በሳውዲ ዐረቢያ የምንገኝ ግፉአን ኢትዮጵያውያን መከራ - በረመዳን ዋዜማ (ክፍል አንድ)

ነቢዩ ሲራክ - ከሳውዲ ዐረቢያ

... በመቶዎች የሚቆጠሩ የመናውያን፣ ኢትዮጵያውያን፣ ሶማሌያውያንና ኤርትራውያን ስደተኞች አደገኛውን የቀይ ባህር በትናንሽ ጀልባዎች ታጭቀው የጨካኝ አሸጋጋሪ ደላሎችን ግፍ የተሞላበት እርምጃ በመቋቋም የማይጨበጠውን ህልምን ለማሳካት ትግል ይዘዋል። አብዛኛው ወንዶች እየተደበደቡ ሴቶች እየተደፈሩ የየመንን በርሃዎች ቆርጠው ወርቅ ይታፈሳል ወደ ተባለበት የቱጃሮች ሀገር ሳውዲ ዐረቢያ ሲገቡ ይያዛሉ። ለወህኒ ከማዳረግ አልፎ በጥይት እየተደበደቡ ደመ-ከልብ ይሆናሉ። ጥቂት የቀናቸው አይሆኑ ሆነው ካሰቡት ሲደርሱ ያላለላቸው በርሃ በልቶዋቸው የመቅረቱን ትኩስ ዜና ሰምተን ሳናጣጥመው ሌላ ህሊና ሊቀበለው በማይችል ዜና መስማት ጀምረናል። በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሳውዲ የጠረፍ ከተማ በጀዛን ድንበር ከተያዙ በኋላ በተጨናነቀው እስር ቤት አሳር መከራ እያዩ መሆናቸውን እንሰማለን። ይህንን ከተለያዩ ምንጮችና ከሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች ማረጋገጥ ቢቻልም ሁኔታውን አሳምረው ከሚያውቁት ከመንግሥታቸን ተወካይ ባለስልጣናት ግን ማረጋገጫ ማግኘት አልተቻለም። ይህ በእንጥልጥል ላይ እንዳለ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በበኩላቸው በጂዳ የግርድና አስከፊ ኑሮ አንገፍግፏቸው ወደ ሀገራቸው የሚመልሳቸው አጥተው ለወራት በእንግልት ላይ መሆናቸውን ሰማሁ። ...

የረመዳን ጾም መዳረሻ በመሆኑ ሁሉም ጥድፊያው ለጾሙ የሚሆነውን ከመገዛዛት ጀምሮ ቤቱን በማሰማመር ላይ ይገኛል። የቀይ ባህር ፈርጥ እየተባለች የምትንቆለጳጰሰው የጂዳ ከተማም ካምና ዘንድሮ አምራና ደምቃ ረመዳንን ትቀበል ዘንድ ዝግጅቱ ተጠናቋል። ረመዳን ጾም ታዋቂ አውራ ዋና መንግዶችን ጨምሮ መናኛ የመንደር አስፓልቶች ሳይቀሩ ጽዳታቸው ከምንጊዜውም በላይ ተጠብቆላቸው ፍንትው የሚሉበት ልዩ አጋጣሚ ነውና ጸዳ ብለዋል። ከትናንሽ የመንደር ውስጥ ለውስጥ ሱቆች ዘመናዊ መላብሶች መጫኒያዎችና የከበረ እንቁ ሺያጭ የሚደራላቸው የከተማዋ ውድ ሱቆች ሁሉም ለረመዳን ዝግጅታቸው የሚሆኑ እቃዎችን በሱቃቸው ደርድረው በመጠባበቅ ላይ ናቸው። ሁሉ ሱቆችን አንድ የሚያደርጋቸውን ረማዳን ከሪም የሚል ጽሁፍን በመጻፍን የተቀደሰችው የረመዳንን ወር መጠባበቃቸው ረመዳን በመጣና በሄደ ቁጥር የሚስተዋል የተለመደ ትዕይንት ሆኖዋል። ከቅርብ ዓመታት ወዲህ እንደ አሸን የፈሉት የዐረብ ቱጃር ትላልቅ ሱቆች በየመንደሩ ተኮልኩለው የሚታዩት የህንድ የፓኪስታን የባንግላዲሽ የየመን የሐበሻና ሌሎች ዜጎች የሚሰሩባቸው ሱቆች የረመዳን ከሪም መልካም ምኞት መግለጫ ሁሉም እንዳቅማቸው ከታላቅ ቅናሽ ማስታወቂያቸው በየበራቸው ለብደው ነዋሪ በማማለል ገበያቸውን በማሞቅ ላይ ናቸው።

