Gonder Timket 2020

በጎንደር የጥምቀት በዓል ላይ የተደረመሰውና የአሥር ሰዎች ሕይወት የቀጠፈው ማማ (እሁድ ጥር ፲፩ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም.)

አሥር ሰዎች ሕይወታቸውን ሲያጡ፣ ከመቶ አርባ ሰዎች በላይ ተጎድተዋል

ኢዛ (እሁድ ጥር ፲፩ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. January 20, 2020)፦ የጥምቀት በዓል በድምቀት ሲከበርባት የዋለው ጎንደር፤ በዓሉ በሚከበርበት ሥፍራ በጥንታዊው የአፄ ፋሲል ገንዳ አካባቢ ለበዓሉ ታዳሚዎች በአጣና ርብራብ የተሰናዳ ማረፊያ (ማማ) ተደርምሶ አሥር ሰዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ፤ ከአንድ መቶ አርባ ሰዎች በላይ ጉዳት እንደደረሰባቸው ተገለጸ።

ለመቀመጫነት የተሰናዳው የእንጨት ርብራብ ድንገት በመደርመሱ የተፈጠረው አደጋ ቀላልና ከባድ ጉዳይ የደረሰባቸው ከመቶ አርባ በላይ ሰዎች ወደ ሆስፒታል መወሰዳቸው ተደምጧል። ከእነዚህም ውስጥ ሁለቱ በጣም አደገኛ ሁኔታ ላይ እንደሚገኙና ወደ ሰማኒያ የሚጠጉ ሰዎች ደግሞ ከፍተኛ አደጋ የደረሰባቸው ሲሆን፣ ከስድሳ ሰዎች በላይ ቀላል ጉዳይ እንደደረሰባቸውና የሕክምና አገልግሎት አግኝተው ወደቤታቸው መሸኘታቸው ተነግሯል።

ከአደጋው መከሰት በኋላ ሲወጡ የነበሩ መረጃዎች የሟቾችን ቁጥር ከሦስት ወደ አስር ያስገባው ሲሆን፣ ቁጥሩ ከዚያም በላይ ሊኾን ይችላል የሚል ግምት ያላቸው ወገኖችም አሉ። የተጎጂዎችም ቁጥር እስካሁን በትክክል አልተገለጸም።

ኾኖም በሟቾች ቁጥር ላይ ያለው ትክክለኛ አኀዝ ቢለያይም፤ ባልተጠበቀውና ምናልባትም በሰው ብዛት የተነሳ ተደርምሷል የተባለው ማማ ባደረሰው አደጋ፤ የውጭ አገር ዜጋን ጨምሮ፣ ሴቶችና ሌሎች የበዓሉ ታዳሚዎች በድምሩ እስካሁን አሥር ሰዎች ሕይወታቸው ማለፉ ታውቋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