ነቢዩ ሲራክ

* ለአንባሳደር አሚንና ለአንባሳደር ውብሸት ባላችሁበት

* ቅጅ፣ ለውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁ

የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር ባለሥልጣናት
አንባሳደር አሚን፣ ዶ/ር ወርቅነህ ገበየሁና አንባሳደር ውብሸት

መረጃን ማቀበሌ ወንጀል ሆኖ "የነቢዩ ሲራክ ልጆች ከሚማሩበት የጅዳ ኮሚኒቲ ትምህርት ቤት እንዲታገዱ" የሚለው የካድሬዎች ሀሳብ ያን ሰሞን ቀርቦ እንደነበር በድጋሜ በማረጋገጤ አዝኘ ነበር ያደርኩት። ... ስለ እውነት ለመናገር፣ ስለ እውነት እየተገፉ መኖር ግድ ይላል ብዬ የሚሰራው ባይደንቀኝም በዘመነ ኦሪት እንኳ ባልታዬ ህግ ልጆች በአባታቸው "ወንጀል" ስማቸው ሲጠራ መስማት ልቤን በሀዘን ሰብሮት አድሯል። እናም ሁሉንም ለመርሳት ልጆቸን እረፍት ወደ ማይሰማ ወደ ማይናገረው ቀይ ባህር ይዣቸው ዘና ልበል ብዬ ማልጀ ስነሳ ሌላ አሳዛኝ መረጃ ደረሰኝ።

መረጃው እንዲደርሰኝ ያደረገው ደግሞ አንድ አደር ባይ ወዳጄ ነበር፣ ወዳጄን እኔን ያመመኝ አሞት ስለማያውቅ የዜጎች ጉዳይ አግብቶኝ የተገፊውን ድምጽ ሳሰማ "ሥራ ፈት ነህ!" እያለ ያላግጥብኝ ነበር። ዛሬ ግን የራሱ የሆነች እህት በሪያድ አየር መንገድ ለቀናት በደረሰባት እንግልት ተደናግጦ "አገር ይያዝ" ጩኸት አሰማኝ። ቀጠለና ዜጎች እየተሰቃዩ ነው የታላችሁ በማለት ከጅዳ ቆንስል እስከ ሪያድ ኢንባሲ ሹም ወዳጆቹን ጨምሮ መረጃውን እኔው ጋር አድርሶታልና አዘንኩ ... ደጋግሞ ሲደውልልኝና መረጃ ሲሰጠኝ ዝም ብየ ሰማሁትና ለመሆኑ እኔ ስናገር ሥራ ፈት እያልክ አልነበር? ዛሬ ችግሩ በዘመድህ መጥቶ መናገር መናደድ ጀመርክ? እስከ አሁንስ የት ነበርክ ? ማለቴ አልቀርም። እሱ ግን አፈረ፣ እኔም ያፈረውን አድርባይ ወዳጄን መጎሻሸሙን አልወደድኩትም ... በወዳጄ ዛሬ መቆርቆር አላዘንኩም የሰጠኝን መረጃ ተከትዬ ያሰባሰብኩት እውነት ግን በእርግጥም ያስከፋል። ይህን መልዕክት እንድጽፍ ላችሁ ያነሳሳኝ ጉዳይም ይኸው የደረሰኝ መረጃ ነው።

ላለፉት ሶስት ወራት ሌት ተቀን ግሩም በሆነ ዝግጅት የከረመው የኢንባሲና የቆንስል መረጃ ቅበላ በመቋረጡ የተከተለውን ውዥንብር እንደ ዜጋ ታዝቤያለሁ። የኢንባሲና የቆንስል መረጃ ቅበላ በማቆሙም ቦታውን ባልተካም በመረጃ እጦት ስደተኛው እንዳይንገላታ ባሳለፍናቸው ሁለት ሳምንታት የምችለው ለማድረግ ሞክሬያለሁ። አሁንም የምቀጥለው በዚሁ መንፈስ ነው ... የኢንባሲና የቆንስል ለመረጃ የተዘጋው በር ከተከፈተ እኔ ብዙም ላይክና ሸር ፈላጌ ዝር ላልል ቃል ልግባላችሁ! ብቻ ለዜጋው መረጃ ያስፈልገዋልና የተዘጋውን በር ክፈቱለት ለማለት ለመማጸንና ለመምከርም ጭምር ነው።