በትላልቅ ሱቆች ከሚታየው ታልቅ ቅናሽ በስተጀርባ ሱቆች እንደ ብቸኛ መዝናኛ ይቆጠራሉና የብዙዎችን ቀልብ ሲስቡ የሚስተዋልበትም በዚሁ በረመዳን ወቅት ነው። ዘመናዊ የህንጻ ጥበብ ያረፈባቸው የሚያማልሉት ሱቆች ወደ ሰማይ በሚምዘገዘግ የሌዘር አንጸባራቂ መብራቶች ተውበው በውስጣቸው ተባዕት ጎልማሶችና አንስታይ ጉብሎች፤ አዲሳቤዎች "ሹገር ዳዲ ፣ ሹገር ማሚ" የሚሉዋቸው ወጣትና እድሜ ጠገብ ባለትዳሮች ሱቆችን ለማድመቅ ተመካክረው ዝግጂት ያደረጉ ይመስላል። በተላይም አብዛኛው የቤቱ አፈና የባሎቻቸው ሁለት ሶስት ቤት መስረታ ለሚያንገበግባቸው አንስታይ ልዩ የመገናኛ ስውር ቦታ የረመዳን ወር የሚደምቁት ትላልቅ ሱቆች ናቸውና በዘንድሮው ዋዜማ የሚስተናገድበት አየር ኮለል ያለ ይመስላል።

በረመዳን በጾም የደከመን መንፈስን ለማስደሰት ዝንጥ ሸንቀጥ ብሎ ሱቆችን በሚሞሉ ወገኖች ይሞላልና ግብይቱ ቀርቶ የሱቁም ገበያም ይደራል መዝናናቱም ሞቅ ደመቅ ያለ ይሆናል። በአንጻሩ በትዳራቸው የኮሩ የዐረብ እመቤቶች ባሎቻቸውን ከጎናቸው ልጆቻቸውን ከፊታቸው እያስቀደሙ ገበያን ገበያይተው ተዝናንተውና ካማሩት የሱቅ ምግብ ቤቶች፤ ሻይና ቡና ብለው የረመዳን ቀለባቸውን በጋሪዎቻቸው ሞልተው የሚያስገቡበትም በዋዜማው ነው። የረመዳን መምጣትን በደስታ ቢቀበሉትም ስራው ጠንቶ የሚያከላትማቸው የድሃ አገር ዜጋ የቤት ሰራተኞች ድካማቸው ቢበዛም አንዳንዴ ሸጎጥ የሚደረግ የገንዘብ ጉርሻ አይጠፋምና ለረመዳን ልዩ ፍቅር አላቸው። ያም ቢቀር ሰርተው ራሳቸውና ቤተሰቦቻቸው የሚደግፉበት ብቸኛው መንገድ ስራ ነውና ረመዳንን የሚቀበሉት በጸጋ ነው። ይህ እንግዲህ ከፍ ወዳሉት ባለጸጋ የህብረተሰብ ክፍሎች ዙሪያ የሚታየው የረመዳን ዋዜማ ዝግጂት የሚስተዋል ሲሆን ወደ መካከለኛውና ወደ ዝቅተኛ የኑሮ ደረጃ ነዋሪዎችን ይህ መሰሉ ውሎ አይነካካውም።

