Ploughing with cattle in southwestern Ethiopia.

"ውድ ልጀ ደባልቄ ሆይ! ፈረንጅ አገር የገባኽበት ዘመን ቢቆጠር የኹለት ጥጃ ዕድሜ ኹኗል፤ ላማችን ቀባሪ በየስድስት ዓመቱ ነው የምትወልደው፣ ሁለት ወይፈኖች አድርሳለች ..." አባትኽ ቢተው

ዘጌርሳም

የሰማዩን ርቀት፣ የምድሩን ስፋት፣ የባሕሩን ጥልቀት ያሕል ለጤናህ እንደ ምን ባጀህ? የሊቦው ጊዮርጊስ የተመሰገነ ይኹንና እኔም ሆንኹ እናትህ አለሙሽ ማንያዘዋል፣ ወንድሞችህ አንሙትና ይርጋ፤ እኅቶችህ ፍትፍቴና ዘርትሁን እንዲሁም እጎቶችህ ደብተራ ዋሴና መምህር መዝሙር፤ ሌላውም ዘመድ አዝማዱ በሙሉ ደኅና ነን። የአንተ ናፍቆት ግን እኔን ጤና ነስቶ እናትህንም ክስት ጥቁር አድርጓታል። ወንድሞችህም ትዳር መሥርተው ጨቅሎች አፍርተዋል፤ እኅትህ ፍትፍቴ ግን የብላታ ባይለየኝን ልጅ፣ ዳምጤን ልናጋባት ፍጥምጥም ተደርጎ፤ ማጫውም ተወስኖ፤ ቀን ተቆርጦ ድግሱ በመደገስ ላይ እንዳለ በውድቅት ሌሊት መንና ገዳም ገባችብን። እኛም የአባት እደሩን ካሣ ከፍለን ታረቅን። ዘርትሁን ግን ማለፊያ በለሴ የባለጠጋ ልጅ አግብታ ውባውብ ጉብሎች እድርሳልች፤ ለእኔና ለእናትህም የዓይን ማረፊያ ሆነውናል። ምኞትና ጠሎታችንም ይኽ ነበር። አንተም የአደባባይ ሰው ሆነኽ ለምድረ ሊቦ ዋስ ጠበቃ ትሆናለህ ብለን ስንመኝኽ፤ የጧት ግንባርህ ኾነና ዳር አገር ጥለኸን ጠፋኽ።

ልጄ ሆይ!

ለመሆኑ አንተስ ትዳር መሠረትኽ፣ ለፍሬስ በቅተህ ይሆን? መቸም የዘመኑ ልጆች የአባት አደሩን ትታችሁ ሚስትም መራጮች እናንተው ኹናችኋል፣ ይኹን እስቲ! ዋናው ነገር የዘር ሐረጉ አለመቆረጡ አይደል!? ወንድ ልጅ ወልደኽ ከሆነ፤ ”የነገው ሰው” ብየዋለኹ፤ ሴት ከሆነችም ”የትና የት” በላት።

አጎቶችህ ደብተራ ዋሴና መምህር መዝሙርም በትምህርታቸው እንዳንተው ትንኩሽት የሆኑ ልጆች አድርሰዋል። ማለፊያና ክፍት አንጎል አላቸው። ለነገሩማ ለአንተ እኮ ሊቀ ጠበብት ይባቤን ለልጀ አንጎሉን የሚከፍት አብሾ ያጠጡልኝ ብየ በጠየቅኋቸው መሠረት ስለአጠጡኽና ከማጅራትኽ አከርካሪ ላይ በጥተው መድኃኒት ስለቀበሩልህ እንጅ፤ እንኳንስ ፈረንጅ አገር ይፋግንም አትሻገር ነበር።

