ክንፉ አሰፋ 3 August 2009

Pairs Ethio-Festival 2009"... ከሁለቱ የመጫወቻ ሜዳዎች ትይዩ ባለች አንድ ዛፍ ጥላ ስር በርጫና ሽሻው ሞቅ ብሏል። ለየት ባለ መልኩ “ለመዝናናት የመጡ” ወጣቶች ሕይወታቸውን ይቀጫሉ። ጫትን በግልጽ መቃምም ሆነ መሸጥ አይከለከልም። “ኢትዮጵያም አይከለከልም” ያለኝ ወዳጄን አልረሳውም። “ይህ የኢትዮጵያን ባህልም የምናንጸባርቅበት መድረክ ነው። ሀገራችን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ሁሉም በግልጽ ነው የሚቅመው።” ነበር ያለው። እውነቱን'ኮ ነው። ለኳስ ከመጣው ለጫት የመጣው ይበልጥ ነበር። በዚሁ ከቀጠለ በቅርብ ጊዜ የስፖርቱ ፌዴሬሽን - የአውሮፓ የጫትና ሺሻ ፌዴሬሽን የማይሆንበት ምንም ምክንያት አይኖርም። ..." በማለት በፓሪስ የተካሄደውን በአውሮፓ የኢትዮጵያውያን የስፖርትና የባህል ፌስቲቫልን የገመገመው ጋዜጠኛ ክንፉ አሰፋ ነው።

 

ስንብት ከፓሪስ

የኢትዮጵያውያን ስፖርት ፌስቲቫል 2009 ግምገማ

2009 Paris, Ethiopians Sport & Cultural Festival

የሣምንቱን መገባደጃ (weekend) ከወዳጅ-ዘመድ ጋር ለማሳለፍ ከአምስተርዳም ቀን ላይ ተነስተን ማምሻውን ፓሪስ ገባን። የዘንድሮው የአውሮፓ ስፖርትና ባህል ፌዴሬሽን ዝግጅት በፓሪስ በኢትዮጵያ ባንዲራና የባህል ሙዚቃ ደምቆ እየተከበረ ነበር የደረስነው። አመሻሹ ላይ በመጫወቻ ሜዳው ያለው ፀብና ከሜዳ ውጭ ያለው ግርግር የበለጠ ግቢውን አቅልጦታል።

 

ከግቢው ገና ሲገባ የሚታዩ ሁለት የእግር ኳስ መጫወቻ ሜዳዎች ውስጥ 18 ክለቦች እንዲጫወቱ ነበር የተደረገው። በሁለት ቀን ውስጥ 18 ክለቦች በሁለት ሜዳ ተጫውተው ... ለማጣሪያ ... ከዚያም ለደረጃና በመጨረሻ ለዋንጫ የማድረስ ዕቅዱን የተካኑ ይመስላሉ የፌዴሬሽኑ መሪዎች። ጥበቡንና አቅሙን በማጣታቸው ግን ካመት ዓመት የሚፈጠረውን ፀብ ይልቁንም እያባባሱት መሆኑን አስተዋልን።

 

የሜዳው እጥረት ብቻ አልነበረም የተስተዋለው፤ የዳኞችም እጥረትና እውቀት ማጣት፤ ... ወዘተ ተደማምሮ አንድ ክለብ በቀን ውስጥ እስክ 4 እና 5 ጫወታዎችን እንዲያደርግ ተደልድሏል።

 

“ለምን?” ብሎ የሚጠይቅ ካለ የሚቀጣ መሰለኝ። ምክንያቱም የለማ! ተጫዋቾቹም ጥያቄ ከማቅረብ ይልቅ ማጉረምረምና ሲከፋ መበጣበጥ ነበር የመረጡት። የአዘጋጆቹ ትኩረትም ያለው ቢዝነሱ ላይ ነው። ቢዝነሱ በጣም ያጓጓል። አንዳንዶቹ “ሕጋዊ ዝርፊያ” ብለውታል። እዚህ ላይ የአውሮፓን ስፖርት ፌዴሬሽን ከሰሜን አሜሪካው የሚለየው፤ የአሜሪካውን ዝግጅት ገቢና ወጪውን የሚቆጣጠረው ፌዴሬሽኑ ሲሆን፣ የአውሮፓውን ግን የሚቆጣጠሩት አዘጋጅ የሆኑት ‘ግለሰቦች’ ናቸው። የፌዴሬሽኑ ሥራ በየዝግጅቱ በመገኘት ሽልማት መስጠት ነው።

