ሰላ አቦምሳ

የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ + ፕ/ር ጌታቸው ኃይሌ

ለተከበሩ ፕሮፌሰር ጌታቸው ኃይሌ፣ ለጤናዎት እንደምነዎት። በእርሶና በፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ መሃል ያለውን የሃሳብ ልውውጥ ከተመለከትኩ በኋላ የግሌን አስተያየት ለመስጠት ወሰንኩኝ። የሃሳብ ልውውጡን እንደተመለከትኩኝ ከሆነ መሪራስ አማን በላይ አንዱ የክርከሩ አካል እንደሆኑ ተረዳሁ። በዚህም መሰረት ስለ መሪራስ አማን በላይ ለማወቅና እሳቸውን በአካል ለማግኘት ካልሆነም ያሳተሟቸውን ለማግኘት ሞከርኩ። በአካል ማግኘት ባይሳካልኝም ፤ 10 የሚሆኑ ያሳተሟቸውን መጻሕፍት አገኘሁ።

መጻሕፍቶቹም የሚከተሉት ናቸው።

1) መጽሐፍ ክቡር
2) ሕይወት እንደገና በሦስት ዓለሞች
3) የልቤ ወዳጅ የሰው ዘር ልጅ
4) በአንድ ሰው ሰውነት የተቀላቀሉ ሦስት አካላቶች፤ በአንድ ሰው ሰውነት የሦስት አካላቶች መዋሃድ
5) መጽሐፈ ፈውስ መዝገበ ጥበብ ወፈለገ ጠቢብ ዘስረወ እጸዋት
6) ሰረገላ ታቦር ኢዮር ሰለ ስነ ፍጥረት ምስጢር
7) መክስተ ምስጢር ሕይወታዊ ርዕዮት
8) መጽሐፈ ሱባኤ ዘባአማን ካልእ:- እየሱስ ክርስቶስ ለሦስት ዓመት በኢትዮጵያ እንደነበረ
9) መጽሐፍ አብርሂት አብርሂ ኢትዮጵያ ለሰለስቱ ኢዮቤልዮታት የእየሱስ ክርስቶስ ደቀ መዛሙርት ቅዱሳን በኢትዮጵያ
10) የጥንቷ ኢትዮጵያ ትንሳኤ ታሪክ

እነዚህን መጻሕፍት ለማግኘት የቻልኩ ሲሆን፣ ሌሎችም ሊኖሩ ይችላሉ። እነዚህን መጻሕፍት ከተመለከትኩ በኋላ መሪራስ አማን በላይ ታሪክን ለማቆየት ሲሉ እውቀታቸውንና ሀብታቸውን ማዋላቸውን የተረዳሁ ሲሆን፣ መጽሐፈ ፈውስ መዝገበ ጥበብ የተባለውን መጽሐፍ ለሕክምና ተመራማሪዎች እንዲጠቀሙበት መፍቀዳቸውን ተመልክቻለሁ።

የኢትዮጵያ ታሪክ የመቶ ዓመት ታሪክ እያሉ የኢትዮጵያ ጠላቶች በሚያደነቁሩን ወቅት፤ በሺህ ዘመን ታሪክ ያላት አገር መሆኗን የሚገልጹ ታሪኮች ሲወጡ የሚያኮራን እንጂ የሚያሳፍረን መሆን የለበትም። መደረግ ያለበት የተረጋጋ ሁኔታዎች በሚፈጠሩ ወቅቶች ወደምርምር ተቋም በመውሰድ ዓለማቀፍ እውቅና የሚያገኝበትን መንገድ መሥራት እንጂ፤ እኛ የማናውቀው ታሪክ ከሚጻፍ የመቶ ዓመት ታሪክ አላት ብለው ደንቁረው የሚያደነቁሩንን መምረጥዎ ባላስፈለገ ነበር። ውሸት የራሱ የሆነ አስተዳደግ ይፈልጋል። በቤተክርስቲያን ታርሞ ያደገን ሰው፤ ውሸታም ነው ብሎ መሳደብ እግዚአብሔርን አለመፍራት ነው። በዚህ ንግግሮዎ መሪራስ አማን በላይን ይቅርታ ሊጠይቁ ይገባል። እኛም የእናንተ ልጆች ነንና ጥሩ ስነምግባርን ልታስተምሩን ይገባል።