ሊቀ ጠበብት ይባቤ በአኹኑ ጊዜ የከምከምን ገበሬ ሞፈር እያሰቀሉ ናቸው፣ ገበሬው በነቂስ በሬ ፈቷል፤ አምርቶ ያቀና የነበረው ሸማች ኹኗል፤ ግብርናውንም ተጠይፎታል፤ በስማ በለው ተጠራርቶ አስኳላ ትምህርት ቤት ይውላል። በአውራ አጣት ካርኒና ቀላጤ ላይ መፈረም ቀርቷል፣ ድፍን ከምከሜ ስሙን ቆሎ እያስመሰለ መጣፍ ችሏል። ትምህርቱ ግን ከዚኽ ያለፈ ያስገኘው ረብ (ፋይዳ) የለም። በንጉሡ ጊዜ እንኳን አስኳላ ትምህርት ቤት መማር ለጠቅላይ ገዥነት፣ ለአውራጃ ገዥነት፣ ለወረዳና ለምክትል ገዥነት ዝቅም ካለ ለአጥቢያ ዳኝነት ከወረደም የፈረሰኛ ዐለቃ፣ ጭቃ ሹምና የጎበዝ አለቅነት ያሾም ነበር፣ ቦሊስና ያስኳላ መሪጌታነትም ቢያንስ አይጠፋም። ባኹኑ ዘመን ግን ተምረው ቢራቀቁም ጠብ የሚልላቸው የለም፣ ከበዛም ክላሽ ታጣቂና ገበሬ አስጨናቂ ከመሆን አይዘልም፣ ውጤቱ ዋግ የበላው የጤፍ ቡቃያ ዐይነት ነው።

ውድ ልጀ ደባልቄ ሆይ!

ይኸውልኽ ከከምከም ወጥተኽ ፈረንጅ አገር የገባኽበት ዘመን ቢቆጠር የኹለት ጥጃ ዕድሜ ኹኗል፤ ላማችን ቀባሪ በየስድስት ዓመቱ ነው የምትወልደው፣ ሁለት ወይፈኖች አድርሳለች፣ እንግዲህ አንተ አገር ለቀህ የሄድኽበት ጊዜ ቢቆጠር በሁለት ወይፈን ሸርፍ አንድ ሙሉ በሬ ኹነኻል ማለት ነው።

እኔ አባትህ የአባቴን ነፍስ ይማርና፤ አብሾ አያጠጡኝ እንጅ በድፍን ከምከም ብቸኛ ሊቅ ነበርኩ። ለጠሎት የሚነበበውን ሁሉ በቃሌ ነበር የማነበንበው፣ ችግሬ መጣፍ አልችልም። ለነገሩማ የወረዳ ገዣችን የነበሩት ባላምባራስ አርምዴም እንደ እኔ የጠሩ ጨዋ ነበሩ፣ ጥሑፍ ከሆነ የሁለታችንም ወዳጅ አውራ ጣት ነው፣ ያም ሁኖ የሚሰጡት ብይን እንደ ጠገራ ብር የነጠረና ዝንፍ የማይል ነበር። እረኛም በጊዜው “አርምዴ የፈረደው የእርብ ውኃ የቀደደው” ብሎ ዘፍኖላቸዋል፤ እናም እኔ አባትህ ድፍን ከምከም የተማረ አቅርብ ተብሎ ቢጠየቅ ከእኔ የሚያልፍ አይደለም።

ደባልቄ!

ለመሆኑ ኸዚያ ከጀርመን አገር የሰው መስተዳድር እንዴት ይመስላል? በኢትዮጵያ ቋንቋስ ያወጋሉ? መብልና መጠጣቸውስ ምን ይመስላል? አስተራረሳቸውስ እንዴት ነው? የእህሉ ሸሬታስ፣ ለመሆኑ ጤፍ ያመርታሉ?

