Prof. Fikre Tolossaአብርሃም ቀጄላ

የፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ ”የኦሮሞ እና የአማራ እውነተኛው የዘር ምንጭ” አዲስ መጽሐፍ በርካታ ኢትዮጵያውያን በተገኙበት በዩናይትድ ስቴትስ ኦፍ አሜሪካ ሦስት ከተሞች ተመረቀ። በሦስት ተከታታይ ቀናት ከዲሴምበር ፫ ቀን ጀምሮ በቨርጂኒያ፣ በዋሽንግተን ዲሲ እና በሜሪላንድ በሚገኙ የኢትዮጵያውያን ሬስቶራንቶች ነው ምርቃቱ የተካሄደው።

የፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ “የኦሮሞና የአማራ እውነተኛ የዘር ምንጭ መጽሐፍ፡-

 በቨርጂኒያ- መዓዛ ሬስቶራንት Dec 03/2016
 በዋሽንግተን ዲሲ-ላሊበላ ሪስቶራንት Dec 04/2016
 በሜሪላንድ- አዲስ አበባ ሬስቶራንት Dec 05/2016

በርካታ ኢትዮጵያዊያን ምሁራንና ታዋቂ ሰዎች በተገኙበት ተመረቀ።

• መጽሐፉን ሰላምንና ፍቅርን፣ የሚሰብክ የሕዝቦች አብሮነትና ብሎም አንድነት እንዲመጣ የሚረዳን ነው።
• መጽሐፉ ባለፉት 25 ዓመታት አማራና ኦሮሞን ለማራራቅ ሲጥሩ የነበሩ ፀረ አንድነት ኃይሎችን አንገት ያስደፋ ነው።
• ሕዝብ ለሕዝብም አስታራቂ መጸሀፍ ነው

ልብ ወለድ የሆኑ፣ ያልነበሩ የሌሉ የፈጠራና የሀሰት ታሪኮችን የሚያከሽፍ የሚያፈርስ፣ የሚደመስስ በተጨባጭ ማረጋገጫና የማስረጃ ምንጭ የተደገፈና የተመሰረተ ብቁ እጅግ ታላቅ መጽሐፍ ነው በማለት በርካቶች አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።

ፕ/ር ፍቅሬ የኦሮሞና የአማራን የተቀረው የኢትዮጵያ ሕዝብ እውነተኛ ትክክለኛ የዘር ምንጭ ምን እንደሆነ ከ5ሺ ዓመታት በላይ ወደ ኋላ ተጉዘው ማስረጃ አስደግፈው ምንጭ ጠቅሰው እሰከ አሁን ድረስ የምናውቀውን የኢትዮጵያ ታሪክ ከስር መሰረቱ የሚሽር፣ በአዲስ ታሪክ የሚተካ አዲስ የኢትዮጵያ ታሪክ ለመጀመርያ ጊዜ በዝርዝርና በጠራ አቀራረብ የሚገልጽ ድንቅ መጽሐፍ አቅርበዋል።

ኑሮአቸው በአሜሪካ የሆነው ተዋቂ የስነፅሁፍ ምሁር ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ በሊንከን ዩኒቨርስቲ በሂዩማኒቲስ የትምህርት ዘርፍ የሚያስተምሩና ከዚህ ቀደም “Heaven to Eden” እና “The Hidden and untold history of the Jewish people and Ethiopians” የሚሉ መጽሐፍ በእንግሊዝኛ ቋንቋ ያሳተሙ ሲሆን ሁለቱም በኢንተርኔት “አማዞን” በተባለ የመጽሐፍ ሽያጭ ድረገጽ ላይ ከተፈላጊ መጸሃፍት ተርታ ተሰልፈዋል። በሙያቸው ፀሃፊ ተውኔትና የሥነ ጽሁፍ ምሁር ሲሆኑ በኢትዮጵያ ታሪክ ላይ ጥልቅ ጥናትና ምርምሮችን በማድረግ ይታወቃሉ።

አንጋፋው ምሁር ፕ/ር መስፍን ወ/ማሪያም በቅርቡ ለንባብ ባበቁት “አዳፍኔ” በተሰኘ መጽሐፋቸው ላይ “የኦሮሞን ታሪክ ሙሉ አድርጎ ሊጽፍ የሚችለው ፕ/ሮ ፍቅሬ ቶሎሳ ብቻ ነው” ሲሉ ለብቃታቸው ምስክርነትና ዕውቅና መስጠታቸው ይታወቃል።

ፕ/ሮ ፍቅሬ ቶሎሳ በርካታ ቲያትሮችን ለመድረክ ያበቁ ሲሆን ከነዚህም መካከል “ጓደኛሞቹ” “ፍቅር በአሜሪካ” “መቃብር ቆፋሪው” ሌሎቹም ይገኙባቸዋል። በቅርብም “ላሟ” ይተሰኘ ባለሁለት ገቢር ቲያትር ጽፈው ማጠናቀቃቸውም ታውቋል።