በኢትዮጵያ አየር መንገድ በረራ ችግር በጅዳና በሪያድ አየር መንገዶች እየተንገላታ ያለው ሰው ለቅሶ ዛሬም ደርሶኛል። በምህረት አዋጁ መራዘም ዙሪያ በሚናፈሰው መረጃ ለሚዋልለው ዜጋ እያደረጋችሁ ያለውን ጥረትና እውነቱን አስረዱት። "የምህረቱ ጊዜ አብቅቷል!" ተብሎ በሳውዲ ፖስፖርት ፖሊሶች እንዳይሳፈሩ መመለስ ስለመጀመሩ ጉዳይ ግልጽ መረጃ ከእናንተ ይጠበቃል። ከቀናት በፊት በጀዛን ትናንት ደግሞ በጅዳ አንዳንድ ተመላሾች "የምህረቱ ጊዜ አብቅቷል!" ተብለው በፖስፖርት ፖሊሶች እንዳይሳፈሩ ተከልክለው እንደነበር ከጅዳ ቆንስል ኃላፊዎች በግል መረጃውን አረጋግጫለሁ። በዚህና በዚያ በተለያዬ አቅጣጫ የሚሰማው መረጃ ብዙዎችን ግራ እያጋባ ይገኛል።

በሚሰራጩት መረጃዎች፣ እየተደረገ ስላለው ጥረትና ተዛማጅ የተመላሽ ዜጎች ጉዳይ በሳውዲ የኢትዮጵያ መንግስት ተወካዮች በምህረት አዋጁ ወቅት ያደርጉት እንደነበረው ሳያቋርጡ መረጃን ሊሰጡ ይገባል የሚለው የብዙ ወዳጅ ተከታዮቸ መልዕክት ነው። በእርግጥም ወቅታዊ መረጃን ሲሰጡ ከርሞ አሁን በወሳኙ ጊዜ ማቋረጥ በመቶ ሽዎች የሚቆጠር ዜጋ ብቻ ሳይሆን በመላ አለም ያለው ሚሊዮን ሀገር ወዳድ እንዳይረጋጋ ያደርጋል። በውል የተጠና የመረጃ ቅበላው ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል። በሪያድ የኢትዮጵያ ኢንባሲ እና የኢትዮጵያ ቆንስላ ጽ/ቤት በወሳኙ ጊዜ ያቋረጣችሁትን የመረጃ ቅበላ ትቀጥሉ ዘንድ እመክራለሁ! በየአየር ማረፊያዎች ቀንና ማታ ቀርቶ ለሰአታት መቋቋም በሚከብደው ደረቅ ሀሩር ጸሃይ ሙቀት እየተለበለበ ያለው ወገን ያለበትን ሁኔታ መከታተልና መደገፍ፣ መረጃ፣ ማብራሪያ በሉት ምክር ካስፈለገ በቦታው እየተገኙ መስጠት ተገቢ ነው እላለሁ!

ይህን ምክር እንድጽፍ ያነሳሳኝ መታበይ እንዳይመስላችሁ። በቂ ምክንያት አለኝ " ላለፉት ሶስት ቀናትበሪያድ አየር መንገድ አውላላ ሜዳ ላይ ተሰቃየን " በሚል የሚደርሱኝ መረጃዎች እጅግ ውስጥን ይረብሻሉ። እናንተም በዚህ ዙሪያ ምንም አይነት ወቅታዊ መረጃ ስለማታቀርቡ በእንግልት ላይ ያሉ ዜጎች የመረጃ እጦት ሌላ ፈተና እንደሆነባቸው መረዳት ችያለሁ! እባካችሁ ዜጎች መረጃን ከእናንተ ከህዝብና መንግስት አገልጋዮች የማግኘት መብታቸውን አለንና እሱኑ መብት አክብሩልን!

የግርጌ ማስታወሻ

ለወዳጆቸና ለተካታታዮቸ፣ ይህ መልዕክት ለኃላፊዎች እንዲደርስ Share እና Like ማደረጋችሁን አትዘንጉ፣ ሁላችንም ስለተገፉት ዜጎች ድምጽ መሰማትና መፍትሔ ማግኘት መትጋት ግድ ይለናል!

ከአክብሮት ሰላምታ ጋር

ነቢዩ ሲራክ

ሰኔ 21 ቀን 2009 ዓ.ም.

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