ወደ ኢትዮጵያ አገር የሚመጡት ፈረንጆች ግብጥ ወይም ጥሊያን ይኹኑ አይታወቅም ሁሉም ነጮች ናቸው፤ ምድር ያፈራችውን ሁሉ ይመገባሉ ማለትን ብሰማ፤ ትንሽ በስጨት አልኩና፤ ”አይ ደባልቄ ልጀ ይኽን አይሠራም” ብየ ከእናትህ ጋር አወጋን። አሁን አሁን የሚመጡት ነጮች ደግሞ ቁመታቸው ከችፍርግ ቁጥቋጦ የማይበልጥ፣ ፊታቸው ጓጉንቸር የመሰሉና ሰባት ቀን እንዳልሞላው የውሻ ቡችላ ዓይኖቻቸው ያልተገለጠ፣ የሰውነት ትክላቸውም እንደ ድግር በአንድ መጥረቢያ የተጠረቡ የሚመስሉ፣ ለምድር የቀረቡና ለሰማዩ የራቁ፣ የሚመገቡትም ከርስ ምድር ያበቀለችውን ሁሉ ከአይጠ መጎጥ ጀምረው የአገራችን በግና ፍየል የተጠየፉትን ቅጠላ ቅጠል ሳይቀር ነው አሉ። ትላትሉም ለነሱ የዶሮ ወጥና ዝግን ምትክ ነው ይላሉ። አንዳንዶቹማ ከኢትዮጵያ ሴቶች ጋርም በመገናኘት ልጅ አስወልደዋል ይባላል። ድሮ ይመጡ የነበሩት ፈረንጆች እንደ ቅርቅሃና ባሕር ዛፍ ጠምበለሎች ነበሩ፣ መዋለዱ ግድ ከሆነ አይቀር እነሱ ሳይሻሉ አይቀርም ነበር፣ አለዚያማ የሚወለደው ልጅ አንተ ጋፍ (ድንክ) እየተባለ ሲሰደብ ሊኖርም አይደል!

ውድ ልጀ ደባልቄ!

እኗኗራችንና ሁለንተናችን ሳያሳስብህ አይቀርም፣ ነገር ዓለሙ ድብልቅልቅ ብሎብናል። ነጣነት፣ መሬት፣ ቤትና ንብረት የድርቅ ቡቃያ ኹነዋል፤ ያኔ በጨቅላነትህ የምታውቀው ሰፊው መሬታችንና የእርሻ ይዞታችን እንደ ሰንበቴ ዳቦ ተቆራርሶ የዳጉሣ አውድማ ያኽል ቀርቷል። ለከብቶች የግጦሽ ሣር፣ የታቦትና የአስክሬን ማሳረፊያ፣ ለሴቶች ውኃ መቅጃና ከብቶችን ውኃ ማጠጫ የሚባሉት ተረት ተረት ኾነዋል። የእርሻ መሬቱ ከልባምና ታታሪ ገበሬ ተነጥቆ ለቦለቲካ ደጋፊና ክላሽ ተሸካሚ የከተማ አውደልዳይ ተሰጥቷል፤ ማረስ ካማረህ ተጠማኝና ሲሶ አራሽ መሆን ነው፤ በግና ፍየልም ከቤት ታስረው ነው የሚውሉት እንጅ ማሰማሪያ ተራራና ሜዳም ጠፍቷል፣ የሚቀጥለው የዶሮ ተራ ሳይሆን አይቀርም።

የኑሮ ውድነቱ አገር ጥላችሁ ጥፉ ያሰኛል፣ ጤፍ፣ ጥራጥሬ፣ ጎመንና ሁሉም ለምግብነት የሚያገለግሉ ቁሶች ሸሬታቸውን ሲጠሩት ለጆሮ ይከብዳል። የጓሮ እሸትና የሽምብራው ማሳ የጫት ማብቀያ ሁኗል፤ ”ሳይደግስ አይጣላም” ይሏል ይኽን ነው። ይኽ ጫት የሚባል ነገር ደግሞ የሰራ አከላትን አደንዝዞ፣ የረኃብ ወስፋትን ገሎ ወተቴ እንደያዘው ከብት አደንዝዞ ሲያነኋልል የሚያውል ዕፅ ነው። አንዳንዶቹማ በጫቱ አንጎላቸውን ሲስቱ እንደ ጠንቋይም መኾን እየከጀላቸው ሕዝበ አዳሙን በማታለል፣ ትዳር ሳይቀር እያፋቱ ይገኛሉ። በአብዛኛው ጫት ሲያመነዥጉ የሚታዩት የምግብ ፍላጎታቸውን ለመግደል ነው የሚሉም አሉ። በቅርቡ አዲስ አበባ አንድ በየቀኑ እራሱን በጫት እያነኾለለ አውቅላችኋለሁ በማለት ብዙ ጥሪት ካፈራ በኋላ በሕዝብ ጥቆማ በቦሊስ ተይዞ ለፍርድ በመቅረብ ዓለም በቃኝ ዘብጥያ ወረደ አሉኝ። በዚህ መርዘኛ ጫት ሰበብ በየቀኑ አያሌ ወንጀል እየተፈጠመ አገሩም ታውኳል፣ መንግሥት፣ ቤተስኪያንና መስጅድም ጆሮ ዳባ ልበስ ያሉ ይመስላል።

