ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር (ሞንጆሪኖ)

ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትርነት የተነሱትና የሕወሓት ምክትል ሊቀመንበር የኾኑት ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር (ሞንጆሪኖ)

ሦስት አዳዲስ ሚኒስትሮች ተሹመዋል

ኢዛ (ረቡዕ ጥር ፲፫ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. January 22, 2020)፦ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር በመኾን ከጥቅምት 6 ቀን 2011 ዓ.ም. ጀምሮ ሲያገለግሉ በቆዩትና የሕወሓት ምክትል ሊቀመንበር የኾኑት ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር ምትክ አዲስ ሚኒስትር ተሾሙ። ለሁለት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶችም አዳዲስ ሚኒስትሮች ተሹመዋል።

ሚኒስትሮቹ ባለፈው ሳምንት መሾማቸው የተጠቀሰውና ዛሬ ጥር 13 ቀን 2012 ዓ.ም. ይፋ በኾነው መረጃ መሠረት፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶ/ር ዐቢይ አሕመድ ከሾሟቸው አዳዲስ ሚኒስትሮች ውስጥ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር እንዲኾኑ የተሾሙት አቶ መላኩ አለበል ናቸው። አቶ መላኩ በአማራ ክልላዊ መንግሥት በምክትል ርዕሰ መስተዳድር ማዕረግ የንግድና ኢንቨስትመንት ቢሮ ኃላፊ ኾነው እያገለገሉ ነበር።

ይህ ሹመት እስከተገለጸበት ጊዜ ድረስ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ሚኒስትር በመኾን ሲሠሩ የቆዩት የሕወሓት ምክትል ሊቀመንበር የኾኑት ወ/ሮ ፈትለወርቅ ገብረእግዚአብሔር (ሞንጆሪኖ) ናቸው። በአዲሱ ሹመት መሠረት እርሳቸው ከኃላፊነት መነሳታቸውን ያረጋገጠ ሲሆን፣ ቀጣይ ማረፊያቸውና ከኃላፊነቱ የተነሱበት ምክንያት አልተገለጸም።

ሁለተኛው አዲስ ሚኒስትር ኾነው የተሾሙት፤ በቅርቡ ኃላፊነታቸውን በመልቀቅ ዩኔስኮ በገቡት ዶ/ር ጥላዬ ጌጤ ምትክ፤ ዶ/ር ኢንጂንየር ጌታሁን መኩሪያ የትምህርት ሚኒስትር ኾነው መሾማቸው ታውቋል። ዶ/ር ኢንጂንየር ጌታሁን መኩሪያ የትምህርት ሚኒስትር ኾነው እስከተሾሙበት ጊዜ ድረስ የኢንፎርሜሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በመኾን አገልግለዋል።

ዶ/ር ኢንጂንየር ጌታሁን የትምህርት ሚኒስትር ኾነው በመሾማቸው እርሳቸውን ተክተው የኢኖቬሽንና ቴክኖሎጂ ሚኒስትር በመኾን እንዲሠሩ በጠቅላይ ሚኒስትሩ የተሾሙት ዶ/ር አብርሃም በላይ ናቸው። ዶ/ር አብርሃም ይህ ሹመት እስከተሠጣቸው ድረስ የኢትዮጵያ ኤሌክትሪክ ኃይል ዋና ሥራ አስፈፃሚ በመኾን እየሠሩ እንደነበር ይታወሳል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ዜና እና ፖለቲካ

ኪነ-ጥበብ

ቪዲዮ

መጻሕፍት

ስለእኛ

ይከተሉን!