 

ብዙ ሰው የኳስ ጨዋታው ላይ አላተኮረም እንጂ እዛ አካባቢ ያሉ ክስተቶች ለአንዳንዱ ሊያስቁ ሌላውን ደግሞ የሚያስቀይሙ ናቸው። ጫወታው 20 ደቂቃ ... ጎል የሚቆጠረው ደግሞ (እንደ ባስኬት ኳስ) በሁለት ዲጅት ነው። 11 ለዜሮ፣ 12 ለ8፣ ... ወዘተ። በ20 ደቂቃ 11 ጎል በአንድ ክለብ ላይ ከገባ ጨዋታው 90 ደቂቃ ቢሆን ደግሞ 49 ጎል ሊቆጠር ነበር እያሉ አንዳንዶች ሲተቹ ስምቼ፤ አንዱን ተጫዋች ብጠይቀው፤ “11 - ለዜሮ የሚሉት ሲያጋንኑ ነው፤ እኛ የተሸነፍነው 10 ለዜሮ ነው" ብሎኛል።

 

በ‘ምርቃና’ ዓይናቸው እንደባትሪ የሚያበራ ተጫዋቾችም አልጠፉም። ቢራ ‘እንደጉድ’ የሚጠጡትን ተጫዋቾች ያየ ግን በፓሪስ የሚጠጣ ውሃ እንደሌለ ነው የሚገነዘበው። አንዳንድ ተጫዋቾች በእረፍት አፋቸውን ለመጉመጥመጥም ቢራ ሲጠቀሙ አይቼ ነበር። ምክንያቱን ስጠይቅ “በሜዳ ውስጥ ነጋዴዎቹ የውሃን ዋጋ ወደ 2 ኢሮ ከፍ ስላደረጉት ነው” አለኝ አንዱ። የ20 ሣንቲሙን ውሃ በ2 ኢሮ ሲቸበችቡ ከማየትም አልፌ እኔው ገዝቼ ጠጣሁ - በዛ ኃይለኛ ሙቀት አማራጭ ሲታጣ ምን ይደረጋል?

 

የምግቡ ዋጋም እንደዛው ነው። አንድ ምግብ ተብላ የምትቀርበውን ጎበዝ ሰው በሁለት ጉርሻ ይጠቀልላታል። ዋጋዋ ግን 10 ኤሮ ነው። አንድ የ9 ዓመት ሕጻን ሁለት ክትፎ ብቻውን 'ጭጭ' ሲያደርግ በአይኔ አይቻለሁ። ይህንን የሚሰማ ምናልባት 'ልጁ በጣም ተርቧል' ወይንም 'ምግቡ ጣፍጦት ነው' ሊል ይችላል። ግን አይደለም። ችግሩ መጠኑ ላይ ነው። ያንንም ለማግኘት መሰለፍ አለ።

 

ይህንን የሰሙት አዘጋጆቹ በማይክራፎን፣ “ክቡራን እንግዶቻችን ምግብ ከ8 ኤሮ በላይ እንዳትገዙ!” ሲሉ ተደምጠው ነበር። (ማሳሰቢያውን በአትኩሮት የሰሙት ከምግብ የራቁ ወግኖች “ምናለ የጫቱንም ዋጋ እንዲሁ ቢያስቀንሱልን?” ሲሉም ተደምጠዋል።)

 

አዘጋጆቹ በጎን ምግብ ለሚሸጡት ወዳጆቻቸው ምግብ ከ10 ኤሮ በታች እንዳትሸጡ ያሉ ይመስላል። ማሳሰቢያው ከልብ ቢሆን ኖሮ ለህዝቡ ሳይሆን ለነጋዴዎቹ ነበር መነገር የነበረበት። ‘ያራዳ ልጆች’ - የምግብ ዋጋ ሳይወርድ ከሜዳ ወጣን።

