ገዢው ፓርቲ ክርስቲያኑንና ሙስሊሙን ማናከሱን ገፍቶበታል

Ethiopia Zare (ማክሰኞ ሰኔ 23 ቀን 2001 ዓ.ም. June 30, 2009)፦ በደሴ ከተማ የቅድስት አርሴማ ቤተክርስቲያን እንድትሠራበት ታቅዶበት የነበረው ቦታ ለረዥም ጊዜ ሲያወዛግብ ቆይቶ፤ የከተማው አስተዳደር ባለሥልጣናት ቦታውን ሙስሊሞች ተቃውመውታል በሚል ሥራው ተቋርጦ በድንኳን ሲቀደስበት ከቆየ በኋላ፤ መንግሥት መልሶ ቦታውን ለሌላ አገልግሎት ይዠዋለሁ በማለቱ ዛሬ በደሴ ከተማ ብዛት ያለው ህዝብ የተሳተፈበት ሠላማዊ ሰልፍ እንደተካሄደና ከሰልፉ በኋላ በምዕመናንና በፌደራል ፖሊሶች መካከል ረብሻ መነሳቱን የዓይን ምስክሮች ገለጹ።

 

ነገሩ እንዲህ ነው። አዘዋ ገደል በሚባል ቦታ ላይ የቅድስት አርሴማ ቤተክርስቲያን እንድትሠራ የአካባቢው ነዋሪዎችና ቤተክህነት በመወሰናቸው ቦታውን እንዲሰጣቸው ያመለክታሉ። በአካባቢው አዲስ የተገነባ መንደር በመኖሩ የቤተክርስቲያኗ ህንጻ እንዳይሠራ “የአካባቢው ሙስሊም ነዋሪዎች ተቃውመዋል” በማለት የአካባቢው ባለሥልጣናት ቦታውን ይከለክላሉ። በመሀከሉም የሙስሊሙ እና የክርስቲያኑ ማኅበረሰብ መሪዎች ሲነጋገሩ ሙስሊሞች ምንም አይነት ተቃውሞ እንዳላቀረቡ፤ እንዲያውም በቦታው መስጅድ ሲሠራ ክርስቲያኑ ማኅበረሰብ ተቃውሞ እንዳላሰማ ይነጋገራሉ።

 

ይሄንን የአስተዳደሩን ማጭበርበር ተከትሎ ምዕመናን ተሰባስበው ወደ አስተዳደር ቢሮ በመሄድ በዛሬው ዕለት ቦታው እንዲፈቀድላቸው የጠየቁ ሲሆን፤ ከአስተዳደሩ ምንም አይነት ምላሽ ባለማግኘታቸው በገደላገደል በተከበበችው ቦታ በመመለስ በተለይ ዲያቆናትና የአካባቢው ነዋሪዎች ጣውላ በማዘጋጀትና የህንጻ መሣሪያዎችን በማቀራረብ የህንጻ ሥራው እንዲጀመር አደረጉ።

 

ይህንን ተከትሎ የፌደራል ፖሊሶች በቦታው በመድረስ በህዝቡ ላይ ተኩስ የጀመሩ ሲሆን፤ በተነሳው ግርግር ምክንያት አንዲት መነኩሴ በገደል ውስጥ ወድቀው መሞታቸውን የዓይን ምስክሮችቹ ገልጸዋል። ይህ ዘገባ እስከተጠናከረበት ጊዜ ድረስ ወላጆች ልጆቻቸውን እየፈለጉና ተኩሱም እንዳልቆመ ለማወቅ ችለናል።

 

ጉዳዩን አስመልክቶ አስተያየታቸውን የሰጡ የአካባቢው ነዋሪዎች፤ መንግሥት በራሱ ምክንያት እምቢም እሺም ማለት ሲችል፤ ሙስሊሙ ማኅበረሰብ ያላለውን ጠቅሶ የሁለቱን ኃይማኖት ተከታዮች ለማጋጨት መሞከሩ በቅርብ ጊዜ እየጨመረ የመጣ አዲስ የአገዛዝ ስልት ሲሆን፤ አስተያየት ሰጪዎች ለዘመናት አበበና ከድጃ፣ ሰይድና ለምለም ተጋብተው በሚኖሩባትና እስላምና ክርስቲያን ተከባብረው በሚያድጉባት ደሴ እንዲህ ያለውን ፀብ የሚያስነሳ ድርጊት መደረጉ አሳዛኝና ህዝቡ በጥንቃቄና በአስተውሎት ሊከታተለው የሚገባ ነገር ነው ብለዋል። አስተያየት ሰጪዎቹ ጨምረውም ኢህአዲግ ያለፈውን ሃያ ዓመት በብሔረሰቦች ግጭት፤ ቀሪውን ሃያ ዓመት ደግሞ በኃይማኖት ግጭት ሥልጣኑን ይዞ ለመኖር ያሰበ ይመስላል ብለዋል።

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!