በድሮውና ደጉ ዘመን በግና ፍየል ተገዝቶ ከአንጋሬ መልስ ሥጋ በነጣ የነበረው፤ ዛሬ የፍየልና በግ ዋጋ የአንድ የእርሻ በሬ መግዣ ያኽል ሲሆን፤ ዶሮም እንደ ፍየልና በግ ኹናለች።

የካሚዎን መንገድ በየደብሩ ተሠርቷል፣ አህያና አጋሰስን ያሳረፈ ቢመስልም፤ ነዋሪውን ግን ረድኤት አሳጥቶታል፣ በየመንደሩና ደብሩ የተገኘውን ምርት አሟጦ ወደከተማ ይጭነዋል፣ ሞኙ ባላገርም ጥሩ ሸሬታ ያገኘ መስሎት ለዘር ያስቀመጠውን ሳይቀር ጎተራውን አሟጦ በማቅናት ለካሚዎን ሲሳይ ያደርገዋል። ክረምቱና የዘር ወቅት ሲመጣ ደግሞ ኹሉም ለማኝና አራጣ ተበዳሪ ይሆናል። ያልቀናውም ለሽቀላ ሥራ ከተማ ይሰደዳል። መተዛዘን የሚሉት ነገር ጠፍቶ መነቻቸፍ ኹኗል፣ የከምክም ውሾች እንኳን ለቆሎ ተማሪ ያዝኑ ነበር።

በመሬቱ ጥበት ምክንያት ገበሬው ጥማዱን፣ ባል ሚስቱን፣ ሚስትም ባሏን እየፈቱ ወደከተማ የሚፈልሱት ስፍር ቁጥር የለውም “ያላወቁት አገር ይናፍቃል” ኾነና ኸዚያ ሲደርሱ ደግሞ በየጥርጊያ መንገዱ እንደ ፎግራ ከብቶች ተኾልኹለው ያድራሉ፣ ኪስ አውላቂውም ጭንቅ ነው ይባላል፤ የሚላስና የሚቀመስ የሚገኘው በአሳር ነው፤ መጠጊያ ቤት ለመከራየት ሕልም ነው፣ መሬት እንደባሶንዳ ገበያ አቡጀዲ በክንድ ተለክቶ ስለሚሸጥ ተመኑም አያሌ ነው፤ ለዚያውም ቤት ልሥራ እንኳን ብትል ንብረትህ ዛኒጋባዋ ብቻ እንጅ ቤቱ የቆመበት መሬት ያንተ አይኾንም፣ ለዘጠና ዘጠኝ ዓመት ተጠማኝ የመሆን መብት ግን አለህ ይላሉ። ስትሞትም ለምትቀበርበት ጉድጓድ ከፍለኽ ነው። ይኽ እንግዲህ በስማ በለውና በነጋሪት ጋዜጣ ተፈጥሞ የተነገረ የመንግሥት ቃል ነው፤ ይኹን እንጅ ሀብትና ንብረቱ በአዋጅ የታገደበት ኹሉ አፈርኩ ያለ ይመስላል፣ ጀንበር ስትጠልቅም እየተጠራራ ይዶልታል፣ በጠሐይማ ፊርማቶሪው እየጠቆመ ዓለም በቃኝ ያስዶለዋል፣ ፊርማቶሪውም እንደ ክረምት አሸን ፈልቷል፤ ሁሉም አፉን የተለጎመ ፈረስ ይመስላል፤ የጎሪጥ መተያየት እንጅ በግልጥ ማውጋት አይደፍርም። የበለሳና መልዛ ጫካ ቢመነጠርም ቀሪው ቁጥቋጦና ተራራው ሆድ ለባሰው መደበቂያና መሸፈቻ መሆናቸው አይቀሬ ነው፣ ባላገሩም በርዕስቱ መሸንሸን ጭስ እንደገባበት የንብ ቀፎ እምምም እያለ በማጉረምረም ላይ ይገኛል። ጥንትም እኮ እንዲህ ይባል ነበር፥

