አሜሪካ በግድቡ ውኃ ሙላት ላይ የሠጠችው መግለጫ አስቆጥቷል
የታላቁ ህዳሴ ግድብ
የኢትዮጵያ መንግሥት በጉዳዩ ላይ መግለጫ ሠጠ
ኢዛ (ቅዳሜ የካቲት ፳፩ ቀን ፳፻፲፪ ዓ.ም. February 29, 2020)፦ የአሜሪካ መንግሥት በህዳሴ ግድብ ዙሪያ እየተደረገ ያለው ድርድር መቋጫ ባላገኘበትና ምንም ዐይነት ስምምነት ሳይካሔድ በህዳሴ ግድብ ውኃ መሙላት መጀመር የለበትም፤ ሙከራም መደረግ የለበትም የሚል ሐሳብ ያለው መልእክት ማስተላለፉን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ከደቂቃዎች በፊት መግለጫ አውጥቷል።
ኢትዮጵያ በሌለችበት የተካሔደውን ስብሰባ ተከትሎ፤ በአሜሪካ ግምጃ ቤት ሴክሬታሪ የወጣውን መግለጫ በከፍተኛ ቅሬታ እንደምትመለከተው በማሳወቅ፤ ኢትዮጵያ ተቃውሞዋን ያንጸባረቀችበት መግለጫ በውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና በውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒስቴር በጋራ የወጣ ነው።
የመግለጫው ሙሉ ቃል የሚከተለው ነው። (ኢዛ)
በታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ ድርድር ዙሪያ የተሠጠ መግለጫ
የኢትዮጵያ ፌዴራለዊ ዴሞክራሲያዊ ሪፐብሊክ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴርና የውኃ፣ መስኖና ኢነርጂ ሚኒሰቴር የአሜሪካ የግምጃ ቤት ዲፓርትመንት ሴክሬታሪ በየካቲት 21 ቀን 2012 ዓ.ም. (እ.ኤ.አ. በ28 ፌብሩዋሪ 2020) የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብን በተመለከተ ኢትዮጵያ ያልተሳተፈችበትን ስብሰባ ተከትሎ የወጣውን የፕሬስ መግለጫ በከፍተኛ ቅሬታ ተመልክተውታል። ስብሰባው የተካሔደው ኢትዮጵያ አስቀድማ ለግብጽ፣ ለሱዳንና ለአሜሪካ ስብሰባው ለሌላ ጊዜ እንዲተላለፍ አሳውቃ እያለ ነው፡፡
የግድቡ ባለቤት የኾነችው ኢትዮጵያ በመርሆዎች መግለጫ ስምምነቱ መሠረት የግድቡን ሙሌት ከግንባታው ትይዩ በፍትሐዊና ምክንያታዊ አጠቃቀምና ጉልህ ጉዳት ያለማድረስ መርሆዎች መሠረት የምታከናውን ይሆናል።
ኢትዮጵያ የግድቡን የመጀመሪያ ሙሌትና የውኃ አለቃቅ መመሪያና ደንብ ለማዘጋጀት የሚደረገው ድርድር ተጠናቋል በሚል የተሠጠውን መግለጫ አትቀበልም። በዋሽንግተን ዲሲ የግብጽ ዐረባዊት ሪፐብሊክ ፈርሞበታል የተባለው “ረቂቅ” የሦስቱ አገራት የድርድርም ሆነ የሕግና ቴክኒክ ቡድኖች ውይይት ውጤት አይደለም። የቴክኒክ ጉዳዮች ድርድሩም ኾነ የሕግ ማዕቀፍ ዝግጅቱ ላይ የሚደረገው ድርድር አልተጠናቀቀም፡፡ ኢትዮጵያ የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ሙሌትና የውኃ አለቃቀቅ መመሪያና ደንብ የሚዘጋጀው በሦስቱ አገራት ብቻ እንደኾነ አቋሟን ቀድማ አሳውቃለች።
ኢትዮጵያ፣ ግብጽና ሱዳን በሚያውቁትና በተስማሙበት፤ እንዲሁም በመርሆዎች መግለጫ ስምምነት መርህ አንቀጽ ስምንት አድናቆታቸውን በሠጡት ሂደት መሠረት ሁሉንም የግድብ ደኅንነት የሚመለከቱ ጉዳዮች በዓለምአቀፍ የባለሙያዎች ቡድን ምክረ ሐሳብ መሠረት የተሠጡትን ምክረ-ሐሳቦች መፈጸሟን ትቀጥላለች።
የታላቁ የኢትዮጵያ ህዳሴ ግድብ የመጀመሪያ ሙሌትና የውኃ አለቃቅ መመሪያና ደንብን ለማዘጋጀት ቀሪ መሠረታዊ ልዩነቶችን ለመፍታት ኢትዮጵያ ከግብጽ ዐረባዊት ሪፐብሊክና ከሱዳን ሪፐብሊክ ጋር የጀመረችውን ሒደት ለመቀጠል ቁርጠኛ ናት።
የካቲት 21 ቀን 2012 ዓ.ም.፣ አዲስ አበባ