2009 Paris, Ethiopians Sport & Cultural Festival

በነጋታው የገጠመን ደግሞ እጅ እጅ ያለ (contaminated) ምግብ ነበር። በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ይሏል እንዲህ ነው። ሰሚ የለ - ለማን ይነገራል? ይህ ንግድ በሞኖፖል ባይያዝ ኖሮ ለምግብ መሰለፍ ባልኖረ፣ በወገንም ላይ እንዲህ አይነት ዝርፊያ ባልተካሄደ ነበር።

 

ከሁለቱ የመጫወቻ ሜዳዎች ትይዩ ባለች አንድ ዛፍ ጥላ ስር በርጫና ሽሻው ሞቅ ብሏል። ለየት ባለ መልኩ “ለመዝናናት የመጡ” ወጣቶች ሕይወታቸውን ይቀጫሉ። ጫትን በግልጽ መቃምም ሆነ መሸጥ አይከለከልም። “ኢትዮጵያም አይከለከልም” ያለኝ ወዳጄን አልረሳውም። “ይህ የኢትዮጵያን ባህልም የምናንጸባርቅበት መድረክ ነው። ሀገራችን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ሁሉም በግልጽ ነው የሚቅመው።” ነበር ያለው። እውነቱን'ኮ ነው። ለኳስ ከመጣው ለጫት የመጣው ይበልጥ ነበር። በዚሁ ከቀጠለ በቅርብ ጊዜ የስፖርቱ ፌዴሬሽን - የአውሮፓ የጫትና ሺሻ ፌዴሬሽን የማይሆንበት ምንም ምክንያት አይኖርም።

 

2009 Paris, Ethiopians Sport & Cultural Festivalከዚህ ባሻገር በበርካታ ገንቢና በጎ ሥራዎች የተሰማሩም ኢትዮጵያውያን ነበሩ።

 

የኢትዮጵያን መልካም ባህል የሚያንጸባርቁ ሥራዎችን የሚያስተዋውቁ፣ በኃይማኖት፣ በፖለቲካውና በሰብዓዊ መብት ዙሪያ የሚንቀሳቀሱ፦ የብርቱካንን፣ የቴዲ አፍሮን ፎቶ፣ ... የግንቦት ሰባት ዓርማ የያዙ ቲ-ሸርቶችና ፍላየሮች የሚበትኑ፣ እንዲሁም የገንዘብ ማሰባሰብ ሥራን የሚሠሩ በቁጥር ብዙ ባይሆኑም ትልቅ ሥራ ሲሠሩ ተስተውለዋል። ከበዓሉ አዘጋጆች አንዳንዶቹ ግን በዚህ አይነቱ እንቅስቃሴ ደስተኛ እንዳልነበሩ ታይቷል።

 

2009 Paris, Ethiopians Sport & Cultural Festivalሻምበል በላይነህ ተበሳጭቶና ተቆጥቶ አግኝተነው፤ ለምን እንደተቆጣ ጠየቅነው። “ሲዲዬን ለማስተዋወቅ ከአዘጋጅ ኮሚቴው አንዱን ጠይቅኩት። ...” ሲል ጀመረልን ንዴቱን እየተቆጣጠረ። “... ‘የኢትዮጵያ ኤምባሲ ስለከሰሰን ሲዲህን ለነጋዴዎች አከፋፍልና አንተ ግቢውን ለቀህ ውጣ!’ አሉኝ።” በማለት መለሰልን። ይህንን ስንሰማ አዘንን። ደግነቱ ግን አዘጋጆቹ ሁሉ እንደዛ አለመሆናቸው ነበር። የኋላ ኋላ የሻምበል ሲዲዎችን ሰዎች በሽሚያ ነበር ይገዙ የነበረው።

 

ቅዳሜ ምሽት ላይ የበዓሉ አዘጋጅ ወዳሰናዳው የምሽት ፕሮግራም ላይ ለመገኘት ቅድሚያ ትኬት ቆርጠን ነበር። ምሽት ላይ ወደ አዳራሹ ስናመራ ከወትሮው የተለይ ክስተት ገጠመን። ግቢው በልዩ የፈረንሳይ ፖሊስ ኃይል ተከብቧል። በግምት አንድ ሺህ የሚጠጋ ኢትዮጵያዊ በሩ ላይ ተኮልኩሏል። ዝናብ ከላይ ይወርዳል። ጩኸት፣ ግርግር፣ ስድብ፣ ... ሁሉም ያጉረመርማል።

