20210302 adwa

Prof. Getachew and Fikres bookየኢትዮጵያ ታሪክ ጽሁፍ ገና ተጀመረ እንጂ አላለቀም

ስሜ ላቀች አክሊሉ ይባላል፣ እዚህ አሜሪካ አገር ከመምጣቴ በፌት በፈረንሳይ አገር ፓሪስ ጥቂት ዓመታት ኖሬአለሁ፤ እኔ የታሪክ ጸሃፊም ተመራማሪም አይደለሁም። ብዙ ግዜም በሚድያ ለሚወጡ ጹሑፎችም መልስ አልጽፍም።

ነገር ግን የኢትዮጵያን ታሪክ ጥናት ከሚያካሂዱ ሰዎች ዘንድ(ነፍሳቸውን ይማርና ከእነ ፕሮፌሰር ዮሴፍ ቱቢያና)ለተወሰነ ጊዜ ተሳትፌአለሁ። የአገሬም ታሪክ እግዚአብሔር ኢትዮጵያዊት አድርጎ እስከፈጠረኝ ድረስ በሰፊው ይመለከተኛል ብየ አስባለሁ። አሁን ይህን ሰሞን በፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ መጽሐፍ ላይ የተነሳውን ስድብና ውዝግብ ማየቴ በግድ ካለሁበት እንድወጣ አድርጎኛል።

ስለ መሪራስ አማን በላይ መጻሕፍት መናገር ካስፈለገ፤ አስር ያህሉን አንብቤአለሁኝ። እኝህም ሰው ብቻቸውን እግዚአብሔር ስለፈቀደላቸው ብቻ ”ለወጣቱ ትውልድ ይድረሰውና አውቆ እንደቻለው ይመራመርበት“ ብለው፤ እናንተ ብትፈልጉም ባትፈልጉም ለኢትዮጵያ ታሪክ እና ለተዋኅዶ ኃይማኖት በጣም ትልቅ አስተዋጽዖ ያደረጉ ሰው ስለሆኑ እኛ እናከብራችዋለን። ወደፊትም የምናየው ይሆናል።

ፕ/ር ጌታቸው ያሉትን ለመጥቀስ ያህል “ታሪክ ሳይጻፍ ቢመጣ ኖሮ፣ ከተጻፈ በኋላ ሆነና ክንፍ የለሽ አሞራ ሆነ” ብለው ሲሉ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ ከሆነ የሚያወሩት፤ ተዉ እንጂ፣ እኛ ከጻፍነው ውጭ ሌላ ታሪክ ጭራሽ የለም አትበሉን፣ ስለ ኢትዮጵያ ታሪክ የምናውቀው በጣም ትንሽ ነውና።

እንዲህም አይነት አዲስ ሰምተነው የማናውቀው ነገር ሲመጣ ከስድብ ውርጅብኝ ይልቅ ወጣቱን ትውልድ ምን ይመስልሃል ብላችሁ አበረታቱት እንጂ እንዴት ተረት ነው ትሉታላችሁ?

ያነበብኩዋቸውን የመሪራስን መጻሕፍት እሳቸው የፈጠሩዋቸው ልብ ወለድ ታሪኮች ናቸው የሚሉኝም ከሆነ ምን አይነት አንጎል ይኅን ሁሉ ተዓምር ይፈጥራል? ሚቶሎጂ ወይም ሚት ደግሞ አፈ ታሪክ ሲሆን፣ ከፈጠራ የተለየና ዱሮ ባንድ ዘመን ታሪክም የነበረ በዘመናት ርቅትም ምክንያት ዋቢው የጠፋ ወይም ያልተመረመረ ሲሆን፤ ብዙ ጊዜ ግን እውነትን ያዘለና ለዚያም አፈ ታሪክ መነሻ ያለው ሆኖ የሚገኝ ነው።

የኢትዮጵያችንም ታሪክ ሁልጊዜ ከኃይማኖታችን ጋር የተያያዘ መሆኑ የሚያስደንቅ ሲሆን፣ አሁንም ፕ/ር ፍቅሬ ይህን መጽሐፍ የሚያሳትምበትን ሰዓት እሱ መርጦ ሳይሆን እግዚአብሔር ሆን ብሎ የኢትዮጵያን ልጆች በአንድነት እንድንስማማ ብሎ እሱ እግዚአብሔር በፈቀደው ጊዜ መታተሙን እመሰክራለሁ።

ይህስ ምን ክፉ አለበት? ያስመሰግናል እንጂ።

ግሪኮች፣ ዓረቦች፣ ፈረንሳዮች፣ እንግሊዞች፣ ጣሊያኖች፣ እስራኤሎችና ጀርመኖችም ስለኛ ታሪክ ብዙ ሰብስበዋል። ስለዚህም አዲሱ ትውልድ ቋንቋ እየተማረ ታሪካችንን ፈልፍሎ እውነቱን ለማውጣት ብዙ ሥራ ይጠብቀዋል።

እኔም ፈረንሳይ በነበርኩበት ግዜ አቅሜ በፈቀደው ስለአገራችን የተጻፉ አንዳንድ መጻሕፍትንም አግኝቼ ሰብስቤአለሁ። መቸም ቢሆን አንዳንድ ሰው በታሪክ ውስጥ አይጠፋምና እንዲሁ አንድ ፈረንሳዊ ለኛ ታሪክ ተቆርቁሮ ከኖህ ጊዜ ጀምሮ ያለውን ያገኘውን ታሪካችንን የሚተርክ መጽሐፍ በ1897 የጻፈውን አግኝቼ ለመተርጎም ጀምሬ በኑሮ ውጣ ውረድ ምክንያት ግዜ አጥቼ በጊዜው ሳላቀርበው ዘገየሁ እንጅ፤ በከፊሉም ቢሆን መውጣቱ አይቀርም። ታሪካችንም የአሊስ ወንደር ላንድ ታሪክና ተረት አለመሆኑንም በተጨማሪ ምናልባት ያገናዝብ ይሆናል።

የታናሽ እኅት ምክር ላበረከት ፍቀዱልኝ፣

አዲስ ታሪክ ሲመጣ ብታበረታቱት ትልቅነታችሁን እናደንቃለን፣ የስድብ ውርጅብኝ ስታወርዱበት ከናንተ የምንጠብቀው ይህ አይደለምና በጣም እናፍራለን። ወደፊትስ ታሪክ እየወጣ ሲመጣ እናንተስ ለምን ታፍሩበት?

የናንተና የመሪራስ ትምህርት በጣም የተለያየ ስለሆነ በኛ መንገድ ካልሄድክ ከማለት ፈንታ አበረታቱት። ፕ/ር ፍቅሬም ቢሆን አስተዋይና ሃሳበ ሠፊ ሰው ስለሆነ መረጃ ሳይዝ የሚናገር አይደለምና አትሳሳቱ ።

እነዚህን ሁለቱንም ሰዎች በያዙት መንገድ እንዲገፉበትና ገና ብዙ እንዲያስተምሩን እግዚአብሔር ይርዳቸው፤ ሁላችንንም ይርዳን። እኔም ፈረንጁ የጻፈውን ቶሎ እንድተረጉም ይርዳኝ።

ላቀች አክሊሉ

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!