የሚነሳ ቅራኔ እጅግ አውዳሚና በቀላሉ ድንበር ተሻጋሪ እንደመሆኑ ኃይማኖትን እያራገቡ የፖለቲካ ቁማር ለመጫወት መሞከር ውጤቱ ምን ሊሆን እንደሚችል ለእናንተ ለማስረዳት አይዳዳኝም። ዛዲያ እንዲህ አይነቱን የወያኔ ሴራ “ሳይቃጠል በቅጠል” የማለት ኃላፊነት የማን ይሆን?
የልዩነት አባዜ የተጠናወተው፣ እየሰነጣጠቀ ለማፍረስ፣ አያላላ ለማውለቅ የማይተኛው ይሄ መንግሥት ትናንት በዘር፣ ዛሬ ደግሞ በኃይማኖት ሊለየን ጉድጓድ እንደሚምሰው ሁሉ፤ ነገ ከእንቅልፉ ሲባንን “ባልና ሚስቶች በጾታ ስለሚለያዩ አብረው መኖር አይችሉም” ብሎ ቢል በበኩሌ አልገረምም። ቁም ነገሩ አንድ ነገር በተፈጠረ ቁጥር “ይህን ከሚያሰማኝ ምነው ሞቼ በነበር” ማለቱን አቁመን፤ ሸሚዛችንን ሰብሰብ፣ መታጠቂያችንን ጠበቅ አድርገን ለመፍትሔ መንቀሳቀስ ሰብዓዊና ሀገራዊ ግደታችን መሆኑን መረዳቱ ላይ ነው።
“ዘጠኝ ሞት ቢመጣ አንዱን ግባ በለው” በሚል አኳኋን የሀገራችንን ጉዳይ ዳር ይዞ ለመታዘብ መምረጥ በተለይ በዚህ ቀውጢ ሰዓት ከማንም ዜጋ የሚጠበቅ አይሆንም። ለራሳችን ነፃነት ብሎም ለሀገርና ለወገን ሠላምና አንድነት ሊከፈል የሚገባውን መስዋዕትነት ከፍለን ይህን የተመረዘና የተበላሸ ሥርዓት የማስወገድ የቤት ሥራ አለብን ጎበዝ!። ወያኔ የህዝብን አንገት ሊቀላበት ቀጥቅጦ የሚስለው ካራ እራሱ አንገት ላይ የሚያርፍበትን ጊዜ የማቅረብ ኃላፊነት የማንም ሳይሆን የኛው የራሳችን ነው።
ፈጣሪ ሀገራችንን ይጠብቅ! እኛንም የዓላማና የውጤት ሰው ይበለን! - አሜን!!!
መሣፍንት ዘፈረንሣይ ለጋሲዮን (አዲስ አበባ)
( This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it. ) ሐምሌ 2001 ዓ.ም.