በቅርቡ ባሰራጩት ጽሁፎ ላይ እንደገለጹት፤ “በመጨረሻም ምንም ስድብ ቢበዛብኝ “ሳባ” የንግሥቲቱ ግዛት እንጂ የንግሥቲቱ ስም አለመሆኑን በጽሞና መቀበልህን ሳይ ጥረቴ በከንቱ እንዳልቀረ ተረዳሁ” ይላል። ፕሮፌሰር ፍቅሬ ቶሎሳ መጽሐፍ ላይ በገጽ 213 ላይ “ሳባ” ኢትዮጵያ ውስጥ በአጼ እስያኤል የተመሰረተች ከተማ ነበረች ይላል። ስለዚህ ወቀሳው ምኑ ላይ ነው። አልገባኝም!? እንዳውም ነገሩ የተገላቢጦሽ ነው። በጽሁፎ ላይ ለእርስዎ እንደገለጸሎት የንግሥተ ሳባ ስም ኢትያኤል እንጂ ሳባ እንዳልሆነ ነው። በመጽሐፉ ውስጥም እውነተኛ ስምዋን ደጋግሞ አብራርቶታል። ነገሩ የተገላቢጦሽ ሆኖ በእዚህ ዕድሜዎ እንዴት ይዋሻሉ?

ሌላው ያሳሰበዎትና አስተያየት የሰጡበት ደግሞ፤ “የጠነዛ” ማለቱ ነው። እርሶ ከዚህ በፊት ከጻፉትና አስተያየት የጻፉበትን ደቂቀ እስጢፋኖስን “በሕግ አምላክ” በሚል ከግዕዝ ወደ አማርኛ የተረጎሙትን እንመልከት። ይህን መጽሐፍ አዲስ አበባ ዩንቨርሲቲይ የመጻሕፍት መደብር በመሄድ ገዛሁት። በገጽ 23 እንዲህ ይላል፤ “ታሪካቸውን እዚህ የማቀርበው አባ እስጢፋኖስ ተከታዮቻቸው (ደቂቀ እስጢፋኖስ) የኢትዮጵያ ቤተክርቲያን የማትቀበላቸው፤ እንዲያውም የተወገዙ አድርጋ የምታያቸው በዓስራ አምስተኛው ምዕተ ዓመት ያበቡ የተሓድሶ እንቅስቃሴ መሪዎች ናቸው። አሕይዎና ተሐድሶ (Revival and Renewal or Reformation) ተደላድሎና ተመቻችቶ በተቀመጠው ሥርዓት (Establishment) ውስጥ የዛገና የሚራገፍ ነገር የሚያይ የአዕምሮ ችሎታና የተፈጥሮ ተስጥዎ ካላቸው ታላላቅ ሰዎች ዘንድ የሚመጡ ሃሳቦች ናቸው” ይላል።

ሌላ ደግሞ ኢትዮጵያ የራሷ እምነትና ክርስትናን ቀድማ የተቀበለች መሆኑ ይታወቃል። እርሶ ከግዕዝ ወደ አማርኛ በተረጎሙት ደቂቀ እስጢፋኖስ ላይ በጀርመን የተነሳውን ማርቲን ሉተርን ሃሳብ ከኢትዮጵያ ካለው ንቅናቄ ጋር በማመሳሰል በገጽ 24-25 እንዲህ ብለው ጽፈዋል፤

“ደቂቀ እስጢፋኖስ የተነሱት በአጼ ይስሃቅ (1406-1421) ዘመን ሲሆን፣ ማርቲን ሉተር ጀርመን ላይ ተመሳሳይ ሃሳብ ይዞ ከመነሳቱ ከሰላሳ ዓመት በፊት ነው። የኢትዮጵያ ቤተ ክርስቲያን ውጉዛን ታድርጋቸው እንጂ፤ ተልኳቸውን ውስጥ ውስጡን በጽሙና እየተቀበለችው በመሄድ ላይ እንዳለች ሥነ ጽሁፍ ይመሰክራል። እንደሚባለው ሳይሆን ሁልጊዜ ሰላማዊና የማይቈረቁር ተሃድሶን የሚቀበል መሪዎች አሏት” ይላል።

እነዚህ ከላይ የገለጿቸው አስተሳሰብ በቀደመው ቤተክርስቲያን የበለጸገውን ኃይማኖታዊ እድገት እንዴት ሊወክል ይችላል? የዛገና የሚራገፍ የሚለው ቤተክርስቲያንን ይወክላል? የበለጸገውና በያሬዳዊ ዜማ ያበበውን የቤተክርስቲያን አመለካከት ከሉተር ጋር እንዴት ይመሳሰላል? በእኔ አስተያየት የዛገና የሚራገፍ ሃሳብ የምለው ኢትዮጵያን ክዶ በጎሣ ፖለቲካ ውስጥ ገብቶ መዳከር ነው።

