አባ ጳውሎስ ከ“ሕገ-ወጦች ጋር” አናብርም አሉ

Ethiopia Zare (ረቡዕ ሰኔ 24 ቀን 2001 ዓ.ም. July 1, 2009)፦ በደሴ ከተማ ፌደራል ፖሊሶች በክርስትና እምነት ተከታዮች ላይ በወሰዱት የጭካኔ እርምጃ ምክንያት የሞቱ ሰዎች ቁጥር ከሁለት ወደ አራት ከፍ ብሏል። ከስፍራው በተቃውሞ ሰልፉ የተሳተፈች ሴትና የፖሊስ ዱላ ያረፈባት ሴት እንደገለጸችልን ከሆነ አንዱ ሟች ከላሊበላ የመጣ በስንቅ የሕክምና ትምህርት የሚከታተል ወጣት ሲሆን፤ አስከሬኑ ወደቤተሰቦቹ መሄዱን ገልጻለች።

 

በከተማው አዲስ በተገነባው አሬራ በተባለው ሰፈር አካባቢ አዘዋ ገደል ጫፍ ላይ አርሴማ ማሪያም ቤተክርስቲያን ቦታ ከሁለት ዓመት በፊት ጀምሮ ሲያወዛግብ የነበረው ቦታ ለቤተክርስቲያኗ ተፈቅዶ መንግሥት ለሌላ አገልግሎት እፈልገዋለሁ በማለቱ ለሁለት ዓመት በድንኳን ሲቀደስ የነበረ ሲሆን፤ ህንጻ ለማቆም ለሚመለከተው ክፍል በተደጋጋሚ ያቀረቡት ጥያቄ ምላሽ ሊያገኝ ባለመቻሉ ብዛት ያለው ህዝብ ሠላማዊ ሰልፍ ለማድረግ አስፈቅዶ በመውጣት ለከተማው አስተዳድር ጥያቄ ቢያቀርቡም ማንም ወጥቶ ሊያናግራቸው ስላልቻለ “ዝምታ እሽ ማለት ነው” በሚል ሰልፈኛው ከብዙ ሰዓታት በኋላ ወደ ቤተክርስቲያኗ በመሄድ በከፍተኛ ትብብር በቆርቆሮና በግንብ ህንጻውን መሥራት መጀመራቸው ይታወቃል።

 

ከዚህ በኋላ የፌደራል ፖሊስ በቦታው በመድረስ በምዕመናኑ ላይ ተኩስ ከፍቶ እስካሁን አራት ሰዎች የሞቱ ሲሆን፤ ከላሊበላ መጥቶ በስንቅ የሚማረውን ወጣት ጨምሮ አንዲት መነኩሴ በገደል ተገፍትረው፣ አንድ አራዳ በሚባል ሰፈር ነዋሪ የነበረ ወጣትና እስካሁን ማንነቱ ያልታወቀ ሌላ ወጣት በደሴ ሆስፒታል አስከሬኑ እንደሚገኝ ታውቋል። ከዚህም ሌላ በርካታ ምዕመናንም ቆስለው በሆስፒታል የሚገኙ መሆናቸውን ለመረዳት ተችሏል።

 

ትናንት ግማሽ የሚሆኑት ምዕመናን በቤታቸው ሌሎቹ ደግሞ በቤተክርስቲያኗ ያደሩ ሲሆን፣ ዛሬ ከኮምቦልቻና ከአዲስ አበባ በመጡ ተጨማሪ የፌደራል ኃይሎች እንዲወጡ የፖሊሶቹ ኃላፊ ምዕመናኑን አግባብቶ ለማስወጣት ቢሞክርም ፍቃደኛ አይደለንም እዚሁ ማደር እንፈልጋለን ቢሉም በግድ እንዲወጡ ተደርጓል። ከቤተክርስቲያኗ አንወጣም ያሉ አንድ መነኩሴ ግደሉኝ እንጂ ከዚች አልለቅም በማለታቸው እዛው ግቢ ውስጥ ያደሩ ሲሆን፤ በአሁኑ ሰዓት ቤተክርስቲያኗ በፌደራል ፖሊሶች ቁጥጥር ስር እንደሆነች ለማወቅ ተችሏል።

 

አንድ ውስጥ አዋቂ ሰው ከአዲስ አበባ እንደተናገረው የሀገረ ስብከቱ ሊቀ ጳጳስ ለዚህች ቤተክርስቲያን መቆም ሕይወቴን እሰጣለሁ ብለው ቢምሉም፤ በጉዳዩ ላይ ጣልቃ እንዲገቡ የተጠየቁትና ሰሞኑን ከአዲስ አበባ ሀገረ ስብከት ሊቀጳጳስና ከረዳት ሊቀጳጳሳቻው ጋር በከፍተኛ ውጥረት ውስጥ የሚገኙት አቡነ ጳውሎስ የሀገረ ስብከቱን ፌደራል ፖሊስን እንዲተባበሩና የተደበቀ አጀንዳ ካላቸው ሕገ-ወጦች ጋር እንዳይተባበሩ አስጠንቅቀዋቸዋል። ባለፈው ሣምንት አባ ጳውሎስ ሁለት ጳጳሳትን ከራሳቸው ሲኖዶስ እውቅና ውጪ ማባረራቸው ይታወሳል።

 

ስለሁኔታው ያነጋገርነውና የኢትዮጵያን ሁኔታ በጽኑ የሚከታተለው ልጅ ተክሌ አስተያየት እንዲሰጠን ጠይቀነው፤ አባ ጳውሎስ ከዚህ ቀደምም በ2001 ዓ.ም. ከሀምሳ በላይ ሰዎች ሲገደሉና አምስት ሺህ ተማሪዎች ከቅድስ ማሪያም ቤ/ክ በወታደር መኪናዎች እየተጫኑ ወደ ሸዋ ሮቢት፣ ኮልፌና ሰንዳፋ ሲወሰዱ፤ ለጉብኝት ኬንያ መጥተው በነበረበት ሰዓት “የታሰሩትም የተገደሉትም ዱርዬዎች ናቸው” በማለት የሰውን ልጅ ያቀለሉና የቀለሉ ሰው ናቸው ብሏል። የሚገርመኝ የሳቸው እንዲህ ማለት ሳይሆን በኢትዮጵያ ሰዉ ተገዶ ነው፤ ነገር ግን በውጭ ሀገር እኚህን ሰው አባት አድርገው የሚቀበሉ ሰዎችና አብያተ ክርስቲያናት መኖሩ ነው ብሏል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!