በመንገድ ዳርና ዝቅተኛ ደረጃ ባላቸው የሱቅ አዳራሾችም ቢሆን ኑሮዋቸውም መካከልና የሆነና ኑሮዋቸው ከእጅ ወደ አፍ የሆኑ ነዋሪዎች ማስተናገዱን አልቦዘኑም። ከአንዱ ሱቅ ወጥተው ወደሌላ ሱቅ ሲንቀሳቀሱ የሚጋረፈውን የሙቀት ወላፈን ተቋቁመው ነውና ከበድ ይላል። ሐበሾች መናህሪያ በሆኑትና ለግብይይት በሚበዙባቸው መዝናኛዎችና የተለያዩ ቁሳቁስ መሸጫ ሱቆችም መተነፋፈሻ የሚያሳጣውን ሙቀት ችለው ከመገበያየት ሌላ አማራጭ ስለሌለ በግርግሩ ደምቀው ዝግጂቱ ገፍተውበታል። ቤተሰብ መስርተው ኑሯቸውን በሳውዲ ምድር ለዓመታት የከተሙትም ሆኑ ወንድና ሴት ላጤዎች በቤታቸው ሆነው ረመዳን በደስታ ለመቀበል የሚያደርጉት ዝግጂት ቀጥሎዋል። ጾሙን ከመላ ቤተሰብ ጋር ለማሳለፍ የታደሉት ሳንቡሳ መስሪያ ስጋ ፤ ለጾም መፍቻ የሚሆን ቴምር ፤ወተታ ወተት ፤ ለጭማቂ መስሪያ የሚሆኑ ዱቄቶችን ጨምሮ የማይቀረውን ቡና እጣንና እንጀራ የመሳሰሉ አስቤዛዎችን ለመግዛት ሁሉም በየፈርጁ ደፋ ቀና ማለታቸውን አልቀረም። በሳምንት አንድ ጊዜ እረፍት የምትወጣው ሴተ ላጤም ሆነች በቀኑ ሃሩር ስራ ናላው ሲነረት የዋለ ላጤ ወንድ እረፍት ሲያገኙ የሚሰራሩዋትን ነገር ለመሸማመት ብቸኛው አማራጭ የረመዳን ዋዜማ ባይሆንም በዋዜማው መሸማመት የተለመደ ነውና ሁሉም ያቅማቸውን ይገዛዛሉ። በዚህ ሁኔታ የእስልምና ኃይማኖት አማኞች ጨረቃ ስትወጣ ጀምሮ ጨረቃ እስክትገባ በሚከወነው በረመዳን የ30 ቀናት ጾም ጸሎት ከፈጣሪ ምህረት ይገኛል ብለው ያምናሉ። በረመዳን ጾሙ ሲጾም ሙሉ ቁርአን "ተቀርቶ" ተነቦ የሚያልቅበት ወር በመሆኑ ፈጂር ዝሁር አሱር መቅሪብና ኢሻ ተብለው ከሚታወቁት አምስት የየስግደት ጸሎት ወቅቶች በተጨማሪ ተራዊህ የሚባለው ጸሎትም በረመዳን አይቀሬ በመሆን ይታወቃል። በዚህ አጋጣሚም የሞላለት በዓመት ከሚያገኘው ገቢ ሲሶ ያህሉንም ለተቸገሩት የሚረዳው በረመዳን ወር ነው። የእስልምና ኃይማኖት መፍለቂያ በሆነችው በመካና በመዲና የሚታየው የጸሎት ስነ ስርአት በአለማችን ታዋቂ በሆኑ ድምጸ መረዋ ኢማሞች እንባቸውን እያነቡ እየተስረቀረቁ የሚወጣወጡት ድምጽና ጸሎት እንኳንስ የሃይማኖቱን ተከታዮች የባይተዋርን ቀልብ ይስባል።

