20210302 adwa

ወንድማገኝ (ከኒውጀርሲ)

Dr. Fikre Tolosa's recent visit to New York

ስለ ኢትዮጵያ ጥንታዊነት ሥልጣኔና አገረ እግዚአብሔርነት ከመጻሕፍትም፣ ከኃይማኖት አባቶችም፣ ከታሪክ አዋቂዎችም ስናነብና ሲነገረን ኑሯል። አንዳንዱም በአገሪቱ ያለነውን ከሰማንያ በላይ ቋንቋ ተናጋሪዎች፣ ከፊሎቻችን ከሴም ሌሎቻችን ከኩሽ ነገድ እንደመጣን፣ ያንዳንዶቻችን ወደ ኢትዮጵያ አመጣጥም በ 700 እና በ 500 ዘመን የተገደበ እንደሆነ፤ ያንዱ ቋንቋ ተናጋሪ ወይም ጎሣ ሌላውን በቅኝ እንደገዛው እየተደረገ ሲወራ፣ አልፎ አልፎም አንዱ ሌላውን በጠላትነት ሲመለከት ቆይቷል፣ አሁንም ይታያል።

በ December 10 እና 11 2016 በኒውዮርክ መሐል ከተማ ማንሐተንና በቀጣዩ ቀን ደግሞ በኒዮርክ የጽዮን ቅድስት ማርያም የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ቤተክርስቲያን የሰማነውና አፋችንን ከፍተን ያዳመጥነው ኢትዮጵያዊነት ግን ለየት ያለ ነው። ባልተለመደ የታሪክ አፃፃፍ በመቅረቡ ያስደምማል። የታሪኩ አቅራቢ የሓዋርያነት ተልዕኮ የተሰጣቸው ይመስላሉ፣ በርግጥ ሥራቸውን ያቀረቡት በጥናትና በምርምር አስደግፈው ነው። የብዙ ሙያም ባለቤት ናቸው። አመጣጣቸው በቅርቡ ያሳተሙትን የኦሮሞና እና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ የሚለውን መጽሐፋቸውን ለማስተዋወቅ ነው፣ መጽሐፉን ሲያስተዋውቁ ግን መጽሐፉ ያካተታቸውን ቁምነገሮች በዕለቱ ለተገኘነው ታዳሚዎች ገልፀውልናል።

የመጽሐፉ ርዕስ ”የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛ የዘር ምንጭ” ይበል እንጂ፤ በውስጡ የያዘው ቁምነገር ግን ኢትዮጵያንና ኢትዮጵያዊነትን ነው። በኢትዮጵያዊነት ውስጥ ደግሞ አንድነትን፣ ፍቅርና ሰላም አለበት። ለዚህ ነው ሐዋርያዊ ተልዕኮ ያላቸው የመሰለኝ፣ እኒህ ምሁር ዶ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ይባላሉ፤ ዜግነታችው ኢትዮጵያዊ ነው፤ ቋንቋቸው ወይም ጎሣቸው ደግሞ ኦሮሞ ነው፣ በኢትዮጵያዊነታቸው ይኮራሉ፣ 4000 ዘመን በላይ ወደ ኋላ ሄደው የሳቸውም የኛም የሁላችንም አባት የሆኑትን በእየሩሳሌም የካህኖች ካህን የንጉሦች ንጉሥ የነበሩትን መልከ ጼዴቅን የኢትዮጵና የሌሎች ልጆች አባትነት መነሻ አድርገው የዘር ግንድ መቁጠር ሲጀምሩ፤ እኔና እንደኔው የሚያዳምጡ መገረም እንጀምራለን። ያም ብቻ አይደለም፤ እኒህ የካህኖች ካህን የንጉሦች ንጉሥ መልከ ጼዴቅ ከሁለት ሺህ ዓመት በኋላ ሞትን ድል አድርጎ የሰውን ልጅ ከሐጢያቱ ለማዳን ከሰው ልጅ ተወልዶ የካህኖች ካህን የንጉሦች ንጉሥ የሚባለውን የእየሱስ ክርስቶስ ተምሳሌት እንደሆኑ ለአባታችን አብርሃም ስለተገለፀለት መልከ ጼዴቅን እጅ ሊነሳና መስዋት ሊያቀርብ አብርሃም ወደ መቅድስ ሄደ ይሉናል። በዚህም እስራኤላውያን በሙሴ ላይ ቅሬታ አንስተው እንደነበር አጫውተውናል። ታዲያ ከመልከ ጼዴቅ ልጅ አንዱ የሆነው ኢትዮጵ ለአባቱ ለመልከ ጼዴቅ ከእግዚእብሔር በተነገረው መሰረት ወደኢትዮጵያ እንደመጣና በጣና ዙሪያ እንደሰፈረ፣ እርሱም 12 ልጆች እንደነበሩት ነበር የነገሩን። እነዚህ 12 ልጆችም አንዱ የአማራ ሌላው የኦሮሞ ሌላው የትግሬ ሌላው የጉራጌው አባት ሌላውም የሌላው ጎሣ እንደሆኑ ይዘረዝራሉ። ባጠቃላይ እኛ ኢትዮጵያውያን እንደሰውነታችን በሌሎች ዓለም ከሚኖሩት ጋር በአዳምና በሔዋን ወንድምና እህት መሆናችን፣ እንደኢትዮጵያውያንነታችን ደግሞ ሁሉም ጎሣ ወይንም ቋንቋ ተናጋሪ ከፍ ሲል የመልከ ጼዴቅ ከዛም ሲቀጥል የኢትዮጵ ከዛም የደሸት ልጆች መሆናችንንና የሁላችንም ማንነት ኢትዮጵያዊነት መሆኑን ነበር የነገሩን።

