ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ

New book by Prof. Fikre Tolossa

ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ “የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ” በሚል ርዕስ ባለፈው ሐምሌ (2008 ዓ.ም.) አዲስ አበባ ላይ አንድ መጽሐፍ አሳትሞ ኖሮ፥ አንድ ዘመድ አንድ ቅጂ አመጣልኝ። አነበብኩት። ስለመጽሐፉ የሚባለውንና ደራሲው ከሰጣቸው ቃለ ምልልሶች (interviews) አንዳንዶቹን ሰምቻቸዋለሁ። ከዚህ በታች የምጽፈው፥ የጽሑፌ ርዕስ እንደሚያመለክተው፥ የደራሲውን አስተዋፅኦ ነው። ድርሰቴ የመጽሐፍ ግምገማ (Book review) ቢመስልም፥ የመጽሐፍ ግምገማ አይደለም።

ግምገማ ቢያስፈልግስ ዶክተር ፍቅሬ ቶሎሳ ዋና ምንጩ ያደረጋቸውን የአማን በላይ መጻሕፍትን እንጂ፥ “የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ”ን አይደለም። ግን ከአማን በላይ መጻሕፍት አንዳቸውም እንደታሪክ ምንጭነት ለግምገማ ከሚያበቃ ደረጃ ላይ ያልደረሱ፥ አልፎ አልፎ በእውነት ታሪክ የተቀመሙ ልብ ወለድ ታሪኮች ናቸው። ዶክተር ፍቅሬ እውነተኛ የታሪክ ምንጮች አድርጎ ተቀብሏቸዋል። ግን ዶክተር ፍቅሬ በአማርኛ ሥነ-ጽሑፍ ስም ያወጣ የምናደንቀው ደራሲያችን እንጂ፥ በታሪክ መስክ ከታሪክ ምሁራን ጋር ተሰልፎ አላየሁትም። እሱ ራሱም ቢሆን “ስለ[ራሱ] አጭር መረጃ” ብሎ መጽሐፉ ውስጥ ራሱን ባስተዋወቀባቸው አንቀጾች ውስጥ ስለ ታሪክ ዕውቀቱ ከዚህ የተለየ ነገር የለባቸውም። መቸም ቢሆን አንድን ምሁር ችሎታው በአንድ መስክ ሥሉጥ ካደረገው በሌሎች መስኮች ላይም (ከመ፡ ዘሥልጣን፡ ቦ፡) ሥሉጥ እንደማያደርገው ለፕሮፌሰር ፍቅሬ የተደበቀ ነገር አይመስለኝም። ሁኔታው ይኼ ሁኖ ሳለ፥ እስካሁን ያለውን የታሪክ ምንጭ በታሪክ ጸሐፊዎች ደረጃ ምሁር ሆኖ ሳያጠናቸው፥ መቅድሙ ውስጥ፥ “ይህ ፅሑፍ ሀተታ እስካሁን የነበሩና የተለመዱ አንዳንድ መሰረታዊ ግንዛቤዎችን ሙሉ በሙሉ ውድቅ የሚያደርግ አዲስ ታሪክ ነው” ይለናል። እውነትም አዲስ ታሪክ ነው። ግን የዶክተር ፍቅሬ ድርሰት የአማን በላይን ልብ ወለድ ታሪክ (ሚቶሎጂ (Mythology) አንዳንድ ነገር እያከለበት ከማስተጋባት አልፎ፥ በውስጡ “እስካሁን የነበሩና የተለመዱ አንዳንድ መሰረታዊ ግንዛቤዎችን ሙሉ በሙሉ ውድቅ የሚያደርግ” ቁም ነገር አላየሁበትም።

በአንዳች ምክንያት የተፈጠረ ልብ ወለድ ታሪክ (mythology) እና እውነተኛ ታሪክ በአንድ ዘመን አንድ መስክ ላይ ስለማይውሉ፥ ተከባብረው ይኖራሉ እንጂ፥ አንዱ ሌላውን ሙሉ በሙሉ ውድቅ አያደርግም። በኔ ግምት መሪራስ አማን በላይና ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ብሔራዊ ሚቶሎጂ ደርሰዋል። ግን ሚቶሎጂና ታሪካዊ ጽድቆች በቅደም ተከተል እንጂ በአንድ ዘመን አይፈጠሩም። ሚቶሎጂ ይቀድማል ታሪክ ይከተላል። ሚቶሎጂ ታሪክ ከጸደቀ በኋል በታሪክነት አይወለድም። ስለዚህ ሁለቱ አብረው ጎን ለጎን አይሄዱም። ሚቶሎጂ እንደ ታሪክ ምንጭ ለብዙ ዘመናት ብቻውን ሲያገለግል ቈይቶ፥ የታሪክ ተመራማሪዎች ተነሥተው እውነተኛውን ታሪክ ሲጽፉ፥ ሚቶሎጂ የታሪክነት ቦታውን ይለቃል። ሲለቅ “ይጣላል” ማለት አይደለም። በሥነ ጽሑፍ ደረጃ ሕፃናት በትምህርት ቤት ይማሩታል። በአንድ በኩል፥ የግሪክን ሚቶሎጂና ታሪክ፥ በሌላ በኩል ክብረ ነገሥትንና የኢትዮጵያ ታሪክ እንደ ምሳሌ መጥቀሰ ይቻላል።

የመሪራስ አማን በላይና የፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ ሚቶሎጂ ብሔራዊ ችግራችንን ለመፍታት በብሔራዊ ችግራችን ጊዜ የደረሰ እንጂ በራሱ ጊዜ አልተፈጠረም። መምጣት ያለበት ታሪክ ሳይጻፍ ነበር። የመጣው ታሪክ ከተጻፈ በኋላ ስለሆነ ክንፍ የለሽ አሞራ ሆኗል።

እርግጥ ደራሲዎቹ ያቀረቡት እንደ እውነተኛ ታሪክ ነው። ይህም አያስገርምም፤ “ታሪክ ነኝ” ማለት የሚቶሎጂ ጠባዩ ነው። ለታሪክ ዐዋቂዎች ግን ዘመኑ ያለፈበት መሆኑን ያልተገነዘበ የበጎ አድራጎት ፈጠራ ነው። ሆኖም ኢትዮጵያ ውስጥ ታሪክ ዐዋቂዎች ጥቂት ስለሆኑ አብዛኛው ሕዝብ ድርሰቶቻቸውን እንደ እውነተኛ ታሪክ ወስዶላቸዋል። ሕዝቡ ታሪክ ለመማር ዕድል እስኪያገኝ ወይም የአገሩን ታሪክ የሚያውቅ አዲስ ትውልድ ተነሥቶ የአንድነታችንን እውነተኛ ምክንያት እስኪረዳ ድረስ በነዚህ መጻሕፍት መጠቀም ሊኖርበት ነው።

እውነተኛ ታሪካችን ከዘመዶቻችን አንዶቹ ቀድመው በያዙት ቦታ ላይ ሌሎች ተከትለው አንድ ቦታ ላይ (ማለት፥ ኢትዮጵያ ውስጥ) ተገናኝተው ልጆቻቸው ለብዙ ዘመናት አብረው ስለኖሩ፥ ዘመን አንድ ሕዝብ አድርጓቸዋል፤ በባህልና በደም አዛምዶናል። ለዚህ ማስረጃ የሚሆኑ ነገሮች ዶክተር ፍቅሬ ቶሎሳ መጽሐፍ ውስጥ በብዛት ይገኛሉ። በሌላ አጋጣሚ ከሌላ ቦታ እንደጻፍኩት፥ ዛሬ አማራ፥ ትግሬ፥ ጉራጌ፥ ኦሮሞ፥ ዶርዜ የምንለው የለበስነው የቡድን የመለዮ (“የማሊያ”) ስሞች ናቸው፤ አርሴናል፥ ሊቨርፑል፥ ቸልሲ፥ ማንቸስተር ዩናይትድ እንደሚባሉት የእንግሊዝ ኳስ ተጫዋቾች ቡድን ማለት ነው። መለዮው አንድ ቡድን ያደረጋቸው ከየቦታው የመጡ ተጫዋቾች ናቸው። የኛም ነገዶች ውስጣቸው ቢገለጥ፥ ከነዚህ ቡድኖች ብዙ አንለይም። አማራ ነኝ፥ ጉራጌ ነኝ፥ ኦሮሞ ነኝ የሚል ሰው ትውልዱን ወደኋላ መቁጠር ቢችል፥ አላለው ላይ ይደርስ ነበር።

ዶክተር ፍቅሬ ሚቶሎጂውን እውነተኛ ታሪክ ለማስመሰል ሲጥር ስለ ምንጮቹ እንዲህ ይላል፤

ታሪኩ የተመሠረተውም በመጽሐፍ መደብሮች በሚገኙ የአማርኛ እና የእንግሊዝኛ ሥነ-ጽሑፎች ላይ ነው። ከእነዚህ ጽሑፎች ሱዳን ኑብያ፣ ጀበል ኑባ በተባለ ስፍራ በአንድ የኢትዮጵያ ተዋህዶ ቤተ ክርስቲያን ፍርስራሽ አጠገብ ተቀብረው መሪራስ አማን በላይ በተባለ ወጣት መናኝ ከ50 ዓመት በፊት የተገኙና አጥረውና ወደ አማርኛ ተተርጉመው “መጽሐፈ፡ ሱባኤ” እና “የኢትዮጵያ ትንሣኤ ታሪክ” በሚሉ ርዕሶች የታተሙ ጥንታውያን የግዕዝ ብራና ጥቅሎች ይገኙባቸዋል። እነዚህ የኢትዮጵያ ብራና ጥቅሎች እስራኤል አገር ኩምራን በተባለ ቦታ በአንድ ዋሻ ውስጥ በእረኞች ከተገኙት የሙት ባሕር ብራና ጥቅሎች ጋራ ተመሳሳይነት አላቸው። እነሱ፣ እነዚህና ሌሎችም መጻሕፍት ከስድስት ዓመት በፊት ድንገት እጄ ገቡ።

ታሪክ የማገኝባቸው መስሎኝ እኔም የአማን በላይን አንዳንድ መጻሕፍት ከዶክተር ፍቅሬ ቶሎሳ ገዝቼ አንብቤያቸዋለሁ። ከዶክተር ፍቅሬ ቶሎሳ ጋርም በስልክ ተችተናቸዋል። አማን በላይ የጻፋቸው ሁሉ በታሪክ ዓይን ሲታዩ ከሚቶሎጂነት አያልፉም። ሰውየው ሚቶሎጂውን የደረሰው ከእውነተኛው የነገሥታት ታሪክ ላይም የሚያስፈልገውን ያህል እየወሰደ ነው። ለምሳሌ የነገሥታቱ ስም ዝርዝር እውነት የሚመስለው ከእውነተኛ ታሪክ ምንጭ ስለተወሰዱ እንጂ ከጀበል ኑባ ተገኘ ከተባለው ሰነድ ውስጥ ተገኝቶ አይደለም። አንድ ንጉሥ አንድ ቀን ብቻ ነግሦ፥ የንግሡ ዕለት ሕዝቡ ሊያየው ሲጋፋ ገደለው የሚለውም ከእውነተኛው የኢትዮጵያ ነገሥታት ታሪክ የተወሰደ ነው። ዶክተር ፍቅሬም እንዲህ ሲል ይስማማል፤

አክሱማዊው ሲራክ በአክሱም የንጉሠ-ነገሥት ውድም አስፈሪ [=አስፈሬ] ልጅ ከነበረው ከሕዝብ ባርኮ [= ባርክ] የሚወለድ ልዑል ሲሆን፣ የቤተ-መንግሥቱ መጻሕፍት ያዥ እና ንብረት ኃላፊም ነበር። እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ879 ዓ. ም. አስቴር በመባል የምትጠቀሰ ዮዲት ጉዲት በወቅቱ የነበረውን መንግሥት ገልብጣ መኳንንቱን ልትገድል ስታሳድድ አክሱማዊው ሲራክ መጽሐፈ ሱባኤን እና ሌሎችንም ጠቃሚ ቅርሶችን ይዞ ከአክሱም ወደግብፅ ተሰደደና በኑቢያ ተቀመጠ። በመጽሐፈ ሱባኤ ውስጥ ታሪከ-ነገሥት ዘኢትዮጵያ የተሰኘ ሌላ መጽሐፍ ነበር። ታሪከ-ነገሥት ዘኢትዮጵያ ከቀዳማዊ ኢትዮጵ ጀምሮ በዮዲት እስከተገለበጠው የመጨረሻው የአክሱም ንጉሠ-ነገሥት እስከ ንጉሥ ውድም አስፈሪ [= አስፈሬ] ድረስ የነበሩትን ነገሥታት የሚዘረዝር ነው። አክሱማዊ ሲራክ ታሪከ ነገሥትን ጨምሮ መጽሐፈ ሱባኤን ከግዕዝ በፊት ከነበረው ከጥንቱ የሱባ ቋንቋ በሦስት ቋንቋዎች ተርጉሞ ለትውልድ እንዲደርስ አድርጓል።

ደራሲው እንደሚለው፥ እነዚህ የኢትዮጵያ ብራና ጥቅሎች የተባሉት እውነት ከቁምራን ብራና ጥቅሎች ጋር ተመሳሳይነት ቢኖራቸው የዓለም ሊቃውንት ለቁምራን ብራና ጥቅሎች የሰጡትን ከፍተኛ ትኩረት ይሰጧቸው ነበር። እነዚህ በሱባ ቋንቋ የኢትዮጵያ የብራና ጥቅሎች የተባሉ ምንጮች ግን አማን በላይ ለሚቶሎጂው የፈጠራቸው ስለሆኑ በአካል የሉም። በዶክተር ፍቅሬ ቶሎሳ መጽሐፍ ሽፋን ላይና ውስጥም ያሉት “የሱባ ቋንቋ” ሥዕሎች የአማን በላይ አንጎል የፈጠራቸውና ብዕሩ የሣላቸው ናቸው። የጥቅሎቹ የመገኘት ታሪክ በዓለም በተከበሩ ምሁራዊ መጽሔቶች ላይ አንድም ቦታ ያልተነበበው ስለነዚህ ነው። ሌሎቹ ቢቀሩ እንኳን፥ አዲስ አበባ የሚታተመው Journal of Ethiopian Studies እና የዶክተር ፍቅሬ ቶሎሳ ፒ.ኤች.ዲ. ፈታኝ የነበረው ፕሮፌሰር ሪቺ ኖፖሊና ሮም ውስጥ ያሳትመው የነበረው Rassegna di Studi Etiopici ታሪኩ እውነት ሆኖ ቢያገኙት ተሽቀዳድመው በደስታ ያወጡት ነበር። ቀርቦላቸው አላወጡት እንደሆነ፥ ፈጠራ መሆኑን ተረድተውት ነው። ይኸን የምለው ከነዚህ እና እነሱን ከመሰሉ ሌሎች መጽሔቶች ጋር የቅርብ ግንኙነት ስላለኝ ነው። ታሪኩ ለምን እነዚህ መጽሔቶች ላይ እንዳልተነበበ ዶክተር ፍቅሬ ቢጠየቅ፥ አሳታሚዎቹን “የኢትዮጵያ ታሪክ ጥናት ጠበብት ተብዬዎች” እያለ ስለሚመጻደቅባቸውና የሚጽፉትንም “የጠነዙ ገለፃዎች” እያለ ስለሚሰድባቸው፥ ምን መልስ እንደሚሰጥ መገመት አያዳግትም። በእሱ ግምት፥ ይኸንን የኢትዮጵያን ታላቅነት የሚመሰክር ምንጭ እንኳን ልናሳትመው ዞር ብለንም እንኳን አናየውም። አንድ ወዳጄ የሆነ ሰው ወዳጁን አማን በላይን፥ “አገኘኋቸው ስለምትላቸው የብራና ጥቅሎች፥ ጌታቸው ኃይሌን አነጋግረው” ብሎት እንደነበረና አማን በላይም ተስማምቶ እንደነበረ ወዳጄ ነግሮኛል። አማን በላይ ወደኔ አልመጣም፤ እዚያው አዳማጭ ካገኘበት ቀርቷል ማለት ነው።

ታሪካችንና አዲሱ ሚቶሎጂ ከማይስማሙባቸው ብዙ ነጥቦች ውስጥ ጥቂቶቹን ላሳይ፤

1. በኢትዮጵያ መልክዐ ምድር ላይ ብዙ በኦሮሞ ስሞች የተጠሩ ቦታዎች አሉ። እነዚህ የቦታ ስሞች ኦሮሞዎች በ16ኛው ምዕት ዓመት ኢትዮጵያን ሲይዙ የተሰየሙ እንጂ፥ ለዶክተር ፍቅሬ እንደመሰለው፥ ጥንታዊነት የላቸውም። ከ16ኛው ምዕት ዓመት በፊት እንደሌሉ ማስረጃው ከዚያ በፊት በተሣሉ ካርታዎች ላይ አለመገኘታቸው ነው።

2. “ጎሣ “ጐሥዐ” ከሚለው የግዕዝ ቃል የወጣ ነው” ይላል። ልክ አይደለም፤ በሁለት ቋንቋዎች ውስጥ ተመሳሳይ ድምፅ ያላቸው ቃላት ሁሉ ተመሳሳይ ሥርና ትርጉም እንዳላቸው የሚያውቅ የፊሎሎጂ ዕውቀት ያለው ሰው ብቻ ነው። አለበለዚያ የእንግሊዝኛውን grocery ከአማርኛው “ጥሮ ግሮ ሠሪ” ጋር ያዛምዳቸዋል። ዶክተር ፍቅሬ ቶሎሳ ተመሳሳይ ድምፅ ያላቸው ቃላት ሲያጋጥሙት ሳያዛምድ አይለቃቸውም። ይኼ folk’s etymology “ሕዝባዊ የቃላት ሥር ትንተና” ይባላል። ለዚህ ጥሩ ምሳሌ የሚሆን አንድ ታሪክ ላንሣ፤ አንድ ጊዜ አንድ መምህር “ዕንቍ ጣጣሽ” ማለት ከየት የመጣ ነው ቢሉት፥ “ንጉሥ ሰሎሞን ንግሥተ ሳባን ሲያግባባት ጣጣሽ ዕንቍ ነው ብሎ ዕንቍ ሰጥቷት ስለነበረ ቃሉ ከዚያ ሲያያዝ የመጣ ነው” አሉ። አቶ ጸጋዬ ገብረ መድኅንም እንዲህ ዓይነት መሠረተ ቢስ የቃላት ትንተና ነበረው።

3. የንግሥተ ሳባ ስም ኤትያኤል የእናቷ ስም አዝሚና ነው። ይህ የአማን በላይ ልብወለድ ታሪክ ከእውነተኛው ታሪክ ጋር አብሮ አይሄድም። እነዚህ ስሞች ከአማን በላይ ሚቶሎጂ ውጪ የትም እሌላ ቦታ አይገኙም። ብሉይ ኪዳን ስሟን ሳይጠራ “የሳባ ንግሥት” (በዕብራይስጥ “ማልከት ሽባ”) ብሎ ነው ያለፈው። ዐረቦች “ቢልቂስ” ይሏታል። ክብረ ነገሥቱ “ማክዳ” የሚለው እሷን ሊሆን ይችላል፤ ግን አጥጋቢ ማስረጃ የለንም።

4. ንግሥተ ሳባን “እየሱስ ክርስቶስ “የአዘቦ ንግሥት” ሲል ጠርቷታል፤ (ይልና ማብራሪያውን እንዲህ ሲል ይቀጥላል) “አዜብ” የሚለው ቃል ከየት የመጣ ነው? ከንግሥተ ሳባ ህልውና 900 ዓመት በፊት ኢትዮጵያን ይገዛ የነበረ ንጉሥ ስም ነው” ይላል። ይኼ አነጋገር ለሚቶሎጂም እንኳን ይበዛል። ወንጌላውያን ቃሉን በግሪክኛ እንደመዘገቡት፥ ኢየሱስ ክርስቶስ ያላት “ባሲሊሳ ኖቱ” ነው። ይኽ ወደ ግዕዝ ሲተረጐም “ንግሥተ አዜብ”፥ ወደ አማርኛ ሲተረጐም “የደቡብ ንግሥት”፥ ወደ እንግሊዝኛ ሲተረጐም “Queen of the south” ይሆናል። ኖቱ፥ አዜብ፥ ደቡብ፥ south አራቱም ትርጉማቸው አንድ ነው። ዶክተር ፍቅሬ ቶሎሳ ወንጌሎቹ የተጻፉት በግዕዝ መስሎታል።

5. ገጽ 101 ላይ በአማርኛ ፊደል የተጻፈ ኦሮምኛ ክርታስ (ጥቅል) አትሞ፥ “የጥቅሉን ዕድሜ በትክክል ልነግርዎ አልችልም፤ እንደሚያዩት ግን ዕድሜ-ጠገብ ይመስላል። ቢያንስ አንድ ሺ ዓመት እገምተዋለሁ። በአንድ ጥንታዊ የኢትዮጵያ ገዳም ውስጥ ነው የተገኘው” ይለናል። አንደኛ፥ ከብራና ጽሑፍ ጋር በቂ ልምምድ የሌለው ሰው ጽሑፉን አይቶ ዕድሜውን መገመት አይችልም። ሁለተኛ፥ የተጻፈው በአማርኛ ፊደል እንጂ፥ በግዕዝ ፊደል አይደለም። እዚህ ጽሑፍ ውስጥ የሚታዩት እነ “ጨ” እነ “ቸ” ከአንድ ሺ ዓመት በፊት አልተፈጠሩም ነበር። ሦስተኛ፤ የጠቅላላ ፊደሎቹ አጣጣል እንደሚያመለክተው፥ የዚህ ጽሑፍ ዕድሜ ከአንድ መቶ ዓመት አይበልጥም።

6. ገጽ 84-89 ላይ (መጽሐፉ ሽፋን ላይም) የሱባ መጽሐፍና ፊደላት ይገኛሉ። ሊተረጕማቸውና ምስጢራቸውን ሊፈታ የሚችለው ፈጣሪያቸው አማን በላይ ብቻ ነው። ግን መዝገበ ቃላትም አብሮ ተገኝቷል ሲል ሚቶሎጂውን ተአማኒ አስመስሎታል።

7. ከ3 ሺ ዓመት በፊት ቀዳማዊ ምኒልክ “ኦቺ” የተባለና ከመደባይ/ኦሮሞ የተውጣጣ ጠንካራ ሠራዊት ነበረው [ቀ]ዳማይ ምኒልክ ይህንን ጦሩን “ጨዋ” (ሸዋ) ብሎ ሰየመው እና የዛሬውን ማዕከላዊ ኢትዮጵያን ወረረ። ከዚያም ጦሩን በወረረው በዚህ ቦታ ላይ አሰፈረና አገሩን በጦሩ መጠሪያ “ጨዋ” (ሸዋ) ብሎ ጠራው” ይላል። ታሪካችን እርግጥ ወታደሮችን ጨዋ ይላቸዋል። ግን “ጨዋ” እና ሸዋ በግድ ካላዛመዷቸው የተፈጥሮ ዝምድና የላቸውም። (“ጨዋ” ከ “ፄዋ” የመጣ ሊሆን ይችላል።)

8. ቀደም ብሎም ቀዳማዊ ምኒልክ የእናቱ ወገን ከሆኑት ከኢትዮጵያውያን ጋር ሲዋጋ ያገዙት ወታደሮች አግኣዚ የተባሉ ከጋዛ የመጡ እስራኤሎች ነበሩ። አግኣዚ የተባሉት ከጋዛ ስለመጡ ነው ይላል። ይህ የልብ ወለድ አባባል ከታሪክ ጋር አብሮ አይሄድም። አግኣዚና ጋዛም ከድምፅ ተመሳሳይነት ያለፈ ግንኙነት የላቸውም። ደግሞስ በምን ምክንያት ነው ቀዳማዊ ምኒልክ የእናቱ ወገን ከሆኑት ኢትዮጵያውያን ጋር ውጊያ የገጠመው?

9. “አክሱማይት እና ሁሉም የአክሱማይት ተወላጅ ነገሥታት ከሜሶፖታሚያ ድረስ ግብር የሚያመጡላቸው ንጉሦች በሥራቸው ነበሯቸው” ይላል። ይኸንን ልብ ወለድ አባባል ሚቶሎጂ ይቀበለዋል፤ ታሪክ ግን አይቀበለውም። በዚያ ዘመን ከሜሶፖታሚያ ተነሥተው ለአክሱም ነገሥታት ግብር ገብረው ለመመለስ ምን ያህል ጊዜ ይወስድባቸዋል? ደግሞስ በዚያን ዘመን በምን ኀይልና መንገድ ነው የአክሱም ነገሥታት ሜሶፖታሚያ (ዒራቅ) ድረስ የሚያስገብሩት?

10. ““አጼ” ወይም “እሴ” ስመ-ክህነቱ “እስያኤል” የተባለው ልዕለ-ሰብዕ ንጉሠነገሥት 480 ዓመት በሕይወት ኖረ ሲባል ያሥገርም ይሆናል” ይላል። በሚቶሎጂ አያስገርምም፤ በታሪክ ግን እርግጥ ያስገርማል። “አጼ” እና “እሴ”ም ከድምፅ ያለፈ ዝምድና የላቸውም።

11. “Magician” የሚለው የእንግሊዝኛ ቃል ማጂ ከሚለው ከኦሮምኛ ስም የተወሰደ ነው ይላል። ሁለቱ እንዴት ተገናኝተው ይህ ሊሆን እንደተቻለ የሚያሳይ ተጨማሪ ተረት ያስፈልጋል።

12. ገጽ 59 ላይ የመናዝል ምስል በረጅም የሚቶሎጂ ታሪክ ታጅቧል። ሥዕሉ ለዓሥራ ሁለቱ ወሮች የተሰጡትን የዓሥራ ሁለቱን ከዋክብት ስሞች ይዟል። ሥዕሉ ለአዲሱ ሚቶሎጂ የጠቀመው እኛ ኢትዮጵያውያን ፕላኔቶቹን ሁሉ ከጥንት ጀምሮ የተመራመርን ለመሆናችን ማስረጃ በመሆን ነው። ዶክተር ፍቅሬ ቶሎሳ ስለ ሥዕሉ እንዲህ ሲል ጽፏል፤ “ከላይ የቀረበውን ምስል በፊርማቸው አረገግጠ‹ወ›ው በኢንተርነት ያደረሱን ዶ/ር አየለ በከሪ ናቸው። ደሸት (?) የዞዲያኩን ምስል የመስራት ሃሳብ የመጣለት ከኖኅ ወደ መልከ ጼዴቅ ከዚያም ወደ ኢትዮጵ በቅብብሎሽ ከመጣና ለኔም ከደረሰኝ የዩኒቨርስን አፈጣጠር ከሚተርክ አንድ ጥንታዊ መጽሐፍ ነው” ይላል። አተራረኩ ጥሩ ሚቶሎጂ ሊሆን ይችላል። በታሪክ አንጻር ሲታይ ግን፥ ሥዕሉ አዲስ አይደለም፤ ስሙም “መናዝል” ይባላል። በባሕረ ሐሳብ የብራና መጻሕፍት ሁሉ በየገዳማቱ ይገኛል። ሥዕሉ የወራትን ስም ስለሚያመለክት ኮከብ ቆጣሪዎች በነዚያ ወሮች የተወለደን ሰው ጠባይ መናገሪያ ያደርጓቸዋል። እውነቱ ግን፥ እኛ ኢትዮጵያውያን ዘዴውን ከነሥዕሉ የወሰድነውም ዐረቢኛ ከምትናገር የግብፅ ቤተ ክርስቲያን ነው። የወሰድነው የከዋክብቱን ስማቸውን እንኳ ወደእኛ ቋንቋ ሳንተረጉም እንዳለ በዐረብኛው ነው። አሰድ (አንበሳ)፥ ሰውር (በሬ)፥ ዓቅራብ (ጊንጥ)፥ ሑት (ዓሳንበሪ)፥ ወዘተ ...

13. ደሸት (ደሴት) ማነው? እንደ ሚቶሎጂው አቀራረብ፥ የአማሮችና የኦሮሞዎች አባት ነው። አማሮችና ኦሮሞዎች ከአንድ አካባቢ ከጐጃም፤ ከአንድ አገር ከኢትዮጵያ የተገኙ ናቸው ለማለት ነው። የታሪክ መጻሕፍት የሚናገሩት ስለ ጣና “ደሴት” ስለሆነ “ደሴት” የኦሮሞና የአማሮች አባት ስም ሆነ። “ደሴት” island ነው። “ደሸት” ከሚለው ስም ጋር ምንም ግንኙነት የለውም። ሆኖም፥ ስለ ደሸት (ደሴት) የተጻፈው ልብ ወለድ ታሪክ “ኦሮሞዎች ከባሕር ወጣን” ለሚሉት ማስረጃ ስለሆነ፥ ሊነበብ የሚገባው ነው። እንዲህ ይላል፤ “ስለ ደሸት ስንናገር ምንም እንኳን ተረት ቢመስልም ሐቅ ስለሆነውና ለየት ስለሚለው ውልደቱ [= ልደቱ] መናገር ጠቃሚ ነው። የቤላም (በልዓም) የልጅ ልጅ የሆነችው እናቱ ነቢይትዋ ሼምሼል መነኩሲት ነበረች። ከወንድ እርቃ በግዮን አካባቢ በገዳምም ውስጥ መንፈሳዊ ሕይወት ትመራ ነበር። አንድ ቀን በግዮን ወንዝ ሳይሆን አይቀርም ገላዋን ስትታጠብ የወንድ ዘር በማሕፀንዋ ዘልቆ ገባና ደሼት (ደሴት) ተፀነሰ። ... ይህ የሆነው ከሦስት ሺ አምስት መቶ ዓመት በፊት ስለሆነ ማስረጃው ሁሉ ቢጠፋ አያስገርምም” ይላል። ኦሮሞዎች ከባሕር ወጣን የሚሉት፥ የኦሮሞና የአማራ አባት ደሼት (ደሴት) እውሀ ውስጥ ስለተፀነሰ ነው ማለት ነው። ግሩም የሚቶሎጂ ትረካ ነው። ግን ከታሪክ ጋር አብሮ አይሄድም። ነቢዩ በልዓም ይኖር የነበረው ሜሶፖታሚያ (ዒራቅ) ነበር። ሚቶሎጂውን ለማሟላት ሼምሼልን ከዚያ አንሥቶ ጎጃም ላይ የጣላትን የነፋስ ሰረገላ ፈጥሮ ታሪኩ ቢጨመርለት ጥሩ ነበር።

“ዓላማ ዘዴን ያጸድቀዋል” እንዲሉ፥ “ዶክተር ፍቅሬ ቶሎሳ ጂግሳ ዓላማው አማሮችና ኦሮሞች በአንድ አገር ውስጥ በወንድማማችነትና በሰላም እንዲኖሩ ምክንያት ለመስጠት ስለሆነ በምንም ዘዴ ቢጠቀም ክፋት አናይበትም” የሚሉ አሉ። እንዳፋቸው ያድርግላቸው።

በመጨረሻ፥ ለመሪራስ አማን በላይ አንድ ጥያቄ ላቅርብ አንዳንድ የታሪከ ነገሥት ቅጂዎች ተገኝተው ታትመዋል፤ የታተሙት ሁሉ የየራሳቸውን አዳዲስ ነገሮች አስተምረውናል። አንተም ያገኘኸው ታሪከ ነገሥት በአድያም ሰገድ ኢያሱ ዘመን የተቀዳ ስለሆነ፥ አንዳንድ አዳዲስ ነገሮች ሊኖሩበት ይችላልና የታሪክ ምሁራን እንዲመረምሩት፥ እባክህ አሳያቸው። ከፈቀድክ ዋናውን አለዚያም የፎቶ ኮፒውን ቅጅ ለአዲስ አበባ ወይም ለደብረ ማርቆስ ዩኒቨርስቲ ልትሰጥ ትችላለህ። መሪራስ ሆይ፤ በጎውን ይምራህ።

ማስታወሻ፤

የሚቀጥለው ጽሑፌ “ሴማዊ፥ ኩሻዊ፥ ሐበሻ፥ ኢትዮጵያ” የሚሉትን ስሞች የሚተች ይሆናል።

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!