ኀሙስ መስከረም 15 ቀን 2001 ዓ.ም. አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ የመንግሥት፣ የግል እና የውጭ የመገናኛ ብዙኀን ጋዜጠኞችን ጠርቶ ጋዜጣዊ መግለጫ ሰጥቷል። በዚህ ጋዜጣዊ መግለጫው ላይ ከሁሉም የመገናኛ ብዙኀን ጋር ተቀራርቦ እንደሚሠራለና ለሁሉም በሩ ክፍት መሆኑን ገልጿል። ከዚህም በተጨማሪ ፓርቲው የአጭርና የረጅም ጊዜ የሥራ ዕቅዶችን አውጥቶ ለመንቀሳቀስ አስፈላጊውን ዝግጅት እያጠናቀቀ መሆኑን ገልጿል። የፓርቲው ሙሉ ጋዜጣዊ መግለጫ እንደሚከተለው ይገኛል።

 

ከአንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) የተሰጠ ጋዜጣዊ መግለጫ

መሰከረም 15 ቀን 2001 ዓ.ም.

 

የቀድሞ ቅንጅትን ዓላማና ራዕይ ወርሶ የተነሳው አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ ፓርቲ (አንድነት) በቅንጅት የተጀመረውን በኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ሥርዓትን የማስፈን ጥረት በአዲስ መንፈስና በአዲስ ተስፋ ለመቀጠል ቆርጦ የተነሳ ለመሆኑ ቀደም ሲል በተለያዩ አጋጣሚዎች አሳውቋል። ትግሉን ለመቀጠል የሚያስችሉ ዝግጅቶችንም አጠናቅቆ ከኢትዮጵያ ብሔራዊ ምርጫ ቦርድ አስፈላጊውን ሕጋዊ እውቅና በማግኘት በፕሮግራሙና በሕገደንቡ መሠረት ለመንቀሳቀስ ተዘገጋጅቷል።

 

አንድነት ዓላማውን ለማሳካት ከተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎች ትብብርና ድጋፍ ያስፈልገዋል። ከእነዚህ ክፍሎች አንዱ የመንግሥትም ሆኑ የግሉ መገናኛ ብዙኀን ቤተሰብ ነው። አንድነት ዴሞክራሲን በኢትዮጵያ የማስፈን ዓላማ የመንግሥትም ሆነ የግሉ መገናኛ ብዙኀን እንዲሁም የተቃዋሚ ፓርቲዎች የጋራ ዓላማ ነው ብሎ ያምናል። ስለዚህ አንድነት ይህን የጋራ ዓላማ ለማሳካት የበኩሉን ጥረት በሚያደርግበት ጊዜ ከመንግሥትም ሆነ ከግል የመገናኛ ብዙኀን ተገቢውን ትብብርና ድጋፍ አገኛለሁ ብሎ ያምናል። የዛሬው መገናኘታችን ይህን የጋራ ዓላማ ለማሳካት ሁላችንም በምናደርገው ጥረት እንዴት መደጋገፍ እንደምንችል፤ ከአለፈው ልምዳችን የታዩ የአሠራርና የአካሄድ ችግሮች ካሉ እንዴት ሊወገዱ እንደሚችሉ ሃሳብ ለመለዋወጥና ለመወያየት ነው። ይህ የዛሬው ግንኙነታችን የመጀመሪያ እንጂ የመጨረሻ አይደለም። ተባብሮ መሥራትና ችግሮችን በውይይት ማስወገድ ጊዜ የሚጠይቅ በመሆኑ አንድነት ከመንግሥም ሆነ ከግል መገናኛ ብዙኀን ጋር እየተገናኘ የሚወያይበት ቋሚ ፕሮግራም አውጥቷል። የዛሬው ግንኙነታችን የዚህ ቋሚ ፕሮግራም የመጀመሪያው እርምጃ ነው።

 

በዚህ አጋጣሚ አንድነት የአጭርና የረጅም ጊዜ የሥራ ዕቅዶችን አውጥቶ ለመንቀሳቀስ አስፈላጊውን ዝግጅት እያጠናቀቀ መሆኑን ለመግለጽ ይወዳል። ዝግጅቱ ድርጅታዊ መዋቅርን በየደረጃው ከመዘርጋትና ከማጠናከር ጀምሮ የዕውቀት፤ የፋይናንስና የአፈጻጸም አቅምን ማጎልበትን ያካትታል። የማዕከላዊ ጽሕፈት ቤትን ማጠናከር፤ የክልል ጽ/ቤቶችን መክፈትና በሰው ኃይልና በቁሳቁስ ማጠናከር፤ የአባላትን ቁጥር ማበራከትና ዕውቀታቸውንና ተሳትፎአቸውን በማጎልበት ለድርጅቱ አበይት ሥራዎች ማዘጋጀት ከአጣዳፊ ሥራዎቻችን ዋናዎቹ ናቸው።

 

አንድነት የመድበለ ፓርቲ ሥርዓት በሀገራችን ትርጉም ያለው እንዲሆን የበኩሉን ጥረት ያደርጋል። ምንም እንኳን ከቅርብ ጊዜ ወዲህ የወጡ የፖለቲካ ፓርቲዎች ምሥረታን፤ ፕሬስንና የሲቪል ማኅበራትን የሚመለከቱ ሕጎች የመንቀሳቀሻ መድረኩን ክፉኛ የሚያጠብቡ ቢሆኑም በሕጋዊነት፣ በዕውቀት፣ በጥበብ፣ በቀና አመለካከት፣ በትዕግሥትና በጠነከረ መንፈስ በመሥራት ታቅዶ የጠበበውን መድረክ እንዲሰፋና በኢትዮጵያ ዴሞክራሲን የማስፈን ተስፋ እየለመለመ እንዲመጣ ማድረግ ይቻላል ብሎ አንድነት በጽኑ ያምናል። መንግሥትም በእልክ መንፈስ ውስጥ በመግባት በአሳሪ ሕጎች የፖለቲካ መድረኩን ከማጥበብ ይልቅ በማስፋትና በማስተካከል የኃላፊነት ባህሪይን በሚያሳይ መልክ የመሪነት ሚናውን እንዲወጣ አንድነት ጥሪውን ያቀርባል።

 

በመጨረሻም አንድነት የመንግሥትም ሆኑ የግል መገናኛ ብዙኀን ራሱን የሚያይባቸው እውነተኛ መስተዋቶች እንዲሆኑና እነሱን በማየት ራሱን እያስተካከለና እያሻሻለ ለመሄዱ ምክንያቶች እንዲሆኑት ይፈልጋል። በርዕሰ አንቀጾቻችሁ፣ በዘገባዎቻችሁና በተለያዩ ዓምዶቻችሁ ከምትሰነዝሯቸው የሰሉ ሂሶችና ሃሳቦች ለመማር ዝግጁ መሆኑንና የህዝቡን የመረጃ ፍላጎት ለማርካት በምታደርጉት ጥረት አንድነት ተባባሪያችሁና በሩም ለሁላችሁም ክፍት እንደሆነ ያረጋግጥላችኋል።

 

የህዝብ መሠረት ያለው ሠላማዊ ትግል ያሸንፋል!

አንድነት ለዴሞክራሲና ለፍትሕ (አንድነት) ፓርቲ

መሰከረም 15 ቀን 2001 ዓ.ም.

አዲስ አበባ

 

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!