 

እየፈጠነች ከግቢው የምትወጣ ወጣት ልጅ፣ “እነዚህ ሌቦች! ... ጎሣዬ አለ ብለው ዋሹን! ... ጎሣዬ አልመጣም ... አዳራሹ ጣራ የለውም። ዝናብ ያስገባል ...” ወዘተ እያለች ሊገባ የመጣውን ሰው ሁሉ ከበር እንዲመለሱ ዘመቻ ጀመረች። የተሳዳቢውና የሚያጉረመርመው ሰው ቁጥር እየበዛ ሲመጣ የፖሊሱ ኃይልም እየጭመረ መጥቶ ግቢውን ሞላው።

 

ሌላ ወጣት ደግሞ ለተኮለኮለው ዕድምተኛ እንዲህ ይላል። “አዳራሹ በተጭበረበረ (ፎርጅድ) ትኬት በገቡ ሰዎች ተሞልቷል።” ... ዕድምተኛው ከውጭም ከውስጥም በዝናብ እየተደበደበ ለሰዓታት ቆሟል።

 

2009 Paris, Ethiopians Sport & Cultural Festivalበነገሩ ግራ ስለተጋባን ወደ አንዱ ፖሊስ ጠጋ ብለን መረጃ ጠየቅን፤ ፖሊሱ በተቆራረጠ እንግሊዝኛ “ይህንን ዝግጅት እኛ አናውቀውም። አዘጋጆቹ ፍቃድ ስላልጠየቁ ዝግጅቱ ሕገ-ወጥ ነው። እናም አይካሄድም።” አለን። ይኽን ስንሰማ ተስፋ ቆርጠን ወደየማረፊያ ክፍላችን አመራን። የቆረጥነውን ትኬት እንኳ ለማስመለስ የምናነጋግረው ተጠሪ አልነበረም። ያለማጋነን ከሺህ በላይ ሰው በዚህ መልኩ ተመልሷል።

 

አሁንም ይህ ለምን እንደተከሰተ ማወቅ የሚቸግረን አይመስለንም። አዘጋጆቹ ለቁጠባ ሲሉ የተከራዩት ደረጃውን ያልጠበቀ አዳራሽና ያሰማሩት ጥቂት የሰው ኃይል የፈጠረው ችግር ነው። ከ3,000 በላይ ህዝብን ያስተናግዱ የነበረው በአንድ በር ላይ ባለ ትኬት ቆራጭ እና ተቆጣጣሪ ነበር። ወጪ ለመቀነስ! ይህንን በማድረጋቸው ግን ቢያንሰ 1,000 ሰው እንዲመለስ አደርገዋል። 30,000 ኤሮ በላይ መሆኑ ነው።

 

ለማጠቃለል የኢትዮጵያ ስፖርትና ባህል ፌዴሬሽን በአውሮፓ ከተመሰረተ እነሆ ሰባተኛ ዝግጅት ማድረጉ ነው። ፌዴሬሽኑ ኢትዮጵያውያንን በማገናኘት ረገድ ባደረገው ጥረት ሊመሰገን ይገባዋል። በየዓመቱ የሚከሰቱ ችግሮችን ግን እልባት የሰጣቸው አይመስልም።

 

ኢትዮጵያውያን በመቶዎች ኪሎ ሜትር አቋርጠው በዝግጅቶቹ ሊዝናኑ በሄዱበት ሁሉ በ“ሕጋዊ ቀማኛ" ተዘርፈው የሚመለሱበት ችግር መቀረፍ አለበት። ወደፊት አዘጋጅ ሀገሮች ከዚህ ስህተት ትምህርት በመውሰድ እንግዶችን በደስታ ተቀብሎ በደስታ ለመሸኘት ከፍተኛ ኃላፊነት እንዲሰማቸው መምከር ተገቢ ነው።

 

በአምስተርዳም (ሆላንድ) በሚደረገው በመጭው ዝግጅት እነዚህ ችግሮች እንደማይደገሙ ተስፋ እናደርጋለን። ትልቅ ጥረትም እናደርጋለን። የከርሞ ሰው ይበለን!


 

ክንፉ ከአምስተርዳም

 

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