የዘንድሮው ረመዳን እኔና መሰሎቸን ጨምሮ ለበርካታ ኢትዮጵያውያን እንደ ወትሮው በፌስታ የምቀበለውና ሠላም የሚሰጥ አልሆነውም። በረመዳኑ ዋዜማ በጎልማሳ እድሜየ ያ ወንድሜ ያወረሰኝና ለዓመታት ሙጥኝ ያልኩት የጋዜጠኝነት ሙያ የጣለብኝ ጣጣ የሚያሰማኝና የሚያሳየኝ ሁሉ ሠላም ለማጣቴ ምክንያት ሆኖዋል። በኑሮ ውድነትን የደቀቀ የቤተሰቦቻቸውን ኑሮ ለመደገፍ ወደ ሳውዲ ዐረቢያ በሕገወጥ መንገድ የገቡ ኢትዮጵያውያን በረመዳን ዋዜማ እየደረሰባቸው ያለው ግፍ በእርግጥም ሠላም አይሰጥም። ከበርካታ ዓመታት የቤት ሠራተኝነት ያልሰመረ ህይወት በኋላ ወደ ሀገራቸው ጠቅልለው የመግባት ፍላጎት በኢትዮጵያውያን ዘንድ ብዙም የተለመደ አይደለም። ሰምተን የማናውቀውን እየሰማንን፤ አይደረግም ያልነው እየተደረገ፤ መጽሐፉ "የፊቱ ወደ ኋላ የኋላው ወደፊት ይሆናል" እንዳለው ሆነ መሰል ሁኔታዎች መቀያየር ይዘዋል። በመቶዎች የሚቆጠሩ የመናውያን፣ ኢትዮጵያውያን፣ ሶማሌያውያንና ኤርትራውያን ስደተኞች አደገኛውን የቀይ ባህር በትናንሽ ጀልባዎች ታጭቀው የጨካኝ አሸጋጋሪ ደላሎችን ግፍ የተሞላበት እርምጃ በመቋቋም የማይጨበጠውን ህልምን ለማሳካት ትግል ይዘዋል። አብዛኛው ወንዶች እየተደበደቡ ሴቶች እየተደፈሩ የየመንን በርሃዎች ቆርጠው ወርቅ ይታፈሳል ወደ ተባለበት የቱጃሮች ሀገር ሳውዲ ዐረቢያ ሲገቡ ይያዛሉ። ለወህኒ ከማዳረግ አልፎ በጥይት እየተደበደቡ ደመ-ከልብ ይሆናሉ። ጥቂት የቀናቸው አይሆኑ ሆነው ካሰቡት ሲደርሱ ያላለላቸው በርሃ በልቶዋቸው የመቅረቱን ትኩስ ዜና ሰምተን ሳናጣጥመው ሌላ ህሊና ሊቀበለው በማይችል ዜና መስማት ጀምረናል። በሺዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በሳውዲ የጠረፍ ከተማ በጀዛን ድንበር ከተያዙ በኋላ በተጨናነቀው እስር ቤት አሳር መከራ እያዩ መሆናቸውን እንሰማለን። ይህንን ከተለያዩ ምንጮችና ከሰብዓዊ መብት ተከራካሪዎች ማረጋገጥ ቢቻልም ሁኔታውን አሳምረው ከሚያውቁት ከመንግሥታቸን ተወካይ ባለስልጣናት ግን ማረጋገጫ ማግኘት አልተቻለም። ይህ በእንጥልጥል ላይ እንዳለ በመቶዎች የሚቆጠሩ ኢትዮጵያውያን በበኩላቸው በጂዳ የግርድና አስከፊ ኑሮ አንገፍግፏቸው ወደ ሀገራቸው የሚመልሳቸው አጥተው ለወራት በእንግልት ላይ መሆናቸውን ሰማሁ።

በርካታ ከፍተኛ መዋእለ ንዋይን በማፍሰስ በረሃን ሰንጥቀው አደገኛውን የባህር መንገድ ከሞት ጋር ተፋጠው ወደ ሚገሰግሱባት ሀብታም ሀገር እንዴት ሰው ልመለስ ይላል? የጋዜጠኛ ብቻም ሳይሆን የሁሉም ነዋሪ ጥያቄ ሆኗል። ለዚህ ጥያቄ መልስ ማግኘት ነበረኝና ስደተኞቹ ፖሊስ ይዞ ይወስደናል በሚል በተኮለኮሉበት በማሃል ጅዳ "ከንደራ" ተብሎ ወደ ሚጠራው ድልድይ አመራሁ። ሙቀቱ በርትቶ በመሰንበቱ የመኪናየ ማቀዝቀዣ ማቀዝቀዝ ተስኖታል። ቁጥራቸው እስከ ሁለት መቶ የሚደርሱ ሐበሾች አብዛኛው ሴቶችና ግን አልፎ አልፎም አንዳንድ ወንዶችን ሃሩር አልበገራቸውም። ወደው ሳይሆን ተገደው እንዲያ ይህንን ኑሮ ብለው በመግፋት ላይ መሆናቸውን በተባለው ቦታ በአይኔ ተመለከትኩ። መኪናየን ከርቀት በማቆም በእግሬ ረመድ ረመድ እያልኩ ተጠጋሁ። በአንድ የድልድዩ መሰሶ ስር በቁርጥራጭ ካርቶኖች ላይ በጀርባው የተኛ ወንድም ተመለከትኩ። ሃዘን ቅስሜን ሰበረው ... የድህነትን አስከፊነት በጠራራው ፀሐይ ላይ በተዘረረው በወንድሜ ላይ ተመለከትኩት ... ለዓመታት የተዘናጋሁበትን የማንነት ጥያቄ አጫረብኝ ... በጸጉረ ልውጥና በአግርሞት አስተያየቴ አዲስ መሆኔን የተረዱ የሚመስሉት የሲሪላንካ የህንድና የባንግላድሽ ለተመሳሳይ ችግር የተዳረጉ ዜጎች ሳላስበው ከበቡኝ።