ባላገር ካፈረ በሬውን ከፈታ

ጅረቱ ከቆመ በቦይ ከተገታ

ጊዜ ነው ወሳኙ ማን እንደሚረታ

በዚህ አዋጅ አያሌ ሕዝብ ተጎድቷል ይባላል፣ በተለይ እንዳንተ ባሕር ማዶ ተቀማጭ የኾኑትን ግምኛ አካስሯቸዋል አሉ፣ የኢትዮጵያን ገንዝብ አየር ባየር ሸርፈው አያሌ ሀብት ካፈሩ በኋላ በርካታ ቤቶችን ሠርተው ስለነበር ደላላና ወኪል ብዙ አጣፍቷቸዋል፣ ለኑሮውም መወደድ ሰበብ የኾኑት እነሱ ነበሩ፣ ድሀውማ ኹሌም መናጢ ድሀ ነው። ያኹኖቹ ገዥዎች በኹሉም ላይ ጨክነዋል፣ ከመጠን ያለፈ ጥጋብና መፎርሸትም ይታይባቸዋል።

መቸም የመሬት ችግርን ከአንሳኹልኽ አይቀር፤ በእኛ ላይ ከደረሰውም የከፋ በጠቅላላው አገርህና በወገኖችህ ላይ ብዙ መከራና የቸገረ ነገር እየተፈፀመ ነው፣ ነገሩ ”እናቱ የሞተችበትና ውኃ ልትቀዳ የሄድችበት እኩል ያለቅሳሉ” ዐይነት እንጅ፤ የእኛስ መሬት ቢጠብና ቢሸነሸን የተካፈለው ያገሬው ሰው ነው። አገሬውም በጋብቻና በአበልዥነት ስለሚተሳሰር ዙሮ ዙሮ አብሮ መጠቃቀሙ አይቀርም፤ ሁሉም ከእጅ ወደ አፍ ኑሮ አያልፍም እንጅ። በሌሎች ጠቅላይ ግዛቶች ግን ኸዚህ የከፋ ነው፣ መሬቱ ከገበሬውና ከዘላኑ እየተነጠቀ ከዳር አገር ለመጡ ሕዝቦች ፓኪስታን፣ ሕንድ፣ ዐረብ፣ ጥሊያን እና ለሌሎች ፈረንጆች ለእያንዳንዳቸው ከአንድ ደብር አገር ስፋት የሚልቅ መሬት በዝቅተኛ ሸሬታ እየተተመነ እየተሰጣቸው ነው። የአገሬውም ሰው “ባይሆን ለእኔም የገንፎ እንጨት አልሱኝ” እንደተባለው ያለውን ሽጦና አራጣ ተበድሮ፤ እኔም ባይሆን የገንዛ መሬቴን እንድገዛ ይፈቀድልኝ ሲል ሰሚ ጆሮና ፈቃጅ ኃይል አያገኝም፤ የመጨረሻ ምርጫውም ቀየውን ያለ ውዴታው እየለቀቀ እግሩ ወደ መራው መሰደድ ነው። ይኽ ችግር ከፍቶ የሚታየው በሐረር፣ በባሌ፣ በሲዳሞ፣ በገሙጎፋ፣ በጅማ፣ በኤሉባቦር፣ በጋምቤላ፣ በወለጋ፣ በጎጃም፣ በጎንደርና በአፋር አካባቢዎች ሲኾን፤ በተለይ ጎንደርንማ ከውስጥም ከውጭም እንደ ቋንጣ እየዘለዘሉት ይገኛሉ። አንተና ጓደኞችህም መሬት ለአራሹ ይሰጥ ብላችሁ ፍዳ ስታዩበት የነበረውና የከፈላችሁት መሥዋዕትነት ሁሉ እንዲህ ውኃ በልቶት ቀረ። ወይ ነዶ! ዛሬማ ወንድ ነኝ የሚል ሽፍታም ጠፍቷል፤ ድሮ እንኳን አንድ ጀግና አመረርኩ ብሎ ሸፍቶ ጫካ ሲገባ ተከታየ እየበዛ ብዙ ጀግኖችን ያፈራ ነበር፤ ያ ለራሱም ያልኾነ ደርግ የሚሉት ጉግ ማንጉግ መንግሥት፤ የኢትዮጵያን ሕዝብ እንደባብ አራስ አራሱን ቀጥቅጦ ሐሞተ ቢስ አርጎት ሄደ። እኔ የአንተ አባት እርጅና ባይጫነኝ ኑሮ ተከታይም አላጣ ነበር፤ ይኽን የአኹኑን አውሬ መንግሥት ነኝ ተብየ ጉድ አፈላበት ነበር፤ ምን ያድርግ “እንኳን መሞት ማርጀት አለ” ተብሎ የለ! ይኸውልህ አንድ እንደኔ የተከፋ ባላገር እንዲኽ ብሎ አቅራራ፣

ወይ ነዶ ወይ ነዶ ወይ ነዶ መሞት

እንደ ሻማ ቀልጦ ጭሶ እንደ ኩበት

ልጀ ደባልቄ!