ሌላው ደግሞ በቅርቡ በጻፉት ጽሁፍ፣ “ይህ የሃሰት ታሪክ የኢትዮጵያ አንድነት በሚያንሰፈስፋቸው ኢትዮጵያውያን ስሜት ከመቀለድና ከመጠቀም አልፎ በክልልና በጎሣ ፖለቲካ የሚያምን አንድ የኦነግ ሰው ነፍስ አይማርክም። የተረቱ ሰለባ የሆኑት የአንድነት ተስፋ የናፈቃቸው ምስኪንና አንድነቶችን ብቻ ናቸው” ይላል።

በእውነቱ ከሆነ ኦነግ የኢትዮጵያ ኦሮሞዎችን ወኪል ነው ያለው ማነው? እርሶስ ቢሆኑ የአማራ ወኪል ማን አደረገዎት? ይህ አገላለጽዎ የኢትዮጵያን ዜጎች በክብር አለማስቀመጥዎን ያመለክታል።

በመጨረሻም ትንቢተ ኢሳያስ በምዕራፍ 45፣ ቁጥር 14 ስለ ኢትዮጵያ የተነበየውን እንመልከት፤ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል የግብጽ ድካምና የኢትዮጵያ ንግድ ቁመተ ረጅሞችም የሳባ ሰዎች ወዳ አንተ ያልፋሉ፣ ለአንተም ይሆናሉ፣ እጆቻቸውም ታስረው ይከተሉሃል በፊትህም ያልፋሉ፣ ለአንተም እየሰገዱ በእውነት እግዚአብሔር በአንተ አለ ከእርሱም ሌላ አምላክ የለም ብለው ይለምኑሃል ...

መዝሙር፣ ምዕራፍ 72፣ ቁ.10፤ የተርሴስና የደሴቶች ነገሥታት ስጦታን ያመጣሉ፤ የዓረብና የሳባ ነገሥታት እጅ መንሻን ያቀርባሉ።

ትንቢተ ኤርምያስ፣ ምዕራፍ 39፣ ቁ. 14-18፤ "ኤርምያስንም ከግዞት ቤት አደባባይ አወጡት፥ ወደ ቤቱም ይወስደው ዘንድ ለሳፋን ልጅ ለአኪቃም ልጅ ለጎዶልያስ ሰጡት፤ እንዲህም በሕዝብ መካከል ተቀመጠ። በግዞትም ቤት አደባባይ ታስሮ ሳለ የእግዚአብሔር ቃል እንዲህ ሲል ወደ ኤርምያስ መጣ። ሂድ ለኢትዮጵያዊውም ለአቤሜሌክ እንዲህ በለው። የእስራኤል አምላክ የሠራዊት ጌታ እግዚአብሔር እንዲህ ይላል። እነሆ፥ ለበጎነት ሳይሆን ለክፋት ቃሌን በዚህች ከተማ ላይ አመጣለሁ፤ በዚያም ቀን በፊትህ ይፈጸማል። በዚያ ቀን አድንሃለሁ፥ ይላል እግዚአብሔር፤ በምትፈራቸው ሰዎች እጅ አልሰጥህም። ፈጽሜ አድንሃለሁ ነፍስህም እንደ ምርኮ ትሆንልሃለች እንጂ በሰይፍ አትወድቅም፥ በእኔ ታምነሃልና፥ ይላል እግዚአብሔር።"

ትንቢተ ኤርምያስ፣ ምዕራፍ 13፣ ቁ. 23፤ በውኑ ኢትዮጵያዊ መልኩን ወይስ ነብር ዝንጕርጕርነትን ይለውጥ ዘንድ ይችላልን?

