ለመላው የእስልምና እምነት ተከታዮች
እንኳን ለ1442ኛው የረመዳን ወር በሰላም አደረሳችሁ! ረመዳን ሙባረክ!
ኢትዮጵያ ዛሬ

Prof. Getatchew Haileሙሉጌታ ውዱ

መግቢያ፤

ዶክተር ዶናልድ ሊቫይን የሚባል በቺካጎ ዩኒቨርሲቲ አስተማሪ የሆነ አንድ "አይሁድ" አሜሪካዊ የዛሬ አሥራ ስድስት አመት አካባቢ እኔ ወደምኖርበት አካባቢ መጥቶ ደወለልኝና በቀጠሮ ተገናኝተን በአንድ የኢትዮጵያ ምግብ ቤት ውስጥ አብረን መመገብ ጀመርን። በጭውውታችን መካከል ስለ ኢትዮጵያውያን "ምሁራን" አነሳና አስተያየቱን ይሰጠኝ ጀመር። ከሁሉም የሚወደው (my favorite በሚል አገላለፅ) እንድርያስ እሸቴ የሚባለውን ሰው እንደሆነ ነገረኝ። አከታትሎም በእንግሊዝኛ አግቦ አነጋገር ኢትዮጵያዊ ሊቅ (በምዕራባዊ ትምህርት) እኮ የለም አለኝ። የተጠቀመው የእንግሊዝኛ ቃል "true scholar" የሚል ነበር። ያን ጊዜ ብዙ ኢትዮጵያውያን "ምሁራን" (በምዕራባዊ ትምህርት) አሉ ብየ የማስብበትና ደረቴን የምነፋበት ጊዜ ስለነበረና ገና ብዙ ያልመረመረ የጎልማሳነት ስሜት ሰለነበረኝ በሰውየው አነጋገር ስሜቴ ተጎዳ። እኔም ጥድፊያ ከሚበዛባቸው ሥራዎቼ ፋታ ሳገኝ የኢትዮጵያን ጉዳይ እና ታሪኳንም ማጥናት ጀመርኩ።የዶክተር ዶናልድ ሊቫይንን ሥራዎችም በቅርብ ማየት ጀመርኩ።

በዚህ ጊዜ ነበር ዶክተር ሊቫይን ዋና ሥራው ሰላይነት መሆኑን የተረዳሁት። በዚህም ጊዜ ነበር በአግቦ አነጋገር 'በምዕራባዊ ትምህርት ኢትዮጵያዊ ሊቅ የለም' ያለው እውነት እንደሆነ ያወቅሁት። በምዕራባዊ ትምህርት ኢትዮጵያዊው ይደነቁራል እንጂ አዋቂ አይሆንም። ምዕራባውያን ኢትዮጵያዊውን በነሱ ትምህርት የሚያሰለጥኑት ልክ ውሻን ለአደን ወይም በአሳዳጅነት ሊገለገሉበት እንደሚያሰለጥኑት ኢትዮጵያዊውም አገሩን አፈራርሶ በቅርጫ እንዲሰጣቸው ነው። ጉዳዩ እነደዚህ መሆኑን እያንዳንዱ ኢትዮጵያዊ "ምሁር" የሚሰጣቸውን አስተያየቶችና የሚሰራቸውን ሥራዎች በመመርመር ማረጋገጥ ይቻላል። ኢትዮጵያ የነበሯትም፣ ያሏትም ሊቃውንት በተለይ በቤተክርስቲያን አካባቢ ያሉ ቤተክርስቲያን 'ምሁራን በኅበ እግዚ' የምትላቸው ከእግዚአብሔር የተማሩ ብቻ ናቸው። በምዕራባዊ ትምህርት ወይም ፍልስፍና ወይም እምነት "አዋቂ" ወይም "ምሁር" የሚባሉትን ቅዱስ መጽሐፍ በጠላት የተዘሩ "እንክርዳድ" ይላቸዋል። ይህን የማቀርበው ለእርማት እና ለመማማር እንጂ ማንንም ለመንቀፍ አይደለም፤ ምክንያቱም በምዕራባዊ ትምህርት እኔም አልፌበታለሁና።

በኢቲዮሚዲያ በዶክተር ፍቅሬ ቶሎሳ እና በሌሎች ሰዎች የሚደረገውን ልውውጥ ሳነብ ስለ ኢትዮጵያ የሚጽፉ ፈረንጆች ለምን ተወቀሱ የሚል አቤቱታ ብዙ አያለሁ። ፈረንጆች የአፍሪካን መልክዓ ምድርና ጥሬ ሃብቶቿን ከአፍሪካውያን ፈልቅቀው ለመውሰድ መቋመጥ ከጀመሩበት ጊዜ ጀምሮ "የኢትዮጵያ ታሪክ ክብር ስቧቸው ከክብሩ ለመካፈል" የሚማሩና የሚጽፉ የፈረንጅ ምሁራን የሉም። ጥቁሮች በመሆናቸው የኢትዮጵያ ታሪክ ክብር ከሳባቸው ከማርቆስ ጋርቬ እና ከሃንስበሪ በቀር ከክብሩ ለመካፈል የሚጽፍ አንድም የፈረንጅ "ምሁር" የለም። ከላይ ከጠቀስኩት ጊዜ ወዲህ ያሞካሼ እየመሰለም ቢሆን ስለኢትዮጵያ የሚጽፍ ፈረንጅ የሚጽፈው በቅርብ ወይም በርቀት አላማ የኢትዮጵያን መልክዓምድርና ፀጋ ከኢትዮጵያውያን ነጥቆ ለመውሰድ ነው። ለናሙና እንዲሆን ኢትዮጵያን ይወዳሉ አትንኩብን ተብለው ከተጠቀሱት የፈረንጅ "ምሁራን" መካከል ሬኔ ሌፈርት የተባለው ፈረንጅ በኢትዮሚዲያ በቅርቡ የጻፈውን እንመልከት፤

... "In other words, what is at stake is the place that should be assigned to the “people’s fundamental freedoms and rights” enshrined in the constitution, collective rights. How can the country make the transition from a bogus and ethnically weighted federalism to real decentralization, which would bring about a more authentic and ethnically fairer federalism, or even confederalism? The immemorial “national question” remains as acute as ever: what will the name Ethiopia come to refer to? In other words, why should and how can an Ethiopian state exist, and on what basis? What will the name Ethiopia come to refer to?

"This question has deep historical roots. From the mid-nineteenth century onwards, the economic centre of gravity shifted from the North – Abyssinia – towards the Centre. But power always remained Abyssinian. At stake in the current crisis is a historic break that would also shift power to the Centre, i.e. to Oromya. Despite their internal divisions, this claim unites the vast majority of Oromo, justified by their numbers and their major contribution to the economy. It is generally agreed that a genuine application of the constitution would be sufficient for this claim to be satisfied."1