ተወኝ እባክህ ልጀ! የቱን ጀምሬ የቱን እጨርስልኻለሁ፤ ሌላም አንገት አስደፊ ጉዳይ አጋጥሞናል። በድሮው ዘመን ለትምህርት፣ ለደጅ ጥናትና ለእንጀራ ፍለጋ በአመዛኙ ቀየውን ለቆ የሚሰደደው ወንዱ ነበር፤ ጥሪት አፍርቶ ወደ ትውልድ አገሩም እየተመለሰ ተጋግዞ መኖር የተለመደ ባህል ሆኖ ቆይቷል። በአሁኑ ጊዜ ደግሞ የተገላቢጦሽ ሆኗል። ለአቅመ አዳም ያልደረሱ ልጃገረድ ጉብሎች ሳይቀር ለግርድና ሥራ ወደ ዐረብ አገሮች በደላላ እየተጭበረበሩ ተወልደው ያደጉበትን አገርና ወላጆቻቸውን እየተዉ ለአሰቃቂ አደጋዎችና ለሞት እየተጋለጡ ያሉበት ዘመን ደርሰናል። ሠርቶ መብላቱ ነውር ባይሆንም በነዚኽ እምቦጥ ጉብሎች ሕይወት ኢሰብአዊ ግፍ እንደሚፈፀምባቸው አያሌ ሰዎች በኀዘኔታ ይተርኩታል፤ ለደላላው የሚከፍሉት መጠንም ከአቅማቸው በላይ ስለመኾኑ በይፋ ይነገራል፤ ”ከወረቱ ስንቁ ልቁ” እንዲሉ! ደላላዎቹም ከመንግሥት ፈቃድ የተሰጣቸው ስለመኾናቸው በአደባባይ ይወጋል። ለግርድና ሙያ የሚቀጥራቸው ዐረባዊ ቤተሰብም እነዚኽን ለአገራችን ተስፋ ሊሆኑ ይችሉ የነበሩ ታዳጊ ጉብል ልጃገረዶች የተፈጥሮ የፀሐይ ሙቀትን እንኳን ለመሞቅ እንዲችሉ ፈቃድ አይሰጧቸውም ይባላል፤ ጀንበር ወጥታ ተመልሳ እስከምትጠልቅ ድረስ ከአንዱ ቤት ወደሌላው እየተዘዋወሩ በሥራ ሲባዝኑ ነው የሚውሉት።