"እንታ ሐበሽ ..." አለኝ አንዱ በተኮለታተፈ ዐረብኛ ... አዎ አልኩትና መልሸ ለምን ጠየቅከኝ አልኩት ሳላስበው በቁጣ መንፈስ. ንዴቴ ውርደቴ እንዲያ እንዳደረገኝ ገባቸው መሰል ከፊቴ ገለል በማለት ሁለት ሐበሾች ይዘውልኝ መጡ። እንደዚህኛ ወንድሜ በህመም ተዳክመው ባይጠቁም በቁመናቸው ወዛቸው ረግፎ ሰውነታቸው መንምኖና ልብሳቸው አይሆኑ ሁኖ ማየቱን ያልጠበቅኩት ቢሆንም ግራ ተጋብቸ ፈገግ ለማለት እየሞከርኩ ሠላምታ ተለዋወጥን። ነጻ ሆነው ያወሩኝ ዘንድ ራሴን አስተዋወቅኩዋቸውና ስለዚህ ወንድም ችግር የሚያውቁት ካለ በሚል ጠየቅኩዋቸው። የተጋደመውን ወንድም ችግር ትናንት ምሽት አንዲትን እህት በማስገደድ ሊወስድ ከመጣ ወመኔ ጋር ግብግብ ገጥሞ ራሱን እንደተፈነከተና በቂ ህክምና ባለማግኘቱ ደሙ እያዞረው በጠና መታመሙን ገለጹልኝ። ከተጋደመው ወንድም አጠገብ መድምጀ ተቀመጥኩ። ከዛሬ ግፉአን "ከጨሱት" የትናንት ጮሌና ንቁ የሀገሬ የከተማ ልጆች ጋር ወጌን ቀጠልን። ሁሉም አንደበታቸው ርቱእ ነው። ቃላቱ በበሽታና በችግር ከተዳከሙት ወንድሞቸ የሚወጣ መሆኑን እስክጠራተር ድረስ ውጣ ውረዳቸውን ሰቆቃ ውሎ አዳራቸውን በተመስጦ እህ ብየ አደመጥኩዋቸው። ግራ ቀኙን ሰማሁ። የእኒህ ወጣቶች መከራ ሕገወጥ ሆነው የሃገሪቱን ሕግ ሳይጥሱ መስራታቸው መሆኑ እንደሆነ ገባኝ። ከንግግራቸው እንደገባኝ ለዓመታት በገፉት ኑሮ ገንዘብ የሚታፈስበትን ሕገወጥ ስራ አልተቀላቀሉም። ላብ አደሮች ነበሩ። ያም ሆኖ ወደ ሳውዲ የገቡበት በሕገ ወጥ መንገድ ነውና ሕግ አይደግፋቸውም። በእርግጥም በጉልበታቸውና በላባቸው ለማደር በቤት ሠራተኛነት፤በዘበኛነት፤ በእረኝነትና በጉልበት ስራ ሲባዝኑ የገፉት ኑሮ ትርፉ በሽታና ድካም ሆኖባቸዋል። ይህ ሆነና ኑሮ አልተመቻቸላቸውም። "እዚህ ያሳየነውን ትጋት በሀገራችን ብናሳይ ማደግ እንችላለን ባናድግም ደመ-ከልብ ሆነን ከምንጠፋ ለድሃ ቤተሰቦቻችን መኖራቸን እንኳ ተስፋ ይሁን" ብለው ወደ ሀገር ለመግባት እንደሚፈልጉ አጫወቱኝ። ቀጥለውም የቅርብ ርቀታችን ከሚገኙት እህቶች አንዳንዶቹን እያስመጡ ታሪካቸውን አጫወቱኝ። የሴቶችም ታሪክ ቢሆን ከወንዶች የተለየ አይደለም። "የቤት ሠራተኝነቱ ኑሮ ጎዳን። እረፍት የሌለው ስራ በበሽታ ላይ ጣለን። ሬሳቸን ሳይሆን እኛው ሳንሞትና በጋሪ ሳንገፋ በጊዜ በሠላም ሀገራቸን እንግባ" ነው የሁሉም ጥያቄ።

