Ambassador Fitsum Arega (L) and Dr. Eng. Seleshi Bekele, Minister of Water, Irrigation and Energy (R)

በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ፍጹም አረጋ (በግራ በኩል)፣ የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂንየር ስለሺ በቀለ (በቀኝ)

“እስካሁን ምክክር ቢደረግም፤ ስምምነት ላይ የሚያደርስ ሰነድ አልተዘጋጀም” አምባሳደር ፍጹም አረጋ

ኢዛ (ረቡዕ የካቲት ፬ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. February 12, 2020)፦ በዋሽንግተን ዲሲ ከግብጽና ሱዳን ልዑካን ጋር የተደረገውን የሕግ ማዕቀፍ ድርድር ውጤት ከኢትዮጵያ ልዑካን ጋር እየገመገም እንደኾነ ታውቋል። በህዳሴ ግድብ ዙሪያ በሦስቱ አገራት መካከል እስካሁን ምክክር ቢደረግም፤ ስምምነት ላይ የሚያደርስ ሰነድ አለመዘጋጁቱን አምባሳደር ፍጹም አረጋ ገልጸዋል።

ይህ በየአገሮቹ ልዑካን ቡድን ጋር እየተደረገ ያለው ግምገማ በዛሬው ዕለት የሚቀጥል ስለመኾኑ ተገልጿል።

የሕግ ማዕቀፉ ድርድር ውጤትን ለመገምገም በውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስትር ዶ/ር ኢንጂንየር ስለሺ በቀለ የተመራው ቡድን ሰኞ የካቲት 2 ቀን 2012 ዓ.ም. ዋሽንግተን መግባቱ ታውቋል። ቡድኑ ይህንኑ የግምገማ ሥራ እያከናወነ ስለመኾኑ በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር አቶ ፍጹም አረጋ በፌስቡክ ገጻቸው ገልጸዋል።

ይሁን እንጂ ቡድኑ በበርካታ ጉዳዮች ላይ ምክክር ያደረገ ቢሆንም፤ ስምምነት ላይ ሊያደርስ የሚችል ሰነድ በጋራ ማዘጋጀት አለመቻሉን አምባሳደሩ ገልጸዋል። የድርድሩና የስምምነቱ ውጤት በብዙዎች ዘንድ በጉጉት እየተጠበቀ ቢኾንም፤ ከግብጽና ከሱዳን ጋር እየተደረገ ያለው የሕግ ማዕቀፍ ድርድር በዚህኛው ዙርም አገራቱ ስምምነት ላይ ሊደርሱ እንደማይችሉ፤ የአምባሳደሩ ገለጻ ከወዲሁ አመላካች ኾኗል።

በዛሬው ዕለትም በሚቀጥለው ምክክር ሊገኝ የሚችለው ውጤት ባይታወቅም፤ አምባሳደር ፍጹም አረጋ፤ “ኢትዮጵያ በፍትሐዊና ምክንያታዊ ተጠቃሚነት የምታምን ሲሆን፤ በዓባይ ውኃ የመጠቀም መብቷን አሳልፎ የሚሠጥ ምንም ዐይነት ስምምነት አትፈጽምም” ሲሉ በዋሽንግተን በሚካሔደው የሦስቱ አገራት ምክክር ዙሪያ የሠጡት መረጃ ያመለክታል።

በዚሁ የዋሽንግተን የሕግ ማዕቀፍ ድርድር ውጤት ላይና ግምገማን በተመለከተ ዶ/ር ኢንጂንየር ስለሺም ከአምባሳደር ፍጹም አረጋ ጋር ተመሳሳይ የኾነ መረጃ ትዊት አድርገዋል። (ኢዛ)

አዲስ ቪዲዮ

ይከተሉን!

ስለእኛ

መጻሕፍት

ቪዲዮ

ኪነ-ጥበብ

ዜና እና ፖለቲካ