እነዚኽ ታዳጊ ወጣት ሴቶች በዚኽም ይብቃችሁ አልተባሉም፤ ፈጣሪ ለኢትዮጵያ ሴቶች ያደላቸው የተፈጥሮ ውበት ተደራቢ ጠላት ኹኗቸዋል። ቀጣሪዎቹ ዐረባዊ እመቤቶች ባሌን ቀና ብለሽ አየሽ ወይም ፈልጎሽ ይኾናል በሚል እርኩስና ሰይጣናዊ ዕኩይ ስሜት በመገፋፋት በወጣቶቹ ላይ የሚያደርሱባቸው ያካልና የአእምሮ ጉዳት እጅግ ዘግናኝ ስለመኾኑ በየገበያው ሕዝቡ በአርምሞ ሲያወጋው መስማት ለሕሊና ዕረፍት የሚነሳ ጭንቀት ፈጥሮብናል። መከራው በዚህም ይብቃ አላላቸውም፣ በሚደርስባቸው የአካልና የአእምሮ ጉዳት ምክንያት ለሞት የበቁና የአልጋ ቁራኛ ኹነው የቀሩ ቁጥራቸው በርካታ ነው። ከመንግሥት እውቅናና ፈቃድ ተሰጥቷቸው በወጣቶቹ ላይ ይኽን ኹሉ መከራና ግፍ የሚያደርሱት ስግብግብና ሆዳም ነጋዴዎችና የመንግሥት ተቀጣሪ ሠራተኞች ናቸው። ለዜጎች መብት የሚቆረቆር ሕግ ቢኖር ኖሮ ለፍርድ ሊቀረቡ በተገባ ነበር፤ ለማን አቤት ይባላል? “ባላገር ተበድሎ ማሩኝ ይላል ዙሮ” የተባለው ዐይነት ሆነ። በኢትዮጵያ ወጣት ሴቶች ላይ እየተፈፀመ ያለው ግፍ የባሪያ ሽያጭ ዘመን ተብሎ ከሚታወሰው ጊዜ የከፋ ኹኗል። በነዚህ ወጣት ጉብሎች ጉልበት ደላላው የባለ ትልልቅ ፎቅ ቤቶች ባለቤት ለመሆን በቅቷል፤ ገንዘቡን ከየት አመጣኸው ብሎ የሚጠይቀውም የለም፤ የጥቅሙ ተካፋይ ከላይ እስከ ታች ያለው የሥልጣን ተዋረድ ነው ይባላል። ከቶ ይኽ ቀን ያልፍ ይኾን? ለዚህም ነበር አንዷ እንዲህ ብላ ያንጎራጎረችው፥

ያልፍልኛል ብየ ዐረብ አገር ሂጀ

መጣሁ ተመልሸ እንደ በግ ታርጀ

ኢትዮጵያዊነቴን ክብሬን አዋርጀ

አዲስ አበባ የሚመላለሱ ሲራራ ነጋዴዎችና በይግባኝ ሙግት ምክኛት የሚንገላቱ ያገርህ ሰዎች እንዳወጉኝ፤ ወደ ዳር አገር ለሚሄዱና ከዚያም ለሚመለሱ የኬላ ማለፊያ ወረቀት (እናንተ ቢዛ ነው አሉ የምትሉት) ለማውጣት እንደ አርበኛ ዘማች ተሰልፈው የሚውሉና የሚያድሩ ዕድሜያቸው በአሥርና ሃያ ዓመት መካከል የሚካተቱ እምቡጥ አበባ የሚመስሉ ልጃገረዶች አብዛኞቹ የዐረቡን አገር አለባበስ በቅድሚያ ተለማመዱ የተባሉ ይመስላል፣ ግማሽ ፊታቸውን ሸፍነው ዙሪያ ጥምጥም ሰልፍ ላይ ቁመው ሲታዩ አንጀትን ይበላሉ አሉ። ለማጋነንም አይደለም በግምት እስከ አምስትና ስድስት ዙሪያ ጥምጥም የቆሙበት ሰልፍ ተዘርግቶ በመጫኛ ቢለካ ከግማሽ በላይ የሚደርሰውን የአዲስ አበባ ወገብ ርዝመት ሳይሸፍን አይቀርም። ይህ እንግዲህ የአንድ ቀን ክስተት ሳይሆን፤ በየቀኑ የሚታይ ትይንት ነው። ከወጪ የኬላ መውጫ ፈቃድ ጠያቂው ባሻገር፤ ቢያንስ በየቀኑ ከአሥር የማያንሱ አስከሬኖች በወሮብላን እንደሚገቡ ውስጠ አዋቂዎች አበክረው ይናገራሉ። መቸም ጆሮ አይሰማው የለም አንዳንዶቹማ በቁማቸው እንደ አገርህ ዱር በእሳት እየተለበለቡና እንደ ዶሮ በፈላ ውኃ እየነፈሩ የተገደሉም አሉ ነው የሚባለው። አይ እርጅና! አገሬና ወገኖቸ እንዲህ ተዋርደው ልይ! በቁሙ የሞተ አለ ቢባል እኮ እኔ ነኝ። ለመኾኑ አንተ ከምትኖርበት አገር ያሉ ፈረንጆች ስለእኛ ምን ያወጋሉ? መቸም መሳቂያና መሳለቂያ እንዳደረጉን ነው የምገምተው።