ካሳተሟቸው የአማርኛ መጻሕፍት ውስጥ “ወለላ” የተሰኘ የልብ ወለድ መጽሃፍ እና “ይቺ ናት ሀገሬ” የተሰኘ የግጥም መጽሐፋቸው ይገኙበታል። በ2000 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ 2008) “multicolored flowers” (የተቅለመለሙ አበቦች) የተሰኘው ፊልማቸው ለሕዝብ እይታ ማብቃታቸው ይታወሳል።
በዲሲና በቨርጅኒያ የሚገኘው ናፍቆት ኢትዮጵያ የተባለው መጽሔትና አሳታሚ ድርጅት መጽሐፉን አሳትሞ፣ መጽሐፉ በአሁኑ ጊዜ በሽሚያና በወረፋ እየተሸጠ ያለ ከመሆኑም በላይ በዚሁ ሳምንት በድጋሜ እንደገና ለህትመት እየተዘጋጀ መሆኑና በተጓዳኝ በእንግሊዘኛ እንደሚታተም የናፍቆት መጽሔት ዋና አዘጋጅ አቶ ግርማ ዘገዬ ገልጾልናል።

ናፍቆት ኢትዮጵያ መጽሔት አሳታሚ ድርጅት የታሪክና የሌሎችንም ማህበራዊና ፖለቲካዊ መጻሕፍት ለምሳሌ ያህል የታላቁን የሙዚቃ ሰው የአቶ ተስፋዬ ለማን “የኢትዮጵያ የሙዚቃ ታሪክ” የተባለ መጽሐፍ እና “ሁሉም ነገር ወደ ጦር ግንባር” የሚለውን የጀኔራል ውበቱ ፀጋዬ መጽሐፍ ከማሳተም በተጨማሪ የአርትየት ሥራ እና የግራፊክስ ሥራዎችን፣ የታይፒንግ ሥራዎችን የሚሠራ ድርጅት ከመሆኑም ባሻገር የማርክ የታክስ አገልግሎት ይህንን በመደገፍ ግንባር ቀደም ተባባሪ በመሆን ሙሉ ድጋፍ ያደርጋል።

መጽሐፉ ባለፉት ወራቶች በኢትዮጵያ ውስጥ “ነባዳን የሚዲያ ማማከር ኃ/የተ/የግል ማኅበር” በተባለ አሳታሚ ድርጅት ታትሞ በአገሪቱ ውስጥ በዓመቱ ከታተሙ መጻሕፍት በከፍተኛ ሁኔታ በመሸጥ ላይ የነበረ ከመሆኑ በላይ ከዚህ ቀደም በኢትዮጵያ ታሪክ ዙሪያም ሆነ በሌሎች ርዕስ ጉዳዮች ላይ ከታተሙት መጻህፍት በአንድ ወር ጊዜ ውስጥ ብዛት ክብር ወሰን ማስመዝገቡ ታውቋል።

ፕ/ር ፍቅሬ ከበርካታ ሕዝብ በቀረበላቸው ጥያቄ መሰረት መጽሐፉ በቅርቡ በአፋን ኦሮሞ (ኦሮምኛ) በላቲን ፊደልና እንደዚሁም በአፋን ኦሮሞ በኢትዮጵክ ኦሮሞኝ ፊደል (በዘልማድ ግዕዝ ተብሎ በሚጠራው) ተተርጉሞ ለማሳተም ጥረት እየተደረገ ተጀምሮ እንዳለና በቅርቡ እውን እንደሚሆን ገልጸዋል።

በቀጣይ ሂደትና ጊዜያት በተቻለ መጠን ኢትዮጵያዊያን በሚገኙበት ሁሉም የአሜሪካን ስቴቶችና ከተሞች እንዲሁም በአውሮፓና አፍሪካ ባጠቃላይ በመላው ዓለም መጽሐፉን ለማደረስ ጥረታቸውን እያካሄዱ ነው። በመላው አሜሪካ የምገኙ ኮሚኒቲዎችና ስብሰቦች ጥሪ በቅደም ተከተል ወረፋ ተራ በመጠበቅ ላይ ይገኛሉ።

ፕ/ር ፍቅሬ ቶሎሳ በሌሎች ስራዎቻቸውና በተለይም በዚህ መጽሐፍ አበርክቶሻቸው በኢትዮጵያና በውጭም ባሉት ጭምር “ሐቀኛ የኦሮሞ ልጅ የኢትዮጵያ ልጅ”፣ “የመከራ ቀን ደራሽ”፣ “የመከራ ቀን ልጅ”፣ “የታሪክ እና የፍቅር አባት”፣ “የኢትዮጵያ መድን”፣ “የሕዝብ ዕርቅ አባት”፣ “አስታራቂ”፣ “የኢትዮጵያ ቤዛ”፣ “ነብይ” ተብለዋል። ተሰኝተዋል።

“ነብይ በአገሩ አይከበርም” የሚለው ተረት ፈርሶ ለአገር ቁም ነገር ያበረከቱ ግለሰቦችንና ሥራዎቻቸውን ማክበር ማመስገን ማወደስ መተባበር ማገዝ መረዳት በዚህ አዲስ መጽሐፍ መነሻ አዲስ ባህላችንና ልማዳችን እንዲሆን በአንድንቆት ተብሏል፣ ተዘክሯል፣ ተነግሯል።

አብርሃም ቀጄላ (ከዋሽንግተን ዲሲ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