ማቅ የመሰለውን ጥቁር አበያ ከጸጉር እስከ ጥፍራቸው ተጀቡነው ባዘኑላቸውን ወገኖች ችሮታ ሲያገኙ ቀማምሰው ሲያጡ ቀዝቃዛ ውሃቸን ጠጥተው በተስፋ የመያዣ ጊዜያቸው ይጠብቃሉ። ያም ሆኖ ወደ ሀገራችን እንግባ በማለት ከድልድይ ስር ካርቶን አንጥፈው ኑሮን በገፉ ሠላም የሚሰጣቸው ግን አላገኙም። ጅዳን መሃል ለመሃል ሰንጥቆ በሚያልፈው "ከንደራ" ተብሎ በሚጠራ ድልድይ ስር ኑሮን ሲገፉ የሚጸዳዱባቸው ከቅርብ ርቀት የሚገኙ የመስጊድ መጸዳጃ ቤቶች ነበሩ። ከቀን ቀን እንያዝ እያሉ የሚሰባሰቡት ኢትዮጽያውያን መበራከት የመስጊድ መጸዳጃ ቤቶች ይዘጋባቸው ዘንድ ምክንያት ሆነና ይህም ሌላ ችግር ፈጠረ። ይባስ ብሎ ከቅርብ ርቀት በሚገኙ የተለያዩ ዜጎችና ወመኔወች ጥቃት በርታባቸው። እናም ይህን ችግር አስመርሯቸው ወደ ሀገራቸው መንግሥት ተወካዮች አቤቱታቸውን ለማሰማት በረመዳን ዋዜማ በኢትዮጵያ የጂዳን ቆንስል መስሪያ ቤት ዳግም አጨናንቀውት ማርፈዳቸውን ረፋዱ ላይ ሰማሁና ወደዚያው አቀናሁ።

ይህን መሰሉ ችግር ያገነፈልው እንቅስቃሴ ከዚህ በፊት ታትቶ ስለማይታወቅ ዲፕሎማቶችን የቆንስል ምስሪያ ቤቶችን ብቻም ሳይሆን የጉዳዩን ለማስፈጸም በቆንስል መስሪያ ቤቱ የተገኘውን ነዋሪ ግራ ሲያፋባ የዓይም ምስከር ለመሆን በቃሁ። አቅመ ደካማ እህቶች እንባቸውን እያዘሩ ችግራቸውን ሲናገሩ የነገውን ባለዕጣ ተመልካች የኛን ልብ አባቡት። ከሃምሳ እስከ ስልሳ የሚደርሱ እኒሁ ግፉአን እንደ ዜጋ ተቆጥረን ለወራት ከወደቅንበት ያላዩን የመንግሥታችን ተወካዮች ግፍ ሲሰራብን እንኩዋ ሰብዓዊ መብታቸን አስከብሩልን በሚል በተደጋጋሚ ላቀረቡት ጥያቄ መልስ የሚሰጥ ጠፍቶዋል ... መጉላላት ይዘዋል። ከብዙ ጉትጎታ በኋላ መልስ የሰጡት የቆንስሉ ኃላፊዎች ወደ ነበራችሁበት ድልድይ ስር ተመለሱ የሚል መልስ ከሰጡ በኋላ ጭራሽ መግባባት ጠፋ። ነዋሪዎች "ግቢው ሀገራችን ማለት ነው ሌላው ቢቀር ስንደፈርና ስንደበደብ መብታችን አስከብሩልን" በሚል ላቀረቡት ጥያቄ መልስ የሚሰጥ ማን እንደሆን ለማወቅ ተሳነን።