አየህ ደባልቄ፣

አንተ ያኔ አልተወለድክም እንጅ የምትኖርባቸው ጀርመኖች በሁለተኛው ዓለም ጦርነት ጅልኛ ስለተጎዱ ብዙ ሰውም አልቆባቸው ነበርና ከጦርነቱ በኋላ አገራቸውን መልሶ ለማቋቋም ርካሽ የሰው ጉልበት ስላስፈለጋቸው የኛውን ንጉሥ አጤ ኃይለ ሥላሴን የርስዎን ሰዎች ይስጡንና ከእኛ አገር ሂደው እኛንም ይረዱናል፤ እኛም አስተምረን እራሳቸውን እንዲረዱ እናስችላቸዋለን ቢሏቸው ወገኖቻቸው የሚዋረዱባቸው መስሏቸው አይሆንም ለባርነት የማቀርበው ሕዝብ የለኝም አሏቸው ይባላል። ያኔ ተስማምተው ቢኾን ኖሮ እኔም አፍላ ኮበሌ ስለነበርኹ አንዱ እኾን ነበር። ያኔ ንጉሡ አይሆንም ያሉትም የሕዝባቸውን መማር ጠልተው ሳይሆን እንደውርደት ስለቆጠሩትና ለሃይማኖታቸውም ቀናዒ ስለነበሩ ሕዝቤ የፈረንጅ ሃይማኖት ተከታይ ይኾኑብኛል በሚል ወገናዊና አባታዊ መቆርቆርና ስጋት ነው። ጥሩና ተወዳጅ የአገር መሪ መሆን ማለት ለባንዲራው ለሕዝቦቹ ነፃነትና ክብር ተቆርቋሪ ሲሆን ነው፤ ወረዳ ገዣችን የነበሩት ባላምባራስ አርምዴ እንኳን ባቅማቸው አንድ ሽፍታ ተነስቶ የባላገሩን ቤት እያቃጠለ ዝርፊያ ሲፈጥም የማስተዳድረው ሕዝቤና ወገኔ ተደፈረብኝ በማለት በክተት አዋጅ ተከተለኝ እያሉ በመዝመት ሽፍታውን ካልገደሉ ወይም ከነነፍሱ ካልያዙ ዕረፍት አያገኙም ነበር፤ የአባት አደሩና መልካም አስተዳደር ማለት ይኽ ነበር፤ እናማ ዛሬ ነበር ማለት ብቻ ኾነ።

ውድ ልጀ ሆይ!

ብዙ በሆዴ ውስጥ ያለ የማወጋህ ነበረኝ፣ ያገሩ ርቀት ግን ገደበኝ፤ አሁንም የቻልክ እንደሁ ክረምቱ ጨክኖ ሳይገባና እርብም እንደልማዱ ሞልቶ አላሻግርም ሳይል መጥተኽ ዓይንህን አይተንህ ተመለስ። መቸም ያንተ ነገር ባዶ እጀን አልኼድም ብለኽ እንደምታስብ ስለማውቅ እኛ የሊቦው ጊዮርጊስ የተመሰገነ ይኹንና፤ ምንም የምንፈልገውና የጎደለብን የለም፤ አንተም በየጊዜው ስለላክልን ሙሉ ጌቶች ነን፤ የተመኘነው ዓይንህን ለማየት ብቻ ነውና ከቻልክ የእርሻው ሥራ ሳይጫነን በግንቦትና ሰኔው አካባቢ ለአጭርም ጊዜ ቢኾን አይተኸን ተመለስ፤ እናም ከእንግዲህ እኔንም ኾነ እናትህን እርጅናው እየተጋፋን ነው፤ መንገዳችን እኮ ከአሁን ወዲያ ቁልቁለት ነው። በተመቸህ ጊዜም አምቦ ሜዳ ድረስ በቀጠሮ አስጠርተኽ በስልኪቱ ድምጥህን ብንሰማ ደስ ይለናል፤ በተለይ አናትህ በናፍቆትህ ተሰይታለች፣ እስከምትመጣ ድረስም አደራ ጣፍልን።

የአያት ቅድመ አያቶችህ አምላክ ጤናና ዕድሜ ሰጥቶ በሰላም ወደ አገርህ ይመልስኽ!

አባትህ ባላምባራስ ቢተው አደፍርስ

አናትህ ወይዘሮ አለሙሽ ማንያዘዋል

ቸር ይግጠመን!

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!