ኦሪት ዘኍልቍ፣ ምዕራፍ 12፣ ቁ. 1-8፤ ሙሴም ኢትዮጵያይቱን አግብቶአልና ባገባት በኢትዮጵያይቱ ምክንያት ማርያምና አሮን በእርሱ ላይ ተናገሩ። እነርሱም። በውኑ እግዚአብሔር በሙሴ ብቻ ተናግሮአልን? በእኛስ ደግሞ የተናገረ አይደለምን? አሉ፤ እግዚአብሔርም ሰማ። ሙሴም በምድር ላይ ካሉት ሰዎች ሁሉ ይልቅ እጅግ ትሑት ሰው ነበረ። እግዚአብሔርም ወዲያው ሙሴንና አሮንን ማርያምንም። ሦስታችሁ ወደ መገኛኛው ድንኳን ውጡ ብሎ ተናገረ፤ ሦስቱም ወጡ። እግዚአብሔርም በደመና ዓምድ ወረደ፥ በድንኳኑም ደጃፍ ቆመ፤ አሮንንና ማርያምን ጠራ፥ ሁለቱም ወጡ። እርሱም። ቃሌን ስሙ፤ በመካከላችሁ ነቢይ ቢኖር፥ እኔ እግዚአብሔር በራእይ እገለጥለታለሁ፥ ወይም በሕልም እናገረዋለሁ። ባሪያዬ ሙሴ ግን እንዲህ አይደለም፤ እርሱ በቤቴ ሁሉ የታመነ ነው። እኔ አፍ ለአፍ በግልጥ እናገረዋለሁ፥ በምሳሌ አይደለም፤ የእግዚአብሔርንም መልክ ያያል፤ በባሪያዬ በሙሴ ላይ ትናገሩ ዘንድ ስለ ምን አልፈራችሁም? አለ።

የሐዋርያት ሥራ፣ ምዕራፍ 8፣ ቁ. 26-39፤ የጌታም መልአክ ፊልጶስን። ተነሥተህ በደቡብ በኩል ከኢየሩሳሌም ወደ ጋዛ ወደሚያወርደው ምድረ በዳ ወደ ሆነ መንገድ ሂድ አለው። ተነሥቶም ሄደ። እነሆም፥ ህንደኬ የተባለች የኢትዮጵያ ንግሥት አዛዥና ጃንደረባ የነበረ በገንዘብዋም ሁሉ የሠለጠነ አንድ የኢትዮጵያ ሰው ሊሰግድ ወደ ኢየሩሳሌም መጥቶ ነበር፤ ሲመለስም በሰረገላ ተቀምጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ያነብ ነበር። መንፈስም ፊልጶስን። ወደዚህ ሰረገላ ቅረብና ተገናኝ አለው። ፊልጶስም ሮጦ የነቢዩን የኢሳይያስን መጽሐፍ ሲያነብ ሰማና። በውኑ የምታነበውን ታስተውለዋለህን? አለው። እርሱም። የሚመራኝ ሳይኖር ይህ እንዴት ይቻለኛል? አለው። ወጥቶም ከእርሱ ጋር ይቀመጥ ዘንድ ፊልጶስን ለመነው። ያነበውም የነበረ የመጽሐፉ ክፍል ይህ ነበረ፤ እንደ በግ ወደ መታረድ ተነዳ፥ የበግ ጠቦትም በሸላቹ ፊት ዝም እንደሚል፥ እንዲሁ አፉን አልከፈተም። በውርደቱ ፍርዱ ተወገደ፤ ሕይወቱ ከምድር ተወግዳለችና ትውልዱንስ ማን ይናገራል? ጃንደረባውም ለፊልጶስ መልሶ። እባክህ፥ ነቢዩ ይህን ስለ ማን ይናገራል? ስለ ራሱ ነውን ወይስ ስለ ሌላ? አለው። ፊልጶስም አፉን ከፈተ፥ ከዚህም መጽሐፍ ጀምሮ ስለ ኢየሱስ ወንጌልን ሰበከለት። በመንገድም ሲሄዱ ወደ ውኃ ደረሱ፤ ጃንደረባውም። እነሆ ውኃ፤ እንዳልጠመቅ የሚከለክለኝ ምንድር ነው? አለው። ፊልጶስም። በፍጹም ልብህ ብታምን፥ ተፈቅዶአል አለው። መልሶም። ኢየሱስ ክርስቶስ የእግዚአብሔር ልጅ እንደ ሆነ አምናለሁ አለ። ሰረገላውም ይቆም ዘንድ አዘዘ፥ ፊልጶስና ጃንደረባው ሁለቱም ወደ ውኃ ወረዱ፥ አጠመቀውም። ከውኃውም ከወጡ በኋላ የጌታ መንፈስ ፊልጶስን ነጠቀው፤ ጃንደረባውም ሁለተኛ አላየውም፥ ደስ ብሎት መንገዱን ይሄድ ነበርና።

የኢዮጵያን ትንሳኤ ለማየት ያብቃን። አሜን!

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