አሁን ማንነታችን ጠፍቶብን ለምንደናገረው ትውልድና መጽሐፉን ለመፃፍ ያነሳሳቸውን ሃሳብ በመጽሐፋቸው መግቢያ ላይ እንዲህ ይሉናል።

“ፈረንጆች የፃፉልን ታሪካችን ወጣቶቻችንን በማንነት ቀውስ የከተተ ከመሆኑም በተጨማሪ፤ እርስ በርሳችን እንዳንግባባ እና እንዳንተማመን ከማድረግም አልፎ ደም ያፋሰሰም ሆኗል። ከሁሉም በላይ ደግሞ እያንዳንዱ ብሔረሰብ ለኢትዮጵያ ህልውናና ሥልጣኔ ያደረገውን አስተዋፅኦ እና ክብር እንዳናውቅ ብሎም እንዳናደንቅ እንቅፋት ሆኖብን ቆይቷል። ይህ የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ የተሰኘው መጽሐፍ ግን በእኛ በኢትዮጵያ ልጆች መካከል ያለውን ያለፈ ጥርጣሬ አፅድቶ መነሻ ምንጫችንን አሳይቶ በአኩሪ የጋራ ታሪካችን ውስጥ ሁላችንንም አካቶ ወደሰላምና ስምምነት እንድንመጣ መርቶ በመካከላችን እውነተኛ የወንድማማችነት መንፈስ ያሰፍናል ብዬ ተስፋ አድርጋለሁ”

ሙያዊ ትንታኔውን ለባለሞያዎች ልተወውና፤ ሰው የተለየ የቆዳ ቀለም ስላለው የተለየ ቋንቋ ስለተናገረ ብቻ በጠላትነት ሊተያይ አይገባም። ዘረኝነትና ጥላቻ ከጊዜ በኋላ ከክፉዎች የተማርነው እንጅ ማናችንም ከማናችን የምንበልጥበት ሁኔታ የለም።

ታዲያ ዛሬ በአገራችን የጥላቻን መርዝ የሚረጩ እኩይ የወያኔ ሰዎች እንደመመሪያ አድርገው ሕዝቡን ሲያባሉትና ይባስ ብለው ጮርቃ የትግራይ ሕፃናትን ቃላሚኖን በመሰለ ትምህርት ቤት ጥላቻን እንደትምህርት ወስዶ እንደ አቶ ኤርሚያስ አገላለጥ ኢንዶክትሪን ማድረግ ይቅር የማይባል በደል ነውና፤ ከዚህ መአት ለመውጣት ሁላችንም አንድ ሆነን ወያኔን አስወግደን የጋራ አገራችን እንገንባ።

ዶክተር ፍቅሬ ኦሮምኛ ከላቲን ፊደል ይልቅ የራሱ የሆነው የግዕዝ ፊደል እንዴት ጠቃሚ እንደሆነ ከክርስቶስ ጀምሮ አባታችን ሙሴ እንዲሁም ኖህና ሌሎች ኢትዮጵያ እንደቆዩ ጊዜያቶችን እየጠቀሱ አጫውተውናል የንግሥት ሳባንም እውነተኛ ታሪክ እንዲሁ።

የኔ ማጠቃለያ በሁሉም ወገን ያለን ጥላቻን እንደመርዝ የምንረጭ ወገኖች እራሳችን እንመርምር፤ ከጥላቻ የሚገኘው ትርፍ ሞት ነው። አዎ! ሁለት ሞት፣ በምድርም በሰማይም። ዶክተር ፍቅሬን ብትችሉ በያላችሁበት እንዲመጡ አድርጉና አዳምጧቸው፤ ትረካላችሁ። ትኮራላችሁ። ካልቻላችሁ ደግሞ መጽሐፋቸውን አንብቡ።

እግዚአብሔር ኢትዮጵያንና ሕዝቧን ይባርክ!

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!