ግፉአን ኢትዮጵያውያን አጥጋቢ መልስ እስኪያገኙ ድረስ ከቆንስሉ ግቢ እንደማይወጡ ቢያንገራግሩም ከብዙ ውጣ ውረድ በኋላ ከግቢው ተባረሩና። ከቆንስሉ ፊት ለፊት ባለ ታዛ ስር ተጠልለው ያችኑ የተለመደች ካርቶች ከወዲያ ወዱህ ፈላልገው አግኝተዋልና እሱዋኑ አነጣጥፈው ሌላውን የመከራ ቀን ከባንዴራቸው የቅርብ ርቀት መግፋታቸው ተስፋ ሆኖዋቸዋልና ገፉበት። ለሁለትና ሶስት ቀናት ሀገር ጉድ እስኪል ቀጠሉ ... በቆንስሉ በር ነዋሪው ምግብና ውሃ እያቀረበላቸው ውለው ሲያድሩ ሲዎጡና ሲገቡ የሚያዩዋቸው የቆንስሉ ኃላፊዎች "ድልድዩ ስር ሂዱ እዚያ ጉዳያችሁን እንከታተለን " የሚለውን መልስ ከመስጠት ባይታቀቡም ምን መተማመና ትሰጡናላችሁ ለሚለው የግፉአኑ መሰረታዊ ጥያቄ መልስ ማቅረብ አልቻሉም። ... ህጻናት ነፍሰ ጡርና በበሽታ የደከሙ የሚገኙበት አብዛኛው ኢትዮጽያውያን እህቶችና በጣት የሚቆጠሩ ወንድሞች ለተከታታይ በአምስት ቀን የቆንስል በር ቆይታቸው አንዳንዶች በጠና እየታመሙ በአንቡላንስ ወደ ህክምና መወሰድ ጀመረዋል ... ባለመግባባቱ ዙሪያ ግን አሁንም ለውጥ አይታይም። ሁኔታው የጂዳ አካባቢዎችን ኢትዮጵያን ቀልብ ሳበና ነዋሪው ቆንስል መስሪያ ቤቱ ላይ ከተለያየ አቅጣጫ ጥያቄ ማንሳት ጀመረ።

ከቆንስል መስሪያ ቤቱ በር ለወደቁት ወገኖች በመጀመሪያ ቀናት ውሃና ምግን በማቅረብ አኩሪ ኢትዮጵያዊነት ስነምግባርን ያሳየው የጂዳ ኮሚኒቲ እንቅስቅሴ ግን የኮሚኒቲው አመራር በሆኑት ካድሬዎች ተቃውሞ አጋጠመው ተባለና ድጋፉ ተቁዋረጠ። በኮሚኒቲውና በቆንስሉ አስተባባሪነት የተቁዋቁዋመው የችግር አስወጋጂ ኮሚቴ ከሰበሰበው ገንዘብ ጋር የት እንደሄደ ቀድሞውኑ ጥያቄ ላይ የወደቀ ቢሆንም፤ አሁን ይህ ጥያቄ በሹክሹክታም ቢሆን መነሳቱ አልቀረም። መልስ ግን እስካሁን የለም። ሌላው ቀርቶ በህዝብ ድጋፍ የተሰራው ሁለት ክፍል መጠለያ እንኩዋ ለታመሙትና ለህጻናት መጠለያ ይሁን የሚል ሃሳብ ያቀረቡት የኮሚኒቲ ጥቂት የሥራ አስፈጻሚዎች በጉዋዶቻቸው አስፈጻሚ የፓለቲካ ካድሬዎች እንደ መንግሥት ተዋቃሚ ተቆጠሩና መናገር እንዳይችሉ ተሸበቡ። ችግሩ እየፈጠጠ ሲመጣ መፍትሄ ከማፈላለግ ይልቅ ህዝባዊ ግልጋሎትና ወገናዊነቱን ፈንግለው የኃላፊዎቻቸውን ወንበር ለማስጠበቅ ብቻ የሚተጉት የዘንድሮ አዳዲስ አፈጮሌ ካድሬዎችም በኮሚኒቲና በልማት ማህበራት ጉያ ተሸጉጠው የግፉአን ወገኖቻቸውን ችግር ከመቅረፍ ይልቅ ውንጀላውን ተያይዘውታል። ከአለቆቻቸው የተሰጣቸውን ትዕዛዝ ለማስፈጸም ነዋሪዎችን በማግባባት ወደ ድልድይ እንዲሄዱ በተላያየ መንገድ መማጸኑን ቀጥለውበታል። በዚህ ስራ የተሰማራውን ወንድም ተገፊዎቹን ሲያባብሉ ደረስኩ። ፊት ለፊት መጠየቁ ችግር እምዳያመጣ በሚል በኮሚኒቲው ካፍቴሪያ አገኘሁዋቸውና ወጋችንን ጀመርን። የሚሉትን ሁሉ ሰማሁና ወደ መጨረሻ ጥያቄየን አቀረብኩ።

ሌላ መፍትሄ ጠፋና ነው ይህን አማራጭ የምታቀርቡ? አልኩዋቸው፤ አፈጮሌ ወዳጀን ያምና ካድሬ ... "እንዴት መሰለህ እነኝህ ዜጎች እዚህ ተደርድረው ለቪዛ የሚመጡና ጉዳይ ለሚያስፈጽሙ ወገኖች የሰማንያ ሚሊዮንን ህዝብ ገጽታ ያጎድፋሉ። ብዙዎች ችግር የለባቸውም ከቤታቸው ጠዋት ጠዋት ነው በታክሲ የሚመጡት። እዚህ ሊያዙ ከቻሉ ሰው ሁሉ ቆንስሉን ስለሚያጨናንቅ ለወደፊት ችግር ይፈጠራል። ፖሊሶችም ቢሆን እዚህ አካባቢ አይዟቸውም።" ሲሉ አራምባና ቆቦ መልስ ሲመልሱልኝ እዚህ የመጡበት ምክንያት እኮ እዚያ ተደበደብን መጸዳጃ እንኳ አጣን በሚል ነው ለዚህ መልሱ እዚያ ተመለሱ ሊሆን ይችላል ወይ? በማለት ጥያቄየን አከታተልኩ ... "ይህንን አትመን "ሲሉ መለሱ ... በስጭት ብየ ከቅርብ ርቀት ከቅንድቡዋ ስር የተፈነከተችን ደክማ እህት ደሟ እንኩዋ ያልደረቀና በወጉ ያልተሰፋ ገላና ተመሳሳይ ድብደባ የደረሰበትን ወንድም ለማሳየት ሞከርኩ። መልስ የለም … ዝምታ ነገሠ ... የምላስ ወለምታ በቅቤ አይታሽም እንዲሉ ምስኪኑን ሰብስቦ ሲያንቡዋትሩ ያርፍደዋልና በስራቸው ያፈሩ መሰለኝ ... ወንድሜ ... በትዕቢት ቀና ብሎ የነበረውን አንገት ትንሽም ቢሆን ቀለስ አለ። ይህንን ይቀበሉታልን ስል ብጠይቅም ያ ጮሌ አንደበትና ምላስ ተሳሰረ። ግራ ተጋብዋልና በሃፍረት ተፋጠጥን። መልሱ ከየት ይምጣ! መልሱ ቢጠፋ አስቀድሜ የጠየቅኩትን ጥያቄ ነጠቁኝና "ታዲያ አንተስ መፍትሄው ምንድነው ትላለህ?" በማለት መልስ አጥቼ የጠየቅኩዋቸውን ጥያቄ እኔኑ ጠየቁኝና አረፉት ... ተግባብተናልና በትዝብት ተለያየን ...

የረመዳን ዋዜማ እየተገባደደ ቢሆንም ግፉአን ዜጎች ጩኸታቸውን ሰምቶ የሚያጽናናቸው እንዳጡ በቆንስሉ በር ሃሩሩን ተጋፍተው ሲኖሩ ላለፉት አምስት ቀናት ይገለገሉበት የነበረው የኮሚኒቲ መጸዳጃ ቤትም በተደጋጋሚ እየተዘጋባቸው ችግሩ እዚህም ተከትሎዋቸው መጥቶዋል ... ይህ የሆነው ግፉአኑን ለማስለቀቅ በኒያ ወንድሞቸ ትእዛዝ የተወሰደ መሰሪ ተንኮል ስለመሆኑ ግን እውነት እላችኋለሁ የማውቀው ነገር የለም። ... "ግመሉ ይጉዋዛል ... ውሾቹም ይጮሃሉ ነው" ያሉት ሰውየው? የውሾች ባይሆንም ጩኸቱ ቀጥሎዋል ... ጭኸቱን የሰማን የምስክርነት ቃላችን የመስጠት ሙያዊና ሀገራዊ ግዴታ አለብንና እኔም ሆንኩ መሰል ዜጎች የሆነውን ሁሉ እየተከታተልን በማስታወሻ መመዝገቡን ቀጥለናል ... (ይቀጥላል ...)

ቸር ይግጠመን !


ነቢዩ ሲራክ - ከሳውዲ ዐረቢያ

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