ይህ ፈረንጅ ከፊት ለፊት የሚታየውን ጉዳይ በ"ምሁራዊ ዘገባ" ያቀረበ በሚመስል አነጋገር ያስተላለፈው መልእክት ኢትዮጵያ ትበታተን የሚል ነው። በኢትዮጵያ ውስጥ ባለፉት አምሳ አመታት አገር በመበተን ሥራ የተሰማሩትን፣ አገር የበተኑትን፣ አሁን በስልጣን ላይ ያሉትንና አገር ገና እንበታትናለን የሚሉትን ሁሉ ያሰለጠኑ ከዚህ ከላይ የሚታየውን የእንግሊዝኛ ጽሑፍ እንደጻፈው ሰውየ አይነት "ኢትዮፕያኒስት ምሁራን ነን" የሚሉ ፈረንጆች ናቸው። እነዚህ ፈረንጆች የሥራቸው አላማ ከኢትዮጵያ ጥቅምን ለፈረንጅ ማስገኘት እንጂ ስለ ኢትዮጵያ እውነትን መመስከር አይደለም። ይህን ጽሑፍ የጻፍኩበት አንዱ ምክንያትም እነዚህ ፈረንጆች የኢትዮጵያውያንን ፀጋ ኃይል ለመበተን ኢትዮጵያውያንን በመጠቀም የተከሉትን መርዝ በእግዚአብሔር ኃይል መንቀል አለብኝ ከሚል ከመቆርቆር ስሜት ነው። ይሁንና በዚህ ጽሑፍ ውስጥ የፈረንጅ "ምሁራን" ያቀረቡትን መረጃዎች ልጠቀም እችላለሁ፤ ነገር ግን የነሱን መረጃዎች የምጠቀመው ሌሎችን የመንቀሳቀስ መብት ነፍገው በአለም ላይ እየተዘዋወሩ መረጃዎችን ሰብስበው ስለያዙ ወደ ጥሬ መረጃዎቹ ለመድረስ እንጂ የፈርንጆቹን በጥቅም ላይ የተመሠረተ የተዛባ አስተያየት መረጃ ነው ብየ ለማቅረብ አይደለም።

የዶክተር ፍቅሬ ቶሎሳን መጽሐፍ ገዝቼ ማንበብ ጀምሬ በሥራ ብዛት ምክንያት አንብቤ አልጨረስኩም። ስለዚህ አንብቤ ስላለጨረስኩት መጽሐፍ አስተያየት መስጠት አልችልም። በዚህ ጽሑፍ የማተኩረው ዶክተር ጌታቸው ኃይሌ ስለ ንግሥተ ሳባ በሰጡት የተሳሳተ አስተያየት ላይ ነው። ፈረንጅ ባስቀመጠልን ወጥመድ ተይዘን እኛ ኢትዮጵያውያን ያለንን ፀጋ ሁሉ እያጣን ስለመጣን፤ እኛ ማን ነን? ታሪካቸን ምንድን ነው? ጠላታችን ማን ነው? ወዳጃችንስ ማን ነው? የሚሉትን ጥያቄዎች በትክክል ካልመለስን በቀር ነፃነታችን ልናገኝ አንችልም። ስድብ እኔም አልፈልግም። ዶክተር ጌታቸው በምወዳት በቅድስት ድንግል ማርያም አስይዘው እንዳትሰድቡኝ፣ አርሙኝ ስላሉ በጠየቁት መሠረት የገባኝን ለማቅረብ ነው።

ከላይ ከጠቀስኩት ፈረንጆች አፍሪካን ለመቦጫጨቅ ከቋመጡበት ጊዜ ጀምሮ ስለ ኢትዮጵያ የሚጽፉትና የሚተርኩት ሁሉ ቅኝቱ "ከጅብ ጅማት እንደተሰራ ክራር እንብላው፣ እንብላው" የሚል ነው። አፍሪካን ለመቀራመት ሲነሳሱ የሠሯቸው ካርታዎች አፍሪካ ውስጥ አገር እንደሌለ፤ አፍሪካ 'ኑ ውሰዱኝ' እያለ አፉን ከፍቶ እንደሚጠብቅ ነጻ ሜዳ እንደሆነ የሚያሳዩ ነበሩ። ታሪክ ብለው ሲጽፉም፤ ለምሳሌ የአክሱም ግዛት (kingdom of Axum) ሲሉ አክሱም ከተማ ብቻ እነደሆነች እንጂ እነኳን ሌላ አድዋንም የአክሱም ግዛት ውስጥ ለመጨመር አኪያሄዳቸው አይፈቅድም ነበረ። የታሪኩ የትርካ ባለቤት (authority) ፈረንጆቹ እራሳቸው ይሆኑና ስልታቸውም 'የመጨረሻውን ዝቅተኛውን ልቀቅ' (concede the bare minimum) የሚል መሠሪነት ነበረው። አሁንም አለው። የመሠሪነቱን ስልት ምሳሌ ለመስጠት ለምሳሌ አድዋ ውስጥ አክሱምን የሚጠቅስ መረጃ ካልተገኘ አድዋ የአክሱም አልነበረችም ተብሎ ይወሰዳል። በሌላ አነጋገር ውዱ የሙሉጌታ አባት ለመሆኑ ማረጋገጫ እስካልመጣ ድረስ ሙሉጌታ "ሙሉጌታ" እንጂ "ሙሉጌታ ውዱ" አይደለም የሚል ነው።

ዶክተር ጌታቸው ኃይሌ የሳባ ንግሥት የኢትዮጵያ ሰው አይደለችም የሚል የተሳሳተ አስያየት ሰጥተዋል። የሳባ ንግሥት የኢትዮጵያ ሰው ለመሆኗ ብዙ ማረጋገጫዎች አሉ። ነገር ግን በጽሑፋቸው እንዳቀረቡት ዶክተር ጌታቸው ንግሥተ ሳባን የኢትዮጵያ ሰው አይደለችም ለማለት ያነሳሳቸው ንግሥናዋ ለሳባ ነው፤ ሳባ ደግሞ ኢትዮጵያ ሳትሆን የመን ናት የሚለው እምነታቸው ነው። ሳባ ኢትዮጵያ አይደለችም የሚለውን አስተሳሰብ ያገኙት ደግሞ ከላይ በመሠሪነት ይተርካሉ ካልኳቸው ከፈረንጆች ነው። ይህ ከፈረንጅ ያገኙት 'ብሔረ ሳባና ኢትዮጵያ ለየቅል' የሚል አስተሳሰብ ንግሥተ ሳባና ንግሥተ አዜብ ለየቅል ወደሚል አስተሳሰብም ወስዷቸዋል። ለዚሀ አስተሳሰባቸው ቀላል ማነፃፀሪያ የሚሆን ምሳሌ መውሰድ እንችላለን፦ ጄኔራል አማን ሚካኤል አንዶም የተባሉት ሰው ዘፀጋ፣ ሐማሴን ስለተወለዱና አሁን ኤርትራ ለብቻዋ አገር ስለሆነች እሳቸው ኢትዮጵያዊ አልነበሩም የማለትን ያህል ስህተት ነው። ብሔረ ሳባና ኢትዮጵያ ለየቅል እንዳልሆኑ ከተገነዘቡ ምናልባት ዶክተር ጌታቸው ስህተታቸውን ሊያርሙ ይችሉ ይሆናል፡፡ ሌሎችም ይህን የሚያነቡና የሚሰሙ ኢትዮጵያውያን በፈረንጅና በዐረብ ማታለያዎች ወይም ማደነጋገሪያዎች እየደነበሩ እንቋቸውን ለጅብ እየጣሉ ከመሸሽ ይድናሉ ብየ ተስፋ በማድረግ መረጃዎችን አቀርባለሁ።

የአፄ ዘርአ ያዕቆብ ቅኔ

ከራሳቸው ጥቅስ ልጀምርና የአፄ ዘርአ ያዕቆብ ቅኔ ለዶክተር ጌታቸው ኃይሌ ምስክር አይደለም።

"ሰላም እብል ለካሌብ መነኮስ፤
እመንገለ ክብሩ ንጉሥ፤
ይሜርድ ባሕረ ከመ እንተ የብስ፤
ብሔረ ሳባ በጺሖ፤
ለአይሁዳዊ ነጽሖ፤
ወበውስቴቱ ሐነጾ ለአምካክ ጽርሖ።"

ባለቅኔው ብሔረ ሳባ ማለታቸው የመን ለብቻዋ አገር ነበረች ማለታቸው አይደለም። ብሔር ወረዳም ነው። ብሔረ ቡልጋ ማለት ቡልጋ እራሱን የቻለ፣ ለብቻው የሆነ አገር ነው ማለት አይደለም። ብሔረ ሳባ የሚለው ቃል የተለየ አገርን እንደማያመልክት ዶክተር ጌታቸው አይጠፋቸውም። ነገር ግን ይህን ቅኔ ምስክር ይሆነኛል ብለው የጠቀሱበት ምክንያት አፄ ካሌብ ባህር ተሻግሮ ቤተክርስቲያን ሠራ የሚለው ስንኝ ፈረንጆች የነገሯቸውን "አፄ ካሌብ ክርስቲያኖችን ሊያግዝ ባህር ተሻገረ እንጂ አገር አለኝ ብሎ የአገር ደህንነትን ለመጠበቅ አይደለም የተሻገረው" የሚለውን አስተሳሰብ የሚደግፍ ስለመሰላቸው ነው። ሆኖም ግን የአፄ ዘርአ ያዕቆብ ቅኔ ያንንም አስተሳሰብ አይደግፍም። የአፄ ዘርአ ያዕቆብ ቅኔ አይሁዱ የእግዚአበሔርን አዳራሽ ቢያፈርሳት መነኩሴው ካሌብ እነደገና አነፃት የሚል እግዚአብሔርን ስለመውደድ ጉዳይ ነው። በቅኔው የተለየ አገርን የሚጠቁም አንድም ስንኝ የለበትም።

ከዐረቦች ወረራ በፊት የመን የኢትዮጵያውያን አገር፣ የአከሱም አውራጃ ነበረች። ከዚህ ቀደም የነበራቸውን ዝንባሌ አሻሽለው ዶክተር ጌታቸው ድሮ የመን የዐረቦች አገር አልነበረችም የሚል አሰተያየት ላይ መድረሳቸው ተስፋ ሰጥቶኛል። አሁንም ከአፄ ዘርአ ያዕቆብ ቅኔ ጥቅሳቸው አያይዘው ፥ የቅዱስ ዳዊትን ጥቅስ ጠቅሰው፤ ቅዱስ ዳዊት "ነገሥተ ሳባ ወዐረብ ያለው ነገሥተ የመን ወዐረብ ለማለት ፈልጎ ነው፤ በዛን ጊዜ የመን ገና የዐረቦች አገር አልነበረችም" ብለው ያቀረቡትን አስተያየት ሙሉ ጥቅሱን ጠቅሼ አስተያየት ልስጥበትና ወደሚቀጥለው መረጃየ ልሂድ። ቅዱስ ዳዊት በመዝሙር ፸፪ ከቁጥር ፯ -፲ የሚለው እንደሚከተለው ነው።

ወይሠርጽ ጽድቅ በመዋዕሊሁ፤ ወብዙኅ ሰላመ እስከ ይኀልፍ ወርኅ።
ወይኴንን እምባሕር እስከ ባሕር፤ ወእምአፍላግ እስከ አጽናፈ ዓለም።
ይገንዩ ቅድሜሁ ኢትዮጵያ፤ ወጸላእቲሁ ሐመደ ይቀምሑ።
ነገሥተ ተርሴስ ወደሰያት አምኃ ያበውኡ፤ ነገሥተ ሳባ ወዐረብ ጋዳ ያመጽኡ።

ኢትዮጵያ የሚለው ቃል ኩሽ ለሚለው ቃል ሰባ ሁለቱ እብራውያን ሊቃውንት ክርሰቶስ ከመወለዱ ከሶስት መቶ አመት በፊት ተስማሚ ነው ብለው የተጠቀሙበት ቃል ነው።

ከላይ ያለው ግዕዝ ወደ አማርኛ ሲተረጎም፦

በዘመኑም ጽድቅ ያብባል፥ ጨረቃም እስኪያልፍ ድረስ ሰላም ብዙ ነው።
በባሕር እስከ ባሕር ድረስ፥ ከወንዝም እስከ ምድር ዳርቻ ድረስ ይገዛል።
በፊቱም ኢትዮጵያ ይሰግዳሉ፥ ጠላቶቹም አፈር ይልሳሉ።
የተርሴስና የደሴቶች ነገሥታት ስጦታን ያመጣሉ፤ የሳባና የዓረብ ነገሥታት እጅ መንሻን ያቀርባሉ።

ቅዱስ ዳዊት በመዝሙሩ የተቀኘው እሱ እራሱ ስላለበት ዘመን ሳይሆን እሱ ከነበረበት ጊዜ አንድ ሺህ አመት በኋላ ስለሚሆነው ስለ ክርስቶስ መምጣት እና ስለ ክርስትና ነው። በሌላ አነጋገር መዝሙሩ ትንቢት ነው። በመዝሙሩም የጠቀሳቸው ሰዎች ኢትዮጵያውያን ናቸው። ይህን በማስረጃ ላረጋግጥ።

የመን የኢትዮጵያ አውራጃ እንደነበረች በማያሻማ መረጃ ወደኋላ እናያለን። አስከዛው ግን በየመን የነበሩ የኢትዮጵያ ነገሥታት ሁሉንም ባይሆን በዋና ከተማቸው አቅራቢያ (ሰነዓ፣ ናግራን ወዘተ አጠገብ) የሚኖሩትን ዐረቦች ያስተዳድሩ እንደነበር በአለት ላይ የተቀረፁ መረጃዎች ያሳያሉ። በዚህም ምክንያት ነው አፄ ካሌብም ሆኑ በአክሱም ንጉሠ ነገሥት ስር የነበሩ የየመን ንጉሦች ማእረጋቸው የሳባና ባጠገባቸው የሚኖሩ ዐረቦች ንጉሥ የሚል ማዕረግ የነበረበት። ሰርገው ሃብለስላሴ በመጽሐፋቸው እንዳሰፈሩት የየመን ንጉሦች ማዕረግ፥

የሳባ እና የረዳ እና የሃሳርሞት እና የአመነት (የመን) እና ባጠገባቸው የሚኖሩ አረቦች ንጉሥ።2 የሚል ነበር። ይህ ማእረግ እራሱ የአፄ ካሌብም ማእረግ እንደነበረ ሰርገው ሃብለስላሴ በመጽሐፋቸው አስፍረዋል።

ይህ ማእረግ ዶክተር ጌታቸው 'ሳባን ለምን ኢትዮጵያ አላላትም' ላሉት ጥያቄ መልስ ይሰጣል። ለዚህ ላለንበት ዘመን አመለካከት ምቹ ባልሆነ ሁኔታ የመን እና ሳባ የተለያዩ እንደሆኑ አድርጎ ነው ማዕረጉ የሚያሳየን። ነገር ግን ቀርበን ስናየው እነዚህ ቦታወች የተለያዩ እንዳልሆኑ እንረዳለን። በየመንና በአክሱም፣ በየሃም የተገኙ የአለት ጽሑፎች የሚያሳዩት በአክሱሙ ወይም ከዛ በፊት በአዜባው (አሳባው) ንጉሠ ነገሠት ሥር የነበሩ ወረዳዎች የየራሳቸው ንጉሦች እንደነበሯቸው ነው። ለምሳሌ የፈርም ያናብ ልጅ የሳባ ንጉሥ ብቻ ነበር።3 አራብቶ እና በከፊልም ይሁን በሙሉ ዘርዝሮ መጥራት የዛ ዘመን ዘይቤ ነበር ማለት ነው። በተመሳሳይ ሁኔታ መጽሐፍ የሳባ ንግሥት ሲላት የኢትዮጵያ አይደለችም ማለት አይደለም ነገር ግን እንደዛ ዘመን ባህል የመጣችበትን ሰፈር ባጭር ለመግለፅ መጽሐፍ የተጠቀመበት ዘይቤ እንደሆነ ነው የምንረዳው።

በአክሱም አለት ላይ ተጽፎ የሚገኘው የንጉሠ ነገሥት አብርሃ (ኢዛና) ማዕረግ ምን እንደሚል እንመልከት (የሆሄ አጣጣሉ እና አጠራሩ [የካይብ፣ የሳልስ፣ የራብዕ ወዘተ] ግድፈት ሊኖርበት ስለሚችል በቅድሚያ ይቅርታ እጠይቃለሁ)

ኢዛና፡ ንጉሠ፡ አክሱም፡ ወሑመራ፡ ወረዳ፡ ወካሱ፡ ወሳባ፡ ወሰላሓኑ፡ ወጸርድ፡ ወሕብስት፡ ወበጌ፡ ንጉሠ ነገሥት ...4

ወደ አማርኛ ሲተረጎም፥

ኢዛና የአክሱም ንጉሥ፣ የሑመራም፣ የረዳም፣ የካሱም፣ የሳባም፣ የሰለሃኑም፣ የጸርድም፣ የሕብስትም፣ የበጌም ንጉሠ ነገሥት ...

ካሱ ኩሽ ነው። ንጉሠ ነገሥት አብርሃ በመግለጫቸው የሚነግሩን ኢትዮጵያና ሳባ አንድ መሆናቸውን ነው። እንደገናም ሕብስት የሚለው በአሁኑ ዘመን የሚኖረው ሰው ሓበሻ እያለ የሚጠራውን ቃል እራሱን ነው።

በየመን በአለት ላይ ተቀርጾ የሚገኘውን ሙንሮ ሄይ የሚባለው የኢትዮጵያ ወዳጅ ያልሆነ ፈረንጅ በመጽሐፉ የጠቀሰውን በሱ ትርጉም የጻፈውን እንመልከት፥

Shamir of Dhu-Raydan and Himyar had called in the help of the clans of Habashat for war against the kings of Saba ...5

ወደ አማርኛ ሲተረጎም፥

የረዳና የሑመራ ሹም የሳባን ንጉሥ ለመውጋት እንዲረዳው የሕብስት ወገንን ጠየቀው። የሚል ነው።

እንድምናየው አሁን ዐረቦች ይስፈሩበት እንጂ፤ በየመን የሚገኘው አሻራ፣ ኮቴ፣ አለቱም፣ የታሪክ አየር መዓዛውም፣ ቅርሱም ሁሉ ኢትዮጵያ ኢትዮጵያ ይሸታል። ዶክተር ጌታቸው ድሮ የመን የዐረቦች አገር አልነበረችም ብለዋል። መልካም ብለዋል። ድሮ የመን የማን አገር እንደነበረች ጥንት የተፃፈው መጽሐፍ ቅዱስ ለዶክተር ጌታቸው መልስ ይሰጣል። እንዲህም ይላል፥

እግዚአብሔርን የፍልስጥኤማውያንና በኢትዮጵያውያን አጠገብ የሚኖሩትን የዓረባውያንን መንፈስ በኢዮራም ላይ አስነሣ።6

የመንን ዐረቦች ከመውሰዳቸው በፊት ባዶ ሜዳ አልነበረም። ሰዎች ነበሩበት። የአፍሪካ ስዎች የተፈጥሮ መኖሪያቸው ነበር። እነዚህም ሰዎች ኢትዮጵያውያን እንደነበሩ እነሆ ቅዱስ መጽሐፍ ምስክርነት ሰጠ። ታዲያ ከነዚህ ከኢትዮጵያውያን መካከል ተነስታ የሶሎሞንን ጥበብ በእንቆቅልሸ ለመፈተሽ የሄደችው እንዴት ዐረብ ልትሆን ትችላለች?

ከቀይ ባህር ግራና ቀኝ (አሁን የመንና ኢትዮጵያ በሚባሉት) ቦታዎች የሚኖሩት ኢትዮጵያውያን ለመሆናቸው አይተው የመሰከሩ የውጭ ስዎች መረጃወች፤

የአቡነ ቆስማስ ምስክርነት

የኢትዮጵያ ወዳጅ ያልሆነው ሙንሮ ሄይ የሚባለው ሰው "ጽላተ ሙሴን ፍለጋ" በሚለው መጽሐፉ ከዘጠኝ መቶ ሃያ ሶስት እስከ ዘጠኝ መቶ ሰላሳ አራት ዓ.ም. (እ.አ.አ) የግብፅ ፓትርያርክ የነበሩትን የአቡነ ቆስማስ ሶስተኛን ታሪክ ሚካኤል ጢኒዝ እንዳሰፈረው ብሎ ያቀረበው የጥንቱ የግብፅ ፓትሪያርክ ቃል በሙንሮ ሄይ ትርጉም እነደሚከተለው ይላል፤

‘al-Habasha...is a vast country, namely the kingdom of Saba from which the queen of the South came to Solomon, the son of David the king’7

ወደ አማርኛ ሲተረጎም፥

ሃገረ ሐበሻ ሰፊ አገር ነው። የሳባ ግዛት ነው። የደቡቧ ንግሥት የንጉሡን የዳዊትን ልጅ ሰሎሞንን ልታይ የመጣችው ከዚህ አገር ነው።

የግብጽ ፓትሪያርኮች ጳጳሳትን ወደ ኢትዮጵያ ሲልኩ ኖረዋል። ኢትዮጵያ ከየት እስከየት ድረስ እንደነበረች ያውቃሉ። እነሆ ፓትሪያርኩ መሰከሩ።

የጵሮቆጲዮስ ምስክርነት

እንደ አውሮጳውያን አቆጣጠር በአምስት መቶ ስላሳ ሶስት ዓመተ ምህረት (የዛሬ አንድ ሺህ አምስት መቶ አመት ገደማ) የባይዛንታይን ንጉሥ ኢዮስጦንዮስ የጦር ጄኔራል የነበረው ቤልሳሪዮስ ወደ ቀይ ባህር መጥቶ ሳለ አብሮ አጀቦት የነበረው የታሪክ ጸሐፊው ጵሮቆጲዮስ በቀይ ባህር ጉዟቸው ያዩትን በጽሑፍ አስፍሮት አልፏል። እንዲህም ብሎ በጽሑፉ አሰፈረ፥

About opposite the Homeritae on the opposite mainland dwell the Aethiopians who are called Auxomitae, because their king resides in the city of Auxomis. And the expanse of sea which lies between is crossed in a voyage of five days and nights, when a moderately favouring wind blows. For here they are accustomed to navigate by night also, since there are no shoals at all in these parts; this portion of the sea has been called the Red Sea by some. For the sea which one traverses beyond this point as far as the shore and the city of Aelas has received the name of the Arabian Gulf, inasmuch as the country which extends from here to the limits of the city of Gaza used to be called in olden times Arabia, since the king of the Arabs had his palace in early times in the city of Petrae. Now the harbour of the Homeritae from which they are accustomed to put to sea for the voyage to Aethiopia is called Bulicas; and at the end of the sail across the sea they always put in at the harbour of the Adulitae. But the city of Adulis is removed from the harbour a distance of twenty stades (for it lacks only so much of being on the sea), while from the city of Auxomis it is a journey of twelve days.8

ወደ አማርኛ ሲተረጎም፥

ከሑመራ (የመን) ባሻገር ቀይ ባህርን አቋርጦ የሚገኘው የሑመራ ሰዎች ዋና ቦታቸው በሆነው ስፍራ የሚኖሩት አትዮጵያውያን ናቸው። አክሱሞች ይባላሉ ምክንያቱም ንጉሣቸው በአክሱም ከተማ ስለሚኖር ነው። ተስማሚ ነፋስ ባለበት ወቅት ከሑመራ ባህሩን ለማቋረጥ የአምስት ቀንና ምሽት ጉዞ ነው። በዚህ አካባቢ ያለው ባህር የጉብታ እንቅፋት ስለሌለበት በምሽትም ይቀዝፋሉ። በዚህ አካባቢ ያለውን ባህር አንዳንዶች ቀይ ባህር ብለው ይጠሩታል። ከዚህ በኋላ እስከ አየላስ ከተማ የሚሄደው የዐረብ የባህር ሰላጤ የሚል ስም አግኝቶ ነበር፤ ከዚያ እስከ ጋዛ ድረስ ያለው ቦታ በድሮው ጊዜ ዐረቢያ ተብሎ ነበረ፤ ምክንያቱም የዐረቦች ንጉሥ ቤተ መንግሥት በፔትራይ ከተማ ስለነበረ ነው። አሁን የሑመራ ሰዎች ወደ ኢትዮጵያ ዘወትር ሲጓዙ የሚነሱበት ወደብ ቡሊቃስ ይባላል፤ ከባህሩ ባሻገር የሚያርፉበት ወደብ የአዳል ወደብ ይባላል። የአዱሊስ ከተማ ከወደቡ ሃያ ሰታዴ (አራት ኪሎ ሜትር ያህል) ይርቃል። ከአክሱም ከተማ እስከ አዱሊስ ከተማ ድረስ የአስራ ሁለት ቀን መንገድ ነው።

እንደምናየው ድሮ የመንና ኢትዮጵያ የዛሬው ወልቂጤና አዲስ አበባ እንደማለት ናቸው።

የናግራን ከተማ ምስክርነት

ከክቡራን አንባቢያን ጋር ወደኋላ አንድ ሺህ አምስት መቶ አመት ተጉዘን እሰኪ በናግራን ከተማ እንንሸራሸር። ዶክተር ጌታቸው ኃይሌ ፈረንጆች (በተለይ አይሁድ ነን የሚሉት) የቀመሙት የብልጣብልጥ የፈጠራ ተርት እውነት መስሏቸው የመን በአይሁድ ንጉሥ ትተዳደር እንደነበረና የንጉሠ ነገሥት ካሌብ ዘመቻ ክርሰቲያኖችን ለማዳን ብቻ እንጂ አገር አለኝ ብሎ እንዳልሆነ አስመስለው፤ "አንድ አይሁዳዊ ንጉሥ ናግራን ከተማ ያሉትን ክርስቲያኖች ሲያሠቃይ ፥ ንጉሥ ካሌብ ባሕር ተሻግሮ የመን ድረስ ዘምቶ ..." ብለው ጽፈዋል።

በመሠረቱ ይህ አይሁዳዊ ንጉሥ ያሉት ሰው እራሱን ንጉሥ ብሎ የጠራ ሽፍታ ነው። ሽፍታ ለመሆኑ እራሱ ይመሰክራል። እንደ ኢትዮጵያ አቆጣጠር በ፭፻፲፮ ዓ.ም. (አምስት መቶ አሥራ ስድስት ዓ.ም.) የዛሬ አንድ ሺህ አምስት መቶ አመት (ከዐረቦች ወረራ በፊት) አሁን የመን ተብላ የምትጠራው አገር ሑመራ ትባል ነበር። ነዋሪዎቿም ኢትዮጵያውያን ነበሩ። ማእከሏ አክሱም የሆነች የኢትዮጵያ አውራጃ ነበረች። በንጉሠ ነገሥት አብርሃ አዋጅ መሠረት የኢትዮጵያ ሃይማኖት ክርስትና በመሆኑ የሑመራም ሃይማኖት ክርስትና ሆነ። በቀሩት የኢትዮጵያ ግዛቶች እንደነበረው ሁሉ በሑመራም ክርስቲያን አንሆንም ብለው የቀሩ አይሁዶች ነበሩ። እንደሌሎች የኢትዮጵያ ግዛቶችም ሑመራ ንጉሥ ነበራት። የሑመራ ንጉሥም የሚሾመው በማእከላዊው አገር አክሱም በሚገኘው ንጉሠ ነገሥት ነበረ። አንድ ቀን የሑመራ ንጉሥ ከዚህ ዓለም ሲለይ የክረምት ወራት ስለነበረ ሌላ ንጉሥ ለመሾም የአክሱሙ ንጉሠ ነገሥት ወደ ሑመራ ለመጓዝ ክረምቱ አግዷቸው ዘገዩ። በዚህ ጊዜ ከአምስት መቶ አመት በኋላ እንደተነሳችው እንደ ዮዲት ጉዲት አይነት አመጸኛ በሑመራ ተነሳ። ይህ ሰው በዐረቦችና በውጭ ሰዎች የሚታወቀው ዱ ኑዋስ (ኩርዲዳ ራሱ) ተብሎ ነው። ይህም ሰው ሃያ ሺህ የሚሆኑ ኢትዮጵያውያን የሑመራ ቅዱሳን ክርስቲያኖችን ክርስቶስን ካልካዳችሁ ብሎ አረዳቸው። ካረዳቸው በኋላም በየመን አቅራቢያ በሂርታ ይኖር ለነበረው ለዐረቡ ንጉሥ ለሙንድሂር ሰለፈፀመው "ጀብዱ" ደብዳቤ ላከለት። በዛን ጊዜ ዐረቦችን ክርሰቲያን ለማድረግ ኢትዮጵያውያንና ከነሱም ጋር አብረው ቅዳሴ የሚገቡት የሲሪያ ሰዎች ወደ ዐረቦች ይሄዱ ስለነበር ክርስትናን ለዐረቦች ለመስበክ የሄዱት የሲሪያ ሰዎች ከዐረቡ ንጉሥ ሲገናኙ "ክርስትናን እኮ የሑመራ ሰዎችም እየጣሉት ነው፤ ምን ክርስቲያን ሁን ትሉኛላችሁ?" ብሎ አይሁዱ ሽፍታ የላከለትን ደብዳቤ አሳያቸው። እነዚህም ክርስትናን ለዐረቦች ሊሰብኩ የሄዱ የሲሪያ ካህናት ጉዳዩን መዝገበው በሲሪያ ገዳም አኖሩት። ደብዳቤውም በከፊል እነሆ፥

ቅዱስ ስምኦን፣ የቤተ አርሻም ሊቀ ካህን ለአባ ስምኦን፣ የጋቡላ ካህን በጥር ወር ፭፻፲፮ (አምስት መቶ አሥራ ስድስት) ዓመተ ምህረት የሑመራን ሰማእታት አስመልክቶ የጻፉት ደብዳቤ።

የተወደዱ ሆይ ጥር ሃያ ሁለት ቀን አምስት መቶ አስራ ስድስት ዓመት ምህረት በንጉሡ በእዮስጦስ ከተላኩት ከኤፍራስዮስ ልጅ ከካህኑ ከአብርሃም ጋር ሆነን ከንኡማን ተነስተን ከዐረቦች ንጉሥ ከሙንድሂር ጋር ሰላም ለመፍጠር ወደሂርታ አመራን። ሰለእርሳቸውም በመጀመሪያው ደብዳቤያችን ገልጸናል። ጉዳያችን በተመለከተ ላደረጉልን እርዳታ ከምእመናን ጋር አመስግነናቸዋል። ከዚህ ቀደም ስለጻፍነውም ሆነ አሁን ስለጻፍነው ጉዳይ ያውቃሉ።

ለአሥር ቀናት በደቡባዊ ምስራቅ አቅጣጫ በበረሃ ተጉዘን ከአሸዋ ተራራ ባሻገር ከሚገኘው በአርብኛ ቋንቋ ራማላህ ከሚባለው ቦታ ደረስን። ከሙንድሂር ሠፈር ስንደርስ መአዲያዎችን አገኘን። እነሱም፥ "ምን ልታደርጉ ትችላላችሁ? የናንተን ክርስቶስ ሮማውያን፣ የፔርዢያ ሰዎችና የሑመራ ሰዎች አልተቀበሉትም" አሉን። እንዲህ ብለው ስለተሳለቁብን በጣም ሃዘን ተሰማን። ጭንቀትም አደረብን ምክንያቱም እዛው እኛ ባለንበት የሑመራ ንጉሥ መልእክተኛ ትእቢት የተሞላበት ደብዳቤ ይዞ ለዐረቡ ንጉሥ ለሙንድሂር ሰጠው። ደብዳቤውም ከዚህ በታች ያለው ነው።

"ወንድሜ ንጉሥ ሙንዲህር ሆይ - በአውራጃችን ኩሾች (አክሱሞች) የሾሙት ንጉሥ እንደሞተ ክረምት መጣ። ክረምትም በመሆኑ ኩሾች ባህሩን ተሻግረው ወደኛ አውራጃ በመምጣት ሁልጊዜ እንደሚያደርጉት የክርስቲያን ንጉሥ ሊሾሙ አልቻሉም ነበርና እኔ መላውን የሑመራ ምድር መምራት ጀመርኩ። በዚህ ጊዜ በሑመራ በክርስቶስ የሚመኩ ክርስቲያኖችን ሰብስቤ አጎርኩና እንደኛ አይሁድ እንዲሆኑ አዘዝኳቸው። እነ ዘካሪያስና እነ ሚካኤልን ጨምሮ ሁለት መቶ ሰማንያ የክርስቲያን ካህኖችን ቤተክርስቲያናቸውን ከሚጠብቁት ኩሾች ጋራ ገደልኳቸው። ቤተክርቲያናቸውንም የኛ የአይሁዶች መቅደስ አደረኩት። ከዛም አንድ መቶ ሃያ ሺህ ሠራዊት ይዤ ወደ አክሱሞች ዋና ከተማ ወደ ናግራን ገሠገሥኩ። ለጥቂት ቀናት ከተማዋን ከአጠቃሁ በኋላ ልቆጣጠራት ስላልቻልኩ መሃላ ማልኩላቸው። መሃላ ብምልላቸውም ለጠላቶቼ ለክርስቲያኖች ቃሌን ለመጠበቅ አልወደድኩም። አሠርኳቸውና ያላቸውን የወርቅና የብር ንብረት እንዲያመጡ አስገደድኳቸው። አመጡም። እኔም ሰበሰብኩ። ጳውሎስ የተባለውን ዋናውን ካህናቸውን ፈለግሁት። ሞቷል ብለው ሲነግሩኝ መቃብሩን እስኪያሳዩኝ ድረስ አላመንኳቸውም ነበር። የሱንም አጽም ከመቃብር አውጥቼ አቃጠልኩት። ካህኖቹን እና በቤተክርስቲያን ውስጥ የተደበቁትን ክርስቶስን እና መስቀሉን እንዲክዱ አስገደድኳቸው። እነሱ ግን እምቢ አንክድም፥ እሱ የቅድስት ድንግል ማርያም ልጅ እግዚአብሔር ነው እያሉ ለሱ ሲሉ መሞትን መረጡ።

"አለቃቸው በእኔ ላይ ብዙ ነገር ተናገረ፣ ሰደበኝም። ስለዚህ አዋቂዎቻቸው በሙሉ እንዲገደሉ አዘዝኹ። ሚስቶቻቸውንም አመጣንና ባሎቻቸው ስለክርስቶስ እያሉ ሲታረዱ እያዩ ክርስቶስን እንዲክዱ ጠየቅናቸው። ሚስቶቻቸውም ክርስቶስን ለመካድ አልፈለጉም። የጽዮን ልጃገረዶች (መነኩሴዎች) የተባሉት መጀመሪያ እኛ እንታረድ አሉ። የአዋቂዎቹ ሚስቶች ግን የጽዮንን ልጃገረዶች (መነኩሴዎች) ተቆጧቸው ፥ መሞት ያለብን ከባሎቻችን በኋላ ነው አሏቸው። ንጉሥ ሊሆን ከነበረው ሚስት ከርሑሚ (ምሕረት) በቀር ሁሉም እንዲገደሉ አደረግን። እሷም ክርስቶስን ክዳ አይሁድ ሆና ያላትን ንብረት እንደያዘች ለልጆቿም ምህረት አግኝታ እንድትኖር ጠየቅናት። ሄዳ እንድታስብበትም በኛ ወታደሮች ታጅባ ወደ ቤቷ ላክናት።

"ይሁንና ከእውቀት ጊዜዋ ጀምሮ በአደባባይ ታይታ የማትታወቀው ይህች ሴት ክንብንቧን አውልቃ በየመንገዱ እየዞረች እንዲህ እያለች መጮህ ጀመረች፥ 'የናግራን ሴቶች፣ የኔ ክርስቲያኖች፣ አይሆዶችም የሆናችሁ፣ ጣኦትም አምላኪዎች ሁሉ፥ የማን ዘር እንደሆንኩ፣ የማን ክርስቲያን ልጅ እንደሆንኩ ታውቃላችሁ። ወርቅና ብር፣ የወንድና የሴት አገልጋዮች፣ ሰፊ መንደርና የሃብት ምንጭ እንዳለኝ ታውቃላችሁ። አሁን ባለቤቴ ለክርስቶስ ሲል ተሰውቷልና ባል ላገባ ብፈልግ ባለቤቴ ካስተረፈልኝ ሃብት ሌላ አርባ ሺህ ብር፣ የወርቅና የብር ጌጣጌጥ፣ አልማዝና የሚያምሩ ልብሶች አሉኝ። ይህም ሃሰት እንዳልሆነ ታውቃላችሁ። ለሴት ልጅ በትዳር ከምትኖርበት ዘመን የላቀ ደስታ እንደሌላት ታውቃላችሁ። ደግሞም እራሳችሁን ታውቃላችሁ፥ ከትዳር ጊዜ ጀምሮ ሴት ልጅ በወሊድ ጊዜ ምጥ አለባት። ልጆች ሲሞቱባትና ስትቀብራቸው ሃዘን አለባት። እኔ ግን ከአሁን በኋላ ከሁሉም ነጻ ነኝ። በመጀመሪያው የትዳሬ ቀን ደስ ተሰኘሁ። አሁን በልቤ ደስታ አምስት ልጃገረድ ልጆቼን ለክርስቶስ አዘጋጅቻለሁ። ተመልከቱኝ ጓደኞቸ፥ መጀመሪያ ጫጉላ ቤትና አሁን ደግሞ በሁለተኛው እንደ መጀመሪያው ክንብንቤን አውልቄ ወደ ክርስቶስ ወደ ጌታየ ወደ እግዚአብሔር፣ ወደ ልጆቼም ጌታ እና እግዚአብሔር፣ በፍቅሩ ዝቅ ብሎ ስለኛ መከራን ወደተቀበለው፡ ወደእሱ እየሄድኩ አያችሁኝ። ከናንተ በቁንጅና የማንስ አይደለሁምና እኔን ምሰሉ። ቁንጅናየን እንደያዝኩ፣ የአይሁዶች ርኩሰት ሳያገኘኝ ወደ ክርስቶስ እየሄድኩ መሆኔን ተመልከቱ። ቁንጅናየም በጌታየ ፊት ምስክር ይሁን የአይሁድ ክህደት አልደፈረውምና። ወርቅና ብሬን አልወደድኩም፤ የወደድኩት እግዚአብሔርን ነው። ይሄ አመጸኛ እንድክድ ይጠይቀኛል። እግዚአብሔር ያሳያችሁ እኔና ልጆቼ የምናምነውን ክርስቶስ እንዴት እክዳለሁ። የተጠመቅኩት በስላሴ ስም ነው፣ መስቀሉን እወዳለሁ። ስለሱ እኔና ልጆቼ በደስታ እንሞታለን እሱ ስለ እኛ በሥጋ ተሰቃይቷልና። የሚያሳሳውና ለአይን እና ለሰውነት የሚያጓጓው ሁሉ ሃላፊና ጠፊ ነው። የማያልፈውን ግን ከጌታየ አገኛለሁ። ወገኖቼ ከሰማችሁኝ ትባረካላችሁ። ቃሌን ስሙ፣ እውነትን እወቁ፥ እኔና ልጆቼ የምንሞትለትን ክርስቶስን አፍቅሩ። ከአሁን በኋላ የእግዚአብሔር የሆኑ ሰላምና ደህንነትን ያገኛሉ። ይህችን ከተማ ለክርስቶስ ሆና ከቀረች ለክርስቶስ ሲሉ የተሰውት ወንድሞቼና እህቶቼ ደም ግድግዳ ሆኖ ይጠብቃት። እነሆ ክንብንቤን አውልቄ ለጊዜው የቆየሁባትን ከተማ እተዋታለሁ፣ ከልጆቼ ጋር ሆኜ ወደዘላለማዊዋ ከተማ እሄዳለሁ። በዚያ ይሞሸራሉ። ክርስቶስ እንዲቀበለኝ ለምኑልኝ። ባለቤቴ ሦስት ቀን ቀደመኝ።'

"በከተማው የዋይታ ድምጽ ስንሰማ እንዲያጅቧት የላክናቸው ተመልሰው ወደኛ መጡ። ስንጠይቃቸውም ከላይ የተጻፈውን ነገሩን። ርሑሚ በከተማው እየዞረች እያበረታታች እንደሆነ ነገሩን። በከተማውም ዋይታ ሆነ። አጃቢዎችንም እንዲህ ስታደርግ ዝም ብለው በማየታቸው ልንገድላቸው እስኪቃጣን ድረስ ገሰጽናቸው። ርሑሚም እንደ እብድ ሴት ክንብንቧን አውልቃ ከልጆቿ ጋር መጥታ ያለ ሃፍረት በፊቴ ቆመች። ልጆቿን ለሠርግ እንደታጩ አልብሳ እጅ ለጅ ተያይዘው ከፊቴ ቆሙ። ሹርባዋን (ቁንዳላዋን) ከፊቴ ላይ ፈትታ፣ ጸጉሯን በእጆቿ ይዛ ከአንገቷ አጎነበሰችና በጩኸት፥ 'እኔም ልጆቼም ክርስቲያኖች ነን፣ ለክርስቶስ እንሞታለን፣ ወደ ወንድሞቻችንና እህቶቻችን፣ ወደ ልጆቼም አባት እንሄዳለን፥ ይሄውና አንገታችን ቁረጡ' አለች።

"እኔም ይህን እብደት ካየሁ በኋላ ሰው ነው እንጂ እግዚአብሔር አይደለም ብላ ክርስቶስን እንድትክድ ገፋፋኋት። እሷ ግን ክርስቶስን መካድ አልፈለገችም። ክርስቶስን እንድትክድ በመጠየቄ ምክንያት አንደኛዋ ልጇ ሰደበችኝ። ርሑሚ ክርስቶስን በፍጹም እንደማትክድ ስረዳ ሌሎች ክርስቲያኖችን ለማስፈራራት ከወለሉ ላይ እንዲወረውሯት አዘዝኹ። ከወለሉ ላይ እንደተዘረጋች ልጆቿ ሲታረዱ የደማቸው ፍሳሺ ወደ አፏ ተንቆረቆረ። ከዚህ በኋላ አንገቷ ተቆረጠ።

"በአዶናይ እምላለሁ ርሑሚና ልጆቿ ውብ ቁንጅናቸውን ይዘው መሞታቸው አሳዝኖኛል። እኔና ካህኖቼ ልጆቹ ስለወላጆቻቸው መሞታቸው በህጋችን ተገቢ አልነበረም አልን። በዚህም ምክንያት ወንዶችና ሴቶች ልጆች ከወታደሮች ጋር እንዲያድጉ መደብን። ካደጉ በኋላ አይሁድነትን ከመረጡ መልካም። ክርስቶስን ካሉ ግን መሞት አለባቸው። ለክቡርነትዎ ይህን የምጽፈው ክርስቲያን የተባለ በመካከላችሁ እንዳታኖሩ ለመምከር ነው። በእርስዎ አስተዳደር ውስጥ ያሉ አይሁዶችን ግን በርኅራሄ ይጠብቋቸው። ወንድሜ ሆይ ቃልዎን ይላኩልኝ፣ እኔም የሚፈልጉትን እልክልዎታለሁ።"9

በዚህ ምስክረነት የምናየው በመጀመሪያ ራሴን ንጉሥ አድርጌያለሁ ያለው አይሁዱ እራሱ "ክረምት በመሆኑ ኩሾች ባህሩን ተሻግረው ወደኛ አውራጃ በመምጣት ሁልጊዜ እንደሚያደርጉት የክርስቲያን ንጉሥ ሊሾሙ አልቻሉም ነበርና እኔ መላውን የሑመራ ምድር መምራት ጀመርኩ" ብሎ እንደመሰከረው በየመን ንጉሥ መሾም የኢትዮጵያ የዘወትር ሥርዓት እንጂ አይሁድ ነን የሚሉ ፈረንጆች እንደሚያወሩት ተረት ተርት ንጉሠ ነገሥት ካሌብ "በወረራ የጀመሩት" ነገር አይደለም። የመንም በታሪክ በመሠሪ ፈረንጆችና በዐረቦች ተረት ተረት ካልሆነ በቀር ደቡብ ዐረቢያ ተብላ አታውቅም።

ከከተማው ነዋሪ፣ ከተቀደሰችው፣ ከሰማእቷ፣ ከውቧ ኢትዮጵያዊት ከርሑሚ (ከምህረት) ጋር ናግራንን በጽሑፉ ታሪክ ሽርሽር ተዘዋውረን ያየነው የየመን ሰዎች ጥቁሮች መሆናቸውን ነው። እራሳቸውም ከአንደበታቸው አውጥተው ኢትዮጵያውያን (ኩሾች) ነን ይሉ ነበር። ፀጉራቸውን ሹሩባ (ቁንዳላ) ይሠሩ ነበር። ወንዶቹ ፀጉራቸው ኩርዲዳ ነበር። እንዳሁኖቹ ኢትዮጵያውያን ወደ ቤተክርስቲያን ሲሄዱ እንደ ሙሺራ ነጭ ልብስ ይለብሱ ነበር። የመን መልኳም፣ ልቧም ኢትዮጵያዊ ነበር። ስለዚህ ከየመንም ተነስታ ብትሄድ የሳባ ንግሥት ኢትዮጵያዊነቷ አይለወጥም።

የዚህ ትውልድ ሰዎች ኃላፊነት አለብን። የርሑሚ፣ የልጆቿ፣ የባለቤቷ፣ የሃያ ሺህ ወንድምና እህቶቿ ደም ወደ እግዚአብሔር ይጮኻል። እኛም እነሆ እየሰማነው ነው። ዐረቦች የመንን ከወረሩ በኋላ በዛ ያገኟቸውን ኢትዮጵያውያን ረግጠው፣ ከሰብአዊነት ውጭ በሆነ አረመኔያዊ ግፍ ማንነታቸውን እስከማያውቁ ድረስ ከእንስሳ በታች አውለው እስከ አሁን ድረስ በአሰቃቂ ግፍ እየገዟቸው ነው። ስምም ሰጥተዋቸዋል፥ አክሃዳም (ውዳቂዎች) ይሏቸዋል። ዐረቦች እንኳን በነሱ በኛ ላይ ሰልጥነዋልና የመን ድረስ ሄደን ነፃ ልናወጣቸው ባንችልም እግዚአብሔር ነፃ እንዲያወጣቸው በፀሎታችን ልናስባቸው ይገባል።

ንግሥተ ሳባ ወይስ ንግሥተ አዜብ?

ዶክተር ጌታቸው ኃይሌ ብሉይ ኪዳን ንግሥተ ሳባ ያላት የኢትዮጵያ አይደለችም የኢትዮጵያ ንግሥት ንግሥተ አዜብ ናት በማለት ሁለት ንግሥቶችን ፈጥረዋል። መድኃኒታችን ክርሰቶስ ንግሥተ አዜብ ያለው ንግሥተ ሳባን እነደሆነ አዲስ ኪዳን ይመሰክራል። እንደምገምተው ዶክተር ጌታቸው ኃይሌ ይሄ ጠፍቷቸው ሳይሆን አነጋገራቸው 'የክብረ ነገሥት ደራሲ ተሳስቷልና እኔ መውጫ መንገድ ልስጠው' ማለታቸው ይመስላል። የተሳሳቱት እሳቸው እንጂ ክብረ ነገሥቱ እንዳልሆነ እስካሁን አይተናል። ነገር ግን እሳቸው ክርሰቶስ "ንግሥተ ሳባ" በማለት ፋንታ "ንግሥተ አዜብ" አላት ብለው አነጋገሩን እንደማሳሳቻ እንጂ ግልጽ እንደማድረጊያ አድርገው ስላልወሰዱት ክርስቶስ ለምን ንግሥተ አዜብ እንዳላት እኔ አውቃለሁ ባልልም ለሳቸው አስተሳሰብ ሰፋ ያለ አድማስ ለመስጠት አማራጭ ላቀርብላቸው እሞክራለሁ።

በመጀመሪያ ቢሊቅስ የምትባል ልእልት በየመን ልትኖር ትችላለች። በየሃ የተገኙት የአለት ላይ ጽሑፎች ብዙ ልጃገረድ ልዕልቶች እንደነበሩ እንመደሚያመለክት ሙንሮ-ሄይ የተባለው የምዕራባውያን "ምሁር" ፤ "ፅላተ ሙሴን ፍለጋ" በተባለው መጽሐፉ አስፍሯል። ታዲያ እቺን ቢሊቅስ 'ጅኒ ጠልፎ ሙስሊም ሊያደርጋት በአየር ላይ ወደ ሰሎሞን ወሰዳት' የሚለው የተለመደው የዐረብ ተረት እንደሆነ ትንታኔ የሚያስፈልገው አይመስለኝም። ለዐረቦች ተረት ተረት መነሻ ዐረቦች የመንን ሲወሩ ያገኟቸው ስሞችና ታሪኮች ናቸው። እዚህ ላይ ጊዜ ላለማጥፋት ዐረቦች ንግሥተ ሳባ ከኛ ናት ማለታቸው የበኋለኛ ዘመን ሰዎችን ጥርጣሬ ላይ ይጥላል። ክርሰቶስ የአዜብ ንግሥት ያላት በመጨረሻ ዘመን እምነቷን ይዛ የምትቀረው ቤተ ክርሰቲያን ማን እንደሆነች ግልፅ ለማድረግ ነው። ሁለት አማራጮች አሉ። የሃንስበሪ ጽሑፎች መጽሐፈ አክሱምን ጠቅሰው እንሚያሳዩት ከአክሱም በፊት የአክሱም ከተማ ስም አዜባ (ሙንሮ ሄይ ደግሞ አሳባ ብሎ ነው ያቀረበው) ነበር። ትርጉሙም ደቡብ ማለት ነው (ደቡብነቷ ከባህር ሳይሆን አይቀርም)። በብሉይ ኪዳን የሠፈረው የንግሥቷ ማዕረግ ንግሥተ ሳባ ወይም ንግሥተ አዜባ ወይም ንግሥተ አሳባ ወይም ንግሥተ አዜባ እና ንግሥተ ሳባ ሊሆኑ ከሚችሉ አማራጮች ሊሆን ይችላል። ከነዚህ ውስጥ አንዱ ከሆነ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ግልፅ አድርጎታል። ይህ ሳይሆን ቀርቶ መድኃኒታችን የነገረን የንግሥቷ ግዛት ደቡብነት ከጥንቷ ኢየሩሳሌም ወይም እሱ ራሱ ከቆመበት ቦታ ከሆነ ደግሞ መድኃኒታችን ኢየሱስ ክርስቶስ ንግሥተ አዜብን ምሳሌ አድርጎ በመጨረሻው ዘመን የምትኖረው የተመረጠችው ቤተክርሰቲያን ማን እንደሆነች ግልፅ አድርጎታል። በዓለም ካርታ ላይ ለጥንቷ ኢየሩሳሌም ቀጥተኛ ደቡብ ባህሩን አቋርጦ ኢትዮጵያ ብቻ ናት (ኬንያን ጨምሮ)። የመረጃዎቹ መደምደሚያ፥ መንገዱም፣ ክርክሩም ተዘዋወረ አልተዘዋወረ ለውጥ አያመጣም። መደምደሚያው አንድ ነው። ንግሥተ ሳባ፥ ንግሥተ አዜብ ናት። ኢትዮጵያዊ ናት። 

እግዚአብሔር የተመሰገነ ይሁን!

ሙሉጌታ ውዱ This email address is being protected from spambots. You need JavaScript enabled to view it.
ጥር ፩ ቀን ፳፻፱ ዓ.ም.

ዋቢዎች

1 Lefort, René, Ethiopia's Crises: Things fall apart: will the center hold?, ethiomedia.com, November 23, 2016

2 Sergew Hable-Selassie, Ancient and Medieval Ethiopian History to 1270 (Addis Ababa, 1972)

3 Inscription cited by: Munro-Hay, Stuart, Aksum: An African Civilization of Late Antiquity, 1991

4 በአክሱም በአለት ላይ ተጽፎ የሚገኘው የንጉሠ ነገሥት አብርሃ (ኢዛና) መግለጫ (ሰነድ)።

5 Munro-Hay, Stuart, Aksum: An African Civilization of Late Antiquity, 1991, p.73

6 መጽሐፈ ዜና መዋዕል ካልዕ ም. ፳፩፣ ቁ. ፲፮

7 Cited by Stuart, Munro-hay, The Quest for the Ark of the Covenant: The True History of the Tablets of Moses, 2004, p.68

8 Procopius, History of the Wars, Book I and II The Persian War, page 60

9 The Chronicle of Zuqnīn, Parts III and IV: A.D. 488-775፣ pp.78-79 : Translated to English by Amir